አዲስ አበባ፦ ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨት የሚደረጉ ሴራዎች ካሁን በኋላ ቦታ እንደሌላቸው የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል አደም መሐመድ አስታወቁ። የሰራዊቱ ወታደራዊ ቁመና የአገሪቱን ሉዓላዊነት እና የሕዝቡን ደህንነት በአስተማማኝ ሁኔታ መጠበቅ የሚያስችል እንደሆነም አመለከቱ።
ጄኔራል አደም መሐመድ በተለይ ከአዲስ ዘመን ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ከህግ ውጪ ሆኖ፤ በተለይ በሕዝቦች መካከል ቁርሾ በመፍጠር፤ ግጭት በመፍጠር፤ በሃይማኖትና በተለያዩ ምክንያቶች ሰዎች እየተፈረጁ ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨት የሚደረጉ ሴራዎች ካሁን በኋላ ቦታ እንደማይኖራቸው አስታውቀዋል።
ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጩ፤ ሃይማኖትን ከሃይማኖት የሚያጋጩ፤ ጎሳን ከጎሳ የሚያጋጩ ስራዎች ሆነ ተብለው የሚሰሩ ከሆነ፤ አድገው ወደ ዘር ማጥፋት፣ ወደ እልቂት የሚያመሩ በመሆኑ መንግስት እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቀዋል ። በእንደዚህ አይነት ሁኔታ ውስጥ መንግስት እርምጃ መውሰድ ካልቻለ የመንግስትነት ተልዕኮው ምን ሊሆን ይችላል? እንደዚህ አይነት ጥፋቶች አድገው እንደ ሩዋንዳና ሌሎች አገሮች እንደሆኑት የሚጠብቅ ከሆነ ሕገመንግስታዊነቱ በምን ይገለጻል ሲሉም ጠይቀዋል ፡፡
” ግልጽ መሆን ያለበት መንግስትና የመከላከያ ሰራዊት ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጩ እና አገርን የሚበትንና የሚያዳክም ማንኛውም ህገወጥ የሆኑ ተግባራትን እያየ ዝም አይልም ፡፡ ይህን ማስቆም በህገመንግስቱ የተሰጠው ኃላፊነት ነው ። የሰራዊቱም ተልዕኮ ይሄ ነው፡፡ መንግስትም ቢሆን የሀገርን ሉዓላዊነት የማስጠበቅ ኃላፊነት ፤ ግዴታም አለበት” ብለዋል ፡፡
የመከላከያ ሰራዊቱ የኢትዮጵያውያን ሰራዊት ነው ፤ተልእኮውም የሚመነጨው ከህገ መንግስቱ እንደሆነ ያመለከቱት ጄኔራል አደም ፣ ህገ መንግስቱ የሰጠውን ኃላፊነት በአግባቡ ይወጣል ለዚህም ዝግጁ ነው ብለዋል ። የሰራዊቱ ተልእኮ የሚመነጨው ከህገ መንግስቱ በመሆኑም ተልእኮውን ከየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ርዕዮተ ዓለም ጋር አይይዞ ማየት እንደማያስፈልግ ገልጸዋል ። ህዝቡም እንደዚህ አይነት አስተሳሰቦችን ሊታገል እንደሚገባም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የመከላከያ ሰራዊት ኢትዮጵያውያንን እኩል ሊያገለግል የሚችል ተቋም ሆኖ እየተገነባ መሆኑን አመልክተው፣ የጸጥታ ተቋማት የማንም ፓርቲ ዕሴት ወይም ሀብት ሳይሆኑ የኢትዮጵያ ሀብት ናቸው ሲሉም ተናግረዋል፡፡ በአንድ ፓርቲ ፕሮግራም ሊቀረጽና ሊገነባ የማይገባው እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡ በኢትዮጵያውያን ዕሴቶች፣ በአገር ሉዓላዊነት፣ ደህንነትና ብሔራዊ ጥቅም ተመስርቶ መገንባት ያለበት ተቋም ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡
በሰራዊቱ ውስጥ ለነበሩ በርካታ የሰራዊት የግንባታ ጥያቄዎች ብዙ ኪሳራዎች እንደነበሩ ጠቁመው፤ በአብዮታዊ ዲሞክራሲ የተቋም ግንባታ ላይ የተቀመጡ አስተሳሰቦችን በግለሰብ ደረጃ አለመቀበል እንደ ኃጢያት ይቆጠር ነበር፡፡ በዚህም የከሰርናቸው ኪሳራዎች አልነበሩም ማለት አይቻልም ብለዋል፡፡ ከዚህ ቀደም አንዱን ጠባብ ብለህ ታባርራለህ፤ ወይ ትከስሳለህ፡፡ ወይ አንዱን ትምክህተኛ ብለህ ትጠረጥራለህ፤ ታባርራለህ፤ ወይ ትከስሳለህ ነው ያሉት፡፡
የሰራዊቱም ጥንካሬ ከአንድ ፓርቲ የፖለቲካ ጥንካሬ የሚነሳ መሆን የለበትም፡፡ ከአንድ ፓርቲ የፖለቲካ ጥንካሬ የሚነሳ ከሆነ፤ ፓርቲው ሲጠነክር አብሮ የሚጠነክር ይሆናል፡፡ ሌላውን እያዳከመ የሚኖርም ይሆናል፡፡ ያ ፓርቲ ሲደክም፣ ነገ በሌላ መንገድ ወደ ስልጣን የሚመጣ ኃይል ደግሞ የሚንደውና የሚያፈርሰው መሆን የለበትም:: ይሄ ተቋም የአገር እናየሕዝብ ተቋም ሆኖ በትውልዶች መገንባት መቻል አለበት ብለዋል፡፡
ፓርቲዎች በራሳቸው በሚያደርጉት ጭቅጭቅና ንትርክ ይሄንን ተቋም መጠቀሚያ የሚያደርጉበት ሁኔታ ከተፈጠረ የሆነ ፓርቲ ወደስልጣን በመጣ ቁጥር እየወደቀና እየፈረሰ እንደገና የሚገነባ ይሆናል፡፡ እየፈረሰ እየተገነባ የሚሄድ ተቋም ደግሞ ይህችን ታላቅ አገር አይመጥንም ብለዋል ጄኔራል አደም፡፡
የመከላከያ ሰራዊቱ ከለውጡ በፊትም ሆነ በኋላ የልማት እና የሰላም ጀግና ሆኖ እየተንቀሳቀሰ እንደነበር ያመለከቱት ጄኔራል አደም፤ በዚህ በኩል ትልቅ ዝናና ስም ያለው ሰራዊት ነው፡፡ አሁንም በውስጥም ሆነ በውጪ ያሉ ማንኛውንም የሀገር እና የህዝብ ስጋቶችን በመከላከል ከፍተኛ ስራ እየሰራ ነው ብለዋል። በአገር ውስጥ ሰላምና መረጋጋትን በማረጋገጥና በማስከበር ሚናው ከፍተኛ እንደሆነም አስታውቀዋል ፡፡
ህገ መንግስቱ ሰራዊቱ ከፖለቲካ ገለልተኛ መሆን አለበት፤ በፖለቲካ ጉዳዮች እጁን አያስገባም ፣የፖለቲካ አዋላጅም መሆን እንደሌለበት በግልጽ ያስቀመጠ ቢሆንም ቀደም ባለው ጊዜ ሰራዊቱ የሚገነባበት የፖለቲካ ኢንዶክትሪኔሽን ህገ መንግስቱ ካስቀመጠው ከሰራዊቱ ዓላማና የግንባታ መርሆዎች አንጻር በተጻራሪው በአብዮታዊ ዴሞክራሲ አስተሳሰብ ፤ በአንድ ፖለቲካ ፓርቲ ርዕዮተ ዓለም ላይ የሚያተኩርና የሚያጠነጥን እንደነበር አመልክተዋል ።
የተለያዩ ርዕዮተ ዓለም እና አመለካከቶች ያላቸው ፓርቲዎች ህገ መንግስታዊ እውቅና አግኝተው እየተንቀሳቀሱ ባሉበት አገር፤ ሰራዊቱን በአንድ ፓርቲ ፕሮግራም ላይ፣ በአንድ ፓርቲ ርዕዮተ ዓለም ላይ መቅረጽና መገንባት ተገቢ እንዳልነበር ጠቁመዋል፡፡
በሪፎርሙ ከተከናወኑ ስራዎች አንዱ እና ትልቁ ሰራዊቱ የሰራዊት ግንባታ ዓላማ እና የሰራዊቱ ተልዕኮ ከየትኛውም የፓርቲ ፕሮግራም ወይም ርዕዮተ ዓለም በላይ እንዲሆን ማድረግ ነው ብለዋል ፡፡
በሪፎርሙ ሰራዊቱ በህገ መንግስቱ የተሰጠውን ተልእኮ በግልጽ አውቆ ለህገመንግስቱ ብቻ ታማኝ እንዲሆን በሚያስችል አስተሳሰብ እንዲገነባ ተደርጓል፤ ይሄ በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል ያሉት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ፣ የሰራዊቱ ህገ መንግስታዊ ተልዕኮ እጅጉን የገዘፈ ፤ከአንድ ፓርቲ ፕሮግራምና ዓላማ በላይ የሆነ ፣ የተከበረ፤ የአገርን ሉዓላዊነት፤ የሕዝብ ደህንነት ላይ መሰረት ያደረገ እንደሆነ ጠቁመዋል።
“ኢትዮጵያን እኔ ከሌለሁ ትፈርሳለች ወይም እኔ ካልተጠቀምኩ እናፍርሳት የሚለው አካል ሁል ጊዜ ቢናገርም፤ በእኔ በኩል ኢትዮጵያን የምትፈርሰው መጀመሪያ በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ላይ የሚያምኑት ሕዝቦቿ እና መሪዎቿ ከሌሉና ከሌሉ ብቻ ነው ፡፡ ከዛ በላይ ኢትዮጵያ የምትፈርሰው የመከላከያ ኃይላችን፣ የፀጥታ ኃይላችን፣ የደህንነት ኃይላችን ሲፈርስ፤ ወይም እሱ መስዋዕት ሆኖ ሲሸነፍ ብቻ ነው:: ስለዚህ አሁን ያለን የሪፎርም ስራዎች የአገራችንን ገናናነትና ሉዓላዊነት የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚያደርግ ስርዓት መፍጠር ላይ ያተኮረ ነው፤ የሰራዊት ግንባታውም እንዲሁ ፡፡ በአስተሳሰብም በተግባርም ኢትዮጵያን የበለጠ የሚያጠናክር ስራ ነው እየተሰራ ያለው” ብለዋል፡፡
አዲስ ዘመን ሐምሌ 18/2012
ወንድወሰን ሽመልስ