አዲስ አበባ፤ በኢትዮጵያ የሚካሄደውን ሁሉን አቀፍ ሪፎርም ጀርመን ለመደገፍ ፍላጎት እንዳላት የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየርን አስታወቁ ፡፡ የፕሬዚዳንቱ ጉብኝት ወቅታዊና በሃገሪቱ እየተከናወኑ ያሉ የሪፎርም ስራዎችን ለመደገፍ የሚያግዝ መሆኑን የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ፡፡
ለአራት ቀናት ይፋዊ ጉብኝት በኢትዮጵያ የሚገኙት ፕሬዚዳንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየርን ትናንት በብሄራዊ ቤተመንግሥት ከፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ጋር በተወያዩበት ወቅት እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ የተደረገውን የዴሞክራሲ ሪፎርም እና ሴቶችን ለአመራርነት የማብቃት ሥራ አድንቀዋል፡፡እርምጃውንም ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ብሎም ለተቀሩት ሃገራት በሞዴልነት ይወሰዳል ፡፡
ኢትዮጵያ በቅርቡ እያጋጠሟት የመጡ የኢኮኖሚና ፖለቲካ ተግዳሮቶችን ጀርመን እንደምታውቃቸው ጠቅሰው፣ሀገራቸው ሪፎርሙን እንደምትደግፍ አረጋግጠዋል፡፡
በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ያሉ የሪፎርም ስራዎች አብዛኛው አውሮፓውያን ስለ አፍሪካ ያላቸውን የተሳሳተ ምስል ለማረም እንደሚያግዝ ተናግረው፣ ለሁለቱ ሃገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት አዲስ ምዕራፍ መክፈቱንም ገልጸዋል፡፡
እንደ ፕሬዚዳንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር ገለጻ፤ የሁለቱ ሃገራት ግንኙነት ረጅም ዘመን ያስቆጠረና ትልቅ ቁርኝት ያለው ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት እየታየ ያለውን ሁሉን አቀፍ ሪፎርም አጋጣሚ በመጠቀም የሃገራቱ ግንኙነት ከመደበኛው የልማት አጋርነት ወደ ሪፎርም አጋርነት ማሸጋገር ይገባል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት ለውጪ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ያስቀመጣቸውን የማዕቀፍ ማሻሻያ ቅድመ ሁኔታዎችን እንደሚያደንቁም ፕሬዚዳንቱ ገልፀው፤ ይህም አብዛኛዎቹ የጀርመን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ መዋእለ ንዋያቸውን ኢትዮጵያ ውስጥ ለመጠቀም ፍቃደኝነታቸውን እንዲገልፁ ማገዙን ጠቅሰዋል፡፡ ይህም የሃገራቱን ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት በይበልጥ የሚያሳድግ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በበኩላቸውየጀርመን ፌዴራል ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት በኢትዮጵያ እያደረጉ ያሉት ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ወቅታዊና በሃገሪቱ እየተከናወኑ ያሉ የሪፎርም ስራዎችን ለመደገፍ አጋዥ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
እንደ ፕሬዚዳንቷ ገለጻ፤ በጀርመን ብዛት ያላቸው የቢዝነስ ሰዎች በመኖራቸው ጉብኝቱ የኢትጵያን ኢኮኖሚያዊ ልማት የሚያግዝና በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት የበለጠ የሚያጠናክር ነው፡፡
ጀርመን የኢትዮጵያ ዋነኛ የልማት አጋር መሆኗን የጠቀሱት ፕሬዚዳንቷ፤ የሃገራቱን አጋርነት አሁን ካለው በላይ በማሳደግና በማጠናከር በሃገሪቱ የተጀመረውን ሪፎርም ለማስቀጠል ጉልህ ሚና እንደሚኖረው አስታውቀዋል፡፡
በጀርመንና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ግንኙነት ረጅም ታሪክ ያስቆጠረ መሆኑን የተናገሩት ፕሬዚዳንቷ፣ በቀጣይም የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በንግድ፣ በኢንቨስትመንትና በሌሎች ዘርፎች የበለጠ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ያላቸውን እምነት ገልፀዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የጀርመኑ ፕሬዚዳንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየርን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋርም ትናንት ተወያይተዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 21 /2011
አስናቀ ፀጋዬ