ይቅርታ መጠየቅና እርቅ ማውረድ ካለበት አካል ጋር ሁሉ ይህንን ያደርጋል
መልዐክ ሆኖ ቢመጣ ሰው ሰይጣን በሚል እንደሚያነበው አውቆ ስሙን ይቀይራል
አዲስ አበባ ፡- የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፓሬሽን/ ሜቴክ /ይቅርታ መጠየቅና እርቅ ማውረድ ካለበት አካል ጋር ሁሉ እንደሚያደርግ የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ብርጋዴር ጀነራል አህመድ ሀምዛ አስታወቁ፡፡
ብርጋዴር ጀነራል አህመድ ሀምዛ በተለይ ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንገለጹት፤ ሜቴክ ከሥራ አጋሮቹ ጋር የነበረው ግንኙነት የተበላሸና በጸብ የተሞላ በመሆኑ በአሁኑ ወቅት ይቅርታ መጠየቅና እርቅ ማውረድ ካለበት አካል ጋር ሁሉ ይህንን ይፈጽማል። ተቋሙም የህዝብ እንደመሆኑ ከዚህ በኋላ ሚስጢር አይኖረውም፤ እቅዶች ድረ ገጾች ላይ ይቀመጣሉ፤ ለመገናኛ ብዙኃንም ክፍት ይሆናል ።
ተቋሙ አብረውት ከሚሰሩ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይቶችን እያደረገ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ‹‹አገልግሎት ሰጪ እስከ ሆንን ድረስ ከአገልግሎት ፈላጊው ዝቅ ብሎ ነው መታየት ያለብን›› ብለዋል፡፡ ደንበኞች ለከፈሉት ገንዘብ እንኳን አገልግሎት ሲጠይቁ ይሰጣቸው የነበረውምላሽ በጣም አደገኛና በጸብ የተሞላ እንደነበር በማስታወስ ይህንን ሁኔታ ለመቀየርም እንደሚሰራ አብራርተዋል።
ስኳር ኮርፖሬሽንን ለአብነት በመጥቀስም ከኮርፓሬሽኑ ጋር የነበረው ግንኙነት ጥሩ እንዳልነበረ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ኮርፖሬሽኑ በጣም ከፍተኛ ገንዘብ ከፍሏል፤ ተቋሙ ግን ጨርሶ ያስረከበው አንድም ፕሮጀክት የለም፡፡ ፕሮጀክቶቹን ካለማጠናቀቅም በላይ አንዳንዶቹን ወገብ ወገባቸው ላይ እያደረሰ ነው በሀይል እንዲረከቡ ያደረገው›› ሲሉ ያብራራሉ።
በሌላ በኩል መልካም ስምን ከመገንባት አንጻር አደረጃጀቱን መቀየር ያስፈልጋል ያሉት ብርጋዲዬር ጀነራል አህመድ ፣ ‹‹ሜቴክ ከአሁን በኋላ መልዐክ ሆኖ ቢመጣ እንኳ ሰው ሰይጣን ብሎ ስለሚያነበው ስሙን መቀየር አስፈልጓል››ብለዋል፡፡ ይህንን ለማከናወንም መረጃዎችን የማሰባሰብ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
መረጃ የማሰባሰብ ስራው ከተጠናቀቀ በኋላም በጥቂት ጊዜ ውስጥ አደረጃጀቱንና ስሙን በመቀየር በአዲሱ ስሙም አዲስ ሆኖ እንደሚቀርብና እንደ ማንኛውም የልማት ድርጅት ህግን ተከትሎ መስራት እንደሚጀምር አስታውቀዋል።
በአሁኑ ወቅት በስድስት ወራት ውስጥ ተሰርቶ የሚጠናቀቅ የሪፎርም እቅድ መዘጋጀቱን ገልጸው፣ ይህ እቅድ ሲዘጋጅ ይሳካሉ ተብለው ከተቀመጡ ግቦች መካከል ዋናው የተቋሙን የጠፋ ስም መመለስ፣ በህግና ስርዓት ብቻ ተከትሎ እንዲሰራ ማድረግ የሚሉት ዋና ዋናዎቹ መሆናቸውን አብራርተዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 21 /2011
እፀገነት አክሊሉ