ልጆች የእግዚአብሔር ውድ ስጦታዎች ናቸው፡፡ እናትነት ደግሞ በምንምና በማንም ሊተካ የማይችል፤ ለሴት ልጅ ብቻ የተሰጠ ትልቅ የተፈጥሮ ጸጋ ነው፡፡ ታዲያ ይህ ጸጋ በብዙ ጣርና ምጥ፤ በተለያዩ ድካምና ፈተናዎች ሰቆቃ የታጀበ ነው፡፡
እናት ልጇን በሆዷ ዘጠኝ ወር ተሸክማ ትወልዳለች፤ አጥብታና ተንከባክባ አይኗን ላፍታ ሳታነሳ ታሳድጋለች፡፡ ልፋቷና ድካሟ ፍሬ አፍርቶ ልጇ አድጎ ለቁምነገር ሲደርስ ደግሞ የሚሰጣት ደስታ አጥንት ዘልቆ ነብስን በሀሴት እስከ ማረስረስ ይደርሳል፡፡
እነሆ! ላወጋችሁ የወደድኩት ከነዚህ የተፈጥሮ ጸጋዎቻችን ጀርባ ስላደባው የካንሰር በሽታ፤ በልጆቻቸው ህመም ክፉኛ ተሰቃይተው በሀዘን ስለተኮራመቱ እናቶችና ክፉና ደጉን ለይተው ስለማያውቁ እምቦቃቅላ ሕጻናት ነው፡፡ እነዚህ ሕጻናት ከፈጣሪያቸው በታች ጭላንጭል ተስፋቸውን በማቴዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ ጥለው የነገውን መዳን በተስፋ ይጠባበቃሉ፡፡
ልጃቸውን በዚሁ ክፉ ደዌ የተነጠቁት አቶ ወንዱ በቀለ ‹‹ትውልድ ይዳን በኛ ይብቃ›› በማለት በሟች ልጃቸው ማቴዎስ ወንዱ ስም የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲን አቋቋሙ፡፡ ታዲያ እኚህ ቅንና መልካም አሳቢ ከዛሬ 14 ዓመት በፊት በመኖሪያ ቤታቸው ያቋቁሙት ይህ ማህበር ዛሬ ለብዙዎች እረፍት፣ ተስፋ፣ ፍቅርና እንክብካቤ እየሰጠ ይገኛል፡፡
ወይዘሮ ኤልሳቤት ወርቁ የሁለት ሴት ልጆች እናት ነች፡፡ ከጎጃም ቡሬ ቤት ንብረቷን ትታ ከመጣች ዘጠኝ ወራት አልፏታል፡፡ የስምንት ዓመቷና የመጀመሪያ ልጇ ሰላማዊት ጌትነት የደም ካንሰር ታማሚ ሆናለች፡፡ የልጇን ጤንነት ለመከታተል በአዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ስትደርስ ዘመዴ የምትለው አንድም ሰው አልነበራትምና ማቴዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲን ተቀላቀለች፡፡ በዚህ ውስጥም ማረፊያ፣ ምግብና የህክምና ቁሳቁስ እያገኘች፤ ማህበሩ ባዘጋጀው ተሽከርካሪ በየጊዜው ወደ ሆስፒታል እየተመላለሰች የልጇን ህክምና ትከታተላለች፡፡
ሕጻን ሰላማዊት በኮልታፋና ጣፋጭ አንደበቷ ‹‹ስጫወት ይደክመኛል፤ ይነስረኛል›› በማለት እንደዕድሜ እኩዮቿ መሮጥ፣ መዝለልና መቦረቅ እንዳትችል ስላደረጋት በሽታ ትናገራለች፡፡ ምንሽን አመመሽ ብዬ ላቀረብኩላት ጥያቄ ‹‹የደም ካንሰር›› በማለት መለሰችልኝ፡፡ አብዛኞቻችን እኔን ጨምሮ ስለሕጻናት ካንሰር ምን ግንዛቤ ኖሮን ይሆን?… እነዚህን ታማሚ ሕጻናት ስለሚረዳው ማቴዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ ተቋምስ ምን ያህል እናውቃለን? መልሱን ለናንተ ልተወውና ወደ ሰላማዊት እናት ኤልሳቤት ልመልሳችሁ፤
በጣም የሚገርመው ኤልሳቤት በአሁን ወቅት ከልጃችን ጤንነት የሚበልጥ የለም በማለቷና ቤቷን ትታ ህክምናውን በማስቀደሟ ከባለቤቷ ተጣልታለች፡፡ ባለቤቷ ሁሌም ሕጻኗን ይዘሻት ነይና ወደቤትሽ ተመለሽ ይላታል፡፡ እሱ ሕመሙ የሚድን በሽታ አይደለም ባይ ነው፡፡ ቢድንም ሰባትና ስምንት ዓመት ሙሉ ቤት ንብረት ተትቶ እንዴት? ይላል፡፡ በየጊዜውም በክርክር ይሞግታታል፡፡
ኤልሳቤት እንደምትለው ባለቤቷ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ድረስ እየመጣ ይረብሻታል፡፡ በዚህ ድርጊቱም በጣም ስለመከፋቷ ሲቃ እየተናነቃት አወጋችኝ፡፡ ቤት ንብረቷን፤ ቀዬ መንደሯን ትታ ወጥታ የልጇን መዳን ለምትጠብቅና በጭላንጭል ተስፋ ለተቆራመደች እናት የትዳር አጋር ያውም የልጅ አባት ስሜት እንዲህ ሲሆን ስለምን አያሳዝን? እንዴትስ ሆድ አያስብስ?…
ወይዘሮ ወርቄ መንበሩ ከምስራቅ ጎጃም ብቸና ነው የመጣችው፤ የአምስት ዓመት ልጇ ራሔል በደም ካንሰር ታማባታለች፡፡ ሰውነቷ በእጅጉ ከስቷል፡፡ ቁመናዋ እንደ ዕድሜ እኩዮቿ አይደለም፡፡ ከዘጠኝ ወራት በፊት ህክምናውን በመጀመሯ ለውጥ አግኝታለች፡፡
እናቷ ወይዘሮ ወርቄ ከዕለት ዕለት የልጇን ጤንነት በተስፋ ትጠባበቃለች፡፡ ወርቄ እንደሌሎቹ ወላጆች ሁሉ ቤት ንብረቷንና ሕጻን ወንድ ልጇን ትታ ከመጣች ወራት ተቆጥረዋል፡፡ ማህበሩ በየወሩ የትራንስፖርት ወጪዋን መሸፈኑ እየተመላለሰች እንድታሳክም አግዟታል፡፡
ሌላው ባለታሪክ የ13 ዓመቱ ታዳጊ ኡስማን ሰይድ ነው፡፡ ኡስማን ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ ለስድስት ተከታታይ ዓመታት በማዕከሉ የደም ካንሰር ህመሙን ህክምና ሲከታተል ቆይቷል፡፡ ህመሙ ሲጀምረው የተለየ ድካምና በሰውነቱ ላይ እብጠት መታየቱን ያስታወሱት አባቱ አቶ ሰይድ ለብቸኛውና የመጀመሪያ ልጃቸው ህክምናን በመሻት ከሀገራቸው ወሎ አዲስ አበባ መጥተዋል፡፡
ኡስማን ለተከታታይ ዘጠኝ ወራት ህክምናውን አላቋረጠም፡፡ አባቱም ቢሆን ወደሀገራቸው አልተመለሱም፡፡ ቆይታውን አጠናቅቆ ከሄደ በኋላም ለስድስት ዓመታት እያመላለሱ ሲያስታምሙት ቆይተዋል፡፡ ኡስማን አሁን በሙሉ ጤንነት ላይ ይገኛል፡፡ የእርሱ ጤና መሆን ለሌሎች ጭምር ተስፋ ሆኗል፡፡
የማቴዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ማህበር ከሕጻናት ባሻገር የማህጸን ጫፍና የጡት ካንሰር ታማሚ ለሁኑ አዋቂ ሴቶችም ድጋፍ ያደርጋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ጥቂት የማይባሉ እናቶች በማህበሩ ድጋፍ ህክምናቸውን እየተከታተሉ ይገኛሉ፡፡ ከነዚህም መካከል ከደቡብ ክልል ይርጋለም ከተማ የመጣችው ወይዘሮገነት ደንገሶ አንዷ ናት፡፡
የማህጸን ካንሰር ታማሚ መሆኗን ካወቀች ወዲህ ስምንት ልጆቿንና ቤት ንብረቷን ትታ ወደ ማዕከሉ መጥታለች፡፡ ሁለት ወራት በህክምና የቆየችው ወይዘሮ የጨረር ህክምና ለማድረግ ቀጠሮ ወስዳ ለመመለስ መዘጋጀቷን ትናገራለች፡፡ ገነት ወደቤቷ መመለሷና ከልጆቿ ጋር መቀላቀሏ ቢያስደስታትም፤ ከህመሟ ለመላቀቅ ባላት ጉጉት በሽታ ይዤ ልመለስ ነው በሚል ስጋት ገብቷታል፡፡
ማቴዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ማህበር በዋናነት በሕጻናት ካንሰር፤ በሴቶች የማሕጸን ጫፍና በጡት ካንሰር ላይ የሚሰራ ማህበር ነው፡፡ ማህበሩ በአሁኑ ሰዓት በፕሮጀክት ለተያዙ 86 የደም ካንሰር ታማሚ ሕጻናት እና 91 የማሕጸን ጫፍና የጡት ካንሰር ታማሚ ሴቶች አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ ለሕጻናቱ ማቆያ 18 አልጋዎች ሲኖሩት፤ በቋሚነት ከደቡብና ከኦሮሚያ ክልሎች ለሚመጡ የማህጸን ጫፍና የጡት ካንሰር ታማሚ እናቶች ደግሞ ስድስት አልጋዎች አዘጋጅቶ ድጋፍና ክትትል እያደረገ ነው፡፡ ማህበሩ ከክልል ለመጡና አቅም ለሌላቸው የምግብ፤ የትራንስፖርት፤ የመድሀኒት አቅርቦትና የላቦራቶሪ ወጪ በመሸፈን ድጋፍ ያደርጋል፡፡ በተለይም ለላቦራቶሪ ወጪ በዓመት እስከ አንድ መቶ ሺህ ብር ድረስ እናወጣለን የሚሉት አቶ ወንዱ በቀለ የማህበሩ መስራችና የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ ናቸው፡፡
ማህበሩ የሚንቀሳቀሰው በጥቂት የውጭ አገራት ዕርዳታ ብቻ እንደመሆኑ መንግስት ትኩረት ሊሰጠው ይገባልም ይላሉ፡፡ ማህበሩ ከሚሰጠው ዘርፈ ብዙ አገልግሎት አኳያ በቂ የሚባል በጀት የለውም፡፡ ከችግሩ አሳሳቢነት አንጻር መንግስትም ሆነ የሚመለከታቸው አካላት ተገቢውን ድጋፍ ቢያደርጉለት የተሻለ ተደራሽ እንደሚሆን ይታመናል፡፡
አዲስ ዘመን ጋዜጣም ባደረገው ምልከታ ማህበሩ እየሰጠ ያለው አገልግሎት እጅግ በጣም ጥሩና ሊበረታታ የሚገባው መሆኑን ተገንዝቧል፡፡ ይሁን እንጂ፤ በእጅ የያዙት ወርቅ እንዲሉ… በውጭ ሀገራት ደረጃ ለሦስት ጊዜያት ተሸላሚ የሆነው ይህ ተቋም በአገሩ መንግስት አይን ግን አልታየም፡፡ እውቅናም አላገኘም፤ ማህበረሰቡም ስለማህበሩ ግንዛቤ የለውምና ሚዲያው ትኩረት ቢሰጠው፤ መንግስትም ለዚህ በጎ ተግባር ድጋፍና ክትትል ቢያደርግ መልካም ነው እንላለን፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 15/2011