የኢድ አል አድሃ አረፋ በዓል በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ በየዓመቱ በድምቀት የሚከበር ሲሆን ዘንድሮም ለ1441 ኛ ጊዜ እየተከበረ ይገኛል። የኢድ አል አድሃ በዓል የሚከበረው በዙል ህጃ (የሀጂ ወር) አስረኛ ቀን ሲሆን ዘጠነኛው ቀን ደግሞ አረፋ ይባላል። በተለያዩ ዓለማት የሚገኙ ሙስሊሞች የአረፋን ቀን የሚያሳልፉት በጾምና በጸሎት ነው፡፡ ነገር ግን መካ ለመሄድ እድሉን ያገኙት ደግሞ አረፋ በሚባለው ቦታ በመቆም ጸሎት በማድረስ የሚያሳልፉት ይሆናል። አረፋ የሚባለው ቦታ መካ መዲና የሚገኝ ሲሆን ስያሜው የተሰጠው አደምና ሀዋ ከገነት ከወረዱ በኋላ አንዳቸው ጅዳ አንዳቸው ህንድ ነበርና ያረፉት ከዚያ በኋላ አሁን አረፋ በተባለው ቦታ የተገናኙበትና አወቅከኝ አወቅሽኝ የተባባሉበት በመሆኑ ነው። የአረፋ ቀን በዚህ ሁኔታ ካለፈ በኋላ ህዝበ ሙስሊሙ ሌሊቱን በሙሉ በየመስኪዱ በመሄድ አላህን ሲያመሰግንና ታላቅነቱን በመመስከር ያሳልፋል።
አስረኛውን ቀን ደግሞ ሁሉም ሰው በጠዋት ተነስቶ የቻለ ሶላት ወደሚሰገድበት ቦታ በመሄድ ቀሪውም እቤቱ በመሆን እህል ሳይቀምስ የስግደት ሥነሥርዓቱን ያከናውናል። ከዚህ በኋላ በጀማ ወደሚሰገድበት የሄደው ወደ የቤቱ በመመለስ እንደየአካባቢውና እንደየአቅሙ ከብት፤ በግና ፍየል እንዲሁም ግመል እንደየሁኔታው ያርዳል። እርዱ ከተፈጸመ በኋላ ስጋውን ለሶስት ያካፍልና አንዱን እጅ በአቅራቢያው ለሚገኙ ደሃ ለሆኑ እንዲሁም ወላጅ አልባና ደካማ በመሆን ረዳት ለሌላቸው ችግረኞች የሚሰጥ ይሆናል። አንደኛው እጅ በእለቱ ቤተሰብ ዘመድ አዝማድና ጎረቤት ተሰባስቦ የሚበላው ሲሆን ቀሪው አንድ እጅ ለቤተሰቡ ለሌላ ቀን የሚቀመጥ ይሆናል። በዚህ መሰረት እያንዳንዱ ሙስሊም ካለው ላይ በአካባቢው ያሉትን ችግረኞች የማስታወስና የመርዳት ግዴታ ያለበት ሲሆን እንደዚህ አይነቱ ድጋፍ በምግብ ብቻ የሚወሰን ሳይሆን ችግር ያለባቸውን ሰዎች እንዳይታረዙ ልብስ እንዳይጠሙ የሚጠጡትንም የሚጨምር ይሆናል። ከዚህም በተጨማሪ እነዚህን በችግር ውስጥ ያሉ ወገኖችን ደስተኛ እንዲሆኑ ማድረግ እንደሚገባ በሸሪአ ታዝዟል። ይህ የመረዳዳትና የመደጋገፍ ሃይማኖታዊ ስርዓትም በኢትዮጵያም በስፋት ሲተገበር የኖረና እየተተገበረ ያለ የአንድነትና የህብረት መሰረት ሆኖ ይገኛል። በመዲናችን አዲስ አበባም ይህንን ከሚያደርጉት ቤተሰቦች መካከል የአቶ ይመር ሙሀመድ ቤተሰብ አንዱ ነው።
አቶ ይመር ሙሀመድ የተወለዱት በቀድሞ አጠራር በወሎ ክፍለ ሀገር ቃሉ አውራጃ አልብኮ ወረዳ አባ ወሬሆና ወይንም አሬራ ተብላ በሁለት ስሞች በምትታወቅ አንዲት ትንሽ የገጠር መንደር ነው። አሥራ ሁለት ዓመት እስኪሆናቸውም በተወለዱባት መንደር ካሳለፉ በኋላ አባታቸውን በሞት በማጣታቸው እናታቸውንና አራት እህቶቻቸውን እቤት አስቀምጠው በ1964 አ.ም ጨፋ ወደሚባል አካባቢ ከዛም ወደ ደሴ ያቀናሉ። ወደ ደሴ ያቀኑት ለትምህርት ነበር፡፡ ነገር ግን ሁሉ ነገር የተስተካከለ አልነበርምና የጀመሩትን ትምህርት አቋርጠው የጋራዥ ሥራ ለመጀመር ይገደዳሉ። የጋራዥ ሥራቸውን እየሰሩ ከቆዩ በኋላ አብዮቱ ፈንድቶ የደርግ መንግሥት ወደ ስልጣን ሲመጣ በአካባቢው የነበረው ሁኔታ ጥሩ ስላልነበር ደሴን መልቀቅ እንዳለባቸው ይወስናሉ። የመጣው ለውጥ ሀገራዊ አንደመሆኑ በወቅቱ የደርግ መንግሥት መሬት ላራሹን ሲያውጅ የተወለዱባት ከተማ የነበራቸው የቤተሰባቸው እርስት በመነጠቁ
ወደ ገጠር የመመለሱ ነገር የማይታሰብ ሲሆንባቸው በ1968 ዓ.ም ጉዟቸውን በስም ብቻ ወደሚያውቋት አዲስ አበባ ያደርጋሉ። ይህም ሆኖ ጣፋጭ የልጅነት ጊዜያቸውን ያሳለፉባት የትውልድ መንደራቸው የህይወት መስመራቸውን በልባቸው እንዳስቀመጠች ነበር።
የተወለዱባት መንደር አርባ አባወራዎችን የያዘች ነገር ግን እንደ አንድ ቤተሰብ የሚቆጠር የብዙ ተወላጆች ስብስብ ያለባት ነበረች። ያንን ታላቅና ሰፊ ቤተሰብ የያዘች መንደር የተመሰረተችው በአንድ አባወሬሆ በሚባሉ ታላቅ ባላባት ሲሆን የመንደሯም መጠሪያ ዛሬ ድረስ በእኒሁ ባላባት ስም አባወሬሆ እየተባለ ይጠራል። ከአባወሬሆ በፊት ስለነበረው ትውልድ አመጣጥ በትክክል የሚያውቅ ባይኖርም እስካሁን ድረስ በመንደሯ የሚኖሩት በሙሉ አማርኛና ኦሮሚኛ ቋንቋን አቀላጥፈው መናገር መቻላቸውና ከትውልድ ወደ ትውልድም የሚወለዱት ህጻናት ሁለቱንም ቋንቋዎች በአፍ መፍቻነት መጠቀማቸው የዘር ሀረጋቸው ሰፊ እንደነበር ከኦሮሞም ነገድ የተቀላቀለ እንደነበር የሚያመላክት መሆኑን ይናገራሉ።
በተወለዱበት አካባቢ የአረፋ በዓል በድምቀት ይከበር እንደ ነበር የሚያስታውሱት አቶ ይመር ዛሬ ቁጥሩን በውል ባያስታውሱትም የአርባውም ወንድማማች አባወራ ተወላጅና የልጅ ልጅ ቤተሰብ አንደ አንድ ተካፍሎ ይበላ ይጠጣና በችግርም ጊዜ ይረዳዳ እንደ ነበር ያስታውሳሉ። ዘመኑ የጥጋብ ነበር የእህል ችግር የለም እህል በአስር ሳንቲም ይሸመታል:: በግ በ2 ብር ከሀምሳ ይሸጣል በመሆኑም ችግር ያለበት አልነበረም። ይህም ሆኖ ግን ማንም ገበያ ወጥቶ ቢሸምትም ባይሸምትም በጣም ይደጋገፍ ይረዳዳ ስለነበር በመንደሯ የሚቸግረው ወይም ጾሙን የሚያድር ኖሮ አያውቅም። በመንደሯ እንዳለባት የሰው ብዛትም ጭቅጭቅና አለመግ ባባት ተሰምቶባት አያውቅም። ቁጥራችን ብዙ ቢሆንም ነዋሪው እንደ አንድ የቤተሰብ አባል የሚተያይ በመሆኑ ሁሌም ሰላምና ፍቅር ነን። በዚህ ሁኔታ ስላደኩ እኔ ዛሬም ድረስ ለማንኛውም ሰው ትልቅ ፍቅርና ክብር አለኝ ይላሉ። አቶ ይመር ከልጅነት ትዝታቸው ውስጥ ለሰው ልጅ ክብርና ፍቅር መስጠት እንዳለባቸው እየተማሩ ያሳለፉትንም ጊዜ እንዲህ ያስ ታውሱታል።ከመንደራችን አጠገብ በአካባቢው ነዋሪዎች በስፋት የሚታወቀውና ጀማ ንጉስ እየተባለ የሚጠራው ትልቅ መስኪድ አለ። የእኛን መንደር ከመስኪዱ የሚለየው ወንዝ ብቻ ነው። ይሄ ቦታ ደግሞ በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ በሰፊው የሚታወቅና በአካባቢውና ከአጎራባች ዞንና ወረዳዎች ጭምር በሺዎች የሚቆጠሩ የእምነቱ ተከታዮች ለአምልኮ የሚሰባሰቡበት ትልቅ የሀይማኖት ስፍራም ነው። ይህ ቦታ በተለይ የመውሊድ በዓል በድምቀት የሚከበርበት በመሆኑ በመውሊድ ቀን ከተለያዩ ቦታዎች ለሚመጡ የእምነቱ ተከታዮች የአካባቢው ነዋሪ ያደርግ የነበረው የመረዳዳትና የመደጋገፍ ሥራ ዛሬ ለአቶ ይመር ሌላው የደግነትና ለሰው የማሰብ ትምህርት ቤቴ ነው ይላሉ።
አቶ ይመር አዲስ አበባ ከመጡም በኋላ ነገሮች አልጋ በአልጋ ባይሆኑም ያገኙትን ሥራ እየሰሩ ትንሽ ቆይተው እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን አካባቢ የቀበሌ ቤት በማግኘታቸው የእሳቸውና የቤተሰባቸው ህይወት ምእራፍ ሁለት መስመር እየያዘ መምጣት ይጀምራል። እሳቸውም ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም እርስታቸውን በመነጠቃቸው አዝነው የነበሩትን ባለቤታቸውን፤ እናታቸውንና የእሳቸውን ድጋፍ የሚሹ ሌሎች ቤተሰቦቻቸውን አጎቶቻቸውን አዲስ አበባ እንዲመጡ አድርጓቸዋል። በወቅቱ አቶ ይመር ያስመጧቸውና በተለያዩ ምክንያቶች መተው እሳቸው ዘንድ የተቀመጡት ዘመድ አዝማድ ቁጥርም በየቀኑ ይጨምር ነበር ። በአንድ ወቅትም በቤተሰቡ ውስጥ ከሃያ በላይ ሰው ይኖር እንደነበር የሚያስታውሱት አቶ ይመር ነገር ግን አንድም ቀን ከሚበላውም ከሚጠጣውም ጎድሎ እንደማያውቅ ይናገራሉ። በዚህ ሁኔታ ጥቂት ጊዜያትን ካሳለፉ በኋላ የሚኖሩበት አካባቢ የወንዝ ሙላት አደጋ ይከሰትበታል ተብሎ ይሰጋ ስለነበር መንግሥት ምትክ ቤት ሰጥቶ የአቶ ይመር ቤተሰብና ሌሎች የአካባቢውን ነዋሪዎች ወደ መገናኛ ሃያ አራት ቀበሌ አካባቢ ያዛውራቸዋል።
አዲሱ ሰፈራቸው ከገቡም በኋላ በአካባቢው በርከት ያሉ የእስልምና እምነት ተከታዮች ቢኖሩም ጸሎት የሚያከናውኑበት መስኪድ ስላልነበር በአካባቢው በመሰባሰብ ክፍት ቦታ ፈልገው ጸሎት ያደርሱ ነበር። በዓላትንም የሚያከብሩት ተሰባስበው በድንኳን ውስጥ ሲሆን በዚህ ወቅትም ከጸሎቱ በተጓዳኝ በየበዓላቱ በአካባቢው ካለው የተቸገረውን ሰው በመለየት የጎደለበትን በየአቅማቸው እንዲረዳዱ ያደርጉ ነበር። በዚህ ሁኔታ ላይ እያሉ የሀጂ አመዴ ለማ ልጅ ሙሀመድ አመዴ የሚባሉት ያለባቸውን ችግር በመመልከት ያነጋግሯቸውና ዛሬ ሃያ አራት አመዴ መስኪድ የተባለውን ለመመስረት ይበቃሉ። እነዚህ አጋጣሚዎች ለአቶ ይመር የመተባበር የመደጋገፍና የመተሳሰብ ውጤት ለፍሬ የሚያበቃ መሆኑን ያስተማሯቸው አጋጣሚዎች ነበሩ። ይሄ ሁላ ሲሆን የአቶ ይመር ቤት በቋሚነት ከሚያኖሩት አስራ አንድ ቤተሰብ በተጨማሪ በየቀኑ የሚያስተናግደው እንግዳ አጥቶ እንደማያውቅ ይናገራሉ። ያለውን አዘጋጅቶ ማቅረቡም ትልቅ ልእግስትና ጥበብ ይጠይቃል የሚሉት አቶ ይመር የባለቤታቸውንም እንግዳ ተቀባይነት እንዲህ ይገልጹታል።
“እኔ የጓዳውን ነገር አላውቅም፤ ያለኝን አምጥቼ ለባለቤቴ እሰጣታለሁ፤ እሷ ሁሉንም ነገር ታውቅበታለች። በተለይ ዓመት በዓል በእኛ ቤት ለብቻ ተከብሮ አያውቅም፤ በርካታ እኛ የዳርናቸው ልጆች አሉ ዘመድ አዝማድም ይመጣል፤ ቤቱም በሰው ይሞላል። ይህን ሁላ አብልታ አጠጥታ የምትሸኘው እሷው ናት። በበዓላት ቀናት በጎረቤት ላሉ የክርስትና እምነት ተከታዮችም በቤታችን ምግብ የማዘጋጀት ልምድ አለን፡፡ ጎረቤቶች በሙሉ መጥተው በልተው ጠጥተው ይሄዳሉ። እርድ ስናደርግም በደንቡ መሰረት የቻልነውን ለሌላም ነገር ጨምረን መረዳት ላለባቸው አቅመ ደካሞች እናደርሳለን። ይሄ የኖርንበት ብቻ ሳይሆን የምንኖርበትም ልምድ ነው። ልጆቼም የእኔን አርአያ እየተከተሉ ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት እንኳን ሁለቱ ልጆቼ የኮሮናን መከሰት ተከትሎ ከሌሎች ጓደኞቿቸው ጋር በመሆን እርዳታ እያሰባሰቡ የተቸገሩትን እየረዱ ይገኛሉ፡፡ ይሄ ለእኔ ትልቅ የህሊና እረፍት ነው” ይላሉ አቶ ይመር።
“ለተቸገረ መድረስ ታላቅነት ነገር ነው። የእስልምና ሃይማኖት ያስቀመጣቸውን የመረዳዳትና የመደጋገፍ አስተምህሮ መተግበር ደግሞ ሁሌም የግድ ቢሆንም ዛሬ ባለንበት ወቅት ደግሞ የበለጠ አስፈላጊ ነው” የሚሉት አቶ ይመር፤ ዓለም አቀፍ ችግር የሆነው የኮሮና ቫይረስ መስፋፋት በሀገራችን በርካቶችን የእለት ጉርስ እና የቤት ኪራይ በማሳጣት ለችግር እየዳረገ ይገኛል። እንደነዚህ ዓይነት ሰዎች ደግሞ ዓይናችንን ከፍተን ማየት ከቻልን ሩቅ ሳንሄድ በየሁላችንም ሰፈር ይገኛሉ። በመሆኑም ከተረፈን ሳይሆን ካለን ላይ ማካፈል ይጠበቅብናል። እንዲህ ዓይነቱ ሰናይ ምግባር በምድር የአእምሮ እረፍት በሰማይም ትልቅ ትሩፋት፤ ትልቅ የነፍስ ስንቅ የሚያስገኝ ነው ።
በተጨማሪ መረዳዳታችን መደጋገፋችን ዛሬ እየተከሰቱ ላሉት ቀውሶችም መፍትሄ ይሆናል ብዪ አስባለሁ። ሰው ካልቸገረውና ሥራ ካልፈታ ወደ ክፉ ነገር አያመራም፡፡ ዛሬ በሀገራችን የተለያዩ አካባቢዎች የሚፈጠሩት ብጥብጦች አንዱ መነሻቸው ድህነትና ሥራ ፈትነት ነው። አንዱ እየበላ ሌላው ጦሙን የሚያድር ከሆነ ቅራኔ መፈጠሩ አይቀርም፡፡ በተመሳሳይ ሥራ ፈትነትም ካለ ለብዙ ችግሮች መነሻ ይሆናል፡፡ የተቸገረ ሥራ የፈታ ከሌለ ሌብነቱም ቀማኛነቱም ይቀንሳል። ስለዚህ ያለው ከተረፈው ሳይሆን ካለውም ላይ ቢሆን እየተሳሰበ መረዳዳት አለበት። በተመሳሳይ ጤነኛ የሆነ በሙሉ መስራት አለበት፡፡ እኔ ለዓርባ ዓመታት ያህል በኪራይ ቤቶች ድርጅት በሹፌርነት አገልግዬ ዛሬ በጡረታ ላይ እገኛለሁ፡፡ ነገር ግን ዛሬም መብራት ኃይል ተቀጥሬ በሙያዩ እየሰራሁ ቤተሰቤን እየደገፍኩ እገኛለሁ። ሁሉም ወጣት ከእኛ የሽራን ክቡርነት ሊማር ይገባል። እኔ ልጆቼን የምመክራቸውና የማወርሳቸው ከቤተሰቦቼ ያገኘሁትን መልካምነትን፤ ለትምህርት ትኩረት መስጠትንና ሥራን ማክበርን ነው። ልጆቼም ሆኑ የትኛውም ወጣት እነዚህን የሚያደረጉ ከሆነ የትም ቢሄዱ፤ ከማንም ጋር ቢኖሩ ሁሌ ስኬታማ ይሆናሉ፤ ቤተሰብም ቢመሰርቱ ደስተኛ ህይወት ይኖራቸዋል ይላሉ አቶ ይመር።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 24/2012
ራስወርቅ ሙሉጌታ