አዲስ አበባ ፡- የሃገር ውስጥ ባለሃብቶች ሥራ ሊጀምሩ የኢንዱስትሪ ፓርኮች እየገቡ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ፡፡ በኢንዱስትሪ ፓርኮቹ መግባት ያልቻሉ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን በኢንዱስትሪ ፓርኩ ውስጥ ካሉ የውጪ ኩባንያዎች ጋር በትስስር እንዲሰሩ እየተደረገ መሆኑን ገለጸ፡፡
የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ መኮንን ሃይሉ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፤ የሃገር ውስጥ ባለሃብቶች በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ገብተው እንዲሰሩ መንግሥት ማበረታቻዎችን ያደርጋል፡፡
በዚህም መሰረት በሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ 3 የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ገብተው እየሰሩ መሆናቸውን አቶ መኮንን ጠቅሰው፣ሌሎች 6 ባለሃብቶች ደግሞ ወደ ፓርኩ ለመግባት በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
በግንባታ ሂደት ላይ በሚገኘው የቦሌ ለሚ ሁለት የኢንዱስትሪ ፓርክ 1 የሃገር ውስጥ ባለሃብት ገብቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸው፣ በቅርቡ በተመረቀው የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክም በተመሳሳይ 1 የሃገር ውስጥ ባለሃብት ገብቶ እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ ሦስት ባለሀብቶችም በዚሁ ፓርክ ለመግባት በዝግጅት ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡
በመቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥም እንደዚሁ 3 ባለሃብቶች ለመግባት እየተዘጋጁ መሆናቸውን ገልጸው፣ በድሬዳዋ የኢንዱስትሪ ፓርክ ደግሞ 1 የሃገር ውስጥ ባለሃብት ገብቶ እየሰራ እንደሚገኝ ዳይሬክተሩ አመልክተዋል፡፡
በኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ገብተው መስራት ያልቻሉ የሃገር ውስጥ ባለሃብቶችን በፓርኮቹ ውስጥ ከሚገኙ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ጋር የማስተሳሰር ሥራ እየተሰራ መሆኑን አቶ መኮንን ጠቁመዋል፡፡
በተለይ በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ትስስሩን በስፋት በመስራት15 የሃገር ውስጥ ባለሃብቶች በፓርኩ ውስጥ ከሚገኙ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ጋር በጨርቃጨርቅና አልባሳት ዘርፍ ቁልፍና ዚፕ የመሳሰሉትን ግብአቶች በማቅረብ እንዲሰሩ ተደርጓል ብለዋል፡፡
ይህንኑ አሰራር በሁሉም የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ተግባራዊ በማድረግ የሃገር ውስጥ ባላሃብቶች ውጤታማ፣ ትርፋማና አቅማቸውን በማጎልበት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የሚያስችሏቸው አሰራሮች መዘጋጀታቸውንም ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡
የሃገር ውስጥ ባለሃብቶች በፓርኮቹ ውስጥ ከሚገኙ የውጪ ኩባንያዎች ጋር በትስስር ሲሰሩ የቴክኖሎጂ ሽግግር እንደሚኖር ጠቅሰው፣ልምድና ክህሎት ስለሚቀስሙ ምርቶቻቸውን ለዓለም ገበያ ለማቅረብ እድሎች እንደሚፈጠሩላቸው ተናግረዋል፡፡ በገበያ ረገድ ያሉባቸውን ችግሮች ለመፍታት እንደሚያ ስችላቸውም ዳይሬክተሩ አያይዘው ገልፀዋል፡፡
የሃገር ውስጥ ባለሃብቶች በኢንቨስትመንት ዘርፉ ያላቸውን ሚና ለማጎልበት የሚያግዝ ስትራቴጂ በኢንቨስትመንት ኮሚሽን አማካኝነት መዘጋጀቱ ይታወቃል፡፡ ስትራቴጂው የሃገር ውስጥ ባለሃብቶች ያለባቸውን የፋይናንስና የቴክኒክ አቅም ለማሳደግና የገበያ ትስስር ለመፍጠር ትልቅ ድርሻ እንደሚኖረው ተጠቁሟል፡፡ ስትራቴጂው ፀድቆ ወደተግባር ሲገባ የሃገር ውስጥ ባለሃብቶች ምርቶቻቸውን በይበልጥ በማስተዋወቅ ተጠቃሚ እንዲሆኑና ያላቸውን አቅም የበለጠ በማጎልበት በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ያስችላል ተብሎም ይጠበቃል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 21 /2011
አስናቀ ፀጋዬ