በኢትዮጵያ በትራክተር የማረስ ምጣኔ 25 በመቶ ደረሰ

አዲስ አበባ፦ በኢትዮጵያ በትራክተር የማረስ ምጣኔ ከነበረበት 5 ነጥብ ሰባት በመቶ ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ በተሠሩ ተከታታይ ሥራዎች በአሁኑ ጊዜ 25 በመቶ መድረሱን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

በግብርና ሚኒስቴር የግብርና መካናይዜሽን መሪ ሥራ አስፈጻሚ ተወካይ አቶ እሸቱ ሁንዴ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ በኢትዮጵያ በትራክተር የማረስ ምጣኔ ከአምስት ዓመት በፊት ከነበረበት አምስት ነጥብ ሰባት በመቶ በፍጥነት በማደግ በአሁኑ ጊዜ 25 በመቶ ላይ ደርሷል።

የግብርና መካናይዜሽንን በግለሰብ ደረጃ ማስፋፋት ከዋጋ አኳያ አንድ ኮምባይነር 40 ሚሊዮን ብር አካባቢ በመሆኑ በባለሀብቶች ወይም በተደራጁ ወጣቶች በኩል የማስፋፋት ሥራው ተመራጭ ሆኗል ብለዋል።

የግብርና መካናይዜሽን ትልቁ ሥራው ቴክኖሎጂን እንዲስፋፋ እና አርሶ አደሩ ጋር ተደራሽ እንዲሆን ማድረግ መሆኑን ጠቁመው፣ የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን የግብርና መካናይዜሽን አገልግሎት አሠራር ላይ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

በቴክኖሎጂ በመታገዝ የግብርና ሥራው በተከናወነባቸው አካባቢዎች ምርታማነት እየጨመረ መሆኑን የገለፁት አቶ እሸቱ፤ በ2016/17 የምርት ዘመን አርሶ አደሩ ምርቱን በግብርና ቴክኖሎጂዎች ታግዞ እየሰበሰበ ነው ብለዋል።

በግብርና ሚኒስቴር የ10 ዓመቱ ስትራቴጂክ እቅድ አሁን ያለውን 20 ሺህ ገደማ ትራክተር ወደ 65 ሺህ ለማሳደግ ታቅዶ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ኮምባይነር ከቀረጥ ነፃ ከመሆኑ በፊት በቁጥር ከ500 የማይበልጥ እንደነበር አውስተው፣ አሁን ላይ ሁለት ሺህ 700 መድረሱንና በቀጣይ 15 ሺህ ለማድረስ ታቅዷል። እንዲሁም አርሶ አደሩም በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል።

በግብርና መካናይዜሽን የአነስተኛ አርሶ አደር ምርትና ምርታማነትን በመጨመር ጥራትን በማሻሻል እንዲሁም የቅድመ እና ድህረ ምርት ብክነትን ለመቀነስ ሲሠራ መቆየቱን አንስተው፤ በዚህም ባለፉት ስድስት ዓመታት የግብርና መካናይዜሽን ቴክኖሎጂዎች አቅርቦት አገልግሎት አሰጣጡን አሻሽሏል ነው ያሉት።

የግብርና ማሽነሪዎች ከቀረጥ ነፃ እንዲሆኑ መፈቀዱ ለዘርፉ መዘመን የራሱ አስተዋፅዖ አድርጓል ያሉት አቶ እሸቱ፤ መንግሥት ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ማሽነሪዎቹ ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ ከፈቀደ ወዲህ በርካታ ቴክኖሎጂዎች ገብተዋል፤ እየገቡም ይገኛሉ። በዓይነትና በቁጥር በርካታ የሆኑ ማሽነሪዎች ሀገር ውስጥ በመግባታቸው በርካታ የመካናይዜሽን አገልግሎት ሰጪዎች እየተፈጠሩ እና የኪራይ አገልግሎት የሚሰጡ ባለሀብቶች ከአርሶ አደሩ ጋር እየተሳተፉ ነው ብለዋል።

ከአምስት ዓመት በፊት አምስት ሺህ ያህል ትራክተር እንደነበር አስታውሰው በአሁኑ ጊዜ ወደ 20 ሺህ ትራክተር ማሳደግ ተችሏል። የማሽነሪ ዋጋ ከቀረጥ ነፃ እንዲገባ የተደረገበት ሁኔታ የፍላጎት መጨመር መፈጠሩንና አርሶ አደሩ ቴክኖሎጂን በስፋት እንዲጠቀም ማስቻሉን ገልፀዋል።

በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነው በኮሪያ መንግሥት የገንዘብ ድጋፍ የተገነባው የግብርና መካናይዜሽን የልህቀት ማዕከል ተጠናቅቆ ማሽነሪዎችን እያስገባ መሆኑን ጠቁመው፣ የጥገና እና የሥልጠና ማዕከል ሆኖ አገልግሎት ለመስጠት አስተዋፅዖ እንደሚኖረው አመልክተዋል።

በኢትዮጵያ በትራክተር ማረስ እና የግብርና መካናይዜሽንን መጠቀም በኦሮሚያ ክልል ባሌ እና አርሲ አካባቢ ቀደም ብሎ ሥራ ላይ የዋለ መሆኑን አስታውሰው፣ አማራ፣ ሶማሌ እና አፋር ጨምሮ ወደ ሁሉም ክልሎች ሰፊ እንቅስቃሴዎች እንዳሉ ጠቁመዋል።

በየክልሉ 10 ያህል የእርሻ መካናይዜሽን አገልግሎት የሚሰጡ ማዕከላት መኖራቸውን ጠቁመው፤ ከዩኒየኖች ጋር በመሆን ማሽነሪዎችን መግዛት የማይችሉ አርሶ አደሮች በኪራይ እንዲያገኙ እየተደረገ ነው። አቅም ያላቸው ባለሀብቶች ገዝተው የማከራየት አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ ብለዋል።

አጨዳ ላይ ምርት ቀድሞ በሚደርስባቸው ቆላማ አካባቢዎች አገልግሎት ከሰጡ በኋላም ወደ ሌላ አካባቢዎች በመሄድ አገልግሎት እየሰጡ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የግብርና መካናይዜሽንን ከማስፋት አኳያ አገልግሎት አቅራቢ መሆኑን ጠቁመው፤ በሊዝ ፋይናንስ ችግር እየተቀረፈ ነው ብለዋል።

አሁን ላይ በትራክተር የማረስ ሁኔታው አምስት ሚሊዮን ሄክታር ደርሷል ነገር ግን ይህ በቂ ባለመሆኑ በቀጣይ 10 ዓመቱ ስትራቴጂክ እቅድ ወደ 11 ሚሊዮን ሄክታር በትራክተር ለማረስ እንደሚሠራ አመላክተዋል።

በመኸር ወቅቱ ከበጋ መስኖ ወጪ አምስት ሚሊዮን ሔክታር መሬት በትራክተር መታረሱን የግብርና ሚኒስቴር መግለፁ ይታወሳል።

በኃይሉ አበራ

አዲስ ዘመን ጥር 13 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You