የስምንተኛ ክፍል ተማሪዎቹ ዐሊ መሐመድና ሄኖክ ከበደ በአዲስ አበባ ከተማ እሸት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የምገባ መርሀ ግብር ተጠቃሚ ናቸው፡፡ ለመርሀ ግብሩ በትምህርታቸው ላይ ትኩረት አርገው እንዲሰሩ እንደረዳቸው ይገልጻሉ፡፡ ይህን የተመለከቱት ወላጆቻቸውም ደስተኞች መሆናቸውን የሚገልጹት ተማሪዎቹ፣ ሁሌም መምህራኑን ሲመርቁ እንደሚሰሙ ነው የሚናገሩት።
ሁለት ልጆቻቸውን በዳግማዊ ብርሃን አፀደ ህፃናትና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚያስተምሩት ወይዘሮ ዓለምነሽ ጥላሁን ቀን ቆሎ ፣ ምሽት ደግሞ መንገድ ዳር ድንች አብስለው እየሸጡ ይተዳደራሉ፡፤ ልጆቻቸውም ከትምህርት ቤት ሲመለሱ በየቦታው እየተንቀሳቀሱ ትናንሽ ሶፍት እንዲቸረችሩ ያስገድዳቸው እንደነበር ይገልጻሉ። የልጆቻቸው በትምህርት ቤት ምገባ በመካተታቸው ደስተኛ መሆናቸውን የሚናገሩት ወይዘሮ አለምነሽ፣ ልጆቻቸው ከዚህ በኋላ ስለትምህርታቸው ብቻ እንዲያስቡ ዘወትር እንደሚመክሯቸው ይናገራሉ፡፡
የእናት ወግ የበጎ አድራጎት ማህበር ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ በተለይ በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የተማሪዎች ምገባ እያካሄደ ይገኛል። በያዝነው ዓመት በትምህርት ሚኒስቴር በኩል ገንዘብ ተመድቦ በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የህፃናት ምገባ ለማካሄድ ዝግጅቱ ተጠናቋል።
በአዲስ አበባ መሳለሚያ በሚገኘው የዳግማዊ ብርሃን የአፀደ ህፃናትና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ሽመክት ግርማ የህፃናት ምገባ ፕሮግራም ከቤተሰብ የኢኮኖሚ አቅም ችግር ጋር በተያያዘ በምግብ እጦት ምክንያት ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ፣ እንዳይቀሩ እንዲሁም ደካማ ውጤት እንዳያመጡ ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡ ተማሪዎች ስለ ምግባቸው በማሰብ ከትምህርታቸው እንዳይዘናጉ ይረዳል ይላሉ።
እንደ አቶ ሽመክት ማብራሪያ፤ ከትምህርት ቤቱ 2ሺ239 ተማሪዎች መካከል 616ቱ የአፀደ ህፃናት ተማሪዎች ናቸው። በትምህርት ቤቱ የተማሪዎች ምገባ ከተጀመረ 4ኛ ዓመቱን አስቆጥሯል። የተጀመረውም በትምህርት ቤቱ መምህራንና ሠራተኞች ባደረጉት ውስን ድጋፍ የነበረ ሲሆን፣ አሁን በእናት ወግ በጎ አድራጎት ድርጅት ድጋፍ እየተደረገለት ይገኛል፡፡ በተያዘው ዓመት በእናት ወግ በጎ አድራጎት ድርጅት 103 እንዲሁም በመምህራኑና ሠራተኞች 68 ተማሪዎች የምገባው ተጠቃሚዎች ናቸው፡፡
የከተማው ትምህርት ቢሮ ዘንድሮ ለ260 ተማሪዎች ኮታ መፍቀዱን አቶ ሽመክት ጠቅሰው፣ ለዚህም ተማሪዎችን የመለየት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ያስታውቃሉ። በዚህም ከ400 በላይ ተማሪዎች ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሁኔታ እንደሚመቻች ይጠቁማሉ፡፡
እንደ አቶ ሽመክት ገለጻ፤ ተመጋቢ ተማሪዎችን ለመለየት መምህራኑ ከተማሪዎቹ ጋር ስለሚውሉ ገፍተው የሚመጡ ችግሮችን ለአስተዳደር ገልፀው ታይቶ ተጣርቶ ይታቀፋሉ ቤተሰቦቻቸውም በአካል መጥተው ችግራቸውን ይናገራሉ የወላጆች ኮሚቴ ባለበት መኖሪያቸው ሄደው ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ በማጣራት በምገባው እንዲሳተፉ ይደረጋል።
በምገባው ቁርስና ምሳ እንደሚቀርብ የሚናገሩት አቶ ሽመክት፣ ቁርሳቸውን ገብተው እንዲመገቡ እንደሚደረግ ፣ ምሳቸው ደግሞ ከሌሎች ተማሪዎች እንዳይለዩና ለስነ ልቦና ችግር እንዳይዳረጉ በሚል በምሳ ዕቃቸው እንደሚደረግላቸው ይጠቁማሉ፡፡ የምሳ ዕቃ ያልያዙም ካሉ በተዘጋጀ ክፍል እንዲመገቡ አንዳንድ ጊዜም እንዲመርጡ ተደርጎ እንደሚዘጋጅላቸው ያብራራሉ።
በእሸት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የእናት ወግ በጎ አድራጎት ድርጅት የምግብ ባለሙያ ወይዘሮ ፋንቱ ካሳሁን ትምህርት ቤቱ የሚገኝበት የአውቶቡስ ተራ አካባቢ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው እና በሴተኛ አዳሪነትና የተሰማሩ ሰዎች የሚበዙበት መሆኑን ጠቅሰው፣ከዚህ ማህበረሰብ የወጡት ተማሪዎች በምገባው መካተታቸውን ይናገራሉ፡፡ በአቅራቢያው የሚገኙ ባንኮችና የህንፃ ባለቤቶችም በዚህ በጎ ተግባር ድጋፋቸውን እንደሚሰጡ ወይዘሮ ፋንቱ ይጠቅሳሉ።
ከትምህርት ቤቱ አቅራቢያ የሚገኘው የሸዋ ፀጋ ህንጻ ባለቤት እስካለፈው ዓመት ድረስ ለስምንት ዓመታት 64 ተማሪዎችን በራሳቸው ፈቃድ ምን እንርዳችሁ ብለው በመጠየቅ ቁርስና ምሳ ይረዱ እንደ ነበር የጠቀሱት ወይዘሮ ፋንቱ፣ ወርልድ ለርኒንግ የተባለ ድርጅትም ለአምስት ዓመት 130 ተማሪዎችን የደንብ ልብስ፣ ቦርሳና ሌሎች የትምህርት ቁሳቁስ ይረዳ እንደነበር ይጠቅሳሉ፡፡
እነዚህን ወገኖች በጤና፣ በስነ ልቦና፣ በትምህርት ከመደገፍ በተጨማሪ የተመጋቢ ተማሪ ወላጆችን በማደራጀት የኢኮኖሚ አቅማቸውን የማጎልበት ሥራ መሥራቱን አንድ የትምህርት ቤቱ መምህር ይጠቅሳሉ።
አምስት ኪሎ አካባቢ የሚገኘው የዐፄ ናዖድ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የተማሪዎች ምገባ አስተባባሪ አቶ ባዩ ወዳጆ እንደሚሉት፤ በትምህርት ቤቱ የተማሪዎች ምገባ የተጀመረው በእናት ወግ ከሦስት ዓመት በፊት ነው፡፡ እስከ አለፈው ዓመት ድረስም 70 ተማሪዎችን ሲመግብ ቆይቷል፡፡
ዘንድሮ ከአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ በተፈቀደ ኮታ ተጨማሪ 230 ተማሪዎች ምገባውን እንዲቀላቀሉ መደረጉን አቶ ባዩ ጠቅሰው፣ ምገባው ከተጀመረም አንድ ሳምንት ሆኖታል ይላሉ፡፡
በጥቃቅንና አነስተኛ የተደራጁ በምግብ ማዘጋጀቱ እንደሚሳተፉ ጠቅሰው፣ አንድ መጋቢ ለ30 ያህል ተማሪዎች መመደቡን ይናገራሉ፡፡ ምገባው ተማሪዎቹን ውጤታማ ለማድረግ ታስቦ መዘጋጀቱን የሚናገሩት አቶ ባዩ፣ ተማሪዎቹን በስነ ምግባርም በትምህርትም የተሻሉ እንዲሆኑ እንመክራቸዋለን ይላሉ።
በአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ የህፃናት ጤና ምገባ አስተባባሪ ወይዘሪት ሜቲ ታምራት፣ ምገባው ተማሪዎች የተሻለ ውጤት እንዲያመጡ እያስቻለ ነው ይላሉ፡፡ በአዲስ አበባ ከሚገኙ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 51ሺህ ተማሪዎች በምገባው እንደሚታቀፉ ጠቁመው፣ ለዚህም ለመጀመሪያ ዙር 66 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር መመደቡንና በጀቱም በታኅሳስ ወር መለቀቁን ይናገራሉ።
በተማሪዎች ምገባ ሦስት ደረጃዎች እንዳሉ የሚናገሩት ወይዘሪት ሜቲ፣ እነዚህም መደበኛ ምገባ፣ የአስቸኳይ ጊዜ ምገባ ወይም ድንገተኛ አደጋ በሚደርስባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ተፈናቃዮች ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ታስቦ የሚሰጥ ምገባ እንዲሁም ሦስተኛው አነስተኛ ኢኮኖሚ ያላቸው ወላጆች ተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም ናቸው።
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ጥር 21 /2011