ዳንኤል ዘነበ
የወጣትነት የእድሜ ዘመን ነፃነት የሚፈልግበት እና እምቢ ባይነት የሚጠነጠንበት ዘመን ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የወጣትነት የእድሜ ዘመን እምቅ ጉልበት ለሀገር ግንባታ የሚውልበትም ዘመን ነው። እዚህ ጋር ታላቁ ደራሲ ስብሃት ገብረእግዚአብሄር በትኩሳት መጽሀፉ ላይ የገለጸውን ሀሳብ ይህን ያጠናክራል። «…ወጣትነት ጥሩ ነው። ገንዘብ ባይኖርህም ጤና ይኖርሃል። መልክ ባይኖርህም አንጎል ይኖርሃል። እውቀት ባይኖርህም ጉራ ይኖርሃል። ደስታ ባይኖርህም ንዴት ይኖርሃል። ፍቅር ባይኖርህም ተስፋ ይኖርሃል። መጨቆን ቢበዛብህ ሪቮሉሽን ታነሳለህ። መኖር ቢያስጠላህ ወይም ቢያቅትህ ራስህን ትገድላለህ። ወጣት ነህና….» ሲል ወጣትነትን ገልፆታል።
የጋሽ ስብሀት ገለፃ፤ ወጣትነት በሁለት ተቃርኗዊ ስሜቶች የሚናወጥ የሰው ልጅ ወሳኙ የእድሜ ምዕራፍ እንደሆነ መረዳት ያስችላል። ወጣቱ በሀገር ግንባታ ሂደት ላይ የወጣቱን እምቅ አቅምና እውቀት መጠቀም እንደሚያስፈልግ ያስገነዝባል። መንግስታት በፈተና ወጀብ የተሞላውን ወጣቱን መሰረት አድርገው ቢሰሩ፤ ዘመን ተሻጋሪ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚችሉ ሳይታለም የተፈታ ነው።
የወጣቱን ተፈጥሯዊ ችሮታን በመዘንጋት አግላይ በሆነ መልኩ የሚጓዙ ከሆነ ውጤቱ ተቃራኒ ይሆናል። በሀገራችን ነባራዊ ሀቁን ስንፈትሽ ይሄንኑ ውጤት ይሰጣል። በኢትዮጵያ ያለ አግባብ እየባከነ ያለ ትልቁ ሀብት ወጣትነት እንደሆነ ይሰማኛል። ከሀገሪቱ ህዝብ የወጣቶች ቁጥር 70 በመቶ የሚደርስ ቢሆንም፤ የወጣቱን እምቅ አቅምና እውቀት ለመጠቀም በስፋት ሲሰራ አይታይም።
ወጣቱን መሰረት በማድረግ ተሰሩ ተብለው የሚቀርቡ ሪፖርቶች ቢኖሩም፤ መሬት ላይ ካለው እውነታ ፍጹም የሚቃረኑ ናቸው። በሀገራችን ወጣቱን ከማበረታታት ይልቅ አግላይ በሆነ መልኩ የተዘረጉት አሰራሮች ወጣቱን ወደ አልተገባ አቅጣጫ እየወሰዱት ስለመሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነው። በተለይ ባለፉት ሶስት አስርት ዓመታት የወጣቱ ተስፋ ወደ ጥልቅ ጉድጓድ እንዲገባ ሲደረግ ነበር። በሀገራችን በሲጋራ፣ አልኮልና ጫት ሱሶች የተጠመዱ ወጣቶች ቁጥር ከቀን ወደ ቀን ለመጨመሩ ትልቅ ሚና ነበረው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የስፖርት ውርርድ ቁማር ሱስ የወጣቱ ተስፋ የሚያጨልም አዲስ ክስተት በመሆን ብቅ ብሏል።
በኢትዮጵያ በከፍተኛ ፍጥነት እየተስፋፋ የሚገኘው የስፖርት ውርርድ (ቢቲንግ) የወጣቱን የህይወት ምዕራፍ ወደ ተስፋ ቢስነት ማሸጋገር ከጀመረ ውሎም፤ አድሯል። ከብሄራዊ ሎተሪ የተገኘው መረጃ በአዲስ አበባ ከ65 በላይ ቅርንጫፍ ያላቸው የቁማር ድርጅቶች መኖራቸውን ያመላክታል። ድርጅቶቹ ውርርዱን ለማካሄድ የሚያስችል መመርያ በኢትዮጵያ መንግስት ፀድቆ፤ ፍቃድ የሚያገኙ ድርጅቶች በህግ ማዕቀፍ ሆነው ውርርዱን እንዲያጫውቱ ተደርጓል። የብሄራዊ ሎተሪ አስተዳደር አፈፃፀሙን በመከታታልና በመቆጣጠር አብሮ ይሰራል።
በመንግስት እውቅና ድጋፍ እየተደረገለት በተለያዩ ካፌዎች፣ ባሮች፣ የእግር ኳስ ማሳያ ቦታዎች ውስጥ የስፖርት ቁማር የሚያጫውቱ ድርጅቶች እየተበራከቱ ይገኛሉ፡፡ ታዳጊዎች፣ ወጣቶች እና ተማሪዎች ከእነ ዩኒፎርማቸው በእነዚህ የስፖርት ቁማር ማጫወቻ ቤቶች በር ላይ ተደርድረው በተደጋጋሚ ጊዜ የሚታዩ መሆኑ አሳሳቢነቱን ከፍ እንደሚያደርገው ይነገራል፡፡
አዲሱ ገበያ አካባቢ ከሚገኙ ስጋ ቤቶች በአንዱ ተቀጥሮ የሚሰራ አንድ ወጣት የራሱን የህይወት ተሞክሮ መሰረት በማድረግ ይሄንኑ ነበር ያረጋገጠልኝ። የ27 ዓመቱ ናትናኤል ተገኝ በስፖርት ውርርድ መሳተፍ ከጀመረ ሁለት አመታትን ማሳለፉን ያስታውሳል። የስፖርት ቁማሩ ቀን ሲሰጥ ውርርዱ ያልታሰበ ሲሳይ ይዞ ይመጣል፡፡ ቀን ሲጥል ደግሞ በአንጻሩ ላልተፈለገ ዕዳ የሚዳርግ ሱስ መሆኑን ይገልፃል።
«አራት መቶ ብር አስይዤ፣ 11 የሚሆኑ የእግር ኳስ ጨዋታዎችን ውጤት ቀድሜ በመተንበይ 34ሺ ብር አሸንፌ አውቃለሁ፡፡» ሲል የፍስሃ ዘመኑን የሚያስታውሰው ናትናኤል በሌላ ጊዜ 5000ሺ ብር «የተበላበትን» ውርርድ በቁጭት በማስታወስ የስፖርት ቁማሩ እያሳሳቀ የሚወስድ ወንዝ ስለመሆኑ ይናገራል። የልኳንዳ ቤት ሰራተኛው ናትናኤል፤ በስፖርት ቁማር ህይወቱ እየተዘበራረቀ እንደሆነ ቢረዳም፤ ከስፖርት ውርርድ ቤቶች ቤተኛነቱን ለማቋረጥ ፍላጎት እንጂ አቅም በማጣቱ ቁማሩን እያጧጧፈው ይገኛል። በሀገራችን በተለይ በከተማችን አዲስ አበባ እንደ ስጋ ቆራጩ አይነት ወጣቶችን ማግኘት እየቀለለ መጥቷል።
የ23 ዓመቱ ወንድምአገኝ ታደሰ ደግሞ ለዚህ ትልቅ ማሳያ ይሆናል። የአዲስ አበባ ነዋሪው ወንድምአገኝ፤ የስፖርት ቁማርን እንደ ገቢ ምንጭ በማድረግ ሲጫወት እንደነበር ያስታውሳል። «በቁማር ተስቤ ልክ ወዳልሆነ የህይወት ምዕራፍ እስከመግባት ደርሼ ነበር። በፈጣሪና በቤተሰቦቼ እገዛ ቀላል በማይባል ሁኔታ ለማቆም ችያለሁ» ሲል የበግ ለምድ የለበሱ ህጋዊ አቋማሪ ተኩላዎች ሰለባ ሆኖ በትግል መውጣት መቻሉን ገልጿል። የስፖርት ውርርዱ አንዴ ከገቡበት ለመውጣት ፈታኝ መሆኑን የራሱን ልምድ በመጥቀስ የሚናገረው ወንድምአገኝ፤ ተወራራጆች ከጊዜያት በኋላ በረቡ ባልረቡ ጨዋታዎች ላይ ሳይቀር ተጠምደው ገንዘባቸውን ሲያፈሱ እንደሚያስተውል ይናገራል። ስሜቱ ልጓም ካልተበጀለት የተጫዋቾችን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ህልውና ከማናጋት እንደማይመለስ ይጠቁማል፡፡
አንድ ሱሰኛ ማናቸውም ነገሮችን በማድረግ ሱሱን ለማሟላት እንደሚጥረው ሁሉ ይሄንንም የውርርድ ሱስ በየትኛውም መንገድ ለማስታገስ ብዙ ርቀት የሚሄዱ ሰዎች እንዳሉም ይናገራሉ። ወጣቱ ወንድምአገኝ «የማውቃቸው ብዙ ወጣቶች፣ ጎልማሶች፣ ህጻናት፣ ሴቶች ሳይቀሩ በተመሳሳይ ችግር ውስጥ ናቸው »ሲል ነበር የችግሩን ስር መስደድ ያወጋኝ ።
የሐምሌ 19/67 መምህሩ ወጣት ስንታየሁ ግርማ፤ የስፖርት ውርርድ ቤቶች ጉዳይ መፍትሄ የሚሻ ስለመሆኑ ይናገራል፡፡ የቁማር ድርጅቶች በህጋዊ ፈቃድ የሚሰሩና ለመንግስት የገንዘብ ምንጭ ቢሆኑም፣ ውድ በሆነው ወጣት ሃይል ላይ የሚያስከትሉትን ቀውስ መመልከት አስፈላጊ መሆኑን ይጠቅሳል፡፡ የስፖርት ውርርድ በከፍተኛ ደረጃ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ያስከትላል። በተለይ በአህጉር አፍሪካ ሀገራት ላይ የችግሩ ጥልቀትና አሳሳቢነት ጎልቶ ይታያል። የስፖርት ውርርድ በከፍተኛ ደረጃ የተስፋፋበት ጎረቤት ሀገር ኬንያ አንዷ ማሳያናት ናት። «በኬኒያ በርካታ ቁጥር ያላቸው ወጣቶች የአቋማሪ ድርጅቶች ሰለባ ሲሆኑ ወጣቶች ጊዚያቸውን እና ገንዘባቸውን ለቁማሩ በማዋል ያሳልፋሉ፡፡ ተማሪዎች ለትምህርታቸው የሚሰጡትን ጊዜ በእዚህ የቁማር ውርርድ እየተሻማ ከመሆኑም በላይ፤ በሱሱ የተያዙ ራሳቸውን እስከማጥፋት የደረሱ ይገኛሉ››፡፡ ይላል፡፡
በዚህ የስፖርት ቁማር ውርርድ መንግስታት ከሚያገኙት ገቢ ይልቅ ሀገር ተረካቢውን ትውልድ እያሳጣ መሆኑን ይጠቅሳል። የሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ ከዚህ ብዙም የራቀ አይደለም ባይ ነው። የተወራራጆቹ እድሜ ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊ ተማሪዎች ለትራንስፖርት ተብሎ በሚሰጣቸው ገንዘብ ሳይቀር ይቋመሩበታል። ይህም አብዛኛዎቹ አወራራጅ ድርጅቶች በውርርዱ ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎችን ሲሳተፍ ክልከላ የማያደርጉ መሆኑን ያመላክታል።
በዚህ ረገድ ስንመለከተው በሀገሪቱ ያለው ሁኔታ ከሌሎቹ ሀገራት በይበልጥ አሳሳቢ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል። መምህር ስንታየሁ አክሎ፤ «የስፖርት ውርርዱ ‹ሥራ ሠርቼ እለወጣለሁ› የሚል ሳይሆን በቁማር እንደሚያልፍለት የሚያስብ ትውልድን እየፈጠረ ነው። ጤናማ ያልሆነ የዕድገት ሁኔታን ለወጣቶች የሚያስተምርና የአገሪቱን እሴትና ባህሎችንም የሚሸረሽር ነው። በተለይ በአገሪቱ ከሚስተዋለው ችግር ዋነኛው የአስተሳሰብ ድህነት በመሆኑ ወጣቱ ንቃተ ሕሊናው መልማት እንዳለበት ዕሙን ነው። በመሆኑም መማር፣ መሰልጠንና ለውጤታማነት መትጋት ይገባዋል። ካልሆነ ግን ይህን መሰሉ ድርጊት ትውልድ በመግደል ሀገር ያለተረካቢ ያስቀራልና፡፡ ሳይቃጠል በቅጠል» ሲል አፋጣኝ መፍትሄ ሊሰጥ እንደሚገባ አሳስቧል።
የስፖርት ውርርድ እንዲህ ጽንፍ እና ጽንፍ ላይ ከቆሙ ስሜቶች ጋር በፍቅር የሚላተም «ቁማር» ነው፡፡ ያም ቢሆንም ቅሉ ከህጋዊነት አላገደውም። በአዲስ አበባ ብቻ ከብሄራዊ ሎተሪ ፈቃድ አግኝተው የሚንቀሳቀሱ 65 ያህል የውርርድ ድርጅቶች እንደሚገኙ መረጃው ያመላክታል፡፡ የስፖርት ቁማር ውርርድ በሀገር አቀፍ ደረጃም በተመሳሳይ እየተስፋፋና ወጣቱን አደራ በላተኛ እያደረገ ይገኛል፡፡
የስፖርት ውርርድ ለማካሄድ የሚያስችል መመርያ በኢትዮጵያ መንግስት ፀድቆ፤ ፍቃድ ያገኙ ድርጅቶች በህግ ማዕቀፍ ስር ሆነው ውርርዱን እንዲያጫውቱ ተደርጓል። የብሄራዊ ሎተሪ አስተዳደር አፈፃፀሙን በመከታታል በመቆጣጠር አብሮ ይሰራል። በመንግስት እውቅና ድጋፍ በሚደረግለት የስፖርት ቁማር ወጣቱ በእድሜ ዘመን ነፃነቱ፣ እምቢ ባይ የተፈጥሮ ችሮታውን መሰላል በማድረግ ዘመኑን ወደ ጨለማ እያሻገረ ይገኛል። ስለዚህ በስፖርት ሽፋን የሚደረገው «ቁማር» ሊቆም እንደሚገባ የብዙዎች ጥያቄ ከሆነ ውሎ አድሯል። በመንግስት በኩል ተመሳሳይ የሆነ ፍላጎት የነበረ ሲሆን፤ የቁማር ድርጅቶች ላይ እርምጃ እንደሚወስድ ከአመት በፊት ቃል ተገብቶም ነበር።
የሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር የወጣቶች ስብዕና ልማት ዳይሬክተር አቶ አለሙ ሠዒድ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት ድርጊቱን ቁማር መሆኑን አረጋግጠው፤ የስፖርት ውርርድ ችግር በቅርብ የመጣና በአገሪቱ የተለያዩ ከተሞች እየተስፋፋ የሚገኝ አሉታዊ መጤ ድርጊት ነው። በርካታ ጠቀሜታ የሌላቸው ጎጂ እሴቶችና ባህሎች የወጣቶችን ባህሪ፣ ጤናማ ሕይወታቸውን ብሎም የማህበረሰቡን ኢኮኖሚ እየጎዱ እንደሆነ ጭምር ተገንዝበዋል።
ድርጊቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተስፋፋ በመሆኑ በተግባር ደረጃ የተወሰደ የእርምት እርምጃ እንደሌለ ገልጸው የነበሩት ዳይሬክተሩ፤ የቁማሩ ዓይነት የስፖርት ውርርድ መባሉ ብቻ ሳይሆን ፈቃድ አሰጣጥ ላይ ችግር እንዳለ ነበር ያመላከቱት።
ለአደንዛዥ ዕፅ ንግድም ፈቃድ ይሰጣል። ይህም ትልቁ ክፍተት ያለው ፈቃድ ሰጪ አካል ዘንድ ነው። ፈቃድ ሲሰጥ ለአገሪቱ ያለው መልካም ገፀ-በረከትና ጉዳት በሚገባ ለይተው መመርመር ላይ በርካታ ክፍተቶች ይስተዋላሉ። ከዚህ አንፃር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተነጋግሮ ለመፍታት ሚኒስቴሩ ከንግድ እንዲሁም ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጨምሮ ሌሎች 26 አጋር አካላትን በማስተባበር ችግሮቹን ለመከላከል እየተሰራ ይገኛል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በቀጣዩ አንድ ወር ግብረ ሀይል በማቋቋም መፍትሔ ለማምጣት እየሰራ ስለመሆኑ ከአንድ አመት በፊት አቶ አለሙ ሠዒድ ተናገረው ነበር።
በስፖርት ቁማር ላይ የተባለው መፍትሄም ሆነ አቋማሪ ድርጅቶች በአዲስ መልኩ ስራቸውን እያቀላጠፉ ይገኛሉ። የወደፊቱ ዓለምና የሰው ልጅ እጣ ፋንታ ያለው በአዋቂዎች እጅ ሳይሆን ባብዛኛው በወጣቶች አእምሮ ውስጥ ነው። ዛሬ ያልተኮተኮተና ያልታረመ ማሳ ነገ በአረምና በአራሙቻ ይወረራል። ስለዚህ የስፖርት ለምድ የለበሱ ተኩላ አቋማሪ ድርጅቶች በወጣቱ እንዲቆምሩ ህጋዊ ፍቃድ ተሰጥቷቸው የሚያደርጉትን ጉዞ መቋጫ ሊያገኝ ይገባል። ታዲያ እነዚህ የስፖርት ካባ የለበሱ ቁማርተኞች ሀይ ባይ ያስፈልጋቸዋል።
አዲስ ዘመን ህዳር 25 ቀን 2013 ዓ.ም