እፀገነት አክሊሉ
የውበታችን አንዱ መገለጫ የምንመገበውን ምግብ የመጀመሪያ ዙር ፈጭቶ መላኪያ ነው ጥርሳችን። ይህ ብዙ አገልግሎት ያለው የሰውነታችን ክፍል ታዲያ ሊደረግለት የሚገቡ ጥንቃቄዎች ብዙ ከመሆናቸውም በላይ እነሱ በሚጓደሉበት ጊዜም ከፍተኛ የሆነ የህመም ስሜትን የሚፈጥር ነው።
ዛሬ ዛሬ ደግሞ የምንመገባቸው ምግቦች ይዘታቸውን በመቀየራቸው ምክንያት ብዙዎቻችን የጥርስ በሽታ ታማሚዎች ስለመሆናችን ነጋሪ የማያሻው ሀቅ ነው። ታዲያ ለዚህ አስፈላጊ የሰውነት ክፍላችን ተገቢውን ጥንቃቄ በተለይም ጽዳቱ እንዳይጓደል በማድረግ ከሚያስከትለው ህመም መዳን እንደሚቻል ባለሙያዎች ይመክራሉ።
እንግዲህ ስለ ጥርስ ይህንን ያህል ያወራነው አለምክንያት አይደለም፤ የዛሬ የህይወት እንዲህ ናት አምድ እንግዳችን በጥርስ ህክምናው ብዙ ዓመታትን ያሳለፉት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጥርስ ህክምና ፋኩሊቲ ኃላፊ የሆኑት ዶክተር ላቀው አሰፋ በመሆናቸው ነው። ከዶክተር ላቀው ጋርም ስለ ህይወት ተሞክሯቸው እንዲሁም ስለ አገራችን የጥርስ ህመምና የህክምና አሰጣጥ ደረጃ በሰፊው ተወያይተናል።
የትውልድ ቦታ
የተወለዱት በቀድሞ በወሎ ጠቅላይ ግዛት ደቡብ ወሎ ወረኢሉ አውራጃ ጃማ ወደራ ልዩ ስሙ ቦከረን በሚባል አካባቢ ነው። በ1958 ዓ.ም ይህችን ምድር የተቀላቀሉ ሲሆን ለአርሶ አደር እናትና አባታቸው የመጀመሪያ ልጅ ሲሆኑ ከስራቸው ላሉት አራት ሴትና ሶስት ወንዶች ደግሞ ታላቅ የቤቱም አንጋፋ ልጅ ናቸው።
የዶክተር ላቀው አሰፋ የታላቅነት ጉዞም የተጀመረው እንግዲህ በዚህ ሁኔታ ነው። እናትና አባታቸው የቤተክህነት ትምህርት ተምረውላቸው ድቁናን ከዛም ወደ ቅስና እንዲሄዱ የተመኙ ቢሆንም የዛሬው ስመ ጥር የህክምና ባለሙያ የያኔ ህጻን ልጅ ግን በፍጹም ይህ ሃሳብ አልተዋጠላቸውም፡፡ የቤተሰቦቻቸውን ቃል ለመፈጸም ግን የቄስ ትምህርቱን ቢጀምሩትም አልቀጠሉበትም። እንደውም ዘመናዊ ትምህርት ወዳለበት ሄጄ ልማር በማለት ቤተሰባቸውን ማስቸገሩን ተያያዙት እንጂ።
“ቤተሰቦቼ መካከለኛ ኑሮ ያላቸው ከመሆኑ አንጻር ልጆቻቸውን አካባቢው በሚፈቅደው ልክ ጥሩ አድርገው ነው ያሳደጉን፤ በተለይም እኔ እድሜዬ ለትምህርት ሲደርስ እንድማርላቸው ይፈልጉ የነበረው የቤተክህነትን ትምህርት ነበር፤ የእነሱን ፍላጎት ለማሟላት ያህል ብጀምረውም ልዘልቅበት ግን አልቻልኩም” ይላሉ።
ወደዘመናዊ ትምህርት በከፍተኛ ሁኔታ የተሳቡት ዶክተር ላቀው ቤተሰቦቻቸው በጉዳዩ ላይ አምነውበት ወደሚፈልጉት ዘመናዊ ትምህርት ቤት እስኪልኳቸው ድረሰም የነበራቸውን ጉጉትና እነሱንም መቆሚያ መቀመጫ አሳጥተው የወተወቱበትን ሁኔታ ሲያስታውሱ ይገረማሉ።
“ቤተሰቦቼ የእኔን ጉጉት ተረድተው ይሁን ጭቅጭቄ በዝቶባቸው ባላውቅም ብቻ ዘመናዊ ትምህርት ቤት እንድገባ ፈቀዱልኝ ። በወቅቱ ደስታዬ ወደር ከማጣቱም በላይ ትምህርቴን በከፍተኛ ትጋት በመማር ልዩ ውጤትንም ማስመዝገብ ጀመርኩ”።
ያ በጉጉትና በናፍቆት የተገኘው የትምህርት እድል ገና ከጅማሬው ጥሩ መስመር ይዞ ነበርና ዶክተር ላቀው ትምህርታቸውን በጉብዝና ከመማራቸውም በላይ ከክፍል ክፍል ሲሸጋገሩ እንኳን ደብል እየመቱ የሚያልፉ ጎበዝ ተማሪ ሆኑ። ይህ ደግሞ ቤተሰቦቻቸውን አልፎም መምህራኖቻቸውን በከፍተኛ ሁኔታ የሚያኮራ ሆነ ።
“በወቅቱ በትምህርት ክፍል ውስጥ የምንማር ተማሪዎች ቁጥራችን በጣም ውስን የነበረ ከመሆኑም በላይ ከፍተኛ የሆነ ፉክክር እናደርግ ነበር፤ እኔም ለትምህርቴ ከፍተኛ ትኩረት የምሰጥ ስለነበር ትምህርቱም ብዙ አልከበደኝም፤ ደብልም እመታ ነበር፤ በዚህም በአስር ዓመት 12ተኛ ክፍልን ለማጠናቀቅ ቻልኩ” ይላሉ።
ቤተሰቦቻቸው በቅርባቸው ሆነው የቤተ ክህነቱን ትምህርት ብቻ እንዲማሩ ቢፈልጉም ሳይሆን ቀረ ከዛም በላይ ደግሞ ጎበዝ ተማሪ የሆኑ ዶክተር ላቀው የ12ተኛ ክፍል ትምህርታቸውን አጠናቀውና ብሔራዊ ፈተናን ወስደው ወደከፍተኛ የትምህርት ተቋም መግባትም ግድ ሆነባቸው፤ ቤተሰቦቻቸውም ይህንን አምነው ሊቀበሉ ተገደዱ። እንደውም የብሔራዊ ፈተናው ውጤት በማማሩ (በመሳካቱ) ከአካባቢያቸው ርቀው ወደ አዲስ አበባ መምጣት ቻሉ።
እዚህ ላይ ይላሉ ዶክተር ላቀው “የእኔ በዚህ መልኩ ወደዘመናዊ ትምህርት መቀላቀል ለእህትና ወንድሞቼ መንገድ ከፍቷል፤ በራሳቸው ምክንያት ካልተማሩት ውጪ አብዛኞቹ ዘመናዊ ትምህርትን ተምረው ጥሩ ደረጃ የደረሱ ናቸው”።
የልጅነት ምኞት
ዶክተር ላቀው እንደማንኛውም ልጅ ሳድግ ይሄንን እሆናለሁ እያሉ እየተመኙ ነው ያደጉት። በተለይም ሰባተኛና ስምንተኛ ክፍል ተማሪ በነበሩበት ወቅት የሂሳብ መምህር እንደመሆን የሚመኙት ነገር እንዳልነበር ይናገራሉ።
እንደውም ይላሉ በዛን ወቅት በአካባቢው ባለ ጤና ኬላ እየሰራ አብሯቸው የሚማር ጓደኛቸው ጋር ለማጥናት በማለት ሲያድሩ ሌሊት ህክምና የሚፈልጉ ሰዎች እየመጡ ከእንቅልፋቸው ሲቀሰቅሷቸው እያዩ ለህክምና ሙያ ከፍተኛ የሆነ ጥላቻም አድሮባቸው እንደነበር ያስታውሳሉ።
ጉዞ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ
የገጠሩ ልጅ ዶክተር ላቀው አሁን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በድል አጠናቅቀው ወደ ከፍተኛ ትምህርት ለመግባት ዳር ደርሰዋል፤ እርሱም በመሳካቱ በ1975 ዓ.ም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቱ ሳይንስ ፋኩሊቲን ተቀላቀሉ።
በወቅቱ በአገሪቱ ሶስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የነበሩ ሲሆን እነሱም አዲስ አበባ፣ አስመራ እና ሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ ብቻ የነበሩ ሲሆን እነሱም ተጠቃለው የሚቀበሉት የተማሪዎች ቁጥር ከ 2ሺ የማይበለጥ ነበር። ከዚህ አንጻርም ዩኒቨርሲቲ መግባት እንደ ትልቅ እድልና ጉብዝና የሚታይበት ወቅት ነበር።
ወቅቱ ቀይ ሽብር እየተባለ በርካታ ወጣቶች የሚታሰሩበት የሚገደሉበት ስለነበር በህዝቡ ውስጥ ከፍተኛ ፍርሃት ነበር፤ “ተማሪ ሲኮን ደግሞ ሁኔታው ትንሽ ከበድ ይላል” የሚሉት ዶክተር ላቀው ይህንን ሁሉ ለመጋፈጥ በመቁረጥ ግን ወደ ተመደቡበት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያመሩት በከፍተኛ ድፍረት ደስታና የነጋቸው ብሩህ ነገር እየታያቸው ስለመሆኑም አጫውተውኛል።
“በወቅቱ በፖለቲካውም በአንዳንድ ነገሮችም ተማሪ መሆን ውጣ ውረዱ የበዛና አስቸጋሪ ቢሆንም ግን ደግም ትምህርት አሰጣጥ እጅግ ድንቅ የሆነ ተማሪውም በጣም ተጣርቶ የመጣና ለትምህርቱ የተመጠነ በመሆኑ ልክ እንደሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱ ሁሉ እዛም በከፍተኛ ፉክክር በወኔና በደስታ እንማር ነበር” ይላሉ።
የሂሳብ ፍቅራቸው ወደ ተፈጥሮ ሳይንስ የትምህርት ክፍል እንዲያመሩ ያደረጋቸው ቢሆንም በእዛም ግን ብዙ መቆየት አልቻሉም። በወቅቱ ፖለቲካዊ ሁኔታ ምክንያት ትምህርታቸውን አቋርጠው እርሳቸው መግለጽ ወዳልፈለጉበት ቦታ ሄደው ጊዜን ለማሳለፍ ተገደዱ ።
ሁሉም ነገር ካለፈና ሁኔታዎች ከተረጋጉ በኋላ ግን በቀድሞው የትምህርት ፍላጎታቸው አልቀጠሉም፤ ከዛ ይልቅ በጣም ይጠሉት የነበረውን የህክምና ዘርፍ በመምረጥ እሱን ለመማር ወሰኑ። በውሳኔያቸው በመጽናትም የህክምና ትምህርት ክፍሉን በ 1976 ዓም ተቀላቀሉ።
ሳይንስ ወዳዱ ዶክተር ላቀው የቁጥር ትምህርትን ቢመኙም (ቢፈልጉም) ህይወት በራሷ አቅጣጫ ወደ ህክምናው ሳበቻቸው የህይወትን ጥሪም አሜን ብለው ትምህርታቸውን በሚገባ መማርን ስራቸው አደረጉት። ከህክምናም ደግሞ የብዙዎች ችግር የሆነውን የችግሩን ያህል ግን ትኩረት ያልተቸረውን የጥርስ ህክምና በመምረጥ መማርን ፈልገው ትምህርታቸውን በዛው መንገድ ቀጠሉ።
“ የተወለድኩበት አካባቢ እንኳን የጥርስ ህክምን ቀርቶ ሌሎች መሰረታዊ የሚባሉ የህክምን አገልግሎቶችም ያልተስፋፋበት ነበር፤ በተለይም ጥርስ ደግሞ እጅግ በሚገርም ሁኔታ በባህላዊ መንገድ ህመሙን የማስታገስ ሲብስም የመንቀል ስራ ሁሉ ይሰራ ነበር” ይላሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ ይህ ባህላዊ የህክምና አሰጣጥ በእርሳቸውም ደርሶ አይተውታል፤ ዶክተር ላቀው እንዳሉት በተፈጥሮ አራት ድርብ ጥርስ የነበራቸው ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ሁለቱን ጥርሶቻቸውን በባህላዊ መንገድ በዋንጫ እንደነቀሉላቸውም ያስታውሳሉ።
“ይህ መሰል የጥርስ ጤና ችግር እኔ ተወልጄ ባደኩበት አካባቢ ብቻ ሳይሆን የአብዛኛው ህዝብ ችግር ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ህክምና ከተማርኩ አይቀር ለምን የጥርስ ህክምናን አልማርም በማለት ተቀላቀልኩ” በማለት ወደጥርስ ህክምና ትምህርት ለመቀላቀል ያበቃቸውን ምክንያት ይናገራሉ።
ሰው በህይወት ዘመኑ ሁለት ጊዜ ጥርሶችን ያበቅላል የሚሉት ዶክተር ላቀው በዚህም በተወለደ በስድስት ወሩ ጥርሶችን ማብቀል ጀምሮ በዛ ሂደት 20 የወተት ጥርሶችን አብቅሎ ይጨርሳል። እድሜው ስድስት ዓመት ሲሞላ ደግሞ ቋሚና አብረውት የሚኒሩት ጥርሶች መተካት ይጀምራሉ።
“ የጥርስ ህክምና ተማሪ ስሆን የተረዳሁት ነገር ቢኖር እነዚህን ተፈጥሯዊ አበቃቀሎች እነዛ በእኔ አገር በዋንጫ የሚነቅሉ ሰዎች አለመረዳታቸውን ነው። በዚህም ጥርሱን የታመመ ሁሉ ምናልባትም ቋሚ ጥርስ ሁሉ ይነቀል ነበር። ይህንን በህክምና ትምህርቴ ተረድቻለሁ” ይላሉ።
ይህም ቢሆን ግን አሁንም በአገሪቱ ያለው የጥርስ ህክምን ትምህርት ገና አለማደጉ ብዙ ባለሙያ አለመኖሩ በቴክኖሎጂ በዘመናዊ መሳሪያ አለመደገፉ ያበሳጫቸዋል። የጥርስ ህመም ከየትኛውም ህመም እኩል እንደውም በላይ የሰውን ልጅ የሚያሰቃይ በተለይም አሁን አሁን በርካታ ህጻናት እየተጎዱበት ያለ ቢሆንም በሚመለከታቸው አካላት ዘንድ ዘርፉ እንዲያድግ እየተሰጠ ያለው ትኩረት አናሳ ስለመሆኑም ደጋግመው ይናገራሉ።
“ትምህርቱ በአገራችን ገና በስፋት አልተካሄደም፤ በከተማዋ ብዙ የጥርስ ህክምና መስጫ ያሉ ቢመስልም በሚፈለገው ልክ በባለሙያና በመሳሪያ የተደራጁ ብሎም ለጥርስ ህክምና የሚያስፈልገውን ሁሉ በተሟላ ሁኔታ አሟልተው አገልግሎት መስጠት የሚችሉ አይደሉም” እንደ ዶክተር ላቀው ገለጻ።
የህብረተሰባችን የጥርስ የጤና ችግር የሚመነጨው ገና ከአበቃቀሉ ጀምሮ ነው የሚሉት ዶክተር ላቀው ይህንን ለመከላከል ደግሞ የጥርስ ህክምና ልምድ ማጣት ሲፈለግም በአግባቡና በተመጣጣኝ ዋጋ አለመገኘት ብሎም አሉ የምንላቸው የህክምን መስጫ ቦታዎችም ከላይ እንዳልነው በባለሙያና በመሳሪያ የተደራጁ አለመሆናቸውን እንደ ችግርም ያነሳሉ።
በመሆኑም ህብረተሰቡ በጥርስ በሽታ እንዳይሰቃይ የሚመለከተው ክፍል ለዘርፉ ልዩ ትኩረትን መስጠት እንደሌሎች የህክምና ዘርፎች ሁሉ በተቀናጀ ሁኔታ ህክምናውና ተደራሽነቱ የሚሰፋበትን መንገድ መፈለግም እንደሚገባ ያብራራሉ። አሁን በአጋጣሚ የገቡበትን የጥርስ ህክምና ትምህርት በማጠናቀቅ የስራውን ዓለም መቀላቀል ቻሉ ።
ወደ ስራ ዓለም መቀላቀል
ዶክተር ላቀው የከፍተኛ ትምህርታቸውን አጠናቀው ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ስራ አለም የተቀላቀሉት በወቅቱ አጠራር ጎጃም ክፍለ ሃገር መተከል አውራጃ በሶስት መቶ ብር የወር ደመወዝ ነበር። በተማሩበት የህክምና ሙያም ለሁለት ዓመታት ካገለገሉ በኋላ ወደ አዲስ
አበባ መመለሳቸውን ይናገራሉ። ወደ አዲስ አበባ ከመጡ በኋላም በዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል በመግባት ስራቸውን ቀጠሉ።
የጥርስ ህመም ህጻን አዋቂውን የሚያሰቃይ ከመሆኑ አንጻር ዶክተር ላቀውም አዲሱ መስሪያ ቤታቸው ላይ ብዙ ታካሚዎችን ያስተናግዱ ጀመር። ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉም ስቃይ በዝቶባቸው የመጡትን ሁሉ ከስቃያቸው አረፍ እንዲሉ ለማስቻል በርካታ ተግባራትንም ስለማከናወናቸው ይናገራሉ።
“ስራውን ወድጄው ነበር የምሰራው፤ ችግሩም በስፋት ስለነበር ያለምንም እረፍት ቀኑን ሙሉ እሰራ ነበር። እንደውም አንዳንድ ጊዜ የማላውቀው አይነት ስራ ሲገጥመኝ እዛው ካስቀመጥኳቸው መጻህፍ እያጣቀስኩ መፍትሔ ለመስጠት ከፍተኛ የሆነ ጥረትንም አደርግ ነበር፤ በዛም ተሳክቶልኛል” ይላሉ።
ጥርስ በጣም ጥንቃቄን ከሚሹ የሰውነታችን ክፍሎች አንዱ እንደመሆኑ በአያያዝም ኋላም ሲታመም በማከሙ በኩል ከፍተኛ ጥንቃቄን ይሻል። ጥንቃቄም ብቻ ሳይሆን ማስተዋል ማወቅና ብልሃትንም የሚፈልግ የስራ ዘርፍ መሆኑን ይናገራሉ። አንዳንድ ጊዜ ሲታዩ በቀላሉ ሊሰሩ ይችላሉ ተብለው የተገመቱ የጥርስ አይነቶች በከፍተኛ ደረጃ ተወሳስበው በሰውየው ላይ ብዙ መዘዞችን ሊያመጡበት የሚችሉበት አጋጣሚ ስላለ ስራው ሲሰራ በጣም መጠንቀቅ ማንበብ ማወቅ ከዛ ደግሞ ብልሃትንም መፈለግ ይሻል ይላሉ።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጥርስ ህክምና ክፍል ቆይታ
ይህ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጥርስ ህክምና ክፍል በ1980 ዓ.ም በኢትዮጵያና በጣሊያን መንግስት ስምምነት የተመሰረተ ነው። አመሰራረቱም በጥርስ ህክምናው ዘርፍ መካከለኛ የሆኑ ባለሙያዎችን ለማሰልጠንና ህዝቡን እንዲያገለግሉም ለማስቻል ነው። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ እስከ 1991 ዓ.ም ድረስ በጤና ጥበቃ ስር ሆኖ ነበር ስራውን የሚያከናውነው። ከዛን ጊዜ ጀምሮም የጥርስ ህክምናውን ለማሰልጠን ተሞክሯል ።
በ1983 ዓ.ም የመንግስት ለውጥ ሲመጣ የመጀመሪያዎቹ 17 ነርሶች በአድቫንስድ ዲፕሎማ ለመሰልጠን ተመልምለው ወደ ኮሌጁ ገብተዋል። እነዚህም በ1985 ዓ.ም ትምህርታቸውን አጠናቅቀው ተመረቁ፤ በ1985 ዓ.ም ደግሞ ሁለተኛውን ዙር ለማስተማር ተቀበሉ። እንደዚህ እያለ ኮሌጁ ግስጋሴውን ቀጥሏል።
ዶክተር ላቀውም በ1991 ዓ.ም ኮሌጁን ሲቀላቀሉ ነበር ኮሌጁም ወደ ዩኒቨርሲቲው የገባው። በመምህርነት እያገለገሉ ለአራት ዓመታት ከቆዩ በኋላ ወደ ኃላፊነት መደብ መምጣታቸውን ይናገራሉ።
ኮሌጁ ከተቋቋመበት አላማ አንጻር ያለበት ወይም የደረሰበት ደረጃ ያን ያህል አስደሳች ባይሆንም አሁንም ስራው ላይ መሆኑ ግን እጅግ ያስደስታቸዋል። በጥርስ ህመም ምክንያት የሚሰቃይ ብዙ ወገን ባለበት፣ ጥርስን መታከም ከፍተኛ የሆነ ወጪ የሚጠይቅ ከመሆኑ አንጻርም ኮሌጁ እየሰጠ ያለው አገልግሎት ተደራሽ አለመሆኑም ያስቆጫቸዋል። ነገር ግን አሁንም ተስፋ አይቆርጡም፤ በጥንካሬ ከተሰራም ይሻገራል በማለት ይናገራሉ።
“ …..እንደምፈልገው ባይሆንም አሁንም በጥቂቱ ቢሆን ለውጥ አለ፤ ሆኖም ግን አሁን ያለበት ሁኔታ በውጭ አገር ድጋፍ ሰጪዎችና በውስጥ ባሉ የህክምን ባለሙያዎች ጥረት እየተሰራ ነው። በመሆኑም አሁንም ከዚህ የበለጠ ተጠናክሮ ለጥርስ ህክምና ዘርፉ ትልቅ አስተዋጽኦን አበርክቶ መመልከት ደግሞ ምኞቴ ነው”።
ኮሌጁ በአድቫንስድ ዲፕሎማ ደረጃ የጀመረውን የመማር ማስተማር ስራ አሁን ላይ እስከ ዶክትሬት ዲግሪ ድረስ በማስተማር ላይ ይገኛል። አሁን ላይ ደግሞ ስፔሻሊስቶችን ለማፍራት የሚያስችል የስፔሻሊቲ ስልጠናም መስጠት ጀምሯል።
የጥርስ ህክምና ኮሌጁ አሁን ላይ ስፔሻሊስት የሚባሉ ሀኪሞች ባይኖሩትም ዶክተሮች ግን በበቂ ሁኔታ አሉት፤ እየፈተነው ያለው ችግር ግን አቅርቦት (ግብዓት) መሆኑ ደግሞ ዶክተር ላቀው አጽዕኖት ሰጥተው ይናገራሉ።
በመሆኑም ይላሉ በተለይም የአቅም ማነስ ያለባቸው የውጪውን ገበያ ተቋቁመው መታከም የማይችሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን እንደ ህመማቸው ደረጃ ለማከምና ከችግራቸው ለማላቀቅ ኮሌጁ አይነተኛ ሚና እንዳለው በመገንዘብ በተቻለ መጠን መንግስትም ትኩረት ሰጥቶት ያለበትን የግብዓት እጥረት ሊፈቱለት እንደሚገባም ያነሳሉ።
የአገራችን የጥርስ ህክምና ደረጃ
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በየመንገዱ የተሰቀሉ ማስታወቂያዎች እንዲሁም በመገናኛ ብዙሀን ከሚነገሩ ማስታወቂያዎች አብዛኛውን ሰዓት የሚይዙት የጥርስ ህክምና ማዕከላት ናቸው ቢባል ምንም ማጋነን የለውም። ግን ደግሞ እነዚህ በማስታወቂያ ብዙ የሚመስሉን የህክምና ተቋማት ወደ ስራ ሲገቡ ብሎም ለህብረተሰቡ ሲከፋፈሉ ቁጥራቸው እዚህ ግባ የሚባል ካለመሆኑም በላይ በአገልግሎት አሰጣጣቸውም እጅግ ውድ ስለመሆናቸው ባለሙያው ይናገራሉ።
ጥርስ ህክምና ደረጃችን ገና በሚባል ደረጃ ላይ ያለ ነው ፤ የጥርስ ህክምና ተቋማት ተበታትነው መስራታቸው ውጤታማ እንዳይሆኑ አድርጓቸዋል፡፡ እንዲሁም ህብረተሰቡ ጋር ያላቸው ተደራሽነት ከባዶ ይሻላል ካልሆነ በቀር ምንም ነው ይላሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ በየሰፈሩ የጥርስ ህክምና እንሰጣለን በማለት የሚያስተዋውቁ የከፈቱ ሁሉ በእውነት በሙያው የተካኑ አገልግሎቱንም በትክክል የሚሰጡ ናቸው ወይ ተብሎ ቢጠየቅ ነገሩ ሌላ ነው የሚሆነው።
ይህ ዓይነቱ ችግር እንዲመጣ ያደረገው ደግሞ ትምህርቱ በሚፈለገው ልክ አለመስፋፋቱ ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት አናሳ መሆኑ ነው። ይህ አለመሆኑ ሙያው እንዳያድግ በዛው ልክ ደግሞ የሚቆጣጠረውም አካል እንዳይኖር አድርጎታል ይላሉ።
“የጥርስ ህክምና ሲባል ጠቅለል ያለ ነው ግን ደግሞ በውስጡ በጣም ብዙ ዘርፎች ያሉት ነው። ለምሳሌ መንቀል መሙላት ማሰር ድድና ጥርስን የተመለከተ ህክምናና ሌሎችም ብዙ ዘርፎች አሉ፡፡ ለእነዚህ ሁሉ ደግሞ በየራሳቸው ስፔሻሊቲ ያላቸው በመሆኑ ባለሙያውም በዛው ልክ የበቃ ሊሆን ይገባል”።
ለሙያው አለማደግ እንቅፋት የሆኑ ነገሮች
የህክምና ሙያ ክቡር የሆነ በዛውም ልክ የሰውን ልጆች ህይወት የሚታደግ በጣም በርካታ ሀላፊነቶችን የተሸከመ ቢሆንም የተሰጠው ትኩረት እየተደረገለት ያለው ድጋፍ ግን አሁንም በጣም አናሳ ስለመሆኑ ይነገራል። ለዚህ ደግሞ ዋናው ምክንያት የአገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት ደረጃ ቢሆንም ከዛ ጎን ለጎን ግን በህብረተሰቡ ዘንድ ያለው አመለካከትና የስራ ጫናው መጠቀስ የሚችሉ ናቸው።
ከነዚህ በጣም ትልቅ ትኩረት ከሚሹ ነገር ግን የሚፈልጉትን ትኩረት ከተነፈጉ የህክምና ዘርፎች መካከል ደግሞ የጥርስ ህክምና አንዱ ነው። አንድ የታመመን ጥርስ ለማከም የሚያስፈልገው የሰው ሃይል የመሳሪያ ዓይነትና ብዛት በውል የሚታወቅ እርሱን ለማግኘት ደግሞ ብዙ የውጭ ምንዛሪ ማውጣት የሚፈልግ ቢሆንም እንደ ሌሎቹ የህክምና ዘርፎች ሁሉ አሁንም በችግር ውስጥ ስለመገኘቱ የህክምና ባለሙያው ዶክተር ላቀው ይናገራሉ።
“የጥርስ ህክምና ላለማደጉ ምክንያቶቹን በሁለት ጎራ ከፍሎ ማየት ይቻላል ። አንዱ በዘርፉ የተሰማራው ባለሙያ በብቃት ጊዜውን ሁሉ መስዋዕት አድርጎ መስራት አለመቻሉ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ጤና ሚኒስቴር በራሱ እንደ እናቶችና ህጻናት ጤና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች አስቸኳይና ቅድሚያ ማግኘት አለባቸው በማለት ሙሉ ትኩረቱን ማዞሩ ለዘርፉ የሚሰጠው ድጋፍ እንዲቀንስ አድርጎታል። በመሆኑም ምናልባት የጥርስ ህመም እንደ እናቶች ጤናም ሆነ እንደሌሎቹ ተላላፊ ያልሆኑ ግን ደግሞ አጣዳፊ የሆኑ የህመም ዓይነቶች የሚያስቸኩል ባይሆንም ህብረተሰቡን በማሰቃየት ግን ሚናው ትንሽ ባለመሆኑ ትኩረት ሊያገኝ ይገባል።
ለሙያው ትኩረት ማግኘት የባለሙያው ሃላፊነት
“ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ ባለእዳ አይቀበለውም” የሚል አገራዊ አባባል አለ። አዎ ባለቤቱ ትኩረት ያልሰጠውን ባለቤቱ ይህንን እፈልጋለሁና በዚህ ደረጃ ትኩረት ላግኝ ብሎ ያልወተወተበትን ነገር ማንም ሊያስታውሰው አይችልምና በሙያው ውስጥ ያሉ ባለሙያዎች ለሚሰሩት ስራ ክብርና ፍቅር በመስጠት የሚያስፈልጋቸው ነገሮች እንዲሟሉም የሚመለከተውን አካል መጎትጎት እንዳለባቸው ዶክተር ላቀውም ያምናሉ።
እርሳቸው እንደሚሉትም “ የጥርስ ህክምና ማህበር ተብሎ የተቋቋመው አካል ለዚህ ትልቁን ሃላፊነት በመውሰድና ስራው ምን ያህል ከባድ የሚፈልገው መሳሪያ ዘመኑ የሚጠይቀውን ቴክኖሎጂ የያዘ መሆኑን በማስረዳት ጤና ሚኒስቴርንም ሆነ ሌሎችን መጎትጎት አለበት። ህብረተሰቡም ሲታመም ብቻ ሳይሆን የጥርስ ህክምና ምንድን ነው ? ምን ያስፈልገዋል? ላለመታመም ምን ማድረግ አለብኝ? ስታመም ደግሞ የት ሄጄ ምን ዓይነት እርዳታ ነው የሚሰጠኝ? የሚለውን በማየትና የጎደሉ ነገሮችም እንዲሟሉ መጠየቅን መልመድ ያስፈልጋል” ይላሉ።
ለውጥ እንዲመጣ የራስ ሃላፊነት
የህክምን ክፍሉ እዚህ እንዲደርስ የእርሳቸው አበርክቶ ብዙ መሆኑን ብዙዎች ይናገራሉ። እርሳቸውም ኮሌጁ አድጎ በጥርስ ህክምና ዘርፍ ብዙ አንቱታን ያተረፉ ባለሙያዎች እንዲያፈራ ያላሰለሰ ጥረትን እያደረጉ እንደሚገኙም ይናገራሉ።
“እኔ በተቻለኝ መጠን ይህ የትምህርትና የህክምና ተቋም ራሱን ችሎ እንዲቆም ብሎም በርካታ ችግር ፈቺ የሆኑ ባለሙያዎችን እንዲያፈራ እንዲሁም አገልግሎቱን ፈልገው የሚመጡ የህብረተሰብ ክፍሎችም በምንሰጠው አገልግሎት ረክተውና ከህመማቸው ተፈውሰው እንዲሄዱ የአቅሜን አደርጋለሁ” ይላሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ በውጭም በአገር ውስጥም ያሉና አቅም ያላቸው ሊደግፉት የሚችሉትን አካላት በማሰባሰብ የኮሌጁ ህግን ደንብ በሚፈቅደው መሰረት ስራዎችን እንዲያግዙ ከፍተኛ የሆነ ጥረት እያደረጉም ስለመሆኑ ነው የሚናገሩት።
ከዚህ በተጓዳኝ ግን መንግስትም የትምህርትና የህክምና ማዕከሉ እንዲጠናከር በተለያዩ መንገዶች እገዛውን ቢያደርግ የሚፈለገው ደረጃ ላይ ለመድረስ እንደሚቻልም ነው አስምረው የሚናገሩት።
የጥርስ ህመም በዚህ ደረጃ ለመስፋፋቱ ምክንያት
የሰው ልጅ ጥርስ ሁለት ጊዜ ነው የሚበቅለው። ጥንቃቄም መጀመር ያለበት ከዛን ጊዜ ጀምሮ ነው። በአገራችን ግን የባለሙያው ችግር እንዲሁም ጥርስ በህብረተሰቡ ዘንድም ሲያም ካልሆነ በቀር እንደ ትልቅ ነገር የማይታይ ከመሆኑ አንጻር የሚሰጠው ትኩረት ለማጽዳት የሚደረገው ጥረት እጅግ አናሳ ነው። ያንን ተከትሎም አሁን ላይ በተለይም ህጻናት ለዚህ ህመም በብዛት እየተጋለጡ ይገኛሉ።
ወላጆች ልጆቻቸው ጥርሳቸውን ሲያማቸው ወደ ህክምና ይዘው ይመጣሉ ፤ ነገር ግን አንዳንዴ ችግሩ ከባሰ በኋላ ስለሚመጡም ችግሩን በጊዜ ለመፍታት ልጆቹን ቶሎ ከህመማቸው መታደግ አይቻልም። ይህ ከሚሆን ግን ልጆች ሁለት ዓመት ከሞላቸው ቀን ጀምሮ ጥርሳቸውን ቢያማቸውም ባያማቸውም ወደ ህክምና ባለሙያ በማምጣት አበቃቀሉ እንዴት ነው፤ ውስጡ የተጎዳ ጥርስ አለው የለውም፤ የሚለውን ማሳየት በየጊዜው በሚሰጣቸው ቀጠሮ መሰረት መምጣት ቢችሉ የልጆች ጥርስ ጤናማነቱ እንደተጠበቀ ይቆያል ይላሉ ዶክተር ላቀው።
በጠቅላላው ስለ ጥርስ ጤንነት መልዕክት
ማንኛውም ሰው ህጻንም ይሁን አዋቂ ጥርሱን በቀን ሁለት ጊዜ ማጽዳት አለበት። የመጀመሪያው ጠዋት ቁርስ ከተመገበ በኋላ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ማታ ወደመኝታ ከመሄዳችን በፊት ነው። ህጻናት ልጆች ደግሞ ጣፋጭን ጨምሮ ማንኛውንም አይነት ሀይል ሰጪ (ካርቦሃይድሬት) ምግቦችን ከተመገቡ በኋላ ጥርሳቸውን ማጽዳት እንዳለባቸው ማስተማር ያስፈልጋል።
በሌላ በኩል ደግሞ ጥርስ ከተቦረቦረ ወይም ከጠቆረ እስኪባባስ ከመጠበቅ ይልቅ በፍጥነት ወደጤና ተቋም በመምጣት ማሳየት ከተቻለ ምናልባትም ችግሩ በቶሎ እልባት አግኝቶ ጥርሱም ወደነበረበት ሊመለስ የሚችልበት ሁኔታ ይኖራል።
ምኞት
“በጥርስ ህክምናው ዘርፍ ቢሆን ብዬ የምመኘው የጥርስ ህክምና ግብዓቶች ሞልተውና ተትረፍርፈው ስፔሻሊስት ሀኪሞችም ቁጥራቸው ከፍ ብሎ አገልግሎት ፈላጊውም በደንብ በተመጣጣኝ ዋጋ መገልገል ሲችል ማየት ምኞቴ ነው” ።
መልዕክት
እንግዲህ ይህ ትልቅ የትምህርትን የህክምና ማዕከል ቢሆንም ከላይ እንደገለጽኩት የተሰጠው ትኩረት አናሳ መሆን ብሎም ያልተሟሉለት ግን ደግሞ ቢሟሉለት ብዙ ባለሙያዎችን ማፍራት የሚችል አቅም ያለው መሆኑን ሁሉም እንዲያውቅ የመገናኛ ብዙሀን ሃላፊነት ወስደው ቢሰሩ እፈልጋለሁ።
ሌላው አቅም ያላቸው የውጭም ይሁን የአገር ውስጥ ባለሀብቶች መንግስትን በማገዝ ተቋሙ በቴክኖሎጂ በመሳሪያ እንዲታገዝ ቢያደርጉ በማለትም ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 23/2013