አስናቀ ፀጋዬ
በሁለቱ የዓለማችን ግዙፍ የምጣኔ ሃብት ባለቤቶች አሜሪካ እና ቻይና መካከል ያለው የንግድ እሰጣ ገባ ከግዜ ወደ ግዜ እየተካረረ መጥቷል ፡፡ በተለያዩ ግዜያትም አንዳቸው በሌላቸው ላይ ከፍ ያለ የንግድ ታሪፍ በመጣጣል ኢኮኖሚያዊ የበላይነታቸውን እርስ በእርስ ለመፈታተሽ ሞክረዋል፡፡
በሁለቱ ሀገራት ያለው የንግድ ጦርነት ይበልጥ ተባብሶም በቅርቡ ቻይና ‹‹አይን ያጠፋ አይኑ ይጠፋል›› የሚል አንድምታ ያለውና ጠንከር ያለ አዲስ ህግ ቁጥጥር በሚደረግባቸውና ወደ ውጪ ሀገር በምትልካቸው ምርቶች ላይ ማውጣቷ ይታወሳል፡፡ ይኸው የንግድ ጦርነት ተካሮ የአሜሪካው ኒውዮርክ አክሲዮን ገበያ የሶስቱ ግዙፍ የቻይና ቴሌኮሙዩኒኬሽን ኩባንያዎች የአክሲዮን ድርሻ እንዲፋቅ የወሰደውን እርምጃ ተከትሎ ከቻይና በኩል ጠንከር ያለ የአፀፋ እርምጃ እንደሚኖር ተንታኞች እየገለፁ ይገኛሉ፡፡
ባሳለፍነው ሃሙስ የኒውዮርክ አክሲዮን ገበያ ቻይና ቴሌኮም፣ ቻይና ሞባይልና ቻይና ዩኒኮም የተሰኙ የቻይና ቴሌኮም ኩባንያዎችን የአክሲዮን ድርሻ እስከ መጪው ጥር 7 ወይም ከዛም በፊት እንደሚፍቅ ማስታወቁን ዘገባዎች አስታውሰዋል፡፡ ካለፈው ሰኞ አንስቶም በሆንግ ኮንግ ዝርዝር ውስጥ የተካተቱት ሶስቱም ኩባንያዎች የአክሲዮን ድርሻ እየቀነሰ ስለመምጣቱም የተለያዩ የዜና አውታሮች ዘግበዋል፡፡
ይሁንና የኒውዮርክ አክስዮን ገበያ እርምጃ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ህዳር ከፈረሙት የይፈፀም ትዕዛዝ ጋር የተዛመደና አሜሪካኖች ከቻይና ጦር ኃይል ጋር ግንኙነት አላቸው በተባሉ ኩባንያዎች ላይ ኢንቨስት እንዳያደርጉ የሚያግድ ስለመሆኑም በዘገባዎቹ እየተገለፀ ይገኛል፡፡
ሶስቱ ግዙፍ የቻይና ቴሌኮሙዩኒኬሽን ኩባንያዎች ከአክሲዮን ድርሻቸው እንዲፋቁ በኒውዮርክ የአክሲዮን ግብይት የተላለፈው ውሳኔም ቻይናን ያስቆጣና በዋሽንግተን ላይ ጠንከር ያለ አፃፋዊ እርምጃ እንድትወስድ የሚገፋፋ ስለመሆኑ ተንታኞች እየተናገሩ ነው ሲል ሲ ኤን ቢ ሲ ኒውስ በዘገባው አስነብቧል፡፡ የአክሲዮን ገበያው በመጪው ሃሙስ የቻይና ቴሌኮም፣ ቻይና ሞባይልና ቻይና ዩኒኮም ኩባንያዎች የአክሲዮን ድርሻን እንደሚሰርዝም በዘገባው ተመላክቷል፡፡
የያንግ ሴንግ የመጀመሪያው የአክሲዮን ንግድ ቀን ከተገለፀበት ግዜ ጀምሮ በሆንግ ኮንግ ዝርዝር ውስጥ ያሉት የሶስቱም ኩባንያዎች አክሲዮን ድርሻ ከሰኞ ጀምሮ መውደቁም የገለፀው ዘገባው፤ ቻይና ሞባይል፣ ቻይና ዩኒኮምና ቻይና ቴሌኮም በእስያ ያላቸው ድርሻም ከሶስት በመቶ በላይ መውደቁንም አስታውቋል፡፡
የኒውዮርክ አክስዮን ገበያ እርምጃ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ህዳር ከፈረሙት የይፈፀም ትዕዛዝ ጋር የተዛመደና አሜሪካኖች ከቻይና ጦር ኃይል ጋር ግንኙነት አላቸው በተባሉ ኩባንያዎች ላይ ኢንቨስት እንዳያደርጉ የሚያግድ መሆኑም ዘገባው አስታውሶ፤ ይህም ቀደም ሲል በኮሮና ወረርሽኝ መነሻ ጉዳይ ዙሪያ እርስ በእርስ ሲነታረኩ የቆዩትን ሁለቱ ግዙፍ የዓለም ምጣኔ ሃብት ባለቤት ሃገራት ቻይናና አሜሪካን መካከል ያለውን ውጥረት ይበልጥ እንደሚያጦዘው ተጠቁሟል፡፡
የአሜሪካንን እርምጃ ተከትሎም የቻይና ንግድ ምክር ቤት በምላሹ በመጪው ሃሙስ የቻይና ኩባንያዎችን ህጋዊ መብትና ፍላጎት ለመጠበቅ አስፈላጊውን እርምጃ በቁርጠኝነት እንደሚወስድ አስታውቋል፡፡
‹‹የቻይና መንግስት በአሜሪካ ላይ የበቀል እርምጃ የሚወስድ መሆኑን ማየት ያስፈልገናል ነገር ግን መደረግ ያለባቸው ትክክለኛ ነገሮች ወሳኝ አይሆኑም ብዬአስባለሁ›› ሲሉም በኩባንያዎቹ የፋይናንስ ባለድርሻ ሮናልድ ዋን ገልፀዋል፡፡
ተጨማሪ የቻይና ኩባንያዎች ከዚህ የአክሲዮን ገበያ ውጭ ሊወጡ ይችሉ እንደሆነ የተጠየቁት የኢንቨስትመንት ኩባንያ ‹‹ክሬን ሻሬስ›› ዋና የኢንቨስትመንት ኦፊሰር ብሬንዳን አህረን ‹‹በዚህ የይፈፀም ትዕዛዝ ብቻ ከእነዚህ ሶስት የኩባንያዎች ባሻገር ሌሎችም ከአክሲዮን ገበያው ይወጣሉ የሚል እምነት የለኝም›› ብለዋል፡፡
የኢንቨስትመንት ኦፊሰሩ በተለይ ባለፈው ሰኞ በ ሲ ኤን ቢ ሲ “ስኩዊክ ቦክስ እስያ” በተሰኘው ፕሮግራም ላይ ቀርበው ‹‹ትዕዛዙ አዲሱ የአሜሪካ ተመራጭ ፕሬዚዳንት የሆኑት ጆ ባይደን በጥር 20 ቃለ መሐላ ፈፀመው ስልጣናቸውን ከተረከቡ በኋላ ሊቀየር ይችላል›› ሲሉ ያላቸውን ግምት ሰጥተዋል፡፡ አክለውም በቻይና በኩል ቤጂንግ ለባይደን አስተዳደር በሁለቱ ሀገራት መካከል አዲስ ግንኙነት እንዲጀመር እድል እንደምትሰጥም ጠቁመዋል፡፡
ሮናልድ ዋን በበኩላቸው ‹‹በቤጂንግ በኩል የሚወሰዱ ማናቸውም የአፀፋ እርምጃዎች “ጠቃሚ ሊሆኑ አይችሉም›› ያሉ ሲሆን “የቻይና መንግስት በአሜሪካ ላይ የበቀል እርምጃ የሚወስድ መሆኑን ማየት ያስፈልገናል ፣ ይሁንና የሚወሰዱ እርምጃዎች ያን ያህል ጠቃሚ ናቸው ብዬ አላስብም›› በማለት ተናግረዋል፡፡ ምናልባት በቻይና ወይም በሆንግ ኮንግ ያሉ አንዳንድ የአሜሪካን መንግስት-ነክ አካላት እንቅስቃሴዎችን ሊገድቡ እንደሚችሉ ግን እገምታለሁ ሲሉ ጠቅሰዋል፡፡
ይሁንና በሦስቱ የአሜሪካን አክሲዮን ገበያ ዝርዝር ውስጥ ያሉ ኢንቨስተሮች ወደሆንግ ኮንግ የአክሲዮን ድርሻ ዝርዝር ውስጥ መካተት ወይም መለወጥ እንደሚችሉ ኢራን የተለየ አቋም መያዝዋን ጠቁመዋል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 28/2013