አስናቀ ፀጋዬ
የዓለም ሁለተኛዋ ግዙፍ የምጣኔ ሀብት ባለቤት ቻይና የኮሮና ወረርሽኝ ሊያሳድር የሚችለውን ሁለንተናዊ ተፅእኖ አስቀድማ በመከላከሏ የምጣኔ ሀብት እድገቷ ብዙም ሳይንገራገጭ ወደፊት ማስቀጠል ችላለች።
አሜሪካንን ጨምሮ በኢኮኖሚ የላቀ እድገት ያስመዘገቡ የአውሮፓ ሀገራት ምጣኔ ሀብታቸው በዚሁ ወረርሽኝ ጦስ ሲቃወስ የቻይና ምጣኔ ሀብታዊ እድገት ግን በአንፃሩ የተሻለ አፈፃፀም አሳይቷል።
ከሰሞኑ የአሜሪካው የቢዝነስና ኢኮኖሚ ሚዲያ ሲ ኤን ቢ ሲ ባወጣው መረጃ መሠረት ደግሞ የታይዋን ኢኮኖሚ በሰላሳ ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ያልተጠበቀ እድገት ከማሳየት በዘለለ የቻይናን ኢኮኖሚ ጭምር በልጦ መገኘቱን ዘግቧል።
እንደዘገባው ከሆነ ባለፈው የፈረንጆቹ አዲስ ዓመት መጨረሻ ታይዋን ባልተጠበቀ ሁኔታ የእስያ ምጣኔ ሀብታዊ እድገት ቁንጮ ለመሆን ከመቻሏም በላይ በሰላሳ ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የቻይናን ኢኮኖሚ በልጧል።
የኮቪድ -19 ወረርሽኝን ተከትሎ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ፍላጎት በዓለም አቀፍ ደረጃ መጨመር የደሴቲቱን ሀገር ታይዋን ምርቱን በስፋት ወደ ውጭ በመላክ ኢኮኖሚዋን ለማሳደግ ትልቅ አስተዋፅኦ ማድረጉም በዘገባው ተመላክቷል።
በታይዋን ስታትስቲክስ መስሪያ ቤት ጥልቅ ትንበያ መሠረትም ከቀድሞው ዓመት ጋር ሲወዳደር የታይዋን ምጣኔ ሀብታዊ እድገት እ.ኤ.አ በ2020 በ2 ነጥብ 98 ከመቶ ማደጉ ተነግሯል።
የታይዋን ምጣኔ ሀብታዊ እድገት በ2020 የሀገሪቱ ማዕከላዊ ባንክ ያወጣውን የ2 ነጥብ 98 በመቶ ትንበያ በመብለጥ የቬትናምን የ2 ነጥብ 9 ከመቶ እድገት የተሻገረ ሲሆን አንዳንድ የምጣኔ ሀብት ተንታኞች ደግሞ ቬትናም በ2020 የእስያ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ባለቤት እንደምትሆን አስቀድመው መተንበያቸው ተገልጿል።
ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት የታይዋን ምጣኔ ሀብታዊ እድገት ቻይና ከነበራት የ2 ነጥብ 3 ከመቶ ሙሉ የኢኮኖሚ እድገት በላይ እንደነበረም ዘገባው አስታውሶ፤ የደሴቲቱ ምጣኔ ሀብታዊ እድገት ግዙፏን ጎረቤት ሀገር ቻይና ለመጨረሻ ጊዜ የበለጠው እ.ኤ.አ በ1990 መሆኑን ጠቅሷል።
በወቅቱም የቻይናን 3 ነጥብ 9 ከመቶ የኢኮኖሚ እድገት በ5 ነጥብ 5 ከመቶ እንደበለጠ ከሁለቱም ሀገራት የተገኙ ይፋዊ መረጃዎች እንዳሳዩም ሲ ኤን ቢ ሲ አትቷል።
‹‹2020 ለታይዋን ትልቅ ሪከርድ የተመዘገበበት ዓመት ነው።እናም ኮከቡ ማንፀባረቁን ይቀጥላል ብለን እንጠብቃለን›› ሲሉ በእንግሊዝ ባርክሌይ ባንክ የኢኮኖሚ ባለሙያዋ አንጄላ ሼ ተናግረዋል።
ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት አጋማሽ ደሴቲቱ የወጪ ንግዷን አጠናክራ በተለይ ደግሞ ለመኪና፣ ኮምፒዩተርና የሞባይል ቀፎዎች ወሳኝ አካል ተደርገው የሚቆጠሩ /ሴሚኮንዳክተሮችን/ ወደ ውጭ ሀገራት መላክ በመቻሏ የምጣኔ ሀብቷን ሚዛን በመጠበቅ በኮቪድ- 19 ከተጋረጠባት አደጋ ማምለጥ ችላለች ሲሉም የኢኮኖሚ ባለሙያዋ ገልጸዋል።
በዚህ መነሻነትም የታይዋን የ2021 ምጣኔ ሀብታዊ እድገት ትንበያቸውን ከ1 ነጥብ 2 ከመቶ ወደ 5 ነጥብ 2 ከመቶ ከፍ ያደረጉ መሆናቸውንም የኢኮኖሚ ባለሙያዋ አንጄላ ሼ ጠቅሰው፤ ይህ ትንበያ በይፋ ከተያዘው የ3 ነጥብ 83 ከመቶ የኢኮኖሚ እድገት በላይ ሊሆን የሚችልበት ዕድል እንዳለም ግምታቸውን አስቀምጠዋል።
ከዚህ በዘለለ ታይዋን የኮቪድ ወረርሽኝን ስርጭት በመቆጣጠር ረገድ አንፃራዊ ስኬት እንዳላት የኢኮኖሚ ባለሙያዋ ተናግረው፤ ይህም ኢኮኖሚዋ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሌሎች ሀገራት እንዳደረጉት ጠንካራ የእንቅስቃሴ ገደቦች እንዳያግደው ማስቻሉን ጠቅሰዋል።
ለዚህም የታይዋን የበሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል እስካለፈው እሁድ ድረስ በሀገሪቱ 911 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውንና ስምንቱ ደግሞ መሞታቸውን ያወጣውን ሪፖርት ለማመሳከሪያነት አስቀምጠዋል።
‹‹ታይዋን ለመኪና፣ ኮምፒዩተርና የሞባይል ቀፎዎች ወሳኝ ክፍል ተደርገው የሚቆጠሩ የኃይል ምርቶችን /ሴሚኮንዳክተሮችን/ አምርታ ለዓለም ገበያ በማቅረብ ‹‹የኃይል ቤት›› የሚል ተቀፅላ ስም ማትረፏንም ዘገባው አያይዞ ጠቅሷል።
በተለይ ደግሞ ወረርሽኙ በተጋጋለበት የመጀመሪያው ወቅት አብዛኛዎቹ ሰዎች በቤታቸው እንዲቆዩ በማስገደዱና ሰዎች በቤት ሲቆዩ ላፕቶፕ ኮምፒዩተሮችን ጨምሮ ሌሎች የኤሌክትሮኒክስ ምርቶችን የመጠቀም ዝንባሌያቸው በማደጉና የእነዚህ ምርቶች ሽያጭም ከፍ በማለቱ የሴሚኮንዳክተሮች ገበያ ፍላጎትም በዓለም አቀፍ ደረጃ አብሮ ማደጉንና ሀገሪቱ ምርቱን በስፋት ለዓለም ገበያ እንድታቀርብ በር እንደከፈተላት አስታውቋል።
በቅርቡ ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሴሚኮንዳክተር እጥረት ማጋጠሙንና በዚሁ ምክንያት የአሜሪካው መኪና አምራች ፎርድ ሞተርስና የጃፓኑን ኒሳን ሞተርን ጨምሮ በርካታ መኪና አምራች ድርጅቶች ምርቶቻቸውን እንዲቀንሱ ማስገደዱን ዘገባው አስታውሶ፤ ይህም የሴሚኮንዳክተር ምርት ተፈላጊነት እየጨመረ መምጣቱንና ታይዋንም ይህን ምርት በስፋት በማምረትና ለገበያ በማቅረብ ኢኮኖሚዋን ማሳደግ መቻሏን አመልክቷል።
‹‹ቲ ኤስ ሎምባርድ›› የተሰኘው የምርምር ማዕከል ኢኮኖሚ ባለሙያዎች በበኩላቸው ታይዋንና ደቡብ ኮሪያ 83 ከመቶ ያህሉን የዓለም ‹‹ቺፕስ›› ምርት አቀነባባሪዎችና 70 ከመቶ ‹‹የሚሞሪ ቺፕስ›› አምራች መሆናቸውን ይህም የሁለቱ ምሥራቅ እስያ ሀገራት ኢኮኖሚ ምርቶቹን በማምረት የበላይ ለመሆን ስለመቃረቡ ግምታቸውን አስቀምጠዋል።
ይህ የበላይነት ታዲያ ታይዋን እና ደቡብ ኮሪያ ከሁለቱ ትልልቅ ደንበኞቻቸው በአሜሪካ እና ቻይና በኩል ያላቸውን የኢኮኖሚና ፖለቲካ ስትራቴጂያዊ ተፈላጊነታቸውን ከፍ እንደሚያደርገው ባለሙያዎቹ ተናግረዋል።
ታይዋንና ኮሪያ በአሜሪካና ቻይና ፍጥጫ የፊት መስመር ላይ ያሉ ሀገራት መሆናቸውንና ለኢኮኖሚያዊ እድገታቸው ቻይና ላይ ያዘነበሉ ቢሆንም አሜሪካ የብሔራዊ ደህንነታቸው ዋስትና ናት ሲሉም ይጠቅሳሉ።
ይህ የኢኮኖሚ ድል ለታይዋን ከአሜሪካ በኩል የጦር መሣሪያ ለመግዛት የሚያስችልና ከቻይና በኩል ደግሞ የኢኮኖሚ ጫናን የሚቀንስ ስለመሆኑም የኢኮኖሚ ባለሙያዎቹ ጠቁመዋል።
ቤጂንግ የሚገኘው የቻይናው ኮሚዩኒስት ፓርቲ ዴሞክራሲያዊና ራስ ገዟ ደሴቲቱ ሀገር ታይዋን እንደ አንድ የቻይና ግዛት ሆና እንድትዋሃድ በተደጋጋሚ ቢጠይቅም እስካሁን ድረስ ታይዋንን ማስተዳደር እንዳልቻለ በዘገባው ተጠቅሷል።
የ ‹‹ቲ ኤስ ሎምባርድ›› ኢኮኖሚ ባለሙያዎቹ የአሜሪካ ሴሚኮንዳክተር አቅራቢዎችን ከገበያ ውጪ የሚያደርግ ከሆነ ቻይና በሴሚኮንዳክተር ምርቶች ወደታይዋን ልታዘነብል እንደምትችልም ግምታቸውን አስቀምጠዋል።
ቤጂንግ ከዋሽንግተን ጋር ያላት የንግድ ውዝግብ እያደገ በመምጣቱ በረጅም ጊዜ ሂደት ሴሚኮንዳክተሮችን በራሷ ለማምረት ያለመች ቢሆንም አንዳንድ ተንታኞች ግን ቻይና ይህን ለማድረግ አቅሟ ገና ስለመሆኑ ይናገራሉ።
አዲስ ዘመን ጥር 26/2013