ጽጌረዳ ጫንያለው
ከ38 ዓመት
በላይ 80 ዓመቱን እያከበረ
በሚገኘው የኢትዮጵያ ፕሬስ
ድርጅት ውስጥ ሰርቷል፡፡
በተለይም በበሪሳ ጋዜጣ
የስፖርት አምድ አዘጋጅነቱ
ይታወቃል፡፡ በጋዜጠኝነቱ አገሩን
በመወከል በተለያዩ የውጪ
አገራት ሄዶ የተለያዩ
ስፖርታዊ ውድድሮችን ዘግቧል። ከብዙ
አገራት
ልምዶችንም
ቀስሟል፡፡
በማህበራዊ
ህይወቱም
ቢሆን
አንቱታን
ያተረፈ
ነው፡፡
ይህ
ህይወቱ
በርካታ
ቁም
ነገሮችን
ያነገበ
በመሆኑም
ከህይወት
ልምዱ
እንዲያካፍለን
ለዛሬ
”የህይወት
ገጽታ‘
አምድ
እንግዳችን
አድርገነዋል፤
መልካም
ንባብ።
አዲስ ዘመን፡– እድገት ራስን ይሰራል፤ ትውል ድንም ይቀርጻል።ከዚህ አንጻር የአንተ አስተዳደግ ምን ይመስላል?
ጋዜጠኛ ተሾመ፡– እውነት ነው ሰው በአስተዳደጉ ምክንያት ሊበላሽም ሊስተካከልም ይችላል።አንድን ልጅ ቤተሰብ በስነምግባር ኮትኩቶ ካሳደገውና አካባቢውም ላይ የተመቻቸ መልካም ትስስሮችን ከዘራበት በልጅነቱ ብቻ ሳይሆን በወጣትነቱም ሆነ በጉልምስናው ሰው ወዳድ ይሆናል።ሁሉንም ከፍቅር ጋር እንጂ ከጥላቻ ጋር አያስተሳስረውም።ይህ ደግሞ ከራሱ አልፎ ለጎረቤቱ እንዲሁም ለአገሩ መልካም ዘር እንዲሆን ያደርገዋል።እኔም ዛሬ ከብዙዎች ጋር ተስማምቼ የኖርኩት ለዚህ ይመስለኛል።መጀመሪያ ቤተሰቤ፣ ከዚያ የአካባቢው ማህበረሰብ በሚገባ ጥሩ ዜጋ እንድሆን ለፍቶብኛል።መልካም ነገርም እየነገረ ነው ያሳደገኝ።በተለይም ስለ አገር ወዳድነት የተነገረኝ ነገር ዛሬ ድረስ ከአዕምሮዬ አይጠፋም።በባህሪ ከሰዎች ጋር የሚጋጭ አይነት ሰው ያልሆንኩትም ለዚህ ነው፡፡
ሰውን መውደድ፣ ማክበር እንጂ ጥላቻ የሚባል ነገር አልተሰበከልኝም።ታላላቆችን ማክበር እንጂ እነርሱን ማንጓጠጥና የእኔ አይደሉም ማለትን አልለመድኩም።እንዲያውም ውሎዬ ሁሉ በእድሜ ከሚበልጡኝ ጋር ነበር።ይህ ደግሞ የጋራ ጀግኖች እንዳሉን እንዳውቅ፣ ታሪክን እንድወድና እንዳነብ፣ ነጥሎ በብሔር ማየት የሚባል ነገር እንዳላስብ ያደረገኝ ነው።በተለይ ከሁሉም በላይ መረጋጋት ምግባሬ እንዲሆን አድርጎኛል።
አስቦ መናገር፣ እህ ብሎ ማድመጥንም አስተምሮኛል።ስለዚህም በተወለድኩበት የቀድሞ አርሲ ጠቅላይ ግዛት ጭላሎ አውራጃ ስሬ ወረዳ ባስሎ የምትባል የገጠር ቀበሌ ላይም ከዚህ ውጪ የሚሰበክ ነገር አልነበረም።እናም ከተወለድኩበት 1955 ዓ.ም አርብ ቀን ጥቅምት 23 ጀምሮ ይህንን ብቻ ነው እያየሁ ያደኩት።ይህ ደግሞ ለልጆቼ ሳይቀር ታሪክ ነጋሪና አስተማሪ እንድሆን አግዞኛል።እንደ አንድ ለእናቱ አይነት መጸሐፍት በቤቴ ሙሉ የሆኑትና የመጀመሪያ እትሞች መገኘት የቻሉትም ታሪክ ወዳድ ታሪክ አስረካቢ እንድሆን ተደርጌ ስላደግሁ ነው።
አዲስ ዘመን፡– ከአነበብከውና ከታሪክ ከሰማ ኸው አንጻር የነበርክበትን የኢትዮጵያ ታሪክ እንዴት ትገመግመዋለህ? ዛሬስ ትውልዱ ታሪክን የሚያይበትን ሁኔታ እንዴት አየኸው ?
ጋዜጠኛ ተሾመ፡– የኢትዮጵያ ታሪክ ለእኔ እንደሚገባኝ ለሌላው ላይገባው ይችላል።ምክንያቱም በተሰራንበት ልክ የሚመዘን ነው።የተነገረን ታሪክም ልዩነታችንን፤ እድገታችንና ማንነታችንን የተለያየ ያደርገዋል።ስለዚህም የእኛና የአሁኑ ትውልድ ታሪክን የሚረዳበት ሁኔታ የተለያየው ለዚህ ነው።በዚያ ላይ ታሪክ ጸሐፍቱ ከእውነቱ ጋር ምን ያህል ቃል የተገባቡ ናቸው የሚለው ጥያቄ ውስጥ ይገባል።ስለዚህም የሚወደውን መሪ ወይም ነገስታት መላክ አድርጎ መሳል ይመጣል።የሚጠላውን ደግሞ ሰይጣን ያደርገዋል።እናም ጸሐፍቱ እኛነታችንን፤ የታሪክ አረዳዳችንን ይወስኑታል።ነገር ግን የእኛም ድርሻ አለበት።ህይወት ባለው ነገርና ተጨባጭ የሆነውን ነገር ከታሪኩ ጋር የማዛመድ ሁኔታው የእኛ ሀላፊነት ነው።
የተነገረንን ብቻ የምንቀበል ከሆነ ከታሪክ መማር አንችልም።አሁን ያለን ታሪክ ላይ የተሻለውን ጨምረን ለትውልድ አናስተላልፍም።ከዚያ ይልቅ የተነገረን ሀሳብ አፍሳሽ ነው የምንሆነው።ታሪክ ፈጣሪ ለመሆንም አንችልም።በዚያ ላይ የጋራ ጀግኖቻችንን እንኳን እንድንደብቃቸው እንሆናለን።ለምሳሌ በስፖርቱ አለም ዘመናዊ ስፖርትን ስናነሳ ባህላዊውን ያስቆዩትን እንዘነጋቸዋለን።ባህላዊው ባይኖር ኖሮ ደግሞ ዘመናዊው አይታይም።ዘመናዊው ላይም ቢሆን በከፍተኛ ሁኔታ የተጠራን ብቻ እናነሳና ከእዚያ እኩል ጀግንነትን የፈጸመውን እንዘነገዋለን።
የታሪክን በአግባቡ አለመረዳት ነጭ አምላኪ እንድንሆን አድርጎናል።ምክንያቱም የኢትዮጵያዊያን ታሪክ ሲበላሽ ስናይ አናርምም።ለዚህም አብነት ማንሳት እንችላለን።
በአትሌቲክሱ የአበበ ሰዓት የተዛባና የተለያየ ነው።ከአትሌቲክሱ ውጪ ስንወጣ ደግሞ እንዲደበቁ የሆኑ የጋራ ጀግኖች ተፈጥረዋል።ከእነዚህ ውስጥ አብዲሳ አጋ አንዱ ነው።ይህ ጀግና በጣሊያን በረሀ ውስጥ እያለ ለአገሩ የተሟገተና የታገለ ነው።ዘርዓይ ድረስም እንዲሁ የኢትዮጵያ ባንዲራ እረግጠህ ጨፍር ተብሎ ሲገደድ ያለጎራዴ አልጨፍርም በማለት ሰንደቅ አላማውን አንገቱ ላይ ጠምጥሞ በጎራዴ ስንቱን ያርበደበደ ነው።ግን የእነርሱን ታሪክ ትውልዱ እንዲያነሳውም እንዲያውቀውም አልተሰራም፤ አልተፈለገምም።
እናም ታሪክ በነበረ ጊዜ ትልቅ በሞተ ጊዜ ክብር የሌለው አድርገን ነው የምንቆጥረው።በየዘመናቱ ከነበሩ ታሪኮች እንኳን ትምህርት አለ ብለን መውሰድ አንፈልግም።
ማንኛውም መንግስታዊ ስርዓት ያለ ግዛት ማስፋፋት አልተገነባም።እንደ ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን እንደ አለምም።ስለሆነም ዛሬ የምንፋጭባቸው፤ ታሪካቸው እንዲጠለሽ የምናደርገው ስለምኒልክ በተነገረን የተሳሳተ ትርክት ባንመራ ኖሮ ምን አይነት የአገር ባለውለታ እንደሆኑ እንረዳ ነበር።እርሳቸው ግዛት ማስፋፋት እንጂ ወረራ አላደረጉም።
ግዛት ሲያስፋፉ ደግሞ ሰዎችን አስገብረው ሊሆን ይችላል።ግን ያልሆነ ጥላሸት ቀብተናቸው የእርስ በእርስ መናከሻ ታሪክ ባለቤት አድርገናቸዋል።ይህ መሆን የለበትም።ከዚያ ይልቅ ታሪኮቻችን ዛሬ የምንማርባቸው፣ ነገን የምንሻገርባቸው መሆን ነው ያለባቸው።
ታሪክን ተንተርሶ በየዘመናቱ የሚዘራው ዘር አገር ወዳድነት ሳይሆን የባዕድ አገር ፍቅር ልዕልናን ነው።ይህ ደግሞ ለእናቷ ቡና አፍልታ የማታውቅ ሴት ጭምር አረብ አገር ሄዳ በሰው ቤት ሰራተኛ ሆና እንድትሰራ ተገዳለች።ታሪክንም ስለማታውቅ ስለ አገሯ ማውራት አትችልም።በታሪክማ ቢሆን ለማንም ያልተገዛች፤ ነጭ ጥቁር የሚባልን ልዩነት ካጠፋች አፍሪካዊት አገር ኢትዮጵያ የተገኘች መሆኗነን ትናገር ነበር።ሆኖም ታሪኩ በተቃራኒው በመነገሩና አብዛኛውም በመደበቁ ሥራውም አገር ጠል፤ ሰው ጠል ሆነ።
የኢትዮጵያ ችግሮች መነሻ ወጣቶች እንደሆኑ ይጠቀሳል።ምክንያቱም መጀመሪያ ቤት አልተሰራም።ከዚያም ከ100 ሰው ጋር ተገናኝቶ 100 አይነት አስተሳሰቦችን ይቃርማል።የተሻለ ነው የሚለውን ደግሞ ለማግኘት መደበላለቅና በራሱ መፍጠር ይጠበቅበታል።ይህ ደግሞ አገርን ሊያፈርስም የሚችል ሊሆን ይችላል።በሥርዓት ያልታገደ ከብት ስለሚሆን።በጊዜው ያስተማርናቸው ትምህርት እኔን በ40 ዓመቴ ለሁሉም ሰው እንድታዘዝ የ18 ዓመቱ ልጄ ደግሞ 18 ሞልቶኛልና አታዘኝም ስለሚል አለመታዘዝን አጎልብቷል።ስለዚህ የምናስተምረው ትምህርትና የምንናገረው ታሪክ ትውልድ ይሰራልም፤ ትውልድ ይገላልም።
በእስከዛሬው ሥራችን ፍቅር ሰጥቶ ፍቅር መቀበል ይቻል ነበር።ነገር ግን ጥላቻን ስንቅ አድርገን ስላስቋጠርን ፍሬው መመሰቃቀልን አምጥቷል።መገዳደልና የሌለ ባህላችንን እንድንላበስ አድርጎናል።እንዲያውም ፍቅር ሰጥተን ፍቅር መቀበል በሚቻልበት አለም ውስጥ እንደ አገር የከሰርነው የአማራ፣ የትግሬ፣ የኦሮሞ እያልን በገዢ መደብ ጥሪ መጓዛችን ነው።ስለዚህ ወደ ቀደመ ክብራችን መምጣት ከፈለግን ፍቅርን የሚያስተምሩ ሰዎችን ማክበር አለብን።ቆንጣጭና ተቆጭዎችን ከስህተት የሚመልሱንንም ማብዛት ይኖርብናል።
አዲስ ዘመን፡– የትምህርት ህይወትህ ሲነሳ ጠፍተህ እንደገባህ ይነገራል።ምን ያህል እውነት ነው።እንዴትስ ነበር የሆነው ?
ጋዜጠኛ ተሾመ፡– በእኛ ጊዜ ትምህርትቤት ለመግባት ቤተሰብ ማስመዝገብ ግዴታ አለበት።ከዚያ ውጪ አይፈቀድም።እኔ ግን በሰፈራችን ያሉ ልጆች እርስ በእርሳቸው እየተረዳዱ ሲያጠኑ በየጊዜው ማየቴ ውስጤን ይከነክነው ነበር።አንድ ቀን ታዲያ ከተማሪዎቹ መካከል አንዱን የእድሜ ጓደኛዬን እንዴት ትምህርትቤት እንደሚገባ ጠየኩት።እርሱም ወላጅ ይዞህ ሄዶ ማስመዝገብ አለበት አለኝ።
ግን እኔ ወላጆቼን መጠበቁ ከበደኝና ዝም ብዬ ከቤተሰብ ጠፋሁና ተከትያቸው ወደ ትምህርትቤት አቀናሁ።አንደኛ ክፍልም የት እንደሚገኝ ጠይቄ ተማሪዎችን ተቀላቀልኩ።በክፍል ውስጥ ሌሎች በአጣና በተሰራ ወንበር ላይ ሲቀመጡ አዲስ በመሆኔ ፈራኋቸውና ከፊታቸው በተቀመጠች ድንጋይ ላይ ቁጢጥ አልኩ።
ማንም ውጣ ሳይለኝ የትምህርቱን ክፍለጊዜ አጠናቀቅሁ። እንዲያውም በወቅቱ እድለኛ ነበርኩ።ምክንያቱም መምህሩ አዲስ ስለነበር ስማችንን በአዲስ መዝገብ እንድንጽፍና እንድንመዘግብ አደረገ።ወላጅ አምጣ ተባልኩም።ግን ጠፍቼ ስለገባሁ እንቢ ይሉኛል በሚል ስጋት ከእኔ አራት ደረጃ ከፍ የሚለውን ወንድሜን ወስጄ ተመዘገብኩ።ትምህርቱም በዚህ ሁኔታ ቀጠለ።
መጀመሪያ የትምህርት “ሀ ሁ” የተጀመረው በተወለድኩበት አካባቢ ጫንጌ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርትቤት በዛሬው አርብ ገበያ ሎዴ ነው።ከዚያ እስከስድስተኛ ክፍል ትምህርቴን ከተከታተልኩ በኋላ በዚያው አካባቢ ወደ ሰባተኛ እና ስምንተኛ ክፍልን ‹‹ሁሩታ›› ወይም ንጉስ ሀይለመለኮት ትምህርትቤት ተዛውሬ መማሬን ቀጠልኩ።
ከዘጠኝ እስከ 12ኛ ክፍል ደግሞ አዲስ አበባ በመምጣት ተፈሪ መኮንን ትምህርትቤት መማር ችያለሁ።ለሁለት ዓመታት ያህል ደግሞ የቀድሞ ማስሚዲያ ትምህርትቤት የዛሬው የጋዜጠኝነት ትምህርትቤት በመግባት ለሁለት ዓመታት የጋዜጠኝነት ትምህርት ተከታትያለሁ።የተለያዩ ስፖርት ነክ ስልጠናዎችንም በአገር ውስጥና በውጪ አገራት ተከታትያለሁ።ያመለጡኝ ያሉ አይመስለኝም።
አዲስ ዘመን፡– በ80 ዓመቱ የእድሜ ባለጸጋ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ውስጥ ከ38 ዓመት በላይ እንዳገለገልክ ይነገራል።ለመሆኑ በምን በምን ዘርፍ ላይ ነው የሰራኸው?
ጋዜጠኛ ተሾመ፡– በ12ኛ ክፍል ተወዳድሮ ሥራ ማግኘት ያልቻሉ ለዓመታት ስራ አጥተው የተቀመጡ ሰዎችን አውቃለሁ።በዚህም አንድ ዘመዳችን ካልተወዳደርን ብላ ስትመላለስ እንቢ አልኳት።እሷ ግን እየጨቀጨቀች ሳልፈልግ ከመኝታዬ ቀስቅሳ ወሰደችኝ።እናም ፕሬስን የመቀላቀሌ ምስጢር እርሷ ሆነች።መጀመሪያ ስገባ የተመዘገብኩትና የተሰጠኝ ሥራ ተላላኪነት ሲሆን፤ ምንም አልሰራሁበትም።በቀጥታ ቴሌ ኦፕሬተር ወይም ቴሌክስ የሚባል ክፍል ውስጥ እንድገባ ተደረገ።ይህ ክፍል በዋናነት ከውጪ አገር የሚመጡ ዜናዎችን ከዜና አገልግሎት ተቀብሎ እየቆራረጡ ለየዜና ክፍሎቹ ማዳረስ ነው።ኒውስ ዋየርም ይባላል።እናም ይህንን ስራ ነው ለስድስት ወር ያህል የሰራሁበት።
ቀጣዩ የሥራ ክፍሌ እርም ክፍል ሲሆን፤ የበሪሳ ጋዜጣ አራሚ ሆኜ ለዓመት ያህል ሰራሁ።ከዚያ የዳርክ ሩም ሰራተኛ ተብዬ ተመደብኩ።ከሳምንታት በኋላ ግን ከስራው ጋር ምንም ሙያዬ እንደማይገናኝ ስለተረዱ መልሰው እርም ክፍል አስገቡኝና ለረጅም ዓመታት ማገልገሌን ተያያዝኩት።ጎን ለጎን ደግሞ ለቀበሌ እግር ኳስ እጫወት ነበር።
ይህ መሆኑ ደግሞ የጋዜጠኝነቱን ቦታ እንዳገኝ አግዞኛል።በወቅቱ እርም ላይ እየሰራሁ አንድ ስህተት ተፈጸመ።አለቃዬ የጻፈውን ለመቀበል ተገዳደሩ።እርሱ ጊዮርጊስ አንድ ለሁለት ተሸነፈ ብሎ ጽፏል።ነገር ግን የአሸናፊው መቅደም ነበረበት።ይህ ከሆነ ደግሞ ጊዮርጊስ አሸነፈ የሚለውን ይይዛል።ስለዚህም ቡና 2ለ1 አሸነፈ ማለት ትችላላችሁ አልኳቸው።አሁንም መስማማት አልቻሉም።በመጨረሻ አማራጭ ሲጠፋ ግን ሀላፊነቱን እኔ እንድወስድ ተደረገና ወጣ።ጠዋት ለግምገማም ስህተት ተብሎ ቀረበ።ነገር ግን በግምገማው ትክክል እንደሆንኩ ተረጋገጠ።ከዚያ ቀን በኋላም የአለቃዬ ረዳት ሆኜ መስራት ጀመርኩ።ግን ለዓመታት በአራሚ ደሞዝም ነበር ስሰራ የቆየሁት።
በ1983 ዓ.ም ኢህአዴግ ሲገባ ደግሞ አለቃዬ በመልቀቁ የተነሳ የበሪሳ ጋዜጣ አዘጋጅ ሆኜ መስራትን ተያያዝኩት።እንዲያውም ከስፖርት ጋዜጣ አዘጋጅነት በተጨማሪ እድገቱ ቢሰጠኝም ደብዳቤ የሚባል ሳይደርሰኝ በአራሚነት ደሞዝ የአስፈጻሚነትና የአራሚነትን ሥራ አከናውን ነበር።
ሁለት ዓመት ሙሉም ነጻ በሚባል ደረጃ ሰርቻለሁ።ግን ደግሞ ክፍያዬ ከደረጃዬ ዝቅ ማለትም ነው።ሆኖም የተለያዩ የውጪ አገር የሚመጡ እድሎችን እንድጠቀም ተደርጌያለሁ።እድሎቹ ፈልገው ቢመጡም።ነገር ግን ትዕግስት ወርቅን ያጎናጽፋልና በተከታታይ የውጪ እድሎች መጥተው ሄጄ በስልጠናም በዘገባም ተሳትፌያለሁ።
የኢትዮጵያ ተወዳዳሪዎች ሲሄዱ እንጂ ብቻቸውን ጋዜጠኛ በመንግስት አይላክም።እኔ ግን ትዕግስት ገንዘቤ ስለነበረ ጋዜጠኛ ሆኜ ያላገኘሁትን አራሚ ሆኜ ለዚያውም ተወዳዳሪ ሳይኖር ነበር ደቡብ አፍሪካ የመሄድ እድል የገጠመኝ።ሄጄ ስመለስ ደግሞ የበሪሳ ጋዜጣ ከፍተኛ ሪፖርተር በሚል ደብዳቤ ደርሶኝ እስከዛሬ ድረስ በዚሁ ላይ እያገለገልኩ እገኛለሁ።ከተቋሙ ጡረታ ለመውጣትም አንድ ዓመት ከሰባት ወር ይቀረኛል።ምክንያቱም አርባውን ለመሙላት የሚቀሩት እነዚህ ጊዜያት ናቸው።
አዲስ ዘመን፡– ማህበራዊ ህይወትንና የአንተን ሁኔታ እንዴት ትገልጸዋለህ?
ጋዜጠኛ ተሾመ፡– የሰው ልጅ ማህበራዊ ህይወቱ መልካምና የተቃና እንዲሆንለት ሰው ያስፈልገዋል፡፡ከሰው የሚያስበልጠውም ምንም ነገር አይኖርም።ምክንያቱም አንድ ቦታ ተወልዶ አድጎ እዚያው የሚሞተው ሰው በጣም ጥቂት ነው።መዘዋወርና ከሌሎች ጋር አብሮ መኖር ግድ ይላል።ለዚህ ደግሞ የሚያላምድ ሰው፣ ባህሉን የሚያሳውቅና ለኑሮው እንዲመቻች የሚያደርግ ሰው ግድ ያስፈልጋል።
በዚህም ከቤተሰቤ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ከሰዎች ጋር እንጂ ለብቻ መብላት የማልወድ ሆኛለሁ።መካፈልና ከሰዎች ጋር መጫወት የእኔ መለያ ባህሪም ነው።ይህ ሲሆን ግን የሰውን ፍላጎትና ስሜት እጠብቃለሁ።የማንንም ገደብ ማለፍ አልፈልግም።የእኔም ገደቦች እንዲነኩ እንዲሁ አልፈቅድም።ግን ይህ ነገር ካለ ብቻዬን የምለው አንዳች ነገር የለኝም።ይህ ደግሞ በህይወቴ ደስተኛ አድርጎኛል።በእውቀትም ጥሩ እንድሆን አግዞኛል።በተለይ አንባቢነትንና ማዳመጥን ከማህበራዊ ግንኙነት አንጻር ያካበትኩት ከፍተኛ ልምዴ ነው።
ሰፊ ቤተሰብ ማለትም ከ30 በላይ ቤተሰብ ውስጥ መወለዴ ብቻ አይደለም ማህበራዊ ህይወቴ በመርህ እንዲቃና ያደረገው።ከታላላቆች እግር ስር ቁጭ ብሎ መማር፤ ከእኩዮች ጋር መጨዋወትም ብዙ ቁምነገሮችን እንድጨብጥ አስችሎኛል።
አዲስ ዘመን፡– ስፖርትና አንተ እንዴት ተዋወቃችሁ፤ ዛሬ ድረስስ እንዴት በህይወትህ ውስጥ ዘለቀ?
ጋዜጠኛ ተሾመ፡– ቤተሰብ ጋር ስማር ራቅ ያለ ቦታ ለትምህርት ከጓደኞቼ ጋር ስለምንጓዝ ሩጫ የየእለት ተግባራችን ነበር።አጠቃላይ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችም እንዲሁ መሰረታዊ ተግባራችን እንዲሆኑ አድርጎናል።ከዚያ ደግሞ በትምህርትቤት ውስጥ ኳስ ጊዜ ማሳለፊያችን በመሆኑ የተለየ ብቃቴን አይቼበታለሁ።ትምህርትቤቱን፣ ቀበሌውን እንዲሁም ወረዳውን እየወከልኩም መጫወት በመቻሌ የተለየ ፍቅር እንዲያድርብኝ ሆኗል።በስፖርት ውስጥ ማደጌም ስፖርት ህይወቴ ሆነ።በዚህም ከመጫወቱ አልፌ ከስፖርት አዋቂዎች ጋር በመገናኘቴ የስፖርት ጋዜጠኛ ለመሆን ቻልኩ።
አዲስ ዘመን፡– ስፖርት የመዝናኛ፣ መንፈስን የማደሻና ቤተሰባዊነትን መፍጠሪያ መድረክ እንደሆነ ይታመናል።አሁን ያለው ሁኔታ ግን ከዚህ የተለየ ሆኗል።ምክንያቱ ምን ይሆን?
ጋዜጠኛ ተሾመ፡– ስፖርት ማለት ወዳጅነት፤ ወንድማማችነት፣ ሰላም፣ አንድነት፣ ቤተሰባዊነት፣ አገር ወዳድነት ማጠናከሪያ መድረክ ነው የሚለውን ትርጉም ይይዛል።ከአገርና ከመንደር አልፎ አለማዊ ወዳጅነትም መፍጠሪያ ነው።ይሁንና እንደ አገር ግን ከሰፈር የጀመረ ጥላቻን ይዞ አድጓል።ከስያሜም ጀምሮ ኢትዮጵያ የሚለው ነገር በክልል ደረጃ መዋቀሩ ሌላው የደጋፊውን ስሜት ከአገራዊነት ይልቅ ወደ ክልል እንዲመጣ አስችሎታል።ይህ ደግሞ በተለይ በደጋፊዎች ዘንድ ከፍተኛ የጎጣዊነት ስሜት እንዲያይል አድርጓል።መጀመሪያ የስፖርት ጨዋታ አላማ ከታች ጀምሮ ተጨዋቾችን አፍርቶ ለአገር ማብቃት ነው።ሆኖም ልዩነት ያንሰራራበት በመሆኑ አገር የሚለው ተጥሎ ክልል ወይም ብሔር የሚለው እንዲቀነቀን ሆኗል።
የስፖርት የጨዋታ ህግ የፈረሰው በባለቤቶቹ ወይም በተጨዋቾቹ ሳይሆን ባለቤትነት በሌላቸው አካላት ነው።ተጨዋቾቹ ተሳስመው፣ ተቃቅፈው ሲለያዩ ደጋፊው ግን በጥላቻ መንፈስ እርስ በእርስ ይደባደባል።ጨዋታ ሜዳው ላይ ሳይበቃውም ሰፈር ድረስ ጥላቻውን ይዞ ይዘልቃል።በዚህም ስፖርቱ ዓላማውን ስቶ የአገር ፈተናና የግጭት መንስኤ የጦርነት መድረክም ይሆናል። እንዲያውም አሁን አሁን የፖለቲካ ጨዋታ መከወኛ መድረክም ሲሆን ይታያል።
ፖል ቴርጋትና ሀይሌ ገብረስላሴ ወንድማማች ሆነው እንዲቀጥሉ ያስቻላቸው ዜግነታቸው አይደለም።ደም መቃባትም ቢኖርባቸው ኖሮ 25 ዙር ማለትም 10 ኪሎሜትር ሮጠው በአንድ እርምጃ ተቀዳድመው ወርቅን ያህል ነገር ሲቀማሙ ያደርጉት ነበር።ግን የስፖርት ህግ መሸነፍና ማሸነፍ አለበት ብለው ስለሚያምኑ በመጨረሻ ተቃቅፈው ሩጫውን ቋጭተዋል።የጦርነት ሜዳውንም በዚያው ላይ በመሸናነፍ እንዲያከትም አድርገውታል።ወንድማማችነታቸው በዚያ እንዳያበቃም አጠናክረውት ዛሬ ድረስ አስቀጥለውታል።ከራሳቸው አልፈው ሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጭምር ከእርሱ ጋር ጓደኛማማቾች እንዲሆኑ አድርጓቸዋልም።ምክንያቱም የስፖርት ዋጋ ይህ ነው።ስለዚህም ለአንድ አላማ እየሮጥን ለአንድ አላማ መስራት ካልቻልን በስተቀር ስፖርት አላማውን መሳቱ ብቻ ሳይሆን አገርም መረጋጋት አትችልም።
አዲስ ዘመን፡– ከአፍሪካ እስከ አውሮፓ ድረስ አገራትን በሙያህ ዞረሃል።ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ በአለም አገራት ያላትን ገፅታ እንዴት ተመለከትከው?
ጋዜጠኛ ተሾመ፡– ብዙ አገራት ስንጓዝ የተለያዩ ሙያተኞችን እናገኛለን።በዚህም ኢትዮጵያ እንደዘመናቱ ለሁሉም የተለየች ነች።በተለይ በአትሌቲክሱ ዘርፍ አብሮ የሮጣቸውንና በአዲስ መልክ ሮጦ ያሸነፈውን ሲያዩ ኢትዮጵያን በዚያ ይስሏታል።
ስለሆነም በዘመናቸው የነበረው ሯጭ መጠሪያዋ ይሆናል።ጓደኛም የሆናቸው ካለ እንዲሁ የእርሱ አገር በማለት ነው የሚያስታውሷት። ስለዚህ ኢትዮጵያ ለእነርሱ የቀረበ ሯጭ ውጤት ነች።የአትሌቲክስ ምንጭም አድርገው ይወስዷታልም።
መለያችን አረንጓዴ፤ ቢጫ፣ ቀይ በመሆኑም በአረንጓዴው ጎርፍ ብዙዎች የሚያስታውሷትም አሉ።አረንጓዴው ጎርፍ ማለት ስፔን ላይ በተዘጋጀ የአገር አቋራጭ ውድድር ላይ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተካፈለችበትና ሰባት አትሌቶችን የላከችበት ጊዜ ነው።የአገራቸውን ባንዲራ የያዘውን ልብስ ለብሰው ሰባቱም ተከታትለው ነበር የሚሮጡት።
የዚህን ጊዜ ከላይ ሆኖ የሚቀርጸው ኢሊኮፕተር እነርሱን ብቻ አነጣጥሮ ተመለከተ።በበረሃ ውስጥ የሚምዘገዘግ አረንጓዴ ጎርፍ ይመስላል።እናም ዜናውን የሚያሰራጨው ጋዜጠኛ Look at this green flood/ ‹‹እዩት ይህንን አረንጓዴ ጎርፍ›› ብሎ ተናገረ።ከዚያ በኋላም አረንጓዴው ጎርፍ ተብሎ መጠራት ጀመረ።እናም ይህ ነገር በዓለም መድረክ ላይ ኢትዮጵያ የምትታይበት መልክ እንዲሆን አድርጓል፡፡
አትሌቲክስ ቅብብሎሽ በመሆኑ በየዘመናቱ የሚመጡ አትሌቶች በአለም ጭምር እነርሱ ብቻ መለያ ሆነው ኢትዮጵያን አሳውቀዋታል።ለአብነት ጣሊያን ልትወረን እየተዘጋጀች ሳለ አበበ ቢቂላ በቦታው ላይ በባዶ እግሩ ሮጦ ያሸነፈ ብቸኛ ጥቁር ነው።በአንድ ውድድር ሁለት ሜዳልያ ያጠለቀ ብናነሳ ደግሞ ምሩጽ ይፍጠር እና በማራቶንና በአስር ሺህ ወርቅና ብር ያመጣው ማሞ ወልዴ ነው።ከቅርቦቹ ደግሞ ቀነኒሳ በቀለ በአንድ ጊዜ አራት የወርቅ ሜዳልያ ያጠለቀ ብቸኛ ሰው ነው።
በአለም ታሪክ የመጀመሪያ ሴት በአስር ሺህ ሜትር የወርቅ ሜዳልያ ያመጣች ደራርቱ ቱሉ ናት።በአፍሪካ ታሪክ ደግሞ በማራቶን የወርቅ ሜዳልያ ያመጣችው ፋጡማ ሮባ ነች።ስለዚህም በብዙ ብራንዷ ኢትዮጵያ ለየት ተደርጋ ትታያለች።
አዲስ ዘመን፡– አንጋፋ የስፖርት ዘርፉ ዘጋፊ እንደሆንክ ይታወቃል። በዚህም የተለያዩ ሽልማ ቶችን አግኝተሃል።ምን ምን ናቸው፤ የትኛውስ ላንተ ልዩ ነው?
ጋዜጠኛ ተሾመ፡– እኔ አንዱን ከአንዱ ማስበለጥ አልፈልግም።ሁሉም ለእኔ ነገን እንዳስብና የተሻለ እንድሰራ አድርገውኛል።በዝርዝር ለማየት በጣም ብዙ ስለሆኑ ይከብዳል።በርከት ያሉ የምስክር ወረቀቶችና ሌሎች ሽልማቶች ከአገር ውስጥም ከውጪ አገርም ተበርክተውልኛል።የውጪ አገራቱ ብዙዎቹ በስልጠና አማካኝነት ያገኘኋቸው ናቸው።የአገር ውስጦቹ ደግሞ በሙያዬ ከሰራሁት ሥራ ጋር ይገናኛል።ይዘርዘር ከተባለ ብዙ ስለሆነ ይከብዳል።ሆኖም ትልቅ ስፍራ ያላቸው የኦሎምፒክ ኮሚቴ፣ ስፖርት ኮሚሽን፣ አትሌቲክስ ፌደሬሽን የሸለሙኝ ተጠቃሽ ናቸው።በተለይ የመጨረሻው የ60 ዓመት የባዶ እግር ቱርፋት በሚል ነው ልዩ ተሸላሚ ሆኜ እድሉን ያገኘሁት።
ሽልማት ገንዘብና እውቅና ብቻ አይደለም የሚሰጠው፡፡ከዚያ የላቀውን እውቀትንም ያጎናጽፋል።እናም በተለያየ ጊዜ ሽልማቱ ሲበረከትልኝ ስለዚያ ነገር እንዳውቅና በዚያ ጉዳይ ላይ የበለጠ እንድሰራ እሆናለሁ።የእስከዛሬ ሽልማቶቼም ያስተማሩኝ ይህንኑ ነው።
አዲስ ዘመን፡– ስለ ቤተሰብህ ምን ትላለህ?
ጋዜጠኛ ተሾመ፡– ቤተሰብ ህይወት ነው።መንገድ ጠራጊ፣ ነገን የሚያሳይ፣ ዛሬን የሚያኖር ነው።የራሱ የሆነን ነገር ትቶ ለሌላ የሚኖርበትም ነው።ለምሳሌ ባለቤቴን ሳገኛት ቤተሰቤ የምላቸው ጓደኞቼ መርጠው ሰጥተውኝ ነው።የእርሷም የእኔም ምርጫ አልነበረም።ግን ለሚወዱት የሚወዱት ነገር ይሰጣልና ለሁለታችንም የምንወዳቸው ሰዎች የምንወደውን ሰጥተውናል።ሁኔታው እንዲህ ነው።
በአንድ ጓደኛችን ሰርግ ላይ እርሷ የሴቷ እኔ ደግሞ የወንዱ ሚዜ ሆነን ነው የተተዋወቅነው።ከዚያ ግንኙነታችን ጠበቀ።ግን ወንድምና እህት እንጂ ትዳር የሚባል ነገር አላሰብንም።ጓደኞቼ ግን ለእርሱ ምርጧ እርሷ ነች ሲሉ በጓደኛዋ በኩል ጥናት አደረጉ።አሳኩትና አሁን ላለንበት ህይወትም አበቁን።
ባለቤቴ እናቴ፣ አባቴ፣ እህቴ ሚስቴ ናት።ከእርሷ በላይ ደግሞ ቤተሰቦቿ ለእኔ ልዩ ናቸው።ልክ እንደ ልጃቸው ነው የሚንከባከቡኝ።ስለዚህ ቤተሰብ ሲባል ገደብ ያለውና የሆነ ጎራን የለየ አይደለም ለእኔ።አሁንም ቢሆን ሁለቱን ልጆቼን ሳሳድግ በዚህ መስመር አድርጌ ነው።
አዲስ ዘመን፡– የአገራችን ወቅታዊ ሁኔታን፣ የአንተን የህይወት ተሞክሮ በማንሳት መልዕክት ካለህ?
ጋዜጠኛ ተሾመ፡– ሰዎች በህይወታቸው ውስጥ የሚያደርጉት የተለየ ነገር እንዳለ አምናለሁ።እኔም ካለኝ ቢወሰድ ብዬ የማስበው ከሰዎች ጋር ሲኖሩ በፍቅር መኖርን ባህሪያቸው ቢያደርጉ የሚለውን ነው፡፡ማህበራዊ ህይወታችንን የሚቆርጥብንን በምንም መልኩ መታገስ የለብንም።ምክንያቱም ማህበራዊ ህይወት ራስን የሚሰራና አገርን የሚጠብቅ ነው።የትናንቱን የማያስታውስ የነገን ማየት አይችልምና ትናንትን መርሳት የለብንም።
ፍቅር ሰጥቶ ፍቅር መቀበልን መልመድ ይገባናል።ነገ ይመልስልኛል ሳይሆን ነገ ይመለስልኛል ብሎ ማድረግ ያስፈልጋል።ምክንያቱም መላሹ ፈጣሪ ስለሆነ።ዛሬ ብዙዎች የመጋጨታቸው ምስጢር እከክልኝ ልከክህል በመሆኑ ነው።ብቻውን ማድረግንም ስለለመደ የመጣ ነው።እናም የተዘራውን መጥፎ ዘር በመልካም ፍሬ ለመተካት ህዝቡ፣ መንግስት እና በየዘረፉ ያለው ባለሙያ በመቀራረብና በመረዳዳት መስራት ይጠበቅበታል።
አዲስ ዘመን፡– ስለሰጠኸኝ ማብራሪያ እናመሰግናለን።
ጋዜጠኛ ተሾመ፡– እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ጥር 2/2013