ሞገስ ተስፋ
በሚቀጥለው ዓመት በከፍተኛ ደረጃ ለሰብአዊ ቀውስ ይዳረጋሉ ተብለው ከተሰጋላቸው አገራት መካከል አንዷ የመን ስለ መሆኗ እየተነገረ ይገኛል። ቢቢሲ የዓለም አቀፉ የነፍስ አድን ኮሚቴ ጥናት ጠቅሶ በድረ-ገፁ እንዳስነበበው የመን እ.ኤ.አ በ2021 ለሰብአዊ ቀውስ የተጋለጠች አገር ስትሆን፤ ሰብአዊ ቀውሶች ይባባሱባቸዋል ተብለው ከሚሰጉት ሀገራት ዝርዝር ውስጥም የመንን የመጀመሪያ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡
የዓለም አቀፉ የነፍስ አድን ኮሚቴ (IRC) እንዳስታወቀው አሁንም ድረስ በሀገሪቱ የዘለቀው ግጭት፣ የተስፋፋ ረሃብ እና እየከሰመ ያለው ዓለም አቀፍ የለጋሾች ምላሽ በቀጣዩ ዓመት በየመን ይከሰታል ተብሎ የተፈራውን ቀውስ በአስከፊ ሁኔታ ያባብሱታል።
የአገሪቱም አጠቃላይ ሁኔታ ‹‹ከድጥ ወደማጡ ሆኖ›› ከመሆን ባለፈም፤ ነገሮች ሁሉ እንዳልነበሩ ሊሆኑ፤ የዜጎቿ የወደፊት ተስፋም ሊጨልም እንደሚችልና የየመን ሁኔታ እየባሰበት ሊሄድ እንደሚችልም ድርጅቱ ስጋቱን ከወዲሁ ገልጿል።
የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ ለየመን እጅግ አስፈላጊ ከመሆኑ የሚናገሩት ደግሞ የየመን የእርዳታ ድርጅት ዳይሬክተር ታሙና ሳባድዜ ሲሆኑ እርዳታው ከመቸውም ጊዜ በላይ አሁን አስፈላጊ እንደሆነም ገልፀዋል።
የጉዳዩን አሳሳቢነት የተረዱትና ከአልጀዚራ ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት ታሙና እንዳሉት ግጭቱን ለማስቆም ከውስጥ በተጨማሪ የቀጠናውንና የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ትብብር ከምን ጊዜውም በላይ ድጋፍ እንደሚሹም ተማፅነዋል፡፡
አይአርሲ የተባለው ዓለም አቀፍ ድርጅት የመጪው ዓመት የየመን የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታ አስቸጋሪ እደሚሆን ማስጠንቀቁን የሚነግረን ደግሞ ቢቢሲ ሲሆን፤ ችግሩ ከዋና ከተማዋ ሰንዓ እንደሚጀምር፤ በአሁኑ ሰዓት በየመን ሃያ አራት ሚሊዮን ሰዎች ምግብ፣ ጥበቃ፣ የጤና አገልግሎት፣ ትምህርት ወይም ሌላ አንድ ዓይነት ሰብአዊ እርዳታን እንደሚፈልጉም ጣቢያው አስታውቋል።
ጉዳዩ የመን ላይ ያተኩር እንጂ በየመን ብቻ የሚያበቃ አይደለም። በአይአርሲ ጥናትና ክትትል የሰብአዊ ቀውስ ስጋት የተደቀነባቸውና በደረጃ ከተገለፁት አገራት ዝርዝር ውስጥ የመን፣ አፍጋኒስታን፣ ሶሪያ ኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ፣ ኢትዮጵያ፣ ቡርኪናፋሶ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ናይጄሪያ፣ ቬንዙዌላ እና ሞዛምቢክ በቅደም ተከተል የተቀመጡ ሲሆን የእነዚህ ሀገራት መንግሥታትም ሆኑ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ወደ ለየለት ቀውሱ ከመግባታቸው በፊት አስፈላጊውን የጥንቃቄና መከላከል ስራ ሊሰሩ እንደሚገባም ተገልጿል።
የአይአርሲ የአመጋገብ ምክትል አስተባባሪ አቤር ፎውዚ የመንን አስመልተው በሰጡት አስተያየት “ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የሰብአዊ ቀውስ ስጋት ፊቱን ወደ የመን አዙሯል።በእስከ ዛሬው ሂደት በየመን እንደዚህ ያለ አነስተኛ ድጋፍ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ተደርጎ አያውቅም።ዘንድሮ ነው በዚህ ደረጃ ዝቅ ብሎ የታየው። የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ድጋፍ ኃላፊ የሆኑት ማርክ ሎውኮክም ይህንኑ የአቤር ፎውዚን ሀሳብ የሚጋሩ መሆናቸውን ቢቢሲ የገለፀ ሲሆን፤ እ.ኤ.አ. በኖቬምበር ውስጥ የመን በዚህ ዓመት ከሚያስፈልጋት አስቸኳይ ገንዘብ ግማሽ ያህሉ ደርሶ እንደነበር፤ ለአገሪቱ የሚደረገው የገንዘብ ድጋፍም እየደረቀ፤ 13 ነጥብ 5 ሚሊዮን ከሆኑት የየመን ዜጎች ውስጥ 16ሺህ 500 ያህሉ በረሃብ ድባብ ውስጥ ያሉና ለከፍተኛ የምግብ እጥረት የተጋለጡ መሆናቸውን ተናግሯል።
የተባበሩት መንግሥታት ባለሥልጣናት ድርድሮችን እንደገና ለማደስ እና በዓለም ትልቁ ሰብአዊ ቀውስ በሚል የሚታወቀውን ይህን አደጋ ለማስቆም ተደጋጋሚ ጥረት ማድረጋቸውን፤ ይሁን እንጂ ከ2018 መጨረሻ ጀምሮ የሰላም ድርድር መቆሙን ቢቢሲ በድረ-ገፁ አስነብቧል።
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 8/2013