የኦሮሞ አባ ገዳ እና ሀደ ሲንቄ በኦሮሞ ህዝብ ውስጥ ከፍተኛ ክብርና ቦታ የሚሰጣቸው ናቸው፡፡ የገዳ ሥርዓት የዴሞክራሲ መሰረት፣ የሰላምና አንድነት መድረክ ሆኖም ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ የገዳ አባቶችም ይሄንኑ በተግባር ሲገልጹ ኖረዋል፡፡ ሀደ ሲንቄዎችም የሰላምና እርቅ እናቶች ሆነው ለዚሁ ተግባር ሲተጉ፤ የተጣላን ሲያስታርቁና ለህዝቦች ሰላም ቀን ከሌት ሲተጉ ኖረዋል፡፡ ታዲያ ዛሬ እነዚህን ሥርዓቶች ያፈራው ህዝብ አንድነቱ አደጋ ላይ ሲወድቅና ህብረቱ ሲላላ፤ ከመረዳዳት ይልቅ ሲገፋፋ፤ ከመመካከር ይልቅ ሲወቃቀስ፤ ከመተሳሰብ ይልቅ በፓርቲዎች ጎራ ተሰልፎ ጦር ሲማዘዝ ማየት ከህመምም በላይ የሚያሳፍርና አንገት የሚያስደፋ ተግባር ነው፡፡
ይሄን የተገነዘቡ አባ ገዳዎችና ሀደ ሲንቄዎች ለሳምንት ያክል ሲመክሩና የእርቅ መፍትሄ ሲያፈላልጉ ቆይተው፤ ትናንት ረፋዱ ላይ በኦሮሞ ባህል ማዕከል አለንጋና ሲንቄያቸውን ይዘው በኦሮሞ ህዝብ ስም ተደራጅተው ለሚሰሩ፤ ነገር ግን እንደ ኦሮሞ ህዝብ ፍላጎት መጓዝ ሳይችሉ በመካከላቸው ሰላም ጠፍቶ የህዝቡን ሰላም እንዲጠፋ ባደረጉ ሁለት ፓርቲዎች ፊት ቆሙ፡፡ “እውነት የአባ ገዳ ልጆች ከሆናችሁና ከዚሁ እንደወጣችሁ ካመናችሁ፤ እውነትም በቄሮና ቀሪቲ ትግል ለዚህ ደረጃ ከበቃችሁ፤ እውነትም ከልጅነታችሁ ጀምሮ እስካሁን ለኦሮሞ ነጻነት ታግያለሁ ካላችሁ፤ ህዝቡም ለነጻነቱ ሞቷል፣ አካሉም ጎድሏል፣ ብዙ መከራም ተቀብሏል ብላችሁ ካመናችሁ፤ ስለራሳችሁ ሳይሆን ስለ ህዝቡ ሰላም ብላችሁ ሰላምን አውርዱ፤” ሲሉም ተማጸኑ፡፡
በኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) እና በኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) መካከል የተፈጠረው አላስፈላጊ ግጭት ዛሬ ላይ የኦሮሞ ህዝብ በተለይም የምዕራቡ ኦሮሚያ በሰላም ወጥቶ መግባት እንዳይችል ያደረገው መሆኑን የተናገሩት አባ ገዳ በየነ ሰንበቶ፤ አንድ ሰው ሲፈጠር አንድም ለአገር፣ አንድም ለአፈር እንደመሆኑ ለአፈር እስኪበቃ ለአገር የሚሆን ነገር መስራት እንደሚጠበቅበት ጠቁመዋል፡፡ ሰው ለአገር የሚሆነው ደግሞ አገርና ህዝብ ከእርሱ ምን እንደምትጠብቅ አውቆ ሲሰራ እንጂ ከህዝብ ይልቅ ለራሱ በመቆሙ እንዳልሆነም ገልጸዋል፡፡
የገዳ አስተምህሮም አብሮነትን፣ ይቅር ባይነትን፣ ሰላምና መረዳዳትን እንጂ የበደሉትን በመበደል፣ የደምንም በደም መመለስ አለመሆን በማውሳትም፤ በሁለቱ ፓርቲዎች መካከል ያለው ሽኩቻ በአንድ ህዝብ መካከል የሚደረግ ግጭት እንደመሆኑ ቀዬን ሰላም ያሳጣ፣ ቤትንም ያፈረሰ፣ ህጻናትንም እየቀጠፈ፣ አርሶ አደሩንም ከማሳው እያስቀረ ያለ እንደመሆኑ ለህዝቡ መኖር ሲሉ ለሰላም መቆም እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
የመድረኩ ተሳታፊ የነበሩ አባ ገዳዎች፣ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ ምሑራንና ሌሎችም ባለድርሻዎች ከአባ ገዳና ሀደ ሲንቄዎች ጋር ቆመው ይሄንኑ የሰላም ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡ በወቅቱም መንግስት በሆደ ሰፊነት ችግሮችን ተመልክቶ እንዲፈታ፤ ኦነግም የሰላም ጥሪውን ተቀብሎ ሰራዊቱ ትጥቅ ፈትቶ ከህዝቡ እንዲቀላቀል መልዕክት እንዲያስተላልፍ አሳሰቡ፡፡
አክቲቪስት ጀዋር መሀመድ ከእነዚህ መካከል አንዱ ሲሆን፤ በወቅቱ እንደተናገረው፤ ህዝቡን የሚሰማ ጠፍቶ ችግሩ ለዚህ ደርሷል፡፡ አሁንም ኦዴፓ ቀን ቀን፣ ኦነግ ደግሞ ማታ ማታ ህዝቡን እያሸበሩ በውጭ ግን ሰላማዊነትን እያስመሰሉ መጓዙ በሁለቱም በኩል ሊቋጭ ይገባዋል፡፡ ኦነግ በሐረርጌ ካፕም ከፍቶ ወታደር ሲያሰልጥን፤ መንግስትም ወታደሩን ወለጋ ሲያስገባ የችግሩን ገፈት የሚጎነጨው ህዝቡ ነው፡፡ እናም ሁለቱም ከዚህ ተግባራቸው ታቅበው ህዝቡ የሚደርስበት ሰቆቃ እንዲያበቃ መስራት አለባቸው፡፡
በዚህ መልኩ የቀረበውን ጥሪ ተከትሎ ሁለቱም አካላት በተወካዮቻቸው አማካኝነት ምላሽ የሰጡ ሲሆን፤ የኦዴፓን አቋም ያቀረቡት የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ዶክተር ዓለሙ ስሜ እንዳሉት፤ በአገሪቱ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ በዚህች አገር ጉዳይ ሁሉም በጋራ እንዲሰራ በርካታ እስረኞች ተፈትተዋል፤ በውጭ በተለያየ መልኩ ሲታገሉ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችም በሰላማዊ መልኩ ለመታገል ገብተዋል፡፡ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ሲገቡም ትጥቅ ሊፈቱና ወታደሮቻቸውም በመንግስት የጸጥታ ሃይል ውስጥ ገብተው የሚሰሩበት ሁኔታ እንደሚመቻች ከስምምነት ተደርሷል፡፡ ይሁን እንጂ በአቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራው ኦነግ ይሄን በመተላለፍ በክልሉ በተለይ በምዕራብ ኦሮሚያ ወዳልተገባ ተግባር አምርቷል፡፡
በዚህ መሰረትም ባንኮች ተዘርፈዋል፤ ንብረት ወድሟል፤ የሰው ህይወትም ጠፍቷል፡፡ በጥቅሉ የአካባቢው ህዝብ ወጥቶ መግባት በማይችልበት ደረጃ ላይ ቆይቷል፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን መንግስት የሰላም አማራጮች ላይ ያተኮረ ቢሆንም፤ ሂደቱ ህዝቡ ላይ የጎላ ችግር በማሳደሩ የህዝቡ አቤቱታና የሕግ ይከበርልን ጥያቄ በረትቷል፡፡ እናም መንግስት ሕግ ሲጣስ ሕግ የማስከበር ሃላፊነቱን ተወጥቷል፡፡ ይህ ማለት ግን ጦርነት ከፈተ ማለት አይደለም፡፡ አሁንም ቢሆን ኦነግ ሰላማዊ አማራጩን ከተከተለና ሰራዊቱንም ትጥቅ የሚያስፈታ ከሆነ መንግስት የሚፈልገው ይሄንኑ በመሆኑ ሰራዊቱን ተቀብሎ እንደቀድሞው ያስተናግዳል፤ ከፓርቲው ጋርም በአገር ጉዳይ አብሮ በመስራት ለሰላሙ መረጋገጥ እንደእስካሁኑ በትኩረት ይሰራል፡፡
የኦነግ ሊቀመንበር አቶ ዳዉድ ኢብሳ በበኩላቸው እንዳሉት፤ ኦነግ ወደዚህ ተግባር የገባው በመንግስት በኩል የተገባለት ቃል ተፈጻሚ ባለመሆኑ ነው፡፡ አሁንም ቢሆን አባላቱ እየታሰሩ እንደመሆኑ የደህንነት ስጋት አላቸው፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ መልኩ የሚቀርበው የሰላም ጥሪ እጅጉን አስፈላጊ እንደመሆኑ ጥሪውን በመቀበል ሰራዊቱ ከእርሱ ስር ወጥተው በኦሮሞ ህዝብና በአባ ገዳዎች ስር እንዲሆኑ ወስኗል፡፡ ሆኖም መንግስት ለደህንነታቸው ዋስትና ሊሰጣቸው የሚገባ ሲሆን፤ እነርሱ ግን በሰላም ለመስራት ተዘጋጅተዋል፡፡
በዚህ መልኩ የተነገረውን አቋም ተከትሎ አባ ገዳዎች የኦነግ ሰራዊት በምን መልኩ ወደ ሰላም መግባት አለበት፣ በመንግስት የጸጥታ መዋቅር ውስጥ እንዴት መስራት ይችላል በሚሉ ጉዳዮች ላይ ለመስራት የሚያስችላቸውን 71 አባላት ያለው ኮሚቴ አቋቁመዋል፡፡ ይህ ኮሚቴም 27 አባ ገዳዎችንና 27 ሀደ ሲንቄዎችን፣ 11 ምሑራንን፣ እንዲሁም ከኦነግ 3፣ ከኦዴፓ 3 አባላትን ያቀፈ ሲሆን፤ ኮሚቴው ከዛሬ ጀምሮ ወደስራ እንደሚገባ አባ ገዳ በየነ ገልጸዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 15/2011
በወንድወሰን ሽመልስ