በሀገረ መንግስት ግንባታ ሃገርን የተሻለች፤ ለዜጎቿ ምቹና በተስፋ የሚኖሩባት ለማድረግ ማንኛውም ዜጋ እንደ ዜጋ፣ ገዥው ፓርቲን ጨምሮ የተፎካካሪ ፓርቲዎች እና ሀገራዊ ተቋማት የድርሻውን መወጣት ይኖርባቸዋል። መንግስት ሃገርን እስከ አስተዳደር ድረስ የዜጎችን ሰብአዊ እና ደሞክራሲያዊ መብቶችን በማስጠበቅ በሀገረ መንግስት ግንባታው ጉልህ ሚና መጫወት ይጠበቅበታል። ይህን ማድረግ በህገመንግስቱ ጭምር የተሰጠው ሀላፊነት ነው ።
ሀገራችን ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ ለውጥ ውስጥ ትገኛለች። ለውጡንም ተከትሎ ብዙ ድብልቅልቆሽ ማየት የተለመደ ነው። በርግጥ ይህ የለውጥ ወቅት መገለጫ ቢሆንም አንዳንዱ እውነታ ግን በአግባቡ ሊታሰብበት የሚገባ ነው። ተገቢውን ነገር በተገቢው ሰዓትና ቦታ አለማድረግ በራሱ ትልቅ ዋጋ ሊያስከፍለን እንደሚችል የትላንት ታሪካችን በቂ መማሪያ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ ።
የዛሬ የጽሁፍ መነሻ በገዥው የብልጽግና ፓርቲ ውስጥ አድብተው የሚገኙ አንዳንድ ግለሰቦች ባልተገባ መልኩ እያደረጉት ስላለው ለውጥ አደናቃፊ ተግባር ነው። እነዚህ ተግባራት በለውጥ ሰሞን ሊያጋጥሙ የሚችሉ ቢሆንም ቶሎ የማስተካከያ እርምጃ መውሰድ ካልተቻለ አጠቃላይ በሆነው የለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ ሊያስከትሉ የሚችለው አደጋ ትንሽ እንደማይሆን እገምታለሁ።
አሁን አሁን በፓርቲው በአመራር ደረጃ የሚገኙ እነዚህ ግለሰቦች ከሀገሪቱ ታሪካዊ ጠላቶች ባልተናነሰ ሃገር እና ህዝብ የጣለባቸውን አደራ በመዘንጋት ባልተገቡ ተግባራት ውስጥ ተሳታፊ ሆነው የሚገኑበት ሁኔታ እየተስተዋለ መጥቷል። በቅርቡ የአርቲስት ሀጫሉን ግድያ ተከትሎ በተከሰተው የሁከት ተግባር ተሳታፊ በመሆን ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የሚገኙ አመራሮች አንድ ማሳያ ናቸው ።
የእነዚህ ግለሰቦች ተግባር የብልጽግና ፓርቲ ይዞት የተነሳውን የፖለቲካ አስተሳሰብና ከአስተሳሰቡ የሚጠበቀውን ሕዝባዊ ወገንተኝነት እና ከዚሁ የሚመነጨውን ጠንካራ ዲሲፒሊን ታሳቢ ያደረገ አይደለም። አሁን አሁን በህገ ወጥ የመሬት ወረራ፣ ዜጎችን እርስ በርስ በማጋጨት፣ ፍትሃዊ ያልሆነ ጥቅም በማሳደድ ህዝብን በማማረር ወዘተ በመንግስትና በህዝብ ላይ ጫና እያሳደሩ ይገኛሉ። የለውጡ ሀይል ለጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ ተግዳሮት እየሆኑም ነው ።
እነዚህ ህዝብና መንግስት የሰጣቸውን ሃላፊነት በመዘንጋት ባልዘሯቸው ቦታ የሚበቅሉ ግለሰቦች ፖለቲካ በመርሆ መመራቱን ያልተገነዘቡና ወደ ስልጣን ያመጣቸውን የፓርቲ መርሆ በትክክል ያላወቁ ወይም የፓርቲያቸውን መርሆ በትክክል የተገነዘቡ አይደሉም። ተገንዝበዋል ከተባለም የፓርቲያቸውን መርሆ በጥቅም የሸጡ ናቸው። ወይም ወጥ
የሆነ የፖለቲካ አስተሳሰብ መፍጠር ያቃታቸው፤ በአጋጣሚው መጠቀም ይቻላል ብለው በተሳሳተ መንገድ የሚጓዙ ሊሆኑም ይችላሉ ።
እንደ ሃገራችን ነባራዊ ሁኔታ በለውጥ ውስጥ ከመሆናችን አንጻር የሚጠበቅ ቢሆንም እንደኔ እንደኔ ግን ፅንፈኛ ብሄርተኝነት እና የእውቀት ማነስ ተጨማሪ ችግሮች ናቸው ብዬ እገምታለሁ። የእውቀት ማነስ የሚለውን በብዙ መልኩ ልንመለከተው እንችላለን። አንደኛው የፖለቲካዊ ጨዋታ ልምድ ማነስ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ስለኢትዮጵያ ህዝቦች ስርአተ ማህበር፣ ስለህብረተሰብ እድገት እና የታሪክ ህግጋት ያላቸው እውቀት ማነስ ነው። ስለሆነም መንግስት በነዚህ አካላት ላይ የፈረስ ጭራ የፖለቲካ መርህን ሊከተል ይገባል።
ለመሆኑ የፈረስ ጭራ የፖለቲካ መርህ ምን ማለት ነው? በእርግጥ በሃገራችንም ሆነ በውጭ የፖለቲካ ጨዋታ ውስጥ የፈረስ ጭራ የፖለቲካ መርህን የሚባል ሰምቼ አላውቅም። ይሁን እንጂ የፈረስ ጭራ የፖለቲካ መርህን መንግስት እስካለ ድረስ ያለ እና የሚኖር ዋነኛ ሊባል የሚችል የፖለቲካ ጨዋታ እንደሚሆን እገነዘባለሁ።
ለአንድ ፈረስ ጭራው ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች ቢኖሩትም ዋነኛው የፈረስ ጭራ ጥቅሙ ፈረሱ ባእድ አካላትን ማለትም ዝንብን፣ ትንኝን፣ ወዘተ ነገሮችን ለመከላከል ይጠቀምበታል። ነገር ግን ምንም እንኳን የፈረስ ጭራ ለፈረሱ ይህን ያህል የሚጠቅም ቢሆንም በክረምት ወቅት ጭራው ሊቆረጥ ይገባል። ምክንያቱም በክረምት ወቅት የፈረሱ ጭራ ለፈረሱ ከሚሰጠው ጥቅም ይልቅ በፈረሱ ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ስለሚበልጥ። ምክንያቱም በክረምት ወቅት ጭራው ጭቃ ስለሚይዝና ጭቃው በጭራው ስለሚጠቃለል የፈረሱን አካል ከማቆሸሽም አልፎ በጭራው የተጠቀለለው ጭቃ ፈረሱን እየደበደበ ጉዳት ያደርስበታል። ለዚህም ነው በሃገራችን የፈረስን ጭራ በክረምት ወቅት የሚሸለተው።
ይህን ወደ ፖለቲካው ስናመጣው እንደሚከተለው ልንተረጉመው እና የፈረስ ጭራ የፖለቲካ መርህን የሚል ስም ልንሰጠው የምንችል ይመስለኛል። መንግስት በውስጡ ብዙ መዋቅሮች ይኖሩታል። በእነኚህም መዋቅሮች መንግስት የፖለቲካ እሩጫውን በአቀደለት እና በፈለገው አግባብ ለመከወን እና የሚያስተዳድራትን ሃገር የህዝቦች ይሁንታ ለማግኘት ብሎም በሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች ላይ የፖለቲካ ድል ለመቀናጀት የራሱን ፖለቲካዊ መርህ የሚያስፈፅሙለት ባለስልጣናትን ይሾማል።
ነገር ግን እነዚህ ባለስልጣናት መንግስት ባቀደው ልክ መጓዝ ካልቻሉና አንዳንዴም ያግዙኛል ብሎ ያስቀመጣቸውን መንግስት ውስጥ ለውስጥ ለመቃወም በመፈለግ ስልጣናቸውን ተገን በማድረግ በህዝብ እና በሃገር ላይ በደል ሲፈፅሙ መንግስት እነዚህን አካላት ልክ ጭቃ እንደነካው የፈረስ ጭራ በፈረሱ ላይ ጉዳት ሲደርስ እንደሚቆረጥ ሁሉ መንግስትም ሃላፊነታቸውን በአግባቡ ያልተወጡ ባለስልጣናትን እንደፈረሱ ጭራ ከመዋቅሩ ሊቆርጣቸው ወይም ሊቀንሳቸው ይገባል። ምክንያቱም ጭቃ በውስጡ እንደያዘው ጭራ ባለስልጣናትም የነተበ ሀሳብ በውስጣቸው ስለተሞላ።
“ከጠላት ክፉ የቅርብ” እንደሚባለው መንግስት በውስጡ ያሉ ባለስልጣኖቹን ለይቶ መንቀስ ይገባዋል። በብዙ ድካም የተገኙ ውጤታማ ተግባራትን ጥላሸት ሊቀቡ ይችላሉ። ከዛም ባለፈ ለተጀመረው የለውጥ ጉዞ ዋነኛ ተግዳሮት የሚሆኑበት አጋጣሚ ሊፈጠር ይችላል።
አንድ አንድ ፖለቲከኞች የህወሃትን አካሄድ ሃገር አፍራሽ ነው ሲሉ ይሰማል። አባባሉ ትክክል ነው። ነገር ግን ህወሃት በአንድ ቁርጡ እራሱን በማግለል ሌላውን እንደጠላት የሚቆጥርና በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የስነ ልቦና ጦርነት እና አካላዊ ውንብድና ሲፈፅም የኖረ እና አሁንም በማድረግ የሚገኝ ድርጅት ስለሆነ እንደጠላት የቆጠረህን ትጠነቀቅበታለህ። ነገር ግን ወዳጅ የሚመስሉ እና በውስጥ ያሉ ሐይሎችን መንግስትም ህዝብም በጥንቃቄ ሊመለከታቸው ይገባል ።
ለንፋስ መከላከል አስበህ ከጣራህ ላይ ብዙ ድንጋይ ብትደረድር የድንጋዩ ክብደት የቤትህን ውድቀት እንደሚያፋጥነው ለአፍታም ቢሆን መዘንጋት አያስፈልግም። ምክንያቱም ለጣራህ መጠቀም ያለብህን ሚስማርን አይደለም የተጠቀምከው። ስለዚህ ችግርህን እስከ ወዲያኛው ለማስወገድ ችግርን ማለባበስን እንደ መፍትሄ መውሰድ የተዳፈነ እሳት አይነት ነው። ችግርን ማለባበስ ደግሞ ችግሩ የገነነ ጊዜ ችግሩን ለማስወገድ ብዙ ዋጋ ያስከፍላል። ስለሆነም የብልፅግና ፓርቲ ሃላፊነታቸውን በአግባቡ ባልተወጡ የመንግስት ባለስልጣናት ላይ የፈረስ ጭራ የፖለቲካ መርህን በመጠቀም ውሎ ሳያድር ከስልጣናቸው በማንሳት ለፈፀሙት ህገ ወጥ ተግባር በህግ እንዲጠየቁ ማድረግ ይጠበቅበታል።
እነኚህን መንግስትና ህዝብ የሰጣቸውን ሀላፊነት ትተው ከፅንፈኛ ፖለቲከኞች እና ከፅንፈኛ ብሄርተኞች ጋር ህብረት አድርገው የሚንቀሳቀሱ ሀይሎችን በጠንካራ የፖርቲ ዲሲፕሊን በመገምገም በአጠቃላይ ለአዲሱ ስርአት ፖለቲካዊ አደጋ ከመሆናቸው በፊት ጠንካራ የእርምት እርምጃ ሊወሰድባቸው ይገባል። ይህን እውነታ ችላ ማለት ሀገርና ህዝብን ሊያስከፍል የሚችለውን ዋጋ ማሳነስ እንዳይሆን በአግባቡ ሊታሰብበት ይገባል።
በብዙ የሚታትሩ ቀን ከሌሊት ያለ እረፍት የሚተጉ የፖርቲውን አመራሮች ድካምም ዋጋ የሚያሳጣ ተግባር በመሆኑ አስቸኳይ መፍትሄ ይፈልጋል። ለዚህ ደግሞ መላው ህዝብ ንቁ ተሳታፊ ሊሆን ይገባል። ለውጡ በሱና ለእሱ የመጣ ስለሆነ እነዚህን ግለሰቦች ያለ ይሉኝታ ሊታገላቸውም ይገባል። አረም በጊዜው ካልተነቀለ ሰብል ላይ ሊያደርስ የሚችለው ጉዳት የሚታሰብ ከሚታሰበውም በላይ ሊሆን እንደሚችል መዘንጋት አይገባም። ለዚህ ደግሞ ትክክለኛው ጊዜ አሁን ነው።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 27/2012
በአሸብር ሃይሉ