ኢትዮጵያ ከዓመታት በፊት ጥቅጥቅ ባሉ የተፈጥሮ ደኖች የተሸፈነች፣ በተፈጥሮ የታደለቻቸው የበርካታ ታሪካዊ ቅርሶች ባለቤት፣ የተለያየ ብዝሀ ህይወት መናኸሪያ፣ የውብ መልክዓምድር፣ የተለያዩ ስርዓተ ምህዳሮችና የምቹ አየር ንብረት ባለቤት በአጠቃላይ ምድራዊ ገነት የምትባል እንደነበረች የታሪክ ድርሳናት ያወጋሉ። ያ ሁሉ አለፈና ደኖቿ እየተመናመኑ፣ መሬቶቿ እየተራቆቱና ምድሯ ራቁቷን እየቀረች፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ የደን ሽፋን መጠን በከፍተኛ ሁኔታ እያሽቆለቆለ መምጣቱን መረጃዎች ያመላክታሉ ።
ኢትዮጵያ ካሏት እምቅ ሀብቶች አንዱ ደን ነው። ደንን ማልማትና ጥቅም ላይ ማዋል ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሥነ ምህዳራዊ ፋይዳ አለው። አሁን ላይ ያለው አጠቃላይ የደን ሽፋን 15.5 በመቶ ያህል መሬት በደን የተሸፈነ፣ ሰፊው መሬት ደግሞ የተራቆተ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ።
ሀገሪቱም የኢኮኖሚ ዕድገቷን በዘላቂነት ለማስቀጠል የነደፈችው አቅጣጫ የተፈጥሮ ሀብቷን በአግባቡ ጥቅም ላይ ከማዋል ጋር የተዛመደ ነው። በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ውስጥ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት የሰጠችው ትኩረት የሚደገፍና ያጸደቀችውን አለም አቀፍ የዘላቂ ልማት ግቦች ወደ ተግባር ለመለወጥ የሚያስችል ነው።
ይህም የተራቆተ የደን ሀብት መልሶ እንዲያገግም በማድረግ ፤ የአየር ንብረት ለውጥ እያሳደረ ያለውን ተዕፅኖ በመቋቋም፣ ከደን የሚገኘውን ኢኮኖሚ ለማሳደግም ሆነ አመቺ የአየር ንብረትን ጠብቆ ለማቆየት የጎላ ሚና ይኖረዋል። ለዚህም ከአምና ጀምሮ ትልቅ ትኩረት የተሰጠው አረንጓዴ አሻራ የደን ሀብትን በማስፋፋት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ተስፋ የሚጣልበት ሆኗል። ደኖችን መልሶ በማልማትና በማስፋፋት የአየር ንብረት ለውጡን እንዲቋቋም በማድረግ፤ ኢኮኖሚ ፋይዳቸው ከፍ እንዲል ከማድረግ ጎን ለጎን የሕዝቡን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችል እንደሆነም ይታመናል።
በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ ከሚገኙት ጥቂት የደን ቅሪቶች መካከል አብዛኛው የሚገኘው የብዙ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች መገኛ በሆነው ደቡብ ክልል ነው። ክልሉ ጥቅጥቅ ባሉ አገር በቀል ዛፎች የተሸፈኑት የተፈጥሮ ደኖች መገኛ ሲሆን የከፋና የሸካ ጥብቅ የተፈጥሮ ደኖች በተፈጥሯዊ መስህብነት በባዮስፌር የተመዘገቡ ናቸው።
ከዚህ አንጻር በክልሉ የሚገኙና የሰው ልጅ የኑሮ መሰረት የሆኑትን የተፈጥሮ ሀብቶችን በመጠበቅ፣ በመንከባከብና በማልማቱ ረገድ የተሰሩ ስራዎች መመልከት ተገቢ ነው፤ የደቡብ ክልል የአካባቢ፣ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳሙኤል ቀቀቦ በአካባቢ ጥበቃና በደን ልማት ዙሪያ ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውንና ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የተሰጡት ኃላፊነቶች በርካታና ሰፊ ስራዎች የሚጠይቁ እንደሆነ ያስረዳሉ።
አቶ ሳሙኤል ቀቀቦ እንደሚናገሩት፤ የክልሉ ባለስልጣን መስሪያ ቤት ሦስት ዋና ዋና ተግባራት አሉት። እነዚህም በአካባቢ ጥበቃ ዙሪያ የብክለት ቁጥጥር ፤ የህግ ተጠያቂነት ማረጋገጥና በአየር ንብረት
ለውጥና በአካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ዙሪያ ህብረተሰቡን ግንዛቤ የማስጨበጥና መረጃዎች የመስጠት ስራ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል። የደን ልማትና ጥበቃ ስራዎች በተመለከተም አዳዲስ የደን መሬቶች መፍጠርና ነባሮችን መጠበቅና መንከባከብ ህገወጥ የደን ውጤቶች ዝውውርን የመቆጣጠር ስራ እየተሰራ መሆኑን ይገልጻሉ።
የብዝሃ ህይወት ሀብትን ከማስጠበቅ አኳያ በመጥፋት ላይ ያሉ የእጽዋት፣ የሰብልና የእንስሳት ዝርያዎች መትከል፣ መንከባከብና ማባዛት፤ እንዲሁም ረግረጋማ የሆኑ የመሬት ስርዓተ ምህዳሮችን የመጠበቅና የመንከባከብ ስራዎችም እየተሰሩ መሆኑን አብራርተዋል።
በክልሉ በደን ልማት ዙሪያ ትልቅ ትኩረት በመስጠት እየተሰራ መሆኑን የሚናገሩት ዳይሬክተሩ፤ በዘንድሮ ዓመት አንድ ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል የታቀደ መሆኑን ጠቁመው፤ በመጪው ክረምት ከአረንጓዴ አሻራ እቅድ አኳያ የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ስራዎች ጨምሮ ሁለገብ አገልግሎት የሚሰጡ የዛፍ ዝርያዎች፣ የፍራፍሬ ችግኞችንና የደን ዛፎችን ጨምሮ አምስት ቢሊዮን የሚሆኑ ችግኞች ይተከላሉ። ለዚህም ሲባል የችግኝ ዝግጅትና ለተከላ የሚሆን የመሬት ሰፊ ዝግጅት ስራ ተጠናቅቆ፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ ችግኞችን መትከል የተጀመረ መሆኑን ይናገራሉ።
በአሁኑ ወቅት የክልሉ የደን ሽፋን 22.2 በመቶ ደርሷል። በ2007 ዓ.ም 19 በመቶ የነበረውን የደን ሽፋን በሁለተኛ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ 25 በመቶ ለማድረስ ታቅዶ እየተሰራ ነው። በክልሉ በሁሉም ቦታዎች የሚገኙ የደኖች አካባቢ ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ ነው። በምዕራብ የሀገሪቱ ክልል የሚገኙት ጥብቅ ስፍራዎች ቤንች ማጂ፣ ሸካ፣ ከፋ የተፈጥሮ ደኖች አብዛኛዎቹ ጥብቅ ደኖች በመባል የተመዘገቡ ናቸው። የከፋና ሸካ ደን በጥብቅ ደንነት በዮኔስኮ የተመዘገቡ ሀብቶች ናቸው። በባዮስፎር የተመዘገበው ደን 200ሺህ ሄክታር በላይ መሬት የያዘ ደን ነው። ሸካ ባዮስፌር የሚባለው በአጠቃላይ በሸካ ሦስቱም ወረዳዎች የሚገኙ የተፈጥሮ ደኖችን ያካትታል። የከፋ ባዮስፌር እንዲሁ በከፋ ውስጥ ያሉ ደኖች በሙሉ የሚያጠቃልል እንደሆነ የሚናገሩት ዳይሬክተሩ።
እነዚህ ጥብቅ ስፍራዎች በህብረተሰቡ ተሳትፎ በተለይ በአሳታፊ የደን ሥርዓት በአርሶ አደሩ፣ በመንግስት አስተዳዳርና በህብረተሰቡ በጋራ እየተጠበቀ የሚገኝበት ነው። ከዚያም ባሻገር ማዕከላዊ ዞኖች ላይ አልፎ አልፎ የሚገኙ የተፈጥሮ ሀብቶች አሉ። እነዚህም ተለክተው፣ ተመዝግበውና ካርታ ተዘጋጅቶላቸው የሚገኙ ናቸው። ከእነዚህ ሌላ ያልተለኩትን ጥብቅ ቦታዎችና ደኖችን የመለካትና ካርታ እንዲዘጋጅላቸው የማድረግ ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ ጥብቅ ስፋራዎቹ በአሁኑ ወቅት አስፈላጊው ጥበቃ እየተደረገላቸው መሆኑን አብራርተዋል።
ከብዝሃ ህይወት ሀብት አኳያ በተለያዩ ምክንያቶች በመጥፋትና በመመናመን ላይ የሚገኙ የእጽዋትና የእንስሳት ዝርያዎችን የመጠበቅ ስራ እየተሰራ መሆኑን የሚገልጹት ዳይሬክተሩ ፤ በተለይም የእጽዋትና የሰብል ዝርያዎች፤ ለዘመናት በአርሶ አደሩ እጅ የቆዩ ሀገር በቀል የሆኑ ዝርያዎች መኖራቸውን አመልክተው፤
ለአብነትም የራሳችን ከሆኑ የሰብል ዝርያዎች ገብስንና የተለያዩ የስንዴ ዝርያዎች መውሰድ እንደሚቻል ይጠቁማሉ። አክለውም መድኃኒትነት ያላቸው እጽዋቶች፣ ብሎም ለቅመማ ቅመም ህብረተሰቡ የሚጠቀማቸው ሀገር በቀል የሆኑ የተለያዩ የእጽዋት ዝርያዎች መኖራቸውን ይናገራሉ።
ለብዝሃ ህይወት ሀብት ዝርያዎች ተገቢው እንክብካቤ እንዳይደረግላቸውና እንዲጠፉ ከሚያደርጉት በምክንያት የሚጠቀሱት የአየር ንብረት ለውጥ፣ የከተሞች እና የመንደር እንዲሁም የእርሻ መሬት መስፋፋት ናቸው የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ በዚህም ምክንያት በመጥፋት ላይ ያሉ ዝርያዎች የማፈላለግና የማሰባሰብ ስራ እየተሰራ ነው። ዝርያቸው በመጥፋት ላይ የሚገኙትን ዝርያዎች ዘር ተፈልጎ ከተገኘ በኋላ ይመዘገባል፤ ዝርያቸው የተመዘገበ ዘራቸው ካለበት ተፈልጎ እንደገና በአርሶ አደሩ እንዲባዙ ይደረጋሉ። በመቀጠልም በክልሉ ባሉ ዞኖች 17 ማህበራት ተደራጅተው የተለያዩ የሰብል ዝርያዎች እንዲባዙ የማድረግ ስራዎችም እየተሰሩ ይገኛሉ ።
እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ፤ በአፍሪካም ሆነ በኢትዮጵያ ደረጃ በመጥፋት ላይ ከሚገኙ የእንስሳት ዝርያዎች አንዱ የሸኮ ደልጋ ከብት ንዑስ ዝርያ አንዱ ነው። ይህ የእንስሳት ዝርያ የሚገኘው በደቡብ ክልል ውስጥ ሲሆን፤ በአምስት ወረዳዎች ባሉ 49 ቀበሌዎች ህብረተሰቡን በማደራጀት ዝርያው እንዳይጠፋ የማድረግ ስራ እየተሰራ ነው። የእንስሳት ዝርያው እርስ በርሱ ተላምዶ ዘሩ እንዲራባና ተጨማሪ ላሞች እንዲወለዱ በማድረግ በተሰራው ስራ ትልቅ ውጤት እየተገኘ መሆኑን የሚናገሩት ኃላፊው፤ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ውስጥ እየጠፉ ከሚገኙ የእንስሳት ዝርያዎች ዝርዝር ውስጥ እንዲወጣ ለማድረግ ሰፊ ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በተለይ ከፓርክ ወጪ የሚገኙ የዱር እንስሳት ቁጥጥር ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ሥራዎች ሌላው ነው። ከዚህም በተጨማሪ የዱር እንስሳት መገኛ ቦታዎችን የማጥናት ፤ ያሉበትን አካባቢ የመከለልና የዱር እንስሳቱ እንዲጠበቁ የማድረግ ብሎም ማህበረሰቡ በዱር እንስሳት ላይ ያለውን ግንዛቤ የማስፋትና የዱር እንስሳት የብዝሃ ህይወት ሀብቶች መሆናቸውን በሚገባ ተረድቶ እንዲጠብቃቸው የማድረግ ሥራም እየተሰራ እንደሚገኝ ይገልጻሉ።
በተለይ የተለያዩ የእጽዋት ዝርያዎች የተመናመኑባቸውና የተጋጋጡ ባዶ የሆኑ ስርዓተ ምህዳሮች መኖራቸውን የሚናገሩት ዳይሬክተሩ፤ በእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ የሚሰሩ ስራዎች እንዳሉ ሆነው ቦታዎችን ተከልለው ከእንስሳትና ከእጽዋት ንክኪ ነጻ እየተደረገ መሆኑን ይጠቁማሉ። እነዚህ ቦታዎች ከእንስሳትና ከእጽዋት ንክኪ ነጻ ሲደርጉ በመሬት ውስጥ ያሉት በመሬት ባንክ እንዲቆዩ ያደርጋል። ይህም ማለት አንዳንድ ዝርያዎችና ዘሮቹ በተለያየ ጊዜ መሬት ላይ ወድቀው ምቹ ሁኔታ እስኪፈጠርላቸው ድረስ የመቆየት ሰፊ እድል ያላቸው ስለሆነ እነዚህ ዝርያዎች እንዲበቅሉ እንደገና እንዲያገግሙ የማድረግ ሁኔታ የሚኖር መሆኑን አመልክተዋል። በዚህ ረገድ የሚሰሩ ስራዎች በፕሮግራም ተይዘው እየተሰራባቸው እንደሚገኝ ጠቁመው፤ እነዚህም የክልሉ የደን ሽፋን በተሻለ ደረጃ እንዲጨምር ከማድረግ አኳያ ትልቅ አስተዋጽኦ ያላቸው መሆኑን ያስረዳሉ።
ዳይሬክተሩ እንደሚገልጹት የደን ውጤቶች ዝውውርን የመቆጣጠር ስራ እየተሰራ ነው። ለምሳሌ በህጋዊ መንገድ ለተለያዩ አገልግሎቶች ገበያ ላይ የሚቀርቡ፤ ለግንባታ የሚውሉ የደን ውጤቶች እንደ አጣና፤ ፍልጥ፤ ለኢንዱስትሪዎች አገልግሎት የሚውሉ የጥድ ግንዶች በብዛት ከክልሉ የሚጫኑ መሆኑን ጠቁመው፤ በህጋዊ ለሆኑ ደን ውጤት ነጋዴዎች የይለፍ ወረቀት የመስጠትና ተገቢውን ክፍያ በመሰብሰብ ስራ እየተሰራ ነው። በተመሳሳይ በህገወጥ መንገድ የሚዘዋወሩ የደን ውጤቶች ለምሳሌ እንደ ጣውላ፣ አጣና፣ ፍልጥ፣ የከሰል ምርት…ወዘተ በህገወጥ መንገድ የሚያዘዋውሩ አካላትን በመያዝም ንብረቱን የመውረስና አጥፊዎችን ለህግ የማቅረብ ስራም ይሰራል። በተፈጥሮ ሆነ ሰው ሰራሽ በሆኑ ደኖች ላይ ህገወጥ የደን ጭፍጨፍ የሚያካሂዱ አካላትን ለህግ የማቅረቡ ሥራም እንዲሁ በትኩረት የሚሰራ ነው። ከዚሁ ጋር ተያይዞ በህገወጥ መንገድ አግባብነት በሌለው ሁኔታ የተወረሩ የደን መሬቶች ካሉ ወደ ደን ባንክነት እንዲመለሱ የማድረግ ስራዎችም በስፋት እየተሰሩ ነው። ከዚህም በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ውስጥ 24 ሚሊየን ብር ገቢ መሰብሰቡን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት በደን አካባቢ አልፎ አልፎ የሚያጋጥሙ ችግሮች መኖራቸውን የሚናገሩት ዳይሬክተሩ፤ የደን ሀብት መጨፍጨፍና የደን መሬት ህገወጥ ወረራ አንዳንድ አለመረጋጋቶች በሚፈጠሩበት ጊዜ አልፎ አልፎ የሚከሰቱ መሆናቸው ጠቁመዋል። ህገወጥ ተግባራትን ለመከላከል የሚሰሩ ስራዎች በየቦታው የሚለያዩበት ሁኔታዎች በመኖራቸው በሁሉም አካባቢ ወጥነት ያለው የደን እንክብካቤ ስራ መስራት ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።
የአካባቢ ጥበቃ ስራን በመስራት የደን ማልማት ዋንኛ ስራ መሆኑን የሚናገሩት ዳይሬክተሩ ፤ በአሁኑ ወቅት ትልቁን ትኩረት አረንጓዴ አሻራ ላይ በማሳረፍ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ። የክልሉን የደን ሽፋን ለማሳደግም ሁሉም ኅብረተሰብ በየደረጃው ርብርብ በማድረግና የሚጠበቅበትን በመወጣት ተሳትፎውን አጠናክሮ መቀጠል ግድ መሆኑን ተናግረዋል።
‹‹ከኮቪዲ 19 ወረርሽን ጋር በተያያዘ የዘንድሮን የችግኝ ተከላ እንደአምና ህብረተሰብ ንቅናቄ በመፍጠር በጋራ የማሳተፍ እድል ባይኖርም፤ ነገር ግን ህብረተሰቡ ከቤተሰቡ ጋር በመሆን እራሱን ከኮቪድ ጠብቆ ቫይረሱን በመከላከል የደን ልማት ስራውን መስራት አለበት›› ብለዋል። ኅብረተሰቡ የተተከሉ ችግኞችን የመንከባከብን ስራ በመስራት በክልሉ የሚገኙ የደን ሀብቱን የመንከባከብና የመጠበቅ ስራ መስራት አለበትም ብለዋል።
የደን ልማት ስራው ለአንድ አካል ብቻ የሚተው ሳይሆን ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚመለከትና በደንብ ሊሰራበት የሚገባ የህልውና ጉዳይ መሆን እንዳለበት የሚናገሩት ዳይሬክተሩ፤ ሁሉም ዜጋ የደን ልማትና ጥበቃ ስራውን የራሱ በማድረግ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት አመልክተዋል። ህብረተሰቡ ችግኞችን ከመትከል በዘለለ የደን እንክብካቤ በማድረግ የተከለውን ችግኝ በመንከባከብ ዛፍ እስከሚሆን ድረስ የመጠበቅ ኃላፊነት እንዳለበት መገንዘብ ይኖርበታል ሲሉም ሃሳባቸውን አጠቃለዋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ8/2012
ወርቅነሽ ደምሰው