* በጉባኤው አንድ ሺ አባላት ይሳተፋሉ
አዲስ አበባ፡- የኢህአዴግ የወጣቶች ሊግ በአገሪቱ እየተካሄደ ባለው ሁለንተናዊ ለውጥ የለውጡ አካል በመሆንም እየሰራ መሆኑን ገለጸ፡፡ በአራተኛው ጉባኤው አንድ ሺ ጉባኤተኞች እንደሚሳተፉም አመለከተ፡፡
የሊጉ ሥራ አስፈጻሚ አባልና የአራተኛው ጉባኤ ቃል አቀባይ ወጣት ጫላ ኦሊቃ ለአዲስ ዘመን እንደገለጸው፣ ሊጉ ለውጡን በጥሩ ጎኑ ይመለከተዋል፡፡ የለውጡ አካል በመሆንም እየሰራ ይገኛል፡፡
በአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ሊጉ ሲሰራ መቆየቱን ያስታወሰው ወጣት ጫላ፣ ለውጡን የመደገፍና አብሮ የመስራቱ ሁኔታ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል፤ ጉባኤውም ይህንኑ እንደሚወስን ያለውን እምነት ገልጿል፡፡
የኢህአዴግ የወጣቶች ሊግ ከአራት ድርጅቶች የተመሰረተ በመሆኑ በመካከላቸው ተግባብቶ ከመስራት አኳያ ያለውን ሁኔታ እንዲያስረዳ የተጠየቀው ወጣት ጫላ፤ በግለሰብ ደረጃ የሃሳብ ልዩነት ሊኖር ይችላል፤ ነገር ግን ልዩነታችንን አቻችለን የጋራ በሚያደርጉን ጉዳዮች ላይ አብረን እየሰራን ነው ሲል መልሷል፡፡ እንደ ተቋም በመካከላችን ምንም ልዩነት የለም፡፡ተግባብተን፣ በፍቅር ለአንድ አላማ እየሰራን ነው ሲልም ተናግሯል፡፡
እንደ ወጣት ጫላ ገለጻ የአራተኛው የሊጉ ጉባኤ ተሳታፊዎች አንድ ሺ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 500ዎቹ በድምፅ፤ ቀሪዎቹ 500 ደግሞ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ታዛቢዎችና ያለ ድምጽ የሚሳተፉ መሆናቸውን አስታውቋል፡፡
የሊጉ አባል ድርጅቶች ለጉባኤው ያላቸውን ዝግጅት በተመለከተ በጥሩ ሁኔታ ላይ መሆናቸውን የገለጸው ወጣት ጫላ፤ ሁሉም የሊጉ አባል ድርጅቶች በጉባኤው ለመሳተፍ በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙ አስረድቷል፡፡
በየሁለት አመት ተኩል የሚካሄደው ይህ ጉባኤ ከታህሳስ 19/2011 ዓ.ም ጀምሮ ለሶስት ተከታታይ ቀናት በሀዋሳ ከተማ የሚካሄድ መሆኑን ከቃል አቀባዩ ማብራሪያ ለማወቅ ተችሏል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 15/2011
ግርማ መንግሥቴ