
አገራት ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ ብልፅግናን ለመቋደስ የአንድነትን ሃይል የህብረትንም የድል ምስጢር ጠንቅቀው በመረዳት በተለይ በንግድና ኢንቨስትመንት እርስ በእርስ መተሳሰርን አማራጭ ማድረግ ከጀመሩ አመታትን አስቆጥረዋል።
ከመገፋፋት ይልቅ መደጋገፍ ወሳኝ መሆኑን በመረዳት ራስ ወዳድ እና ስግብግብነትን በማስወገድ እርስ በእርስ ያላቸውን መስተጋብር ለማጠንከር እንዲሁም በኢኮኖሚ አቅም በእኩል ደረጃ መወዳደርም ሆነ መደራደር የሚያስችላቸውን አቅም ለማጎልበት የተለያዩ ተግባራት ሲያከናውኑም ቆይተዋል።
በኢኮኖሚ ልእልና ስማቸው አንቱ የሚባልላቸውን ጨምሮ በርካታ አገራት በዚሁ መንፈስ እየተመሩ መጪውን ጊዜ ለማሳመር በሚተጉበት በዚህ ወቅት ታዲያ ድንገተኛው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የአመታት ልፋታቸውን ከንቱ አድርጎታል።
ወረርሺኙ በአለምአቀፍ ደረጃ የሰዎችን ጤና ከማቃወስና ለህልፈት ከመዳረግ ባለፈ የአገራት ኢኮኖሚ እንዲሽመደመድ፣ ደረጃቸው እንዲያሽቆለቁልና እድገታቸው አደጋ ላይ እንዲወድቅ አድርጓል። የኢንቨስትመንትና የንግድ ትስስራቸውን በጣጥሶታል።
የወረርሽኙ መንሰራፋት ታይቶ በማይታወቅ መጠን በአራቱም አቅጣጫ መጠነ ሰፊ የኢኮኖሚው ድቀት በመከሰት በርካታ ዘርፎች ላይ ያስከተለው ሁለንተናዊ ጉዳት እንደተጠበቀ ሆኖ በተለይም አለምአቀፉን የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት(foreign direct investment /FDI/) ፍሰት ከሚጠበቀው በታች ዝቅ አድርጎታል።
ከሰሞኑ ይፋ የሆነው የተባበሩት መንግስታት የንግድና ልማት (UNCTAD)አመታዊው የኢንቨስትመንት ሪፖርት፣ በዚህ አመት አለም አቀፍ ኢንቨስትመንት ወደ 1 ትሪሊየን ዶላር እንደሚያሽቆለቁል ዕና ይህም እኤአ ከ2005 ወዲህ ታይቶ የማይታወቅ፣ እኤአ ከ2008 ከተከሰተው የፋይናንስ ቀውስም የከፋ ስለመሆኑ ጠቁሟል።
ድርጅት በድንገተኛው ወረርሽኝ ምክንያትም አለም አቀፉ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ለቀጣዮቹ ሁለት አመታት ሸክሙ እንደማይቀልለትና በተለይ በማደግ ላይ የሚገኙ አገራት በቀውሱ ምክንያት ይበልጥ ተጎጂ እንደሚሆኑም ይፋ አድርጓል።
በኮሮና ቫይረስ ቀውስ አለም አቀፉ የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰት በዚህ አመት እስከ አርባ በመቶ ዝቅ እንደሚል ያመላከተው የድርጅቱ ሪፖርት፣ ቀውሱም በመላ አለም በርካታ ኢንቨስተሮችና ኩባንያዎች የኢንቨስትመንት እቅዳቸውን ለመተግበር እንዲያመነቱ አሊያም ለሌላ ጊዜ እንዲያስተላልፉ እያስገደዳቸው መሆኑም አመላክቷል።
ሪፖርቱ በእሲያ አህጉር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ከ30 እስከ 45 በመቶ ያዘቀዝቃል ተብሎ መገመቱን ያመለከተ ሲሆን ከቅርብ አመታት ወዲህ በቀጠናው ኢኮኖሚ ምህዋር በተለይ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ይበልጥ በመሳብ የሚታወቁት ቬትናም፣ኢንዶኖዢያ፣ ታይላንድ፣ የመሳሰሉ አገራት ይበልጥ የቀውሱ ገፈጥ ቀማሽ ሊሆኑ እንደሚችሉን ትንበያውን አስቀምጣል።
የላቲን አሜሪካና የካረቢያን አገራትም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በወለዳቸው የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ እንዲሁም ለአመታት በተጠራቀሙ የኢኮኖሚ ድቀቶች ምክንያት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንታቸውን በእጅጉ እንደሚጎዳ ተጠቁሟል።
የድርጅቱ መረጃ ‹‹የአፍሪካ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትም በ2020 በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እንዲሁም በምርት ዋጋ ማጣት በተለይ በነዳጅ ፈላጊ ማጣት ምክንያት ይበልጥ ይቆስላል››ብለዋል።ወደ አህጉሪቱ የሚፈሰው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትም ከ25 እስከ 40 በመቶ አሊያም ከ25 እስከ 35 ቢሊየን ዶላር እንደሚቀንስ አመልክቷል።
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ እንደየዘርፉ የሚለያይ መሆኑን ያመለከተው ሪፖርቱ፤ በአጠቃላይ ወረርሽኙ የሚያሳድረውን ጫና በፍላጎት፣ በአቅርቦትና በፋይናንስ ዘዴዎች ከፋፍሎ ማየት እንደሚቻል አስረድቷል።
ወረርሽኙ ምክንያት ሁሉም ኢንዱስትሪዎች የቀውሱ ሰለባ መሆናቸው እርግጥ ቢሆንም በርካታ የአገልግሎት ኢንዱስትሪ ዘርፎች በተለይ የአቭየሽን፣ የሆስፒታሊቲ፣ ቱሪዝም፣ የመዝናኛው ኢንዱስትሪ ይበልጥ እንደሚጎዳው ተገምቷል። ከወረርሽኙ ጉዳት ለማገገም ጊዜ እንደሚወስድ የተጠቆመ ሲሆን‹‹የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ስቃይ ደግሞ ከሁሉ ይከፋል››ተብሏል።
የአፍሪካ ኒውስ ዘገባ በአንፃሩ፣ ምንም እንኳን አለም አቀፉ የኢንቨስትመንት ፍሰት ማሽቆልቆሉ እርግጥ ቢሆን ደቡብ አፍሪካ፣ ምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ጋና እንዲሁም ምስራቅ አፍሪካዊቷ ኢትዮጵያ አሸናፊ ሆነው ለመውጣት እንደማይቸገሩ አስነብቧል።
ምንም እንኳን የኢንቨስትመንት ፍሰቱ ከባለፈው አመት ጋር ሲነጻፀር መጠኑ መቀነሱ አይቀሬ ቢሆንም ኢትዮጵያ ከምስራቅ አፍሪካ አገራት ግንባር ቀደም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መዳረሻ ለመሆን እንደማይቸግራትና አገሪቱን ለዚሁ የተለያዩ ተግባራት በማከናወን ላይ ስለመሆኗ ተመልክቷል።
በእርግጥም በተያዘው ዓመት የኢትዮጵያ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ሊጨምር እንደሚችል ሲጠበቅ የነበረ ቢሆንም፣በኮቪድ-19 ምክንያት የተስተጓጎለውን የዓለም አቀፍ ንግድና የዓለም አቀፍ ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ተከትሎ ፍሰቱ ከሚጠበቀው በታች እንደሚሆን ይገመታል።
ሰኔ ወር አጋማሽ ላይ ይፋ በሆነ መረጃ፣ መንግስት በኮቪድ-19 ምክንያት እየተዳከመ የመጣውን የኢንቨስትመንት ዘርፍ ለመደገፍና ከውድቀት ለመታደግ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ማስታወቁም ይታወሳል።
ወደ ኢትዮጵያ የሚገባው የውጭ ቀጥተኛ የኢንቨስትመንት ፍሰት ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ በአማካኝ ከ50 በመቶ በማደግ ላይ የነበረ ሲሆን ከሁለት አመት በፊት ማለትም በ2010 ዓ.ም ወደ 4 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ብሎ ነበር።
ይህም ኢትዮጵያ በውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፍሰት ከምስራቅ አፍሪካ በቀዳሚነት፤ከአፍሪካ ደግሞ በአምስተኛ ደረጃ ላይ እንድትገኝ እንዳስቻላት የተጠቆመ ሲሆን፣ ይሄንንም ውጤት አጠናክሮ ለማስቀጠል መንግስት ካለፈው ዓመት ጀምሮ የንግድ ከባቢውን በማስተካከል ተከታታይ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን ማድረጉን አሳውቋል።
በዚህ ጠንካራ የእድገት ማሻሻያ ስራ ታግዞ በያዝነው ዓመት የሀገሪቱ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ያድጋል ተብሎ ቢገመትም ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የተስተጓጎለው የዓለም የኢንቨስትመንትና የንግድ እንቅስቃሴ ተከትሎ ፍሰቱ ከሚጠበቀው በታች ይሆናል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጽህፈት ቤቱ በመግለጫው አስረድቷል።
ፅህፈት ቤቱ ምንም እንኳን የፍላጎትና አቅርቦት ጫናእንዲሁም ዓለም አቀፍ የፋይናንስ አለመረጋጋት ቢኖርም እስከ አሁን በታየው ሂደት ባለሀብቶች በኢትዮጵያ መዋእለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ጠንካራ ፍላጎት ማሳየት መቀጠላቸውን አመልክቷል።
ወረርሽኙ በኢንቨስትመንቱ ላይ የሚያደርሰውን ተጽዕኖ ለመቋቋም መንግስት ባለሀብቱን በተለያየ ሁኔታ የመደገፍና የማበረታታት ሥራ እያከናወነ መሆኑንና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክም በሀገሪቱ የሚንቀሳቀሱ ባለሀብቶችን ለመደገፍ የሚውል 15 ቢሊዮን ብር ይፋ ማደረጉን አስታውሷል።
በጉዳይ ላይ ሰፊ ትንታኔ በመስራትን አስተያየቶችን በመስጠት ላይ የሚገኙ የተለያዩ መገናኛ ብዙኃንና ምሁራን በአንፃሩ አገራት የኢንቨስትመን ፍሰቱን ለማጎልበት የሚያደርጉት ድጋፍ የሚበረታታና ይበልጥ ሊጠናከር የሚገባው መሆኑን ከማስገንዘብ ባሻገር በቀጣይ ሊደረጉ የሚገባቸውን አበይት ተግባራትም ጠቁመዋል።
በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ አገራት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የሚያደርጉትን ፉክክሩ ይበልጥ እያጦዘው በመምጣቱ የተቀናጀ ጠንካራ ስራ መስራትና ተወዳዳሪነትን ማጠናከር ግድ እንደሚል፣ ኢንቨስትመንት በመሳብ ረገድ አሰራሮች በቀደመው መልኩ ይቀጥላሉ ብሎ መገመት ትልቅ ስህተት ስለመሆኑም አፅእኖት ሰጥቶታል።
‹‹አዳዲስ የፕሮሞሽን ሁኔታዎች እንደሚፈጠሩ ተግባራቸውም በቴክኖሎጂ የተደገፉ መሆኑንና በርካታ አገራትም ይሕን አቅጣጫ ወደ መጠቀም ፊታቸው በማዞር የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ላይ መጠመዳቸው መረዳት ይገባል››ብለዋል።
ኢትዮጵያስ ለዚህ አስተያየት ምን አይነት ምላሽ አላት፣ አቋሟስ በሚል የጋዜጣው ሪፖርተው ያነጋገራቸው የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ተመስገን ጥላሁንም፣ በጣም ጠንካራና ስራ መስራትና ተወዳዳሪነትን ማጠናከር ካልተቻለ እንደ ሌሎች አገራት ኢትዮጵያ ባለፉት አመታት ስትስብ የነበረችውን ኢንቨስትመን ለማስቀጠል እንደምትቸገር ተስማምተውበታል።
ኮሚሽኑም በወረርሽኙ ተፅዕኖ በመረዳት እጁን አጣጥፎ ከመቀመጥ ይልቅ በተለይ የኢንቨስትመት አቅምና አማራጮቻቸውን፣ በዌብ ሳይቶች ላይ በተሻለ ሁኔታ የማሳየት፣ ወደ ኢንቨስትመንቱ የሚመጡ ተዋናዮችም ከምዝገባ ጀምሮ የኢንቨስትመንት ፈቃድ እስከመስጠት ድረስ በቀጥታ የመረጃ መረብ የኦን ላይን ግልጋሎቶችን የማቅረብ ተግባራትን በትኩረት በመከወን ላይ ስለመሆኑም አብራተዋል።
መገናኛ ብዙኃኑና የምጣኔ ሃብት ምሁራኑ፣ አፍሪካውያን ኢንቨስትመንትን ለማጎልበት በተናጠል የሚሰራቸው ስራዎች ትሩፋቱ በርካታ ቢሆንም በጋራ የሚሰራቸው ተግባራት በተለይ እርስ በእርስ በንግድና ኢንቨስትመንት መተሳሰር ቢችሉ ከፍተኛ የኢኮኖሚ አቅም መፍጠር እንደሚችሉ አስረድተዋል።
የየቅል ጉዞን በማስቀረት በሀገራት መካከል ተመጋጋቢ የሆነ የኢኮኖሚና ትስስር ለመፍጠር ደግሞ ከሁለት አመት በፊት በሩዋንዳ ርዕሰ መዲና ኪጋሊ በተደረገ የአፍሪካ ህብረት አባል አገራት ጉባኤ ላይ ይፋ የሆነው የአፍሪካ የጋራ የንግድ ቀጠናን ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።
የምጣኔ ሃብት ምሁራንንና የግሉ ዘርፍ ተወካዮች በስምምነቱ አስፈላጊነት ከመስማማት ባለፈ ተግባራዊነቱ በተለይ መሰል የኮቪድ 19 ወረርሽኞች የሚያስከትሉትን ሁለንተናዊ በተለይ ኢኮኖሚያው ቀውስ ለመሻገር እጅጉን ወሳኝ ስለመሆኑም አስረድተዋል።
‹‹አፍሪካ በዓለም የንግድ ስርዓት ውስጥ ያላትን ቦታ በማሳደግ ከዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ማህበረሰቦች ጋር በእኩል ደረጃ መወዳደርም ሆነ መደራደር የሚያስችላትን አቅም እንድታጎለብት እንዲሁም አገራትም የንግድ ግንኙነት በማጠናከር በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን ህይወት ይቀይራል የሚል እምነት የተጣለበት ይሕ ስምምነት ከወረቀት ወርዶ መሬት ላይ ተግባራዊ ይሆን ዘንድ የአገራቱ ቁርጠኛ መሆን የግድ ነው›› ብለዋል።
አንዳንዶቹ በአንፃሩ የወረርሽኙን ስርጭት እንዴት በማያዳግም መልኩ መግታት ይቻላል የሚለው እስካልታወቀና የዚህ ፈተና መልስ የሚርቅ ከሆነም ፍሰቱን ለማጎልበት አስቸጋሪ መሆኑንና አስተዋፆውም ዳግም ወደ ቀደመ ተክለ ቁመናው ለመመለስም ምናልባት አመታት ሳያስፈልጉት እንደማይቀር ገምተዋል።
ከጨለማው ይልቅ ብርሃኑ የሚታያቸው በሌላ በኩል፣ አገራት የወረርሽኙን ስርጭት ለመከላከል ብሎም ቫይረሱን ሁለንተናዊ ጉዳት ለመቀነስ የወሰናቸው የክልከላ እርምጃዎች ቀስ በቀስ እየኑሱ በሚጓዙበት ወቅት ለውጦች መታየት እንደሚጀምሩና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት (foreign direct investment /FDI/)እኤአ ከ2022 ማግስት ቀስ በቀስ እያንሰራራ እንደሚሄድ፣ ካምፓኒዎችም ወደ መልካም ተክለ ቁመና እንደሚመለሱ ተማምነዋል።
‹‹አፍሪካ ከቅርብ አመታት ወዲህ ከበለፀጉት አገራት ወሳኝ ኢንቨስተሮች በተለይ ከቻይና፣ ዩናይትድ እስቴትስ፣ ብሪታኒያ፣ ፈረንሳይ እንዲሁም ሩሲያ ጋር ፍቅር በፍቅር መሆኗ እና በጋራ ለመስራት መፈራረሟ አህጉሪቱ ከቀውሱ በቶሎ እንድታገግም ድጋፍ ሊሆናት ይችላልም››ብለዋል።
በጉዳዩ ላይ ሰፊ ምልከታቸው የሚያጋሩ መገናኛ ብዙኃንና ምሁራን በአጠቃላይ፣ የጋራ ብልጽግና የተጎናጸፈ አለም መገንባት ወይም ለማሳካት ከተፈለገ ላለፉት ስህተቶችና ስኬቶች የተለየ ትኩረት መስጠት ግድ መሆኑም አመላክቷል። ‹‹አለም አቀፍ ወረርሽኞች የሚፈጥሩትን ተግዳሮቶች ለማስታገስና አዳዲስ የተፈጠሩ እድሎችን ለመጠቀም ወደ ደህንነት ብልጽግና ወይም እድገት ለመተርጎም ተባብሮ መሰራት ግድ ነውም››ብለዋል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 16/2012
ታምራት ተስፋዬ