ውብሸት ሰንደቁ
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የሀገሪቱን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ይመራሉ ተብለው የተለዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መካከል ተጠቃሽ ናቸው።
መንግሥት በተለይ ለአዲስ አበባና ለአዳማ ዩኒቨርሲቲዎች በዙሪያቸው እስከ 200 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎች ጋር ተሳስረውና ተሰናስለው በመሥራት የልህቀት ማዕከላት አቋቁመው አገሪቱን ወደ ፊት ለማራመድ የሚበጅ ሃሳብ እንዲያመነጩ ኃላፊነት ሰጥቷል።
ይህን መነሻ በማድረግ ኢኮስ የተባለ ፋብሪካ ከአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ጋር በመተባበር የተመረጡ አምሥት ሴክተሮች ላይ ለመሥራትም ስምምነት አድርጓል። የዚህ ጥምረት ዓላማው የልህቀት ማዕከሎችን በመመሥረት የኢንዱስትሪዎችን ችግር በጥናትና ምርምር መፍታትና ለአምራች ኢንዱስትሪዎች ምቹ ሁኔታ መፍጠር ነው።
ፋብሪካዎች የሀገር ውስጥ ግብዓቶችን የመጠቀም አቅማቸውን ማሳደግ፤ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በመተካት የውጭ ምንዛሬን ማዳን፤ ምርቶችን በመላክ የውጭ ምንዛሬ ማምጣት፤ የቴክኖሎጂ ሽግግርን ማፋጠን፤ የሥራ ዕድል መፍጠር እና የመሳሰሉት በልህቀት ማዕከላት ትኩረት ተሰጥቶ የሚሠራባቸው ናቸው።
የልህቀት ማዕከሎቹ የችግር ፈቺነት ሚና በትራንስፖርትና ተሽከርካሪ፤ የምርታማነትን ምህንድስና፤ የቁስ ሳይንስና ምህንድስና (Materials science and engineering)፤ በኤሌክትሪክና ኤሌክትሮኒክስ ዘርፍ እና በፋርማሲዩቲካል ዘርፎች ላይ የተመሰረተ ነው።
ለአብነት ያህልም በትራንስፖርት እና የተሽከርካሪ ምህንድስና ዘርፍ እንዲከናወኑ ከሚጠበቁ መካከል በመጀመሪያው ዙር ትናንሽ አቅም ያላቸውን ተሽከርካሪዎች በኤሌክትሪክ እንዲሠሩ ማድረግ ነው። ይህ በዋናነት በገቢ ምርት መተካት ላይ ያተኮረ ነው።
ከአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ጋር የመግባቢያ ስምምነት የተፈራረመው ከመዲናችን አዲስ አበባ ደቡብ ምሥራቅ አቅጣጫ 37 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ኦሮሚያ ክልል የሚገኝ ኢኮስ (EKOS) የብረት ፋብሪካ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማሕበር የሚሰኝው የብረት ፋብሪካ ነው። ፋብሪካው ከዛሬ ሥምንት ዓመት በፊት በቀድሞው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶክተር) ጋባዥነት ከኮርያ ወደ ኢትዮጵያ በመጡ ባለሀብት የተመሠረተ የብረት ፋብሪካ ነው።
በመጀመሪያው ምዕራፍ የተገነባ ብረት አምራች ፋብሪካ 15,200 ሜትር ስኩዬር ላይ አርፏል። ፋብሪካው እ.ኤ.አ ጁን 2014 ላይ የኢንቨስትመንት ፈቃድ አግኝቶ እ.ኤ.አ ኦክቶበር 2015 ላይ ግንባታውን ጀምረና የመጀመሪያ ዙር ግንባታውን ኦክቶበር 16 ቀን 2018 ላይ አጠናቆ አስመረቀ።
የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታው ብቻ 30 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ፈጅቷል። የድርጅቱ ዓላማ ሁልጊዜ መሻሻልን የሚያሳይ ምርት ማቅረብ ነው። ከማህበረሰቡ ጋር አብሮ ማደግም የካምፓኒው አንድ መርህ ነው።
ፋብሪካው ለኢንቨስትመንት ከተረከበው 10 ሔክታር መሬት ውስጥ በ60 ሺህ ሜትር ስኩየር ላይ የማምረቻና አስተዳደር ጉዳይ መፈፀሚያ ሕንፃ ለመሥራት ነው የታቀደው። የመጀመሪያው ምዕራፍ 30 ሚሊዮን ዶላር የወሰደ ሲሆን በ15 ሺህ ሜትር ስኩየር ላይ አርፏል። ፋብሪካው ሥራውን የጀመረ ቢሆንም አሁንም የመጀመሪያው ምዕራፍ ቀሪ ሥራዎች አሉ።
በሁለተኛው ምዕራፍ ላይ የሚገነባው ሕንፃ 45 ሺህ ሜትር ስኩየር ላይ የሚያርፍ ነው። ይህ ፋብሪካ በሙሉ አቅሙ ማምረት ሲጀምር 300 ሺህ ቶን በዓመት ያመርታል። የመጀመሪያው ምዕራፍ አቅም 150 ሺህ ቶን ሲሆን በሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ 150 ሺህ ቶን ለማምረት ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ ነው። አሁን በተለያዩ ምክንያቶች እያመረተ ያለው ፌሮ ብረት ብቻ ነው።
የፋብሪካው በተለያዩ ምዕራፎች የተከፋፈሉት ግንባታዎች ሲጠናቀቁ 300 ሺህ ሜትሪክ ቶን በዓመት እንዲያመርት የታቀደለት ሲሆን አሁን የመጀመሪያው ምዕራፍ እያመረተ ያለው ግማሽ ያህሉን ቶን ነው። በመጪዎቹ አሥር ዓመታት በ2032 ዓ.ም የማምረት አቅሙን 300 ሺህ ቶን ለማድረስም እየሠራ ይገኛል።
የፋብሪካው ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ ኮሪያዊ ሲሆኑ ሥማቸው አቶ ሼል ኤች ቹ ይባላሉ። አቶ ሼል ኤች ቹ እንደነገሩን ፋብሪካው ሲጠናቀቅ ፌሮ ብረት፣ የአንግል ብረቶች፣ ማስተላለፊያ ብረቶች፣ ጠፍጣፋ ብረት፣ የተለያዩ ሽቦዎችንና ሌሎች በርካታ ብረት ነክ ምርቶችን የማምረት አቅም የሚኖረው ሲሆን በአሁኑ ጊዜ በዋናነት እያመረተ የሚገኘው ፌሮ ብረት ነው።
በዚህ ፋበሪካ ፌሮዎች ተመርተዋል ተብለው ጥራታቸው ሳይፈተሽ ለገበያ አይቀርቡም። ከብረት ባለሙያዎች እንደሰማነው ፋብሪካው በየአንድ ሰዓት ከተመረቱ ብረቶች (ፌሮዎች) ቁራጭ ናሙና በመውሰድ የጥራት ፍተሻ ይደረጋል። በዚህም የፌሮዎቹ የመታጠፍ አቅማቸውና የመሸከም ጥንካሬያቸው ይፈተሻል።
ፋብሪካው እስከ 32 ሚሊ ሜትር መጠነ ውፍረት ያላቸውን ፌሮ ማምረት የሚችል ሲሆን አሁን የተጠናቀቀው የመጀመሪያው ምዕራፍ ከ10 እስከ 24 ሚሊ ሜትር መጠነ ውፍረት ያላቸው ፌሮዎች በማምረት ላይ ነው። ለወደፊቱ በጥቅል መልክ ባለ ስድስት እና ባለ ስምንት ሚሊ ሜትር መጠነ ውፍረት ያላቸውን ሽቦዎች ያመርታሉ። ይህ ምርት በሰከንድ ከ24 ሜትር በላይ በሰከንድ መመረት የሚችል ፍጥነት ያለው የብረት ምርት ነው።
በፋብሪካው የሚስተዋሉ አንዳንድ ችግሮች ተቀርፈው በሙሉ አቅሙ ማምረት እንዲችል ከአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ጋር ተጣምሮ መሥራት አስፈልጎታል። በጥምረት መሥራት መቻላቸው አሁን የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት ብቻ ሳይሆን ባለሀብቱ ለወደፊቱ ማልማት ባሰቧቸው ዘርፎች ዙሪም አስቀድሞ በጥናትና ምርምር ላይ የተመሠረቱ ውሳኔዎችን ለመወሰን አጋዥ ነው።
ዩኒቨርሲቲውና ኢንዱስትሪው ባደረጉት የመግባቢያ ሰነድ ፊርማ በተለያዩ መሥኮች ላይ በጥምረት እንደሚሠሩ ከዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንትና ከፋብሪካው ሥራ አስኪያጅ ተገልጧል። የፋብሪካው ሥራ አስኪያጅ በተለይ ለወደፊት በጥምረት ብንሠራባቸው አዋጭ ናቸው ያሏቸውን የኢንቨስትመንት ዘርፎች በዝርዝር አስረድተዋል። በኢትዮጵያ ተገኘ የተባለውን የነዳጅ ተረፈ ምርት በመጠቀምም የተለያዩ ምርቶችን ለማምረት ምቹ ሁኔታዎች መኖራቸውን የፋብሪካው ሥራ አስኪያጅ ገልጸዋል።
በተጨማሪም በሀገር ውስጥ ያሉ ጥሬ ዕቃዎችን በመጠቀም የአፈር ማዳበሪያ የማምረት ሃሳብ እንዳለ በሥራ ዕቅዱ ውስጥ ተካትቷል። ከዚህም ባሻገር ለግብርናው ዘርፍ ግብዓትነት ከውጪ የሚመጡ ናይትሮጅን፣ ፖታሲየምና የመሳሰሉትን ምርቶች ከዚሁ ከሀገር ውስጥ በጥናትና ምርምር ላይ ተመርኩዞ በማምረት የውጪ ምዛሬን ለማስቀረት ታሳቢ ተደርጓል።
እነዚህን ለማምረት የሚያስችሉ ጥሬ ዕቃዎች በብዛት ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚገኙ በተለያዩ ጥናቶች ተረጋግጧል። ይህን በማድረግ ግብርናውን ትራንስፎርም ማድረግ፣ በምግብ ራስን መቻልና ምርታማነትን በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር ይቻላል። በተጨማሪም በኦሮሚያ፣ አማራና ትግራይ ውስጥ በከፍተኛ ብዛት የሚገኘውን ኳርትዝ በመጠቀም የተፈጥሮ የአፈር ማዳበሪያ ማምረት የሚያስችል አቅም አለ። በእርግጥ ይህን ለመሥራት ኢኮስ በሂደት ላይ ይገኛል ብለዋል ሥራ አስኪያጁ።
ከኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ጋር በመሆን ከኮርያ የመጡ ቴክኖሎጂዎች ሙከራ እየተደረገ ነው። በሙከራ ደረጃ ያለው ስኬታማ መሆን ከቻለ ከሀገር ውስጥ ፍጆታ አልፎ ኤክስፖርት የማድረግ ከፍተኛ አቅም ይኖራል።
በዘመናዊ ግብርና ኮርያዎች ትልቅ ልምምድ ስላላቸው ይህን ተጠቅመን ፍራፍሬዎችንና የጓሮ አትክልቶችን እንዲሁም ሌሎች ምርቶችን በመጀመር እና በኢንዱስትሪዎች አምርቶ ለውጭ ገበያና ለሀገር ውስጥ ፍጆታ ለማቅረብ ይሠራል። እጣንና ሞሪንጋ የመሳሰሉትንም ተጠቅሞ ሊሠሩ የታሰቡና ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶች ተጠቃቅሰዋል።
አቶ ሼል ኤች ቹ እንደገለጡት ኢትዮጵያ ለመኪኖች፣ ለጀኔሬተሮችና ለልዩ ልዩ ነዳጅ ተጠቃሚዎች ቢያንስ በየዓመቱ 30 ሚሊዮን ሊትር ከውጪ ታስገባለች። ይህ ፕሮጀክት ተሳክቶ ኢትዮጵያ ውስጥ የተገኙ የነዳጅ ምንጮችን ተጠቅሞ እዚህ መሥራት ከተቻለ 100 በመቶ ከውጭ የሚመጡ የተሽከርካሪና የጀኔሬተር ዘይቶችን በሀገር ውስጥ መተካት ይቻላል።
ይህ የውጭ ምንዛሬን ከማስቀረቱም ባሻገር በዚህ መስክ የሚሠሩ ኢንቨስትመንቶችን በመሳብ በዘርፉ የሀገሪቱን ተፈላጊነት ይጨምረዋል። ሴንቴቲክ ዘይት እና የመሳሰሉት ምርቶች ኮርያ ውስጥ የሚመረቱ በመሆናቸው እና ፋብሪካው የኮሪያ በመሆኑ የአማካሪም ሆነ የቴክኖሎጂ እጥረት እንደማይኖር ባለሀብቱ ገልፀዋል።
ባለሀብቱ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ 1.5 ሚሊዮን ቶን ኬሚካል የአፈር ማዳበሪያ ወደ ሀገር ውስጥ ታስገባለች። ይህን ለማድረግ በርካታ የውጭ ምንዛሬ መጠን ያስፈልጋል። የሚገርመው እንደዚህ እየሆነ ያለው በሀገሪቱ ውስጥ ካሉ ጥሬ ዕቃዎች ግብዓቶችን አምርቶ ኬሚካልና የተፈጥሮ የአፈር ማዳበሪያ ለማምረት አቅም እያለ ነው ብለዋል ሥራ አስኪያጁ።
በግብርናው መስክ ለሚከናወኑ ተግባራት ውጤታ ማነት በአስረጅነት እንደተነሳውም ኢኮስ ከሌሎች ድርጅቶች ጋር የዛሬ 12 ዓመት አካባቢ 2 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስት በማድረግ የኡዝቤኪስታን ገበሬዎችን አሠልጥኖ ያለ አፈር በግሪን ውስጥ እንዴት ማምረት ያስቻለ ሲሆን አሁን ከፕሮጀክቱ በዓመት እስከ 200 ሚሊዮን ዶላር ድረስ ወደ ራሺያ በመላክ ከውጭ ንግድ ገቢ ይገኛል። በዚህ ረገድ ስናየው ኢትዮጵያ ያላት የዓየር ሁኔታ በጣም ጥሩ በመሆኑ በዘርፉ በጣም አትራፊ መሆን የሚያስችል ምቹ ሁኔታ አለ።
በዚህ መልኩ ከተሠራ ይህ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየው ወቅትን ጠብቆ የሚመረት ምርት ይቀርና ከዓመት እስከ ዓመት ማምረት የሚቻልበት ሁኔታ ይፈጠራል። እንዲያውም ለአብነት ባነሳናት ኡዝቤኪስታን ላይ በጣም በረዷማ የሆነ ወቅት ስላለ ይህን ቅዝቃዜ ለመከላከልና የምርት ዕድገቱን ለማስቀጠል ሙቀት ለመስጠት የኤሌክትሪክ ኃይል ይጠቀማሉ፤ ይህ ደግሞ ዋጋው ውድ እንዲሆን ያደርገዋል።
ኢትዮጵያን ስናይ ግን ያን ያህል ቀዝቃዛ ወቅት ስለሌለ የሚከፈል የኢነርጂ ዋጋ አይኖርም። ስለዚህ ኡዝቤኪስታን ታገኘዋለች ተብሎ ከተገለፀው ዓመታዊ ገቢ በላይ ኢትዮጵያ ማግኘት የምትችልበት ዕድል ሰፊ ነው ተብሏል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ በፋርማሲዩቲካ ዘርፉም ትልቅ አቅም ያላት ሀገር ናት። ከርቤን፣ ሞሪንጋንና ሌሎችን በርካታ ነገሮች ብንወስድ መድኃኒት ለመሥራት የሚያገለግሉና በሀገሪቱ በበቂ መጠን የሚገኙ መሠረታዊ ግብዓቶች ናቸው።
የኮርያ ባለሀብቶች እዚህ ላይ ለመሳተፍ ፍላጎት አላቸው። ከነዚህ ግብዓቶች የመጀመሪያው ሂደት ያለቀለት የመድኃኒት ግብዓቶች እንኳን ቢላክ ለኢትዮጵያ አዋጭ መሆኑን አቶ ሼል ኤች ቹ ባሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ በሰጡት ገለፃ አስረድተዋል።
የአዳማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ለሚ ጉታ በበኩላቸው በተለይ በኢንዱስትሪዎች ውስጥ የሚታዩ ችግሮችን በጥናትና ምርምር ለይቶ በመፍታት ረገድ ኃላፊነት መንግሥት ኃላፊነት እንደጣለባቸው የገለጡ ሲሆን ከኢንዱስትሪ ጋር መሥራት ትልቁ መንግሥት የሰጠን ተልዕኮ ነው ሲሉም አክለዋል።
በዚህም ከዩኒቨርሲቲው 200 ኪሎ ሜትር ካሉ ኢንዱስትሪዎች ጋር የመግባቢያ ስምምነት መፈራረማቸውን ገልጠዋል። እንደርሳቸው ገለፃ የዩኒቨርሲቲ መምህራንም ትምህርት በማይኖርበት ጊዜ ኢንዱስትሪዎችን በመጎብኘት እና ችግሮችን በመለየት በጥናት የተደገፈ የመፍትሄ ሃሳብ በማቅረብ ዩኒቨርሲቲዎች አሠራር እንዲሻሻል ያደርጋሉ።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት እንዳሉት በሁለተኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን አቅድ እንደተመላከተው ሀገሪቷ በሚቀጥሉት አምሥት ዓመታት 16 የልህቀት ማዕከላት ይኖራታል። ይህን ተግባራዊ እንዲያደርጉ ኃላፊነት የተጣለባቸው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ እኩል ተካፍለው እየሠሩ ነው።
ለአዳማ ዩኒቨርሲቲ ከተሰጡት ውስጥ የጠፈር ቴክኖሎጂ ላይ ምርምር ማድረግ፤ የቴክኖሎጂ ሥራዎችን መገጣጠምና ማምረት እና ሌሎችም አሉ። ከኢኮስ ጋርም ሰሞኑን በነበረው ከፊርማ ሥነሥርዓቱ ጋር የተለያዩ የልህቀት ማዕከሎችን በማቋቋም ረገድ አብሮ ለመሥራት ተወያይተናል ብለዋል።
ለሥምንቱም የልህቀት ማዕከላት ችግር ፈቺ ጥናቶችን እንዲያካሂዱ የሚያስችል የምር ምር ማዕከላት በመጠናቀቅ ላይ ነው። ይህ ከተጠ ናቀቀና የመሣሪያ ግዢዎች ካለቁ በኋላ ሀገሪቷ የኢንዱስትሪዎችን ችግሮች በምርምር ለመፍታት ትልቅ አቅም ይኖራታል ብለዋል የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት።
አዲስ ዘመን ጥር 12/2013