አስመረትብስራት
ቀጠን ያለች ወጣት ናት። ቆንጆ ፈገግታና ለጆሮ የሚጥም የድምጽ ቅላፄ ያላት ብሩክታዊት ጥጋቡ ከአስራ አራት አመታት በላይ ልጆች የሀገራቸውን ባህልና ስልጣኔ በልጅነታቸው እንዲገነዘቡ ስታደርግ ቆይታለች። ብሩክታዊት የዊዝኪድስ ወርክሾፕ ደርጅት መስራችና ዋና አስተዳዳሪ ነች።
ትውልዷም እድገቷም በመዲናችን አዲስ አበባ ነው። ወላጅ እናቷ መምህርት ሲሆኑ አባቷ ደግሞ በጠንካራ ሰራተኝነታቸው የሚታወቁ፣ በትግል የልጆቻቸውን የተሻለ ቀን ብሩህ ያደረጉ ሰው ናቸው።
እናት ስራቸውን ትተው ልጆቻቸውን ለማሳደግ ሲወስኑ፣ ልጆቹ ቤትም ትምህርት ቤትም በተገቢው መንገድ እንዲማሩ ሆነው አድገዋል። ታዲያ ጠንካራው አባቷም የስራን ክቡርነት አስተምረው ያሳደጓት ይህች ወጣት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን በቦሌ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምራለች።
ከዚያም የከፍተኛ ደረጃ ትምህርቷን በኮተቤ መምህራን ኮሌጅ ከተከታተለች በኋላ መምህርት ሆና ለሶስት አመታት በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት አስተምራለች። በምታስተምርበት ወቅትም ሙሉ ህይወቷን ከህፃናቱ ጋር በማሳለፏ መምህርነት ከሙያዎች ሁሉ በላይ የሆነ ሙያ መሆኑን ስለተረዳች ልጆችን በቂ እውቀት ሰጥቶ ለማሳደግ የተለያዩ ሙከራዎችን አድርጋለች።
የኋላ ኋላ ግን ከተወሰኑ ልጆች በላይ ለብዙ ህፃናት እንዴት መድረስ እችላለሁ በሚል ሀሳብ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ላይ ጥናቶችን መመልከት ጀመረች። ያኔ አንድ መቶ ለሚሆኑ ህፃናት የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቢሰጥም ሌሎቹ ግን ይህን እድል ያላገኙ መሆናቸውን ትረዳለች።
ህፃናት እስከ ሰባት አመት እድሜቸው ድረስ አእምሯቸው ተሰርቶ የሚያልቅበት መሆኑን ጥናቶች ያመላክታሉ። ከታች ከህፃንነት እድሜያቸው ጀምሮ ሳይሰራበት ቆይቶ ሲያበቃ ልጆችን በግድ አንዲያውቁ የሚደረግበት ሁኔታ መኖሩን ስትመለከትና መንግስት ደግሞ መደበኛውን ትምህርት የማድረስ ስራ ላይ የተጠመደበት ጊዜ መሆኑን በመረዳት ክፍተቱን ለመሙላት በሚል ሰብብ ፀሃይ ልትወለድ እንደቻለች ትናገራለች።
በወቅቱ የገንዘብ አቅሟም ደካማ በመሆኑ ትምህርት ቤት ከመክፈት ይልቅ ሌሎች ሀገሮች በቴክኖሎጂ የታገዘ የተለያዩ ማስተማሪያ ፊልሞችን ስትመለከትና እነዚያ ልጆች የላቀ አስተሳሰብ እንዳላቸው ስትረዳ ይህን ተሞክሮ ከአመታት በኋላ ወደ ሃገሯ በማምጣት “ፀሀይ መማር ተወደለች” ፕሮግራሙን በመገናኛ ብዙሃን ማሰራጨት ጀመረች።
ዊዝኪድስ ወርክሾፕ የህፃናትና ወጣቶችን እድገት ጥሩና የተሟላ እንዲሆን ለማድረግ የሚሰራ ድርጅት ነው። ከልጆች እድገት ጠቃሚ የሆኑ ባህልን፤ ቋንቋንና ሌሎች የህፃናትን እድሜ ያገናዘቡ ስራዎች ይሰራል። እድሜያቸው ከአስር አመት በታች የሆኑ ልጆችን በ”ፀሀይ መማር ትወዳለች” ፕሮግራም ለመድረስ ተችሏል።
አራት ፕሮጀክቶች በዊዝ ኪድስ ስር ይሰራሉ። እነዚህም ልጆች ገና በማህፀን ከተቀመጡ ጊዜ ጀምሮ ወላጆች ስለ ልጆቻቸው እድገት የሚያስቡበት የሚዘጋጁበትን እድል የሚፈጥርላቸው ፕሮግራም ነው።
ይህም ከፅንስ ጀምሮ ልጆች የተሟላ እድገት መያዝ እንዲችሉ፣ የህፃናቱን አካላዊና ስነልቦናዊ እንዲሁም አእምሯዊ እድገቶችን ለማሳደግ በሚል የተዘጋጀ ሲሆን በሬዲዮና በቴሊቭዥን ፕሮግራም እንዲሁም በአጭር የጽሁፍ መልእክት በመላክ ለማስተማር ተሞክሯል።
̋ሁለተኛው ከላይ የነገርኩሽ ልጆቹ ከሶስት አመት እስከ አስር አመት አድሜ ላይ ሲደርሱ ባህላቸውን፣ አከባቢያቸውን በተገቢው መንገድ እንዲረዱ የሚያደርግ ፀሀይ መማር ትወዳለች በሚለው ፕሮግራም በጤና፤ በትምህርትና በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ለአስራ አራት አመታት የቀጠለ ፕሮግራም ነው።
ፀሀይ መማር ትወዳለች ፕሮግራም በሰባት የሀገራችን ብሄር ብሄረሰቦች ቋንቋ በሀገር አቀፍ በክልልና በማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያዎች በማስተላለፍ በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ ልጆችን የመድረስ ስራ ይሰራል።” ብላለች።
እነዚህ ሰባት ቋንቋዎች ማለትም በፊት ሲተላለፍበት የነበረው አማርኛ ቋንቋን ጨምሮ ሱማሌ፤ ሀዲይሳ፤ ሲዳምኛ፤ ወላይትኛ፤ ትግርኛ፤ እና ኦሮምኛ ቋንቋዎች በፕሮጀክቱ የተካተቱ ናቸው።
ልጆቹ ከአስር አመት በላይ ሲደርሱ ደግሞ ቅድመ ጉርምስና እድሜ በመሆኑ ሊገጥማቸው የሚችሉ የተለያዩ ባህሪና እድገት ላይ ስለሚደርሱ ለዛ የሚመጥን “የጥበብ ልጆች” የሚል ፕሮግራም ተዘጋጅቷል። ይህም ልጆች የሰውነታቸውን ለውጥ በመከተል ወደፊት የሚጋፈጧቸውን ችግሮች በማሰብ ከ10 እስከ 15 አመት ላሉ ልጆች በመፅሃፍ መልክ፣ በሬዲዮና በቴሊቪዥን እንዲሁም በማህበራዊ ሚዲያ ሊታዩ የሚችሉ ስራዎች ይሰራሉ።
አራተኛው ደግሞ “ወጣት ተመራማሪዎች” የሚል ፕሮግራም ነው። ይህ ሙሉ እድገት እንዲኖራቸው የበቁት ልጆች ያላቸውን እምቅ ችሎታ እንዴት እንደሚያወጡት የሚረዳ፣ ፈጠራቸውን እንዲያሳዩበት ለመርዳት የሚሰሩ ስራዎች ናቸው። ይህ በወጣትነት እድሜ ላይ ልጆቹ ወዳልተፈለገ ነገር እንዳይሄዱ አቅማቸውን በትክክል ተረድተው ህብረተሰቡን እንዲያገለግሉ የሚያደርግ ነው።
ልጆችን በተገቢው ሁኔታ ባህል ወጋቸውን አውቀው እንዲያድጉ በአግባቡ አእምሯቸውን ለማሳደግ የታቀደው አላማ ስኬት ላይ ደርሷል ለማለት የሚያስችሉ ሀሳቦች ለማሳካት የተሰራ ሲሆን እቅዱም በተገቢው መንገድ ተሳክቷል።
̋ይህ ሲባል “ፀሀይ መማር ትወዳላች” ሲሰራ ከሶስት አመት በላይ ለሆኑ ልጆች ታስቦ ስለነበር በመጀመሪያ እድገቱ የተጎዳ ልጅ እንዳይኖር፣ የተሟላ እድገት እንዲኖረው አስበን የተሰራ ነው። ልክ ልጆቹ አስር አመት ሲሞላቸው ከአካላዊ እድገት ጋር ተያይዞ የሚገጥማቸውን ችግር በማሰብ ቀጣይ እና ተከታታይነት ባለው መልኩ መልካም ተፅእኖን ማሳደር በሚያስችል ሁኔታ ማስተማር ተችሏል።
̋በዊዝ ኪድስ ወርክሾፕ ስኬት ጉዞ ነው የሆነው። መጀመሪያ ፀሀይ ስትወለድ ከአንድ የመጀመሪያ ደረጃ መምህርት በካልሲ የተሰራች አሻንጉሊት ነበረች። ይቺ ትንሽ አሻንጉሊት የሀገራችንን ስም በተለያዩ ሀገራት መድረክ ላይ ታስጠራለች ብሎ ማሰብ ቀልድ ሊመስል ይችላል።
በስራዎቼም ከአርባ ሀገራት በላይ በመዘዋወር የተለያዩ ሽልማቶችን ማግኘት መቻሉ ስኬት ቢያሰኘውም የሀገሪቱን ህፃናት ከመድረስ አልፎ የአፍሪካ ልጆችንም የሚደርስ ፕሮግራም ተጀመረ ማለት ሰኬታችን እየደረስንበት የምናልፈው መሆኑን የሚየሳይ ነው።” ትላለች።
እንደ ብሩክታዊት ገለፃ “ስኬት” የሚያድግ፣ የማያቆም ሲሆን በሀገራችን ከሰባት ቋንቋዎች በተጨማሪ በአፍሪካ አራት ቋንቋዎች ለመስራት ነው የታቀደው። በህይወት እስካለሁ ድረስ ልጆችን በሙሉ መድረስ እስክችል ድረስ ‘ስኬት’ አያቆምም በሚል እሳቤዋ ነው።
በአፍሪካ አራት ቋንቋዎች ማለትም እስዋህሊ በሶሰት ሀገሮች ታንዛኒያ፣ ኬኒያ ናዩጋንዳን ይሸፍናል። ሆሳ የናይጄሪያ ትልቅ ማህበረሰብ የሚናገረው ቋንቋ ነው። ፖርችጊዝ ፍሬንች ተናጋሪ ሀገሮች በአፍሪካ ያሉ ሲሆን እነሱንም ለመድረስ ይህን ቋንቋ ለመጠቀም መሞከሩን ትናገራለች። በተጨማሪም እንግሊዘኛ ቋንቋን በመጠቀም የጥበብ ልጆችና ፀሀይ መማር ትወዳለችን ወደዛ የማሳደግ ስራ ይሰራል ትላለች።
̋ቤተሰቦቼ ማለትም ሁለቱ ልጆቼም፣ ባለቤቴም በዚሁ ስራ ተሳታፊ ናቸው። ይህም ማለት ሙሉ ጊዜዬን በስራ ስለማሳልፍ ለልጆቼ ጊዜ የመስጠት እድልንም ከስራዬ ጎን ለጎን እንዲሄደ ሊያደርገው ችሏል።” የምትለው ብሩክታዊት ስራው የተሳካ እንዲሆን የቤተሰቦቿም ድጋፍ እንዳልተለያት ታስረዳለች።
ስራው ከትምህርት ሚኒስቴር፣ ከጤና ሚኒሰቴር፣ ከህፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር እና የተለያዩ ፕሮጀከት ካላቸው ሰዎች ጋር የሚሰራ ስራ መሆኑን ገልፃ በዚህ ሁሉ ወስጥ ልጆች የስራው አካል ሆነው እንዲያድጉ፣ ክህሎቶችን እንዲያዳብሩ ለማድረግ ጥረት ይደረጋል።
በዊዝ ኪድስ ወርክሾፕ በርካታ ኢትዮያዊዊ ህፃናት በቋንቋቸው በጥናት የተደገፈን ለእድገት ጠቃሚ የሆነ ስራን ማግኘታቸው ጠቃሚና የላቀ መሆኑ ሌሎች ሶስተኛ ወገኖች ያደረጉት ጥናት ያመለክታል።
በፀሀይ መማር ትወዳለች ፊደል መለየት የንባብ አቅም መፍጠር መልካም ስነ ምግባር ያላቸው ልጆች ላይ በተደረገ ጥናት ከ20 በመቶ በላይ ውጤታማ መሆኑን ያመላክታሉ። በጤና ላይ የተሰሩ ስራዎችን የተመለከቱ ህፃናት፣ ካልተመለከቱት በእጥፍ እንደሚበልጧቸው ለማሳየት ተችላል።
ልጆችን ደግሞ በተለያየ መልክ ለማስተማር ከስርዓተ ትምህርቱ ጋር በማጣጣም በ425 ትምህርት ቤቶች መፅሀፍ እንዲያነቡ፣ ቪዲዮ እንዲመለከቱ በማድረግ ለሁለት መቶ ልጆች ትምህርቱን በቀላሉ ለማድረስ በአዲሰ አበባና በአማራ ክልል ውስጥ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ለመስራት ተችሏል።
አሁን ደግሞ በሰባት የተለያዩ ቋንቋዎች በመዘጋጀቱ በሀገሪቱ ሁለት ሺ ትምህርት ቤቶች ለመድረስ የተሰራ ሲሆን ይህ ማለትም ከሁለት ሚሊዮን በላይ ህፃናትን በቀጥታ መድረስ ይቻላል ማለት ነው። ይህ ደግሞ ስራው በአግባቡ እየተሰራ መሆኑን አመላካች ነው ትላለች።
በዊዝ ኪድስ ወርክሾፕ በወጣቶች የተሞላ ነው። በሀገራችን ያለው የስራ ባህል የማህበረሰብ ውጤት ነው። በምንም ሁኔታ ውስጥ ያሉ ወጣት ሰራተኞች በወራት ጊዜ ውስጥ ተቀይረው፣ ጥራት ያለውና ጠንካራ ስራዎችን እንዲሰሩ እንዲሁም ብቁና ውጤታማ እንዲሆኑ ጥረት ይደረጋል።
“ሴቶች በተፈጥሯቸው የፍቅር፣ የርህራሄና ሀላፊነትን የመሸከም አቅም ያላቸው ናቸው” ትላለች ብሩክታዊት ጥጋቡ። ስራው እጅግ አድካሚ፣ ዋጋ የሚያስከፍልና የተለያዩ እንቅፋቶች ያሉት ቢሆንም ስራው ልጆቹ ጋር ደርሶ የመጣውን ውጤት በመመልከት ጥንካሬ እንዲኖረን ያደርጋል።
እኔ ሚስትም እናትም የድርጅት አስተዳዳሪም ከአስራ ሁለት ሰዓታት በላይ ስራ የምሰራ ስለሆንኩ ልደክም እችላለሁ፤ በየሶስት ወሩ ለስራው ግብአት የሚሆን ጉዞ አደርጋለሁ፤ በኔ እምነት ሴቶች በጣም ብቁና በርካታ ተፈጥሮ የለገሰቻቸው ናቸው።
ስለዚህ ሁልጊዜ በጥንካሬ ወደፊት እጓዛለሁ። ወንዶች በሀላፊነት ቦታ እንደሚሆኑት ሴቶች ከፊት መስመር ላይ ተሰልፈው ቢሆን አለማችን እንደዚህ አይነት ፈተና ውስጥ ባልገባች ኖሮ እላለሁ።
አሁን በተለያዩ ሀላፊነቶች ውስጥ ብሆንም ለኔ ስኬት ጉዞ ነውና ስኬት በጉዞ መካከል የሚደረስበት ነው። በእያንዳንዱ ትግል ውስጥ ደስታ መፈለጌ ድካሙን ረስቼ አላማዬንና አላማዬን ብቻ እንድመለከት አድርጎኛል። የፈጠራ ስራ ንፁህ ጭንቅላት በመፈለጉ ለኢትዮዽያ ልጆች የጠብታ ያህል አገልግሎት ብሰጥም ጠብታዋም እንዳትቀር ወደፊት እጓዛለሁ።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 25/2013