ትምህርት የዓለም ለውጥ ማሽን መሆኑ ይነገራል። በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት የዚህ ለውጥ ማሽን መልኩን ቀይሯል።አሁን የገጽ ለገጽ ትምህርት የለም።አሁን የትይዩ ተሳትፏዊ መማር ማስተማር የለም፡፡አሁን ተማሪ ተኮር መምህር ተኮር የማስተማር ሂደት የለም።ይልቁንም አንድ አዲስ መንገድን ይዞ መምጣቱ ይነገራል።ይኸውም በቴክኖሎጂ የታገዘ የኢንተርኔት ( የኦን ላይን) መማር ማስተማር።በዚህ ዓይነት መልክ የትምህርት ሥርዓታቸውን የቃኙት የዓለም አገራት በተለይም የአፍሪካ አገራት ውስን እንደሆኑ ጥናቶች ያሳያሉ።በዚህ የተነሳ በቀጣይ በዚህ መልክ መማር ማስተማሩን ሥርዓት የሚያስይዙ ሕግና መመሪያዎች በማዘጋጀት ሂደት አገራት ተጠምደዋል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ተማሪዎች የትምህርቱን ድባብ እንዳይረሱትና እንዳይዘናጉ እንዲሁም የገጽ ለገጽ ትምህርት መዘጋት የተነሳ የሥነልቦና ተጽዕኖ እንዳያሳድርባቸው በሚል እንጂ እንደ ዋና ሥራ የማይመለከቱት ብዙ ናቸው።ኢትዮጵያም በዚህ ተርታ የምትሰለፍ ተጠቃሽ አገር ናት።ከመጋቢት የመጀመሪያ ሳምንት ጀምሮ ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል።በመሆኑም በተለያዩ የመገናኛ አማራጮች ትምህርትን ለተማሪዎች ተደራሽ ለማድረግ ጥረቶች እየተደረጉ ይገኛሉ።የ8ኛ ክፍል ሞዴል ፈተና ሙከራም በዚሁ መንገድ ሊሰጥ መሞከሩ የሚታወስ ነው።ሌሎችንም መጥቀስ ይቻላል፡፡
ትምህርት ሚኒስቴር ፣የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው ተዋረዳዊ መዋቅሮች የተማሪዎችን መማር ማስተማር ሂደት በቴክኖሎጂ ተደራሽ ለማድረግ እንቅስቃሴዎች ቢያደርጉም ለሁሉም ተደራሽ ይሆናል ማለት እንዳልሆነ ይታወቃል።
በመሆኑም እድሉ ያላቸው እንዲጠቀሙ እድሉን የማያገኙት ደግሞ በእጃቸውና በቤታቸው በሚገኙት መጽሐፎች፣ቴሌቪዥኖች እና ሬዲዮኖች እንዲሁም በቤተሰቦቻቸው እየታገዙ እንዲያጠኑ ይመክራሉ።ትምህርት የተዘጋበት ዋና ምክንያትም ይኸው በመሆኑ በእነዚህ ሂደቶች ውስጥ ተማሪዎች እጃቸውን በሳሙና በመታጠብ፣እጃቸውን በሳኒታይዘር በማጽዳት፣ በቤታቸው በመቀመጥ እና አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ከኮሮና ወረርሽኝ ራሳቸውን እና ቤተሰቦቻቸውን እንዲጠብቁ አደራ መባላቸው የሚታወስ ነው።በአልባሌ ቦታዎች የሚያሳልፉ ተማሪዎች ለሕይወታቸውም፣ ለቤተሰቦቻቸውም፣ ለአላማቸውም ሊያስቡ እንደሚገባም ይመከራል።
የዛሬው የአስኳላ አምድ በግል ትምህርት ቤቶች በኩል የመማር ማስተማሩ ሂደት በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ? ፣ከትምህርት ቤት ክፍያ፣ከአስተዳደር ሰራተኞችና ከመምህራን ደመወዝ ክፍያ ጋር በተያያዘ፣ በትምህርት ሚኒስትር በኩል የተላለፉ ውሳኔዎች የአተገባበር ሂደት በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ፣ እና የተወሰዱ መፍትሄዎችን ለማስቃኘት እንሞክራለን፡፡
ሁሉም ባይሆኑ አንዳንድ የግል ትምህርት ቤቶች ትምህርት በመዘጋቱ የተነሳ ለመምህራን ሙሉ ሳይሆን ግማሽ ደመወዝ እንከፍላችኋለን የሚል፣ የተማሪ ወላጆችም ልጆቻቸው በቤት የተቀመጡ በመሆናቸውና ሥራ እንደልባቸው እየሰሩ ባለመሆኑ የትምህርት ቤት አገልግሎት ክፍያ መክፈል የሚችሉበት አቅም እንደሌላቸው የሚገልጹና ሌሎች በርካታ ተያያዥ ችግሮች ሲነሱ እንደነበር በተለያዩ ሚዲያዎች ሲገለጽ ቆይቷል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ ትምህርት ሚኒስቴር ያወጣቸው መመሪያዎች ለምሳሌ ተማሪዎች በቤታቸው ተቀምጠው በሚችሉት አማራጭ በቴሌቪዥን፣በሬዲዮና በኢንተርኔት በኩል ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ፣ወላጆች የትምህርት ቤቶችን ነባራዊ ሁኔታዎች መሰረት በማድረግ ከወላጅ ኮሚቴዎችና ከትምህርት ቤቶች የአስተዳደር አካላት ጋር በመወያየት የትምህርት ቤት አገልግሎት ክፍያዎች ከ50 እስከ 75 በመቶ እንዲፈጽሙ መመሪያዎች አስተላፏል።በአገር አቀፍ ደረጃም ሆነ በከተማ አስተዳደር ደረጃ የሚወጡ ትምህርት ነክ መመሪዎችን እና ስትራቴጂዎችን የማስፈጸም ኃላፊነት የተጣለበት የትምህርት ስልጠና ጥራት ሙያ ብቃት ማረጋገጫ ባለስልጣን የእነዚህን ጉዳዮች አፈጻጸም ክትትል አድርጓል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርት ስልጠና ጥራት ሙያ ብቃት ማረጋገጫ ባለስልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ሸዊት ሻንካ እንደገለጹት፤ መመሪያው ከመውጣቱ በፊት መነሻ ጥናት ተካሂዷል።በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሚገኙ ስድስት ክፍለ ከተሞች፣ በ36 ትምህርት ቤቶች ከአጸደ ሕጻናት እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ድረስ ናሙና ተወስዷል።በዚህ መሰረትም የወጣው አገር አቀፍ መመሪያ አፈጻጸሙ ምን እንደሚመስል በአዲስ አበባ በ1475 ትምህርት ቤቶች በአካል በመገኘት የመስክ ምልከታ ክትትል መደረጉን ተናግረዋል።
በመሆኑም የመማር ማስተማር ሂደቱ በምን አግባብ እየሄደ እንደሚገኝ ማየት ተችሏል ያሉት ሥራ አስኪያጇ በሬዲዮና በቴሌቪዥን እየቀረቡ የሚገኙ የትምህርት አሰጣጥ ሂደቶች በጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛል።እያንዳንዳቸው ትምህርት ቤቶች ካሉበት ነባራዊ ሁኔታዎች በመነሳት ከተማሪዎቻቸው ጋር በተለያዩ የመገናኛ መንገዶች በቴሌግራም፣በኦዲዮ፣በቪዲዮና በኢንተርኔት አማካኝነት እንደሚገናኙና ትምህርታቸውን ተደራሽ ለማድረግ እየጣሩ መሆናቸውን ማረጋገጥ መቻሉን ተናግረዋል።
የትምህርት አሰጣጡ ሂደት ምን ይመስላል?
የትምህርት አሰጣጡ ሂደት መደበኛ የትምህርት ሂደቱን ይተካዋል ባይባልም ተማሪዎች አልባሌ ቦታዎች ላይ እንዳይውሉ ይረዳቸዋል።በዚህም መሰረት ቴክኖሎጂን መጠቀም ለማይችሉት ተማሪዎች በሰነድ (በሞጁል) በማዘጋጀት ከአራት ቀን በኋላ ለወላጆች እንዲደርሳቸው በማድረግ ሲመለስም ከአራት ቀን በኋላ እንዲታረም ይደረጋል። መምህራን ሲያስተምሩ በመቅረጽ በቪዲዮና በኦዲዮ፣በፍላሽ ትምህርቱንና የቤት ሥራዎቹን (አሳይመንቱን) በመጫን እቤታቸው እንዲያነቡና እንዲሰሩ በመላክ፣ በትምህርት ቤቶች ዌብ ሳይትና ‹‹ስኩል ጌት›› በመጠቀም ትምህርቱን የሚያስተላልፉ ትምህርት ቤቶች መኖራቸው (ለምሳሌ፡- ትውልድ ተስፋ፣አርዲ፣አቢየም፣ዩዝ፣ኦሜጋ ትምህርት ቤቶች፣)፣መልዕክት(ሜሴጅ 6158) በመላላክ የሚያስተምሩ እንዳሉ (ምሳሌ፡- አሚጎኒያ ትምህርት ቤት) ማረጋገጥ መቻሉን ወይዘሮ ሸዊት ይገልጻሉ።
በዚህም ተገኝቷል የሚሉትን ውጤት ሲያብራሩ ተማሪዎች ከትምህርት ውጪ እንዳይሆኑ፣ተቀዛቅዞ የነበረውን የመማር ማስተማር ሂደት በተሻለ መንገድ እንዲነቃቃ ማድረጉ፣በተማሪዎች ዘንድ እየተማርን ነው የሚል አስተሳሰብን በማሳደር በወረርሽኙ ምክንያት የሚደርስባቸውን የስነልቦና ጫና ማቃለሉ እና ሌሎችንም ገልጸዋል፡፡
የተወሰዱ ማሻሻያዎችና የማስተካከያ ርምጃዎች
ከመማር ማስተማር ሂደቱ ጎን ለጎንም ከክፍያ ጋር የተያያዙ ከወላጆች የሚቀርቡ ቅሬታዎች በመኖራቸው በተቀመጠው መንገድ እየሄደ ነወይ? በሚል ማረጋገጣቸውን የገለጹት ወይዘሮ ሸዊት፣ 100 ፐርሰንት ሙሉ ክፍያ የጠየቁ 21 ትምህርት ቤቶች ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው ጠቁመዋል።በዚህም 17ቱ ማስተካከል ሲችሉ ቀሪዎቹ (አራቱ) ማስተካከል ባለመቻላቸው በቀጣይ ዓመት (2013 ዓ.ም) እንዳያስተምሩ የእውቅና ፈቃዳቸው ተሰርዟል።ሌሎች በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት 1248 ትምህርት ቤቶች 75 በመቶ፣ 70 ትምህርት ቤቶች 70 በመቶ፣ 67 ትምህርት ቤቶች 65 በመቶ፣ 18 ትምህርት ቤቶች 60 በመቶ፣ ሶስት ትምህርት ቤቶች 55 በመቶ እና 24 ትምህርት ቤቶች ደግሞ 50 በመቶ የአገልግሎት የትምህርት ቤት ክፍያ መቀበላቸውን ማረጋገጥ እንደተቻለ አስረድተዋል።
በአጠቃላይ የኮሮና ወረርሽኝ ያሳደረውን አገራዊ ችግር በመረዳት የመማር ማስተማሩ ሂደት የመረሳት እጣ ፋንታ እንዳይገጥመው ጥረቶች በመደረግ ላይ ይገኛሉ።በዚህ ሂደትም የግል ትምህርት ቤቶችን ያህል የከፋ ችግር ባይጋረጥባቸውም በሁሉም የትምህርት ተቋማትና ተማሪዎች ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ ቀላል አይደለም።ይሄን ሁኔታ ወላጆችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላትና ተቋማት የየድርሻቸውን በማበርከት የትምህርት ቤቶች ሕልውና እንዲቀጥል በመረባረብ ላይ ይገኛሉ።ችግሩ አገራዊ ብቻ ባለመሆኑ ትምህርት በመቅሰም ተደጋግፎ መሻገር አስፈላጊ ነው።
አዲስ ዘመን ግንቦት 28/2012
ሙሐመድ ሁሴን