አስናቀ ፀጋዬ
በፈረንጆቹ አቆጣጠር የካቲት 7 ቀን 2020 የተከሰተውና ኮቪድ 19 የሚል አዲስ መጠሪያ ያገኘው የኮሮና ቫይረስ በመላው ዓለም የሚኖሩ ህዝቦችን ስጋት ውስጥ ከቶ ቆይቷል። ቫይረሱ ከአንዱ ወደ ሌላኛው ሃገር በፍጥነት እየተዛመተ መምጣቱ ደግሞ የስጋቱን ደረጃ ይበልጥ እያጎላው መጥቷል። በቫይረሱ የሚጠቁ ሰዎች ቁጥርም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ከመምጣቱ በሻገር የሟቾች ቁጥርም በዛው ልክ ማሻቀቡን ቀጥሏል።
የኮሮና ቫይረስ በሰዎች ጤና ላይ እያደረሰ ካለው ጉዳት በተጨማሪ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስም ማስከተሉን በተለያዩ ጊዜ ከዓለም አቀፍ የዜና አውታሮች የወጡ መረጃዎች ያሳያሉ። በተለይ ሰዎች ከአንዱ ሃገር ወደሌላኛው ሃገር የሚያደርጓቸው ጉዞዎች በቫይረስ ምክንያት በመቀነሱ በመካከላቸው ያለው ማህበራዊ መስተጋብር ተስተጓጉሏል።
ከዚህም በላይ ቫይረሱ በዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ ላይ ያደረሰው ተፅእኖም ቀላል የሚባል አይደለም።። በዚሁ ቫይረስ ሳቢያም የበርካታ ሀገራት ኢኮኖሚ መሽመድመዱንና ዓለም አቀፍ የንግድ እንቅስቃሴዎችም መዳከማቸውን ከቢ ቢ ሲ እና አልጀዚራ የወጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን በረራዎችም እንደወትሯቸው ህዝቦችን በማጓጓዝና የተለያዩ እቃዎችን ወደ ውጪ ሀገራት በመላክ የሚያገኙት ገቢ እጅግ እንዲያሽቆለቁል አድርጓል። ወደ ውጪ የሚላኩና ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶችም በከፍተኛ ደረጃ ቀንሰዋል። በዚህም ምክንያት በርካታ ሀገራት ከባድ የኢኮኖሚ ኪሳራ አጋጥሟቸዋል።
ከዚሁ ቫይረስ ጋር በተያያዘ ሀገራት ካጋጠማቸው የኢኮኖሚ ኪሳራ ባሻገር ታዲያ በልዩ ልዩ የኢኮኖሚ መስኮች ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞች ከሚሰሩባቸው ድርጅቶች ውስጥ በመቀነሳቸው ስራ አጥ ሆነዋል። በቫይረሱ ምክንያት የሰዎች እንቅስቃሴ መገደቡን
ተከትሎም የቱሪዝም ዘርፉም በከፍተኛ ደረጃ በመጎዳቱ ከዚህ ዘርፍ ተጠቃሚ የነበሩ ሀገራትም በእጅጉ መጎዳታቸውን እነዚሁ መረጃዎች ያመለክታሉ።
የቫይረሱ ስርጭት ከእለት እለት እየጨመረ መምጣትና በቫይረሱ የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ከፍ ማለቱ ደግሞ በዓለማችን ከባድ የኢኮኖሚ ቀውስ ሳያስከትል እንደማይቀር በዘርፉ ያሉ ተንታኞች እያስጠነቀቁ ይገኛሉ። ይህ ቀውስ ሳይበርድ በዚሁ ሁኔታ ከቀጠለም ከዚህ የባሰ ኢኮኖሚያዊ ድቀት ዓለማችን ልታስተናግድ እንደምትችል እየጠቆሙ ይገኛሉ።
በዚሁ የኮሮና ቫይረስ ምክንያት በእጅጉ ከተጎዱ የኢኮኖሚ ዘርፎች ውስጥ አንዱ ኢንቨስትመንት መሆኑንም ተንታኞቹ እየጠቀሱ ሲሆን፤ የኮሮና ቫይረስ የሰዎችን እንቅስቃሴ በእጅጉ የገታ ከመሆኑ አኳያና እንደልብ ተንቀሳቀሶ የመስራት እድልን በመነፈጉ አብዛኛዎቹ የዓለማችን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች ባሉበት ለመቆም መገደዳቸውን አስታውቀዋል።
ከቀውሱ በኋላም ዳግም ለማንሰራራት ጥቂት የማይባሉ ግዚያትን እንደሚፈጁና በዋናነት ደግሞ የውጪ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ከሚይዘው ከፍተኛ የስራ እድልና ከሚያስገባው ገቢ አኳያ ኢኮኖሚውን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚጎዳው አስጠንቅቀዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አሜሪካና እንግሊዝን ጨምሮ ሌሎች የአውሮፓ ሀገራት የኮሮና ቫይረስ ክትባትን እንዳገኙ በተናጥል እየገለፁ ቢሆንም ክትባቱን ለዜጎቻቸው እስኪያዳርሱ ድረስ በሽታው የሚያድረሰው ኢኮኖሚያዊ ተፅእኖ ግን አሁንም ሊቀጥል እንደሚችል ተንታኞች ግምታቸውን ያስቀምጣሉ።
በተመሳሳይ ክትባቱ በታዳጊ ሀገራት ዘንድ እስኪደርስ ድረስ ሊፈጅ የሚችለውን ግዜ ከግምት ውስጥ በማስገባትና ይህንንም ተከትሎ በቫይረሱ የሚያዙና የሚሞቱ አምራች የህብረተሰብ ክፍሎች ቁጥር ሊያሻቅብ ስለሚችል ኢኮኖሚያቸው በከፍተኛ ደረጃ ሊናጋ እንደሚችል ስጋታቸውን አስቀምጠዋል።
ዘጋርዲያን ከሰሞኑ ይዞት በወጣው መረጃ መሰረት ደግሞ ባለፈው መጋቢት ወር ኮቪድ 19 የዓለምን ኢኮኖሚ ሲያናጋ አብዛኛዎቹ ታዳጊ ሃገራትና እያደገ የመጣው ገበያቸው በእጅጉ እንደሚጎዳ ብዙዎቹ ስጋታቸውን ሲገልፁ መቆየታቸውን አስታውሷል። በተለይ ደግሞ እነዚህ ታዳጊ አገራት ኢኮኖሚያቸው በአብዛኛው የተንጠለጠለው ሸቀጣሸቀጦችን ወደ ውጪ ሀገራት በመላክ፣ ወደሀገር ውስጥ በሚያስገቡት የውጪ ሀገር ምንዛሬና ከቱሪዝም በሚያገኝ ገቢ ከመሆኑ አኳያ ኮቪድ በዓለም ኢኮኖሚ ላይ ያደረሰው ቀውስ በታዳጊ ሀገራት ላይ ይብሱኑ ሊበረታታ እንደሚችል ገምተው እንደነበር ጠቅሷል። የፋይናንስ ቀውስ ማእበልና እዳ ሊያጋጥማቸው እንደሚችል ግምቶች እንደነበሩም ጠቁሟል።
ከዚህ በተቃራኒ ግን ኮቪድ 19 ያደረሰው የፋይናንስ ቀውስ ማእበል ከስድስት ሀገራት ማለትም አርጀንቲና፣ ኢኳዶር፣ ቤሊዝ፣ ሌባኖስ፣ ሱሪናም እና ዛምቢያ ውጪ በሌሎች ታዳጊ ሀገራት ድጅ እንዳልደረሰ ዘገባው አመላክቷል። ኮቪድ 19 በተለይም በአፍሪካ ሀገራት ላይ ያደረሰው የኢኮኖሚ ቀውስ ያን ያህል እንደተፈራው እንዳልሆነም ጠቁሟል።
በተለይ በአብዛኛው የአፍሪካ ሀገራት ያሉ ህዝቦች በወጣትነት የእድሜ ደረጃ ላይ መገኘትና በሽታውን መቋቋም መቻላቸው ለዚህ ትልቁን አስተዋፅኦ ማበርከቱን ገልጸዋል።
የጤና ስርዓቶቻቸው ላለፉት ወረርሽኞች ምላሽ በመስጠት ረገድ የህዝቡን አመኔታ ማግኘታቸውም ኮሮና በኢኮኖሚያቸው ላይ ሊያደርስ የሚችለውን ተፅእኖ ለመቋቋም እንደረዳቸውም በዘገባው ተመላክቷል። ከሁሉ በላይ ደግሞ የቻይና ከኮሮና ቫይረስ በፍጥነት ማገገምና ወደ ውጪ የሚላከው የሸቀጣሸቀጥ ምርቶቻቸው ፍላጎት በከፍተኛ ደረጃ እንዲጨምር ማገዙ ኢኮኖሚያቸው በቫይረሱ ሽባ እንዳይሆን በእጅጉ ማገዙንም ጠቅሷል።
አዲስ ዘመንታኅሣሥ 7/2013