አዲስ አበባ፡- በመንግስት ብቻ ተይዘው የነበሩ ትላልቅ ተቋማትን በሙሉ ወይም በከፊል አክሲዮን/ሽርክና የመሸጡን ተግባር ከኢትዮ-ቴሌኮም እንደሚጀምር ተገለጸ፡፡
በገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሀጂ ኢብሳ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፣ በመንግስት ብቻ ተይዘው የነበሩ ትላልቅ ተቋማትን በአክሲዮን/ሽርክና ለመሸጥ መንግስት ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት ኢትዮ ቴሌኮምን በሽርክና በመሸጥ ይጀምራል፡፡
የኢትዮ ቴሎኮምም ሆነ የሌሎች ተቋማት በሙሉ ወይም በከፊል የመሸጥ ስራ አፈጻፀሙን ለማቀላጠፍ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን የገለጹት አቶ ሀጂ፣ ጉዳዩን በባለቤትነት የያዘው መስሪያ ቤታቸው ሁኔታዎችን ከማመቻቸት አኳያ አስፈላጊ የሆኑ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል፡፡
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ካከናወናቸው ዋና ዋና ተግባራት አንዱ የመዋቅር ጥናት መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ ጽህፈት ቤት ለማቋቋም፣ የሰው ሃይል ደረጃ፣ ቅጥር፣ ብዛት፣ የሙያ አይነት፣ ስብጥርና የመሳሰሉትን መለየት የሚያስችለው ስራ ተጠናቅቋል ብለዋል፡፡
ቀጥታ ወደ አክሲዮን/ሽርክና ሽያጭ ከመገባቱ በፊት በርካታ ዓለም አቀፍ ልምዶች ይዳሰሳሉ ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ትላልቅ ተቋማትን በሽርክና መሸጥ ሲያስፈልግ ሂደቱም ሆነ የጨረታው አወጣጥ እንዴት መሆን እንዳለበት ልምድ ካላቸው አገራት ተወስደው ከኛ አገር ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር በማየትና በማጣጣም ወደተግባር ይገባል ሲሉም አስረድተዋል፡፡
የኢትዮ ቴሌኮም የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ት ጨረር አክሊሉ እንደገለጹት፤ እንደ አንድ ግዙፍና ትልቅ ተቋም ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመገኘት መስሪያ ቤታቸው ጠንክሮ እየሰራ ነው፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 15/2011
ግርማ መንግሥቴ