አስናቀ ፀጋዬ
የኮሮና ቫይረስ ከፈተናቸው የኢኮኖሚ ዘርፎች ውስጥ አንዱ ቱሪዝም መሆኑ ይታወቃል። በቫይረሱ ምክንያት ሰዎች ከአንዱ ሀገር ወደ ሌላው ሀገር የሚያደርጉት ጉዞ በመቀነሱም ዘርፉ በእጅጉ ተጎድቶ ቆይቷል። በተለይ ደግሞ ዋነኛ ገቢያቸው በቱሪዝም ላይ የተመሰረተ ሀገራትን ቫይረሱ በእጅጉ ፈትኗቸዋል።
ይሁንና ቻይናን ጨምሮ አንዳንድ ሀገራት በሰሯቸው ጠንካራ ቫይረሱን የመከላከል ስራዎች በአንዳንድ ከቫይረሱ ነፃ በሆኑ ግዛቶቻቸው ላይ የቱሪዝም ዘርፋቸውን ማነቃቃት ችለዋል። አንዳንዶቹም የቱሪዝም መስህቦቻቸውን ከጥንቃቄ ጋር ለጎብኚዎች ክፍት እንዲሆኑ አድርገዋል።
ቱሪዝም ከተነቃቃባቸው የአለማችን ሀገራት ውስጥ አንዷ ቻይና መሆኗን በዚህ ሳምንት የጠቀሰው አልጀዚራ በተለይ የቻይናዋ ‹‹ሃዋይ›› ተብላ የምትጠራው ሃይናን ደሴት የቱሪዝም ፍሰቷ ከእለት ወደ እለት እየጨመረ መምጣቱን አስነብቧል።
እንደዘገባው ከሆነ በአለም አቀፍ ደረጃ ሆስፒታሎች በኮሮና ቫይረስ ታማሚዎች በተጨናነቁበት፣ ምግብ ቤቶች በራቸውን በዘጉበትና ሰዎች በሽታውን ሽሽት በቤታቸው በቆዩበት በዚህ ወቅት በሚሊዮን የሚቆጠሩ የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች በደቡባዊ ቻይና ወደምትገኘው ደሴቲቱ ሃይናን ግዛት እያቀኑ መሆናቸውን ያትታል።
ይህች የቻይናዋ ‹‹ሃዋይ›› የሚል ስምን ያተረፈችውና ልክ እንደ አሜሪካዋ የሃዋይ ደሴት የአለም ቁንጮ የንግድ ደሴት ለመሆን ብዙም ያልቀራትና የታይዋንን ያክል የቆዳ ስፋት ያላት ‹‹ሃይናን›› የተሰኘችው ደሴት ላለፉት ስድስት ወራት ከኮሮና ቫይረስ ነፃ መሆኗን ተከትሎ አሁን አሁን ባለሱቆች ከቀረጥ ነፃ የገበያ ሞሎችን ለመክፈት፣ ጥንዶች ለጋብቻው ፎቶ ለመነሳት እንዲሁም የባህር ላይ ቀዛፊዎች ንፁህ አየር የሚተነፍሱባት በመሆኗ የብዙዎችን ቀልብ እየሳበች መምጣቷን ዘገባው ጠቅሷል።
መረጃው እንደሚያሳየው የኮሮና ወረርሽኙ ከመከሰቱ በፊት ምንም እንኳን የውጪ ሀገር ጎብኚዎች ቁጥር 87 ከመቶ ያህል ዝቅ ቢልም አሁን ባለፈው የጥቅምት ወር ብቻ ዘጠኝ ነጥብ ስድስት ሚሊዮን የሚጠጉ ጎብኚዎች ደሴቲቱን እንደጎበኙና ይህም ቁጥር ቀደም ሲል ከነበረው ዓመት እንዲሚበልጥ ይጠቁማል። ወደ ደሴቲቱ የሚመጡ ጎብኚዎች ቁጥር 90 በመቶ ሲቀንስ ደግሞ ይህ አሃዝ ከየካቲት ወር በጣም የራቀ እንደነበር አስታውሷል።
በፍጥነት እየጨመረ የመጣውን የቻይና የቱሪዝም ዘርፍ የኮሮና ቫይረስ እንዲያንቀላፋ ማድረጉን ተከትሎ በርካታ ዓለም አቀፍ ድንበሮች በመዘጋታቸው እንደ አብዛኛዎቹ የደቡብ ምስራቅ እስያ ሀገራት በተለይ የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ሃይናን ወደመሰሉና ከኮሮና ቫይረስ ነፃ ወደሆኑ መዳረሻዎች ለመምጣት መገፋፋታቸውን መረጃው አመልክቷል።
ለተጓዦች ወጪ የሚደረገው አዲሱ ከቀረጥ ነፃ የ100 ሺ የቻይና ዩዋን/15 ሺ 186 የአሜሪካን ዶላር/ በፊት ከነበረው 30 ሺ ዩዋን ወይም 4 ሺ 592 የአሜሪካን ዶላር ወጪ በሀምሌ ወር ላይ ለውጥ ካመጣ ጀምሮ የቱሪዝም ወጪ እንዲያድግ ማድረጉንም መረጃው አመላክቷል።
ሃይናን በአመቱ መጨረሻ 214 ነጥብ 1 ከመቶ ላይ ለመቆም በቀጣዮቹ አራት ወራት በዚህ አይነቱ ከቀረጥ ነፃ ሽያጭ 12 ቢሊዮን ዩዋን ወይም 1 ነጥብ 8 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ማስመዘገቧንና ይህም የኮሮና ቫይረስ ከመከሰቱ በፊት እአአ በ2019 ከተመዘገበው የ13 ነጥብ 61 ቢሊዮን (2 ቢሊዮን ዶላር) ሽያጭ ጋር ተመጣጣኝ እንደሆነም ዘገባው ጠቁሟል።
በቻይናዋ የደሴት ከተማ ሳንያ ውስጥ በሃይታንግ ቤይ ከቀረጥ ነፃ የገበያ ማዕከል ውስጥ ከሻኔል እስከ ጉሲ ያሉ የቅንጦት ምርቶችን ለመግዛት የሚሽቀዳደሙ ቱሪስቶችን በምሳሌነት ያነሳው ዘገባው ትእይንቱ ከጓሮ ሽያጭ ጋር አወዳድሮታል። በሃይናን ደሴት የታየውም የቱሪስት ጋጋታ የዚሁ ከቀረጥ ነፃ ግብይት ነፀብራቅ ሳይሆን እንዳልቀረ ዘገባው አትቷል።
ምንም እንኳን ሃይናን በ2019 ከጥር እስከ ጥቅምት ባሉት ጊዜያት ውስጥ የተቀበለቻቸው 46 ሚሊዮን ጎብኚዎች ቢሆንም ይህ አሃዝ በአሁኑ ወቅት ወደ 83 ሚሊዮን የአገር ውስጥ እና የውጭ ቱሪስቶች ቁጥር ከፍ ብሏል። በቀጣይም ደሴቲቱን የሚጎበኙ የሀገር ውስጥ ቱሪስቶችን ቁጥር ለመጨመርና ለማሳደግ ዝግጅት መደረጉን ከስፍራ የተገኘ መረጃ ስለመኖሩ ዘገባው አመላክቷል። ይህንንም ተከትሎ ሃይናን በተለይ መጪውን የፈረንጆች ገናና አዲስ አመት የሚያከብሩባት የውጭ ሃገር ቱሪስቶች ቁጥር እንደሚጨምሩ ከወዲሁ ተገምቷል።
ቻይና አሉኝ ከምትላቸው ምርጥ የባህር ዳርቻዎች ካሏቸው ደሴቶች ውስጥ አንዷ የሆነችውና ሃይናን ለውጭ ሃገር ጎብኚዎች ከቪዛ ነፃ ፖሊሲን በማውጣት በቻይና ቀደምት ስፍራን የያዘች ሲሆን ይህም የውጭ ሃገር ጎብኚዎች ያለቅጥ ወደዚች ደሴት እንዲፈሱ በር ከፍቷል። አሁን ደግሞ ከኮሮና ቫይረስ ነፃ መሆኗን ተከትሎ ከቀረጥ ነፃ ግብይትን በመፍቀድ የሀገር ውስጥና የውጭ ሃገር ጎብኚዎች እንዲጎርፉ አድርጋለች ይላል ዘገባውነ ሲያጠቃልል።
አዲስ ዘመን ህዳር 30/2013