
መላውን የሰው ልጅ የመኖርና ያለመኖር ጥያቄ ውስጥ የከተተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የስድስት መቶ ሺ ዜጎችን ነፍስ በመንጠቅ ከጫፍ ከመድረሱ ባሻገር በኢኮኖሚ ልእልና ስማቸው አንቱ የሚባሉ አገራትን ሳይቀር በእጅጉ እየፈተነ ይገኛል።
አገራት የተቃጣባቸውን የቫይረስ ወረራ ጉዳቱን ለመቀነስ ከሆነላቸውም ድል ለማድረግ መፍትሔ ይሆናል የሚሉትን በተቻላቸው አቅም ከመሞከር ባይቦዝኑም ጥረታቸው ግን ፍሬያማ መሆን አልቻለም።ወረርሽኙም በርካታ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ኪሳራን ከመፍጠር የሚያስቆመው አልተገኘም።
በተለይ የዓለም ኢኮኖሚ ከሁሉ በላይ በህዝብ እንቅስቃሴ ላይ መሰረቱን ያደረገ እንደመሆኑ የኮቪድ19 ወረርሽኝ ስርጭት ለመቆጣጠር በተላለፉ ውሳኔዎች ምክንያት ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ክፉኛ መንኮታኮት ግድ ብሎታል።
የወረርሽኙ መንሰራፋት በርካታ ዘርፎች ላይ ያስከተለው ሁለንተናዊ ጉዳት እንደተጠበቀ ሆኖ በተለይ ከመደበኛ እንቅስቃሴ መቋረጥ ጋር በተያያዘ በሆቴል፣ በቱሪዝምና በትራንስፖርት ኢንዱስትሪው ላይ ያሳረፈው ጡጫ እጅጉን ከባድ ሆኖ ተስተውሏል።
ቀውሱም በተለይ የከተማ ኢኮኖሚ ደምስሮችን በመበጣጠስ በርካታ ኩባንያዎችና የንግድ ተቋማት እንዲዘጉ ብሎም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ሙሉ ለሙሉ አልያም በከፊል ሥራ እንዲያጡ ምክንያት መሆኑን ቀጥሏል።
መገናኛ ብዙሃንና የምጣኔ ሀብት ምሁራንም፣ በተለይ ደሃ አገራት ያላቸውን ጥቂት ሀብት ተጠቅመው ቫይረሱን ለመከላከል በሚያደርጉት ጥረት ወረርሽኙ ጥሎባቸው የሚያልፈውን ጥቁር ጠባሳ ከማጉላት ባሻገር በቫይረሱ ምክንያት እያደር የሚቀበሉት ኪሳራ እጥፍ ድርብ እንደሚሆን ግምታቸውን በማስቀመጥ ላይ ተጠምደዋል። ምሁራን፣ ፀሐፍትና መገናኛ ብዙሃኑ ኮቪድ 19 እና የከተማ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማትን በሚመለከት በሚያስተላልፏቸው ሃሳቦች፤ ‹‹በአፍሪካ ምድር የከተማ ልማትና ኢኮኖሚ ግንባታ ላይ ከተሠራው ይልቅ ያልተሠራው ይልቃል።ከታነፀው ይልቅ ያልታነፀው የትየለሌ ነው።ከተገነባው በላይ መገንባት ያለበት ብዙ አለ።ተጀምረው ያላለቁ፣ ገና ምንም ያልተጀመሩና ያልተነኩ ሥራዎች›› አሉ የሚሉ ጠንካራ አቋሞችን አሳይተዋል።
ታዋቂው የኒው ዮርኩ ታይምስ አርታኒ Michael Kimmelman ‹‹ዓለማችን እስከአሁን ካስተናገደቻቸው ወረርሽኞች መካከል በርካቶቹ ‹‹ፀረ ከተማ ናቸው›› እንደሚለው የወቅቱ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ኮቪድ 19ም የአገራትን የከተማ ሕይወት በከፍተኛ ደረጃ ለውጦታል።
አገራት ወረርሽኙን ለመከላከል በሚያደርጉት ጥረት የሰዎች ዝውውር ተገድቧል።በታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የዓለም ሕዝብ 1/3ኛ ከቤቱ እንዳይወጣ ተደርጓል። ለወትሮው በሰዎች ግርግር የሚደምቁ ታላላቅ የዓለምችን ከተሞች ፀጥ ረጭ ብለዋል።
አገራት ድንበራቸውን መዝጋታቸውና የአየር ትራንስፖርት አገልግሎቶችን ማስቆማቸውን ተከትሎም ከውጭ አገራትም ሆነ ከአንድ ከተማ ወደ ሌላ ከተማ የሚዘዋወሩ የሚገቡና የሚወጡ ሰዎች እንዲሁም ጎብኚዎች ቁጥር በእጅጉ ቀንሷል።በተለይም አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ብሎም የንግድ ማዕከላትን እንቅስቃሴ በማሽመድመድ የከተሞችን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴና ልማት አስተጓጉሎታል።
ለአንድ ሀገር ኢኮኖሚያዊ ብልጽግና የከተማ ልማት መጎልበት እጅግ በጣም ወሳኝ ሚና እንዳለውና ከተሞችም የኢኮኖሚ ሞተር ዘዋሪ ስለመሆናቸው አፅንኦት የሚሰጡት ምሁራን፣ ብዙ መዘርዘር ሳያስፈልግ የከተማ ኢኮኖሚ ልማት መጎልበት በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር፤ ለመንግሥትም ቢሊየን የብር ኖቶችን በግብር እንዲያገኝ ምክንያት መሆኑን ያነሳሉ።
ዓለማችን ባላሰበችው ወቅትና መጠን የተከሰተው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ቀውስም የከተማ ኢኮኖሚ ልማቶች በተለይ የአገልግሎት ዘርፎች ለበርካታ ዓመታት መፍጠር የቻሉትን ትሩፋት በአንድ ጊዜ በመንጠቅ በተለይም ሥራ አጦችን ማበራከቱና የአገራት መንግሥታቶችም ከገቢ ግብር የሚያገኙትን አቅም በመቀነስ ከባድ ኪሳራ መፍጠሩን አመላክተዋል።
የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ኢሲኤ መረጃ እንደሚያመላክተው፣ የአፍሪካ ከተሞች ከስድስት መቶ ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች መዋያና ማደሪያ ከመሆን ባሻገር 50 በመቶ ለጠቅላላ የአገር ውስጥ ዋስትና የመስጠት አቅም አላቸው።
ይህ የከተሞች አበርክቶ በአንዳንድ የአፍሪካ አገራት ከዚህም የበለጠ ድርሻ እንዳለው ይታያል።አንዳንድ መረጃዎችም ለአብነት ቦትስዋና፣ ዩጋንዳ እና ቱኒዚያ እንዲሁም ኬንያን በመሳሰሉ አገራት የከተሞች የኢኮኖሚ አቅም ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት እስከ 70 በመቶ ድርሻ እንዳላቸው ያሳያሉ።
መሰል ጥናቶችን ዋቢ የሚያደርጉ ምሁራን የኮቪድ 19 ቀውስ በከተማ ኢኮኖሚ ላይ ካሳደረው ጉዳት አንፃር በተለይ የሥራ ዋስትና ማሳጣቱን ቀዳሚ አድርገውታልበአፍሪካ አህጉር አብዛኛው የሥራ ዕድል የሚፈጠረው ብሎም ሥራ የሚገኘው ከተማ ላይ መሰረታቸውን ባደረጉ የማኑፋክቸሪ ንግድና የአገልግሎት ዘርፎች ላይ መሆኑም ጉዳቱ ከሁሉ በላይ ሚሊየኖችን ሥራ ያሳጣል እንዲሉ ምክንያት እንደሆናቸው አስረድተዋል።
መረጃዎች እንደሚያመላክቱት በአፍሪካ ምድር ከ250 ሚሊዮን ዜጎች መደበኛ ባልሆኑ የከተማ ሥራ ዕድሎች ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ። በርካታ ዜጎችም በዕለት ተዕለትና ተባባሪ ሥራዎች ላይ ህልውናቸውን የመሰረቱ ናቸው።ኮቪድ 19 በርካታ ዘርፎችን ከሥራ ውጪ ማድረጉ ታዲያ በተለይ በከተማ ማዕከላት የሚገኙ በሚሊየን የሚቆጠሩ ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ኑሮ ውስጥ የሚያድሩ ብሎም አነስተኛ ቢዝነስ አንቀሳቃሾችና የሠራተኞቻቸውን ዕጣ ፈንታም አጣብቂኝ ውስጥ ጥሎታል።ወረርሽኙ እያስከተለ ያለው ሁለንተናዊ ጉዳት ጅማሮው እንጂ መቋጫው አለመሆኑ ደግሞ በርካቶች መጪውን እንዲሰጉ ምክንያታ ሆኗል።
መሰል ድንገተኛ አደጋዎች ይከሰታሉ በሚል አስቀድሞ አለማሰብና ቅድመ ዝግጅት አለማድረግን የመሳሰሉ ድክመቶች ከወዲሁ ለተመዘገቡ ኪሳራዎች ዋነኛ መነሾ መሆናቸው የተጠቆመ ሲሆን፣ በተለይ በአፍሪካ ምድር የአገልግሎት አቅራቢና የንግድ ተቋማት መሰል ድንገተኛ ክስተቶች ቢፈጠሩ አደጋዎችን ለመቋቋም የሚያስችል የጊዜ መግዣ አማራጮች የሌላቸው መሆኑ እጃቸውን አጣጥፈው ካለ ሥራና ገቢ እንዲቀመጡ ዋነኛ ምክንያት ሆኗል ተብሏል።መሰል የአማራጭ እጦት ውስንነቶችም በኮቪድ 19 የሚከሰቱ ቀውሶችና ጉዳቶችን ይበልጥ እንደሚያባብሱም ተጠቁሟል።
አንዳንድ መገናኛ ብዙሃንና ምሁራን በሌላ በኩል ኮቪድ 19 የአፍሪካ የከተማ ኢኮኖሚ ግንባታ ውስንነቶች ከማጋለጥ ባሻገር ቀጣይ የከተማ ልማት እቅዶች ምን መምሰል እንዳለባቸው የሚጠቁም ቀይ መብራት ማሳየቱን አስረድተዋል።
ከእነዚህ ፀሐፍትና ምሁራን አንዱ የሆኑት የከተማ ልማት ኤክስፐርቱ ሮጀር ቫን ደን በርግ ዘ ሲቲ ፊክስ ላይ ባሰፈረው ሰፊ ሀተታም፣ ኮቪድ 19 የከተማ ልማት እቅዶችን እንዴት ሊያመሰቃቅል እንደሚችል አስረድተዋል።እ.ኤ.አ በ19ኛ ክፍለ ዘመን የተከሰተው የኮሌራ ወረርሽኝ ዘመናዊ የከተማ ሳኒቴሽን እንዲተዋወቅ ዋነኛ ምክንያት መሆንኑ ያስታውሱት ባለሙያው፣ ኮቪድ 19 ከተሞችን እንዴት መገንባትና ማደራጀት እንዲሁም ቀጣይ ለሚከሰቱ ወረርሽኞች እንዴት የመቋቋም አቅም መፍጠርና ግብረ መልስ መስጠት አለባቸው የሚለውን ያመላከተ ስለመሆኑ አፅንኦት ሰጥተውታል።
በቀጣይ የሚገነቡ ከተሞች እንዴት ከከባቢ ጋር ይበልጥ መግባባት እንዳለባቸው ማጤን፣ እንዲሁም የሰዎች የአሰፋፈር ምጥጥን ተገቢ ማድረግ እንዳለባቸውም አመላክተዋል።‹‹በ20 ዘመን አውሮፓውያኑ የመኖሪያ ቤት ህገ ደንቦችን ተግባራዊ ማድረግ የጀመሩት መሰል ወረርሽኝ ለመቋቋም ነው›› ብለዋል።
‹‹ኮቪድ 19 በተለይም አፍሪካ፣ ህንድ ደቡብና ምሥራቅ እሲያ፣ የቀጣይ ትውልድ ከተማ ሲገነቡ ማድረግ ስለሚገባቸው አበይት ተግባራት አቅጣጫን ያመላከተ ነው›› ያሉት ፀሐፊው፣ እ.ኤ.አ በ2050 ሁለት ነጥብ አምስት ቢሊየን ህዝብ የዓለምን ከተሞች እንደሚቀላቀሉም ጠቁመዋል።
ከእነዚህ መካከል ደግሞ 90 በመቶ የሚሆኑት የአፍሪካና የእሲያ ዜጎች እንደመሆናቸውም በቀጣይ የአፍሪካ የከተማ ኢኮኖሚ በከፍተኛ መልኩ መጨናነቃቸው አይቀሬ ስለሆነ ዝግጅቶች ከወዲሁ መጀመር እንደሚገባቸው አፅንኦት ሰጥተውታል።
‹‹በኮቪድ 19 ወቅት በተለያዩ ዓለም አገራት ለህዝብ ክፍት ሆነው የተመለከትናቸው ወሳኝ የከተማ ቦታዎች መካከል ግንባር ቀደም ሆነው የሚጠቀሱት የከተማ ፓርኮች ናቸው›› የሚሉት ባለሙያው፣ ይህን በመረዳት ቀጣይ የሚገነቡ የከተማ ልማት እቅዶች፣ ክፍት ቦታዎችን፣ የውሃ ማፋሰሻ፣ የደን እንዲሁም ፓርኮች እንዲኖራቸው በአጠቃላይ አረንጋዴ ኢኮኖሚን ስለመፍጠር ታሳቢ ማድረግ እንደሚገባም አስምረውበታል።
የከተማ መናፈሻና ክፍት ስፍራዎች የመዝናኛ አማራጭ ብቻ ሳይሆኑ ጎብኚዎችን እየሳቡ በመሄድ ከተማነትን እንደሚያሳልጡና እንደሚያደምቁ፣ ከሕፃን እስከ አዛውንት ለሁሉም ክፍት እንደመሆናቸውም በአጠቃላይ ጤናማና ደስተኛ ህዝብ ለመፍጠርና በኢኮኖሚ ረገድም በአግባቡ ከተሠራባቸው የገቢ ምንጭ ሊሆን እንደሚችልና፣ በሥራ ፈጠራው ወቅታዊውን ራስ ምታት የማቃለል አቅማቸው ግዙፍ ስለመሆኑ ተመላክቷል።
ከዚህ ባሻገር የከተማና የገጠር ልማት እቅዶችን እርስ በእርስ ማስተሳሰር እንደሚገባም አፅንኦት ተሰጥቶታል።‹‹በከተሞች የሚሆነው ሁሉ ከተሞች ላይ ብቻ ተወስኖና ተዳፍኖ ይቀራል ማለት ሞኝነት ነው›› የሚሉት ፀሐፋቱ፣ በከተማ ኢኮኖሚ ላይ የሚከሰተው ማናቸው የምርትና አቅርቦት የሰንሰለት መቆራረጥና የትስስሩ መንገጫገጭ የኢኮኖሚ ስሜት የገጠሩ መንደር እንደሚዘልቅም ያነሳሉ።እናም የከተማና የገጠር እቅዶችን በተለይም የኢኮኖሚ፣ የኃይል አቅርቦት፣ የትራንስፖርተር ኔትወርክ፣ የምግብ ምርት አቅርቦት ማስተሳሰር ይገባል ብለዋል።
አንዳንዶች ደግሞ ኮቪድ የከተማ ማህበራዊ ኢኮኖሚው ግንባታ ቀሪ የቤት ሥራዎችና ቀጣይ ተግባራት ምን መምሰል እንዳለባቸው ማስረዳትን ምርጫቸው አድርገዋል።ጁሊያን ሪቢን ኪንግ እና ራዳህ ቻንቺኒ Tackling Inequality in Cities Is Essential for Fighting COVID-19 በሚል ርዕስ ባሰፈሩት ሰፊ ሀተታ፣ የከተማ ኢኮኖሚ ማህበራዊ ልማት ላይ በግልጽ የሚስተዋሉ ጉራማይሌ ገፅታ የኑሮ ልዩነት ፈር ማሳይዝም ለወቅቱ ወረርሽኝ ለመፋለምና ተመጣጣኝ ግብረ መልስ ለመስጠት ወሳኝ መሆኑን አፅንኦት ሰጥተውታል።
በዚህ ረገድም ከፍተኛ መጠን ያላቸው ኢንቨስትመንቶችን በመተግበር በተለይም በከተሞች ውስጥ ለሚኖሩ ከሌሎች በእጅጉ ወደ ኋላ ለቀሩ ደሃ ነዋሪዎች መሰረተ ልማቶችን ማዳረስ፤ ከሁሉ አስቀድሞም የውሃ ታንከሮች፣ ተንቀሳቃሽ እጅ መታጠቢያዎችን ሌሎችንም በየአቅራቢያቸው ማድረግ ይገባል ብለዋል።ከዚህ ባሻገር መንግሥታት አቅም በፈቀደ መልኩ ለእነዚህ ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎች የገንዘብ ድጎማ ማድረግ እንደሚገባቸውም አመላክተዋል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 9/2012
ታምራት ተስፋዬ