አስናቀ ፀጋዬ
ከቻይና ሁቤ ግዛት ሁዋን ከተማ መነሻ ያደረገው ኮቪድ- 19 ቫይረስ ወረርሽኝ በሽታ ስርጭት ዓለምን ከማዳረሱ በተጨማሪ መልኩን ቀይሮ ለሰው ልጅ ፈተና መሆኑን ቀጥሏል ።በወረርሽኙ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ ተይዟል ።በርካቶችም ይህችን ዓለም ተሰናብተዋል ።
በሽታው ካደረሰው ሰብአዊ ጉዳት ጎን ለጎን በዓለም አቀፍ ምጣኔ ሀብት ላይም ከባድ ቀውስ አስከትሏል ።በተለይ በወረርሽኙ ምክንያት ዓለም አቀፍ የንግድ እንቅስቃሴዎች በእጅጉ በመዳከማቸውና አብዛኛዎቹ ሀገራትም ሙሉ ትኩረታቸውን ህዝቦቻቸውን ከበሽታው መከላከል ላይ በማድረጋቸው ቀላል የማይባል ኢኮኖሚያዊ ቀውስ አጋጥሟቸዋል ።
ወረርሽኙ እለት በእለት እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ አለመሆኑን የተረዱ አብዛኞቹ ሀገራት ወረርሽኙን ለመከላከል የሚያደርጉትን የእንቅስቃሴ ገደቦቻቸውን በማላላት ተዳክሞ የቆየው ኢኮኖሚያቸው እንዲያንሰራራ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ ።
ይሁን እንጂ ወረርሽኙ በአዲስ መልክ ማገርሸትና አዲስ ለውጥ እያመጣ መሆኑን ተከትሎ ሀገራት የበሽታውን እየተከላከሉ የደቀቀውን ኢኮኖሚያቸውን ለማነቃቃት እያደረጉ ያሉትን ጥርት ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ አድርጎታል ።
አሜሪካንን ጨምሮ ሌሎች የአውሮፓ ሃገራት ለበሽታው መከላከያ የሚሆን ክትባት ማግኘታቸው ቢነገርም ክትባቱን ለዜጎቻቸው በፍጥነት የማዳረሱ ስራ ደግሞ ተጨማሪ ራስ ምታት ሆኖባቸዋል ።ክትባቱ ለዜጎች እስኪደርስ የሚወስደው ግዜም ወረርሽኙን ይበልጥ እንዳያባብስ ስጋት ፈጥሯል ።
የክትባቱ መዘግየት በተለይ እንደ አፍሪካ ያሉ ታዳጊ ሀገራት ላይ ከፍተኛ ስጋት ደቅኗል ።እያጋጠመ ያለው ተደራራቢ ችግር በመጠኑም ቢሆን እየተነቃቃ የመጣውን የዓለም ምጣኔ ሃብት ወደኋላ እንዳይጎትተው የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች እያስጠነቀቁ ይገኛሉ ።
ብሉንበርግ ከሰሞኑ ባዋጣው መረጃ ክትባቶችን በመላው ዓለም አስጀምሮ በፍጥነት ለማዳረስ ረጅም ጊዜ የሚወስድ መሆኑ እያንሰራራ በመጣው የዓለም ምጣኔ ሃብት ላይ ገና ከፈረንጆቹ ዓመት መባቻ አደጋ እንደጋረጠበት ጠቅሷል ።
ካለፈው ዓመት የኢኮኖሚ ውድቀት በመነሳት በተወሰነ ጊዜ ውስጥ በፍጥነት ለማገገም የዓለም ምጣኔ ሃብት እድገት አሁንም በሂደት ላይ ያለ ቢሆንም እድገቱ ረዘም ያለ ጊዜ ሊወስድ ስለሚችል አስቀድሞ እንደተተነበየው ሊሆን እንደማይችል በመረጃው ተመላክቷል ።
የዓለም ባንክም የዚህን ወር የዓለም ምጣኔ ሃብታዊ እድገት ትንበያውን በ4 ከመቶ ማሻሻሉንና በተመሳሰይ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅትም በዚህ ሳምንት ይህን አሃዝ በራሱ አተያይ እንደሚያሻሽለው በመረጃው ተጠቅሷል ።
እንደመረጃው በጃፓን፣ በአውሮፓ ሃገራትና በተለይም በእንግሊዝ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ተጨማሪ የእንቅስቃሴ ገደቦች ተፈፃሚ በመደረጋቸው ድርብ ምጣኔ ሃብታዊ ውድቀት የሚጠበቅ ሲሆን፣ በተመሳሳይ በአሜሪካም የችርቻሮ ወጪዎችና የሰራተኞች ቅጥር ኢኮኖሚውን እየጎተቱ በመሆናቸው የፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አዲስ አስተዳደር ተጨማሪ 1.9 ትሪሊዮን ዶላር ዋጋ ያለው የበጀት ማበረታቻ ያስፈልጋል ።
የወረርሽኙን ስርጭት ወዲያው በማቆም ቻይና ኢኮኖሚዋን በ‹ቪ› ቅርፅ እንዲያገግም ማድረጓንና ነገር ግን ቤጂንግ አሁንም በእንቅስቃሴ ገደብ ውስጥ በመሆኗ ሸማቾችን እንዳሳሰበ የብሎምበርግ መረጃ ጠቅሶ፤ የተሻለ የኢኮኖሚ እድገት በማስመዝገብ ረገድ የፈረንጆቹ አዲስ ዓመት 2021 ገና ከጅምሩ አስጨናቂ እንደነበር አስታውሷል ።
በብሉምበርግ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ የሆኑት ቶም ኦርሊክ ‹‹ክትባቱ በስፋት ከመሰራጨቱ አስቀድሞ የኢኮኖሚ እድገቱ ወደነበረበት ሁኔታ ይመለሳል ማለት የማይመስል ነው›› ሲሉ ገልፀዋል ።
በፈረንጆቹ አዲስ ዓመት 2021 በመጀመሪያዎቹ የወሩ ሳምንቶች ውስጥ የተመዘገበው የዓለም ምጣኔ ሃብት እድገት ጨለማ መስሎ ቢታይም የፋይናንስ ገበያዎች በመንግስት ተስፋ ሰጪ ማብረታቻዎችን ማግኘታቸውን በዚሁ ከቀጠሉና የክትባቱ በፍጥነት መጀመር ምጣኔ ሃብቱ መልሶ ሊያገግም እንደሚችል ቶም ኦርሊክ ተናግረዋል ።
የብሉምበርግ ዘገባ እንደሚያሳየው አሜሪካ፣ ብሪታንያ እና የአውሮፓ ህብረት ክትባቶችን ለዜጎች እያቀረቡ ሲሆን፣ በአንዳንድ የዓለም ክፍሎች ደግሞ ወረርሹኙን በስፋት ለመከላከል ክትባቶቹ በጅምላ የሚደርሱበትን ሁኔታዎች አመቻችተዋል ። ደካማ ኢኮኖሚ ባላቸው ሀገራትም ክትባቱ እንዲደርስ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ ።
የዓለም ጤና ድርጅት የክትባት መርሃ ግብሩ እንዲፋጠን በተለይ የበለፀጉ ሀገራት ታዳጊ ሃገራትን ካልረዱ ኢኮኖሚያቸው ሊጎዳ እንደሚችል በቀጣዩ ሰኞ በሚያደርገው ስብሰባ እንደሚያስጠነቅቅም ፋይናንሺያል ታይምስ የዓለም ንግድ ምክር ቤት ያወጣውን ጥናት ጠቅሶ መዘገቡንም መረጃው አስታውቋል ።
በድሃ ሀገሮች ውስጥ ያለው የክትባት መርሃ ግብር የአሁኑን ጉዞ ይዞ የሚቀጥል ከሆነም ምጣኔ ሃብታዊ እድገቶች በንግድ ሰንሰለቶች መቋረጥ ምክንያት ወረርሽኙ ከመከሰቱ በፊት ዓመታዊ ከነበረው አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርታቸው ውስጥ እስከ 2.4 ትሪሊዮን ዶላር የሚደርስ ኪሳራ እንደሚገጥማቸውም ሪፖርቱን ጠቅሶ ብሉምበርግ አመልክቷል ።
ከዚህ በመነሳትም ‹‹በዋሻው መጨረሻ ያለውን ብርሃን ለማየት ገና ረዥም እና አስቸጋሪ መንገድ ይቀረናል›› ሲሉ የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ኤሪክ ኔልሰን ተናግረዋል ።ወረርሽኙ ዓለምን ማሸበሩን እስከቀጠለ ድረስም የዓለም ምጣኔ ሃብት በቀላሉ ወደነበረበት ሁኔታ ሊመለስ እንደማይችል ያላቸውን ስጋት አስቀምጠዋል፡፡
በመሆኑም ገና በፈረንጆቹ አዲስ ዓመት መባቻ የጨለመውን ዓለም አቀፍ ምጣኔ ሃብት እድገት ወደ ነበረበት ለመመለስ ክትባቱን የሚያገኙ ያደጉ ሀገራት መሪዎች በአስፈላጊው ቦታና በወረርሽኙ ይበልጥ ተጋላጭ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች በትክክል ለማድረስ በሚያደርጉት ጥረት እንደሚወሰን የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ገልፀዋል ።
ሸማቾች እና ሻጮች ኮሮናን መላመድ የሚቻልባቸውን መንገዶች በማግኘታቸው የእንቅስቃሴ ገደቦችና እገዳዎች በአሁኑ ዓመት የፈጠሩት ኢኮኖሚያዊ ተፅእኖ ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር ዝቀተኛ እንደነበርም የብሉምበርግ መረጃ አስታውሶ፤ እያገገመው በመጣው የዓለም ምጣኔ ሃብት የቻይና መሪነት ቫይረሱን መቆጣጠር መቻሏ አንዱ ማሳያ መሆኑን ጠቁሟል ።
‹‹የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከዚህ የከፋ ይሆናል ብለን አስበን ነበር ።ይሁንና የሚዘገይ ነገር ግን የማይዛባ ዓለም አቀፍ ምጣኔ ሃብታዊ ማገገም እናያለን›› ሲሉ የእስያ ፓስፊክ ምጣኔ ሃብታዊ ተንታኙ ሹዋን ሮሽ በመጨረሻ ተናግረዋል ።
አዲስ ዘመን ጥር 19/2013