አገራችን ካለፉት ዘጠኝ ወራት ወዲህ በአዲስ የለውጥ ጎዳና ላይ መሆኗ ይታወቃል፡፡ ይህ ለውጥ ደግሞ አገሪቱን የሚመራው ፓርቲ በምርጫ ተሸንፎ ወይም በመንግስት ለውጥ የመጣ አይደለም፡፡ በመላው የአገሪቱ ህዝብ ግፊት እና ገዢው ፓርቲ ውስጥ ባሉ ለውጥ ፈላጊዎች ቅንጅት የተካሄደ ስር ነቀል ለውጥ ነው፡፡ በተለይ ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል ለለውጡ እውን መሆን ያደረገው ትግልና የከፈለው መስዋዕትነት የላቀ ነው፡፡
በሌላ በኩል በለውጥ ሂደቱ ውስጥ በትጥቅ ትግልም ሆነ በሰላማዊ መንገድ ከህዝብ ጋር ሲታገሉና ሲያታግሉ የነበሩ በርካታ የፖለቲካ ሃይሎችና አክቲቪስቶችም የለውጡ አካል ናቸው፡፡ እነዚህ ሃይሎች በዋናነት ከህዝቡ ጎን በመሆን ለውጡ ወደሚፈለገው ውጤት እንዲያመራ የራሳቸውን አስተዋፅኦ አበርክተዋል፡፡
ያም ሆኖ ግን ከለውጡ በኋላ በአንድ በኩል የውጤቱ ብቸኛ ባለቤት ለመሆን በሌላ በኩል ደግሞ ለውጡን ለመቀልበስ የሚደረጉ ጥረቶች ይታያሉ፡፡ በተለያዩ መንገዶች ህዝብን ወደ ግጭት በማስገባትና ግርግር በማስነሳት በዚህ አጋጣሚ ወደስልጣን ለመውጣት ወይም ከብጥብጥ ትርፍ ይገኛል በሚል የተሳሳተ አስተሳሰብ የሚንቀሳቀሱ ሃይሎች ይኖራሉ፡፡ እነዚህ ሃይሎች በአጠቃላይ ለውጥ አደናቃፊዎች ናቸው፡፡
የለውጥ አደናቃፊዎች ዋነኛ ተልዕኮ ሰላምን ማደፍረስ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ይህ ለውጥ ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች የተከሰቱት ግጭቶችና ጥፋቶች ሁሉ መከሰት ያልነበረባቸው፤ ነገር ግን ለውጡን ለማደናቀፍ ሆን ተብሎ የተቀነባበሩ እንደሆኑ መገመት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም የሚደረጉት የብጥብጥና የማተራመስ እንቅስቃሴዎች ገና አንድ አመት እንኳን ያልሞላውን ለውጥ በአጭሩ ለማስቀረት የሚደረጉ ካልሆኑ በስተቀር ሌላ ትርጉም አይኖራቸውም፡፡
በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በለውጡ ማግስት የተጀመረው የማበጣበጥ ስራም በተለይ አገሪቱን ወደተሻለ ደረጃ ሊያሸጋግሩ የሚችሉ የማሻሻያ እርምጃዎች መወሰድ ሲጀምሩ እየባሰ መሄዱና በየጊዜውም የተለያየ መልክና አቅጣጫ መከተሉ ህዝቡን ለማወናበድ ታልሞ የሚደረግ እንደሆነ ለመገመት ያስችላል፡፡
በተለይ አንድን ብሄር ከሌላ ብሄር ጋር ለማጋጨት በተለያዩ አግባቦች የሚፈጠሩት የግጭት መንስኤዎች የአገራችን የቆየ የመቻቻል ባህልና ሞራላዊ አስተምህሮ ባይኖር የከፋ የርስ በርስ ግጭትና ሊያስከትሉ እንደሚችሉ መገመት አያዳግትም፡፡
በዚህ ሂደት ውስጥ ለውጡን በማምጣት ሂደት የራሳቸው አስተዋፅኦ የነበራቸው የፖለቲካ ድርጅቶችና አክቲቪስቶች አሁን ያለው ለውጥ እንዲቀጥል ህዝቡን ወደ ሰላማዊ መንገድ የመምራት ትልቅ አገራዊ ሃላፊነት አለባቸው፡፡ ነገር ግን ከዚህ አንጻር ገና ያልተሻገርናቸው ችግሮች እንዳሉ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ምክንያቱም እስካሁን ባለው ሂደት አንዳንዶቹ የፖለቲካ ሃይሎች የዳር ተመልካች ሲሆኑ ከፊሎቹ ደግሞ የግጭት መንስኤ ሲሆኑ ይስተዋላል፡፡ ነገር ግን አሁን ባለው ሰላማዊ የፖለቲካ ምህዳር በመጠቀም የፖለቲካ ሃይሎች ህብረተሰቡን በፖለቲካ አስተሳሰብ ማስታጠቅና የተሻለ ግንዛቤን መፍጠር ዋነኛ ስራቸው ሊሆን ይገባል፡፡
እያንዳንዱ የፖለቲካ ድርጅት በአገሩ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ የሚኖረው ድርሻ ከህዝብ ያነሰ መሆኑን መገንዘብና ከህዝብ ጋር በመተባበር ለህዝብ መስራትን መለማመድ ይጠበቅበታል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ህዝብን ከህዝብ በማጋጨት ከሚገኘው ትርፍ ስልጣን ለማግኘት የሚጥር የፖለቲካ ድርጅት ካለ ሊያስብበትና ከወዲሁ መስመሩን ሊያስተካል ይገባል፡፡
ከዚህ በኋላ የአገራችን ህዝብ የሚፈልገው የተጀመረው የለውጥ ሂደት ከዳር ደርሶ በተጨባጭ የትግሉን ፍሬ አፍርቶ ማየት ነው፡፡ በተለይ አሁን የተጀማመሩት የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ጅምሮች ከዳር ደርሰው አገራችንም የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ትሩፋት ተቋዳሽ እንድትሆን፣ በአገሪቱ ያለው የፍትህ ስርዓት ተስተካክሎ ሁሉም በእኩልነት እንዲገለገልበት፣ እያንዳንዱ ዜጋ በአገሩ በነፃነት ሰርቶ እንዲጠቀም እንዲሁም መላው ህዝብ ከድህነት ወጥቶ የበለፀገች አገርን ለመገንባት ሰላማዊ ትግል አማራጭ የሌለው ብቸኛው መንገድ መሆኑን መረዳት ይገባል፡፡
በአገራችን በተደራጀ መንገድ ብሄርን የጨቆነ ብሄር አለመኖሩን መረዳት ይገባል፡፡ ቀደም ሲል የነበረው ችግርም ቢሆን ጥቂት ቡድኖች ለአገዛዝ እንደሚመቻቸው በብሄር ስም የፈጠሯቸው የፖለቲካ ደባዎች እንደነበሩም መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡ በመሆኑም አሁን የተፈጠረውን ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም በብሄር፣ በጎሳ፣ በሃይማኖት ወዘተ ሳንከፋፈል አንዲት የጋራ አገር እንዳለችን ተገንዝበን ባለን አቅምና ችሎታ ልክ ሰርተን የምንለወጥባት አገር ለመገንባት በጋራ መስራት ይጠበቅብናል፡፡
በተለይ እንደ አገር ከአንድ አመት በኋላ የሚጠብቀን አገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲዊ ሆኖ እዲጠናቀቅና ወደሚፈለገው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲያሸጋግረን ከምርጫ በፊት መስተካከል የሚገባቸው መንገዶች መጠረግ አለባቸው፡፡ በቅድመ ምርጫ ሂደቱ ላይ የጋራ መግባባት በመያዝ ከምርጫ በኋላም ሰላማዊ ሁኔታዎች እዲቀጥሉ ለማድረግ ከወዲሁ አጥርተን ልንገባበት ይገባል፡፡
አሁን አልፎ አልፎ የሚታዩ በአቋራጭ ወደስልጣን ለመምጣት የሚደረጉ ጥረቶችና የብጥብጥ መንገዶች ከወዲሁ መስመር ካልያዙና በቅድመ ምርጫው ሂደት ላይ መግባባት ላይ ካልተደረሰ ነገ የሚመጣው ምርጫ የሚያስከትለው ውጤት የከፋ ሊሆን ስለሚችል ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል፡፡
በዚህ ሂደትም በአገራችን የሚገኙ የፖለቲካ ሃይሎች ሁሉ ምርጫ የሚካሄደው የህዝቡን ፍላጎት ለማሟላት እንጂ በህዝቡ ራስን ለመጥቀም አለመሆኑን በመረዳት ለህዝብ መስራትን መለማመድ ይጠበቅባቸዋል፡፡ መርህን አንግቦ ዛሬ ላይ ለሰላም የሚሰራ የፖለቲካ ድርጅት ነገ የህዝቡን ፍላጎት ለመመለስ ችግር እንደማይገጥመውም ሊገነዘብ ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 20/2011