የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በሀገራችን ከተከሰተ አንድ ዓመት ሊሞላው የቀሩት ጥቂት ወራቶች ብቻ ናቸው። ባለፉት ጊዜያት በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ በርካታ ዜጎቻችን ህይወታቸውን አጥተዋል። ሀገር የደከመችባቸው ብዙ ሊሰሩ ፣ ትውልድ ሊቀርጹ የሚችሉ የቀለም አባቶችን አጥተናል። የሀገር ሽማግሌዎቻችንን ተነጥቀናል። ብዙ ተስፋ የተጣለባቸውና ሙያቸውን በብቃት ሲወጡ የነበሩ የህክምና ባለሙያዎቻችንን አይናችን እያየ ሸኝተናል። ገና ሮጠው ያልጠገቡ ወጣቶች ሁሉ ህይወት ተቀጥፏል። ይሄ ዓለምን እያርበደበደ ያለው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ አሁንም ፈተና ሆኖ ቀጥሏል። እኛም ከህሙማን ስቃይና ከምናየው አስከፊ ሞት እየተማርን እንዳልሆነ የሚያሳዩ በርካታ ነገሮች አሉ። ከጥንቃቄው ይልቅ መዘናጋቱ እየጨመረም ነው።
በሀገራችንም የስርጭት ስፋቱ እየተባባሰ እንጂ እየቀነሰ አይደለም። የጤና ሚኒስቴር ሰሞኑን እንዳስታወቀው የቫይረሱ ስርጭት አስከፊ በሚባል ደረጃ ላይ ደርሷል። እስካሁን ባለው የምርመራ ሂደት ከ118 ሺህ በላይ ዜጎች በቫይረሱ ተይዘዋል ፤ ከእነዚህም 98 ሺህ አካባቢ ሰዎች ያገገሙ ሲሆን አንድ ሺህ 818 ሰዎች ደግሞ ህይወታቸውን አጥተዋል። አሁን ባለው ሁኔታ በየዕለቱ በሚደረገው ምርመራ በአማካይ ከ300 በላይ አዳዲስ ህሙማን እየተገኙም ነው። ከታማሚዎች ቁጥር መብዛት ጋር ተያይዞም የጽኑ ህሙማን ማከሚያ ክፍሎች እስከመታጣት ተደርሷል። ይሄ የሚያሳየው የቫይረሱ ስርጭት ምን ያህል አስከፊ ደረጃ ላይ መድረሱን ነው።
ህሙማንን ከአንዱ ወደሌላ ሆስፒታል መንገላላታትና ህክምና ሳያገኙ ሲያልፉ ማየት ደግሞ ምን ያህል ለቤተሰብ ለሀገርም ከባድ እንደሆነ መገመት አያዳግትም። በመሆኑም ‹‹ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ›› የሚለውን ብሂል ቀዳሚ አድርጎ መከተል አማራጭ የሌለው ምርጫ መሆኑን ለአንድም ደቂቃ ሊዘነጋ አይገባም።
ይሁን እንጂ በተለይ አሁን በከተሞች ላይ የሚታየው መዘናጋት ‹‹የኮሮና ቫይረስ አይገድልም፤ ማገገምም ይቻላል›› ከሚል የማዘናጊያ ግንዛቤ የሚመነጭ ነው። በዚሁ የተሳሳተ ግንዛቤ እያንዳንዱ ሰው ማድረግ ያለበትን
ጥንቃቄ እያደረገ አይደለም። ለምሳሌ ያህል ተማሪዎች በትምህርት ቤት ቅጥር ጊቢ ሆነው ቫይረሱን ለመከላከል የሚያደርጉትን ጥንቃቄ ከትምህርት ቤት ተለቀው ወደቤታቸው ሲሄዱ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ እያደረጉ አይደለም። በትራንስፖርት ላይ የአፍና አፍንጫ ማስክ ማድረግ ግዴታ ቢሆንም ይሄንን ተግባራዊ የሚያደርገው ሰው ቁጥር በጣም ጥቂት እየሆነ ነው። ከፍተኛ የህዝብ ብዛት በሚታይባቸው በእምነት ተቋማት ፣ በገበያ እንዲሁም በተለያዩ የስብሰባ ቦታዎች ፣ ምግብና መጠጥ ቤቶች፣ የስፖርታዊ እንቅስቃሴ በሚሰራባቸው ስፍራዎች ላይ የሚታየው ጥንቃቄ የጎደለው እንቅስቃሴም እጅግ አሳሳቢ ነው።
የኮሮና ቫይረስን አቅልሎ የማየቱ ሁኔታ አሁን ዋጋ እያስከፈለ መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል። ‹‹ውሃ ሲወስድ እያሳሳቀ ነው›› እንደሚለው የአበው ተረት ሁሉ አሁንም ኮሮና የለም ፣ አይገልም፣ ታሞ መዳን ይቻላል … የሚሉ አባባሎች ኮሮና ሲወስድ እያሳሳቀ ነው የሚለውን ሊደግመው እንደሚችል መገመት አያዳግትም። አሁንም የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን አቅልሎ ማየቱ የበለጠ ዋጋ እንዳያስከፍል ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል። ጉዳዩ የሚመለከተቻው አካላትም ማሳሰቢያ ከመስጠት በተጨማሪ መመሪያዎቹ አስገዳጅ እንዲሆኑና መመሪያዎችን በሚተላለፉት ላይም አስተማሪ እርምጃ መውሰድ ይኖርባቸዋል።
የኮሮና ወረርሽኝ ዛሬም ድረስ በዓለም ላይ እየተስፋፋ እንጂ እየተገታ አለመሆኑ ግልጽ ነው። እስካሁንም አስተማማኝ የፈውስ መድሃኒት አልተገኘለትም። በተለያየ መልኩ የክትባት ሙከራዎች በጅምር መልኩ እየታየ ቢሆንም አስተማማኝ ስለመሆኑና በመላው ዓለም በአጭር ጊዜያት ስለመዳረሱ አርግጠኛ መሆን አልተቻለም። በመሆኑም በአሁኑ ወቅት በእጃችን ያለው ትልቁና ፍቱኑ መድሃኒት ከጤና ባለሙያዎችና ከመንግስት የሚወጡ የመከላከያ መንገዶችን መተግበር ብቻ እና ብቻ ነው።
አሁንም መዘናጋቱ የበለጠ እንዳይጎዳንና ዋጋ እንዳያስከፍለን ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል። ኮሮና ከፍቷል ስለዚህ መዘናጋቱ ዋጋ እንዳያስከፍለን መጠንቀቁን ልናስቀድም ይገባል!
አዲስ ዘመን ታህሳስ 10/2013