ስሜነህ ደስታ
«እንዲህ ነው… እንዲህ ነው ጋብቻ… ወረት ያልዳሰሰው… » እድምተኞቹ ይጨፍራሉ፤ አዳራሽ ሙሉ ሰው ግጥም ብሏል። የሰዎች ጫጫታ፣ የሙዚቃ ድምጽ እንዲሁም የካሜራ ቀጭ – ቀጭ ጎልተው ከሚሰሙት መካከል ናቸው። ለሙሽሪት ግን ከሁሉም በላይ ውስጧን የረበሻት ከካሜራው የሚሰማው ድምጽ ነው፤ ቀጭ – ቀጭ- ቀጭ የሚለው። ቀጭ የሚለውን ድምጽ በመከተል ብልጭታው ይቀጥላል፤ ይሄም ይረብሻታል። ሙሽራው ደግሞ «ከሠርግ በኋላ ከእኛ ጋር የሚቀረው ፎቶ ነው!» እያለ ፈገግታን ከፊቱ ሳይነጥል በተደጋጋሚ በተለያየ አቋቋም እና ሁኔታ ሙሽሪትን ጠጋ ብሎ መነሳት ይፈልጋል።
ፎቶግራፍ አንሺውም የሙሽራውን ፍላጎት በከፍተኛ ደስታ እየተቀበለ አስተናግዶለታል። ሙሽሪት ግን ፈገግታ ይሁን መኮሳተር ባልለየ ሁኔታ ፊቷን ጥላ፣ ባትወድም መድረኩ ላይ ፎቶ ትነሳለች። ለእድምተኛውም ሆነ ለፎቶ አንሺው አይታይም እንጂ፤ ካሜራው ያንን ቀጭ – ቀጭ የሚል ድምጹን ባሰማ ቁጥር ትደነግጣለች። ሠርጓ ነው፤ «ሠርግ እና ሞት አንድ ነው!» የሚባልበት ቀን… የእርሷ ልዩ ቀኗ።
‹‹አሁን ተጨባብጠን›› ቀጭ
‹‹አሁን ተቃቅፈን›› ቀጭ
‹‹አሁን ስንሳሳም›› ቀጭ – – – ሙሽራው ይወተውታል፤ ፎቶ ግራፍ አንሺው ትዕዛዝ ይፈጽማል።
ሙሽራው‹‹ምንም ሳይሰለች ትዕዛዝ የሚፈጽም ካሜራ ማን ነው!›› አላት
‹‹ነው አይደል¡›› ብላ መለሰች ሙሽሪት
ሙሽራው‹‹ፊትሽን ፈታ አድርጊው እንጂ፣ ‹ወግ ነው
ሲዳሩ ማልቀስ› ይባላል። ማልቀስ ፈለግሽ እንዴ?››
‹‹አዎ!›› ሙሽሪት እንደመሽኮርመም እያለች።
ፎቶ ግራፍ አንሺው ዞር- ዞር ብሎ ሌሎች እድምተኞች ካነሳ በኋላ ወደ ሙሽሮቹ መጥቶ ‹‹እንዴት ያምርባችኋል!›› ቀጭ – ቀጭ – ቀጭ ሙሽራው በደስታ በመፍነክነክ ወደ ሙሽሪት ጠጋ ይላል፣ ያቅፋል፣ ይስማታል – – – ‹‹ሠርግ አይደገም፤ ዘና ብለሽ ፎቶ ተነሽ!›› ይላል።
ፎቶ ግራፍ አንሺው አምስት ዓመት በፍቅረኝነት አብራው የቆየችዋን ሴት ‹‹በዚህ ዓመት መጋባት አለብን›› ሲላት የፈነደቀችው ፍንደቃ እና በደስታ እላዩ ላይ የተጠመጠመችበት ሁኔታ እፊቱ ድቅን አለ።
ቀጭ – ቀጭ ሙሽሪት ምቾት አልተሰማትም እንግዶች የሚያስተናግዱትን እናቷን ጠርታ ‹‹ከእናቴ ጋር እንነሳ›› አለች። እናቷ ደግሞ በበኩላቸው ነጠላቸውን ከፍ እና ዝቅ በማድረግ ዘመድ አዝማዱ ፎቶ እንዲነሱ ጠሩ።
ከፍቅረኛው ጋር ሠርጉ መቼ ይሁን? የሚለው ላይ መግባባት አልቻሉም፤ እሱ ‹‹ቀደም ይበል›› ሲል እሷ ነገሮችን ፈዘዝ ታደርጋለች። እርሱም የጋብቻ ጥያቄ ሲያነሳ እንደ እባብ የተጠመጠመችበት፣ እንደ ሙጫ የተጣበቀችበት ፍቅረኛው አልመስልህ አለችው።
ቀጭ – ቀጭ ከእናቷ ጋር፣ ከእህቷ ጋር፣ ከአባቷ ጋር … ሙሽራው ‹‹ዋናው ቀሪው ፎቶ ነው!›› በማለት ደስታውን ይገልጻል። ሙሽሪት ቀጭ – ቀጭ በሚለው ድምጽ እና ብልጭታ ተረብሻለች።
ሙሽራው ‹‹አሪፍ – አሪፍ በሆነ ፖዚሽን ፎቶ አነሳኸን!›› በማለት ፎቶ ግራፍ አንሺውን አመሰገነው።
‹‹እኔም እንደ እናንተ ለመሆን ያብቃኝ›› ምላሽ ሰጠ ፎቶ አንሺው።
‹‹እኔ የምትወደኝ እና የምወዳት ሚስት ሰጠኝ፤ የመጀመሪያዬ ነች፤ የመጀመሪያዋ ነኝ፤ አንተንም
እግዚአብሔር ይርዳህ።››
‹‹አሜን!››
በተራቸው የሙሽራው ወገኖች ወደ መድረኩ መጡ። ሙሽሪት የሙሽራውን ወገኖች እጅግ የወደደች ይመስል ከመድረኩ እንዲወርዱ ፈቃደኛ አልሆነችም። በጋራ ከተነሳች በኋላ እያንዳንዳቸው በተናጠል እንዲነሱ ‹‹እንዳትሄዱ ለብቻ ደግሞ እንነሳለን›› በማለት መድረኩ ላይ አቆየቻቸው። በተለይ ከሴቶች ጋር ስትነሳ የመውደድ በሚመስል ሁኔታ ሙጭጭ ብላ በማቀፍ ደቂቃዎች እንዲሄዱ ታደርጋለች፤ ቀጭ – ቀጭ- – – ሙሽራው እና እሷ ብቻ ሲሆኑ የምትረበሸውን ዓይነት ረብሻ ሌሎች ሲጨመሩ የሚቀንስላት እየመሰላት ወደ መድረኩ ፎቶ ግራፍ ተነሺ ታሰባስባለች።
ያኔ… ፍቅረኛው የሚገናኙበትን ጊዜ በሰበብ በአስባቡ ታራዝም ጀመር። ግንኙነታቸው በጣም ሲያሳስበው ቁጭ አድርጎ ‹‹ሁኔታሽ አላማረኝም›› ብሎ ብሶቱን ነገራት። ‹‹ጨ.ቀ.ጨ.ከ.ኝ›› ብላ ቁጭ አለበት ጥላው ሄደች። ከአንድም ሁለት ጊዜ ፈልጎ አግኝቷታል፤ ልታናግረው ፈቃደኛ አልሆነችም። ጓደኞቿን አማላጅ ቢልክም ይኼ ነው የሚባል የሚጨበጥ መልስ ማግኘት አልቻለም።
ሙሽራው ፎቶ ግራፍ አንሺውን አሁንም – አሁንም ይጠራዋል። እሱም ከተፎ ነው፤ ገጭ አጠገቡ። ‹‹አሁን ደግሞ ብቻችንን ቆመን›› ሙሽሪት ከሙሽራው ጋር ብቻ ስትነሳ ይጨንቃታል። ቀጭ – ቀጭ – ቀጭ-
ፎቶግራፍ አንሺው ፍቅረኛውን እንዲያናግራት እና እንዲያስማማቸው ጓደኛውን በሽማግሌነት ላከው። ጓደኛው የሽምግልና ሂደቱን ጨረስኩኝ ባለ ጊዜ ‹‹የት እንዳነበብኩት አላውቅም›› ብሎ መልሱን በግጥም ነገረው።
‹‹ሴት ልጅ ከወደደች ከተያዘች ነፍሷ፣
የቤተሰብ ክብር ኢምንት ነው ለሷ፣
ከጠላችህ ደግሞ ለዓይኗ ተጠይፋ፣
እግዜርንም ብትልክ ትሄዳለች አልፋ።››
ግጥሙን ከሰማ በኋላ ስለእሷ አብዝቶ ማሰቡን ቀነሰ፤ ትንሽ ቆይቶ ስለእሷ ማሰቡን አቆመ። ዛሬ እሱ ፎቶ ግራፍ አንሺ፣ እሷ ሙሽራ ሆነው ተገናኙ። የሙሽሪት ጓደኞች አንድ ጠረጴዛ ሞልተው ይበላሉ፣ ይጠጣሉ፣ ይጨዋወታሉ፣ ይሳሳቃሉ፣ ያማሉ እንዲሁም ያሽሟጥጣሉ።
‹‹አሁን ቁርጡን አወቀው ሲያሳዝን፤ ቀደም ሲልም ያሳዝነኛል›› አንዷ
‹‹እሱማ ወንድ ነው! ወዲያው ነው ከልቡ ያወጣት፤ በእሷ ፊት ቆሞ ፎቶ ማንሳቱን አታደንቁም! አሉ እንጂ ሌሎች ወንድነታቸው – – – ›› ሌላዋ
‹‹ወንድነቱማ የሚያጠራጥር አይደለም!›› መኻል ያለችው
‹‹ይኼ መጠጥ ምስጢር አስወጣ¡›› ሌላዋ
‹‹ባለጌ ኧረ እኔ ያልኩት ቆራጥነቱን ነው›› መኻል ያለችው
ሁሉም አንድ ላይ ሳቁ። ሙሽሪት የጓደኞቿ ሳቅ ነገር እንዳለው አውቃለች። ከውጭ ስለመጣላት ባል እንጂ ስለእሱ ማንም እንዲያወራት ስለማትፈልግ የቀድሞው ፍቅረኛዋ ፎቶ ግራፍ ማንሳት መጀመሩን አታውቅም። ካልጠፋ ፎቶ ግራፍ አንሺ እሱ እንዴት እንደመጣ፣ ማን እንዳመጣው፣ ለማሰብ ስትሞክር ቀጭ – ቀጭ- ቀጭ- – –
ጓደኞቿን ፎቶ እንዲነሱ ጠራቻቸው። ‹‹ተነስተናል፤ ሌሎች ካንቺ ጋር ያልተነሱ ዕድሉ ይድረሳቸው›› ብለው በአክብሮት መለሱላት። ከፊት ለፊት ያለው ፎቶ ግራፍ አንሺ ሳይሆን መድፍ ተኳሽ መሰላት። ቀጭ – ቀጭ የሚለው ድምጽ ደግሞ የመድፍ ይመስል ቀጭ ባለ ቁጥር ያስደነግጣታል፤ ከጆሮዋም ቶሎ አይጠፋም።
አዲስ ዘመን ጥር 28/2013