በቅርቡ የተከናወነውን ለውጥ ተከትሎ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ለውጡን የሚመጥኑ ማሻሻያዎችና እርምጃዎች ሲወሰዱ ቆይተዋል፡፡ በአንጻሩ ለውጡን ካለመቀበልም ሆነ የግል ጥቅምን ለማስጠበቅ በሚያስችል መልኩ ሰላምና ጸጥታን በማደፍረስ የህዝቦችን ደህንነት ስጋት ላይ ለመጣልና ህዝቦች ለውጡን እንዲጠራጠሩ ለማድረግ የሚደረጉ ጥረቶች በስፋት ይስተዋላሉ፡፡ ታዲያ «ሃምሳ ሎሚ…» እንደሚባለውም ሰላምና ጸጥታን አስጠብቆ ለውጡን የማስቀጠል ሥራው በመንግሥት ላይ የተንጠለጠለ፣ ለፌዴራሉ ወይም ለክልሎች ብቻ የተተወ ሳይሆን፤ እንደ ህዝብ ከግለሰቦች፣ እንደ አገር ደግሞ ከቀበሌና ከተሞች ጀምሮ በጋራና በቅንጅት መሥራት ያለበት መሆኑ እሙን ነው፡፡ እኛም ለዛሬው እትማችን በአዳማ ከተማ ባለው የሰላምና ጸጥታ አጠባበቅ ዙሪያ ከአዳማ ከተማ አስተዳደርና ፀጥታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ለማ ኃይሌ ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ ይዘን ቀርበናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በለውጡ ማግስት የከተማዋን ጸጥታ በሚያስጠብቅ መልኩ ለመሥራት በ2011 በጀት ዓመት ምን አቅዳችሁ ወደሥራ ገባችሁ?
አቶ ለማ፡- በ2011 በጀት ዓመት የአዳማ ከተማን ፀጥታ ለማስፈንና የተገኘውን የለውጥ ሂደት ለማስቀጠል፣ ህዝቡም የሰላም ባለቤት እንዲሆን በቅድሚያ ከህዝቡ ጋር ውይይት በማድረግ፤ መዋቅሮቻችንንም በመፈተሸና በማስተካከል ነው ወደሥራ የገባነው፡፡ ቀድሞ የነበረውን አወቃቀር የማስተካከል፣ የአሰራር ክፍተቶችን የማጽዳትና ችግር ውስጥ የገቡ አንዳንድ የሥነምግባር ችግር ያለባቸውንም አካላት ለማጽዳት የጸጥታ አካላት በአዲስ መልኩ በህዝብ እንዲመረጡና ችግር ያለባቸውም በህዝብ ተተችተው እንዲወጡ ተደርጎ በአዲስ መልኩ ነው ያዋቀርነው፡፡
እንደ አዳማ ከተማ የፖሊስ መዋቅሩ እንዳለ ሆኖ፤ የአስተዳደርና ጸጥታ መዋቅሩ በከተማ፣ በክፍለ ከተማና ቀበሌ ደረጃ አለ፡፡ የቀበሌ ታጣቂዎችና ደንብ አስከባሪዎች፤ ብሎም አብዛኛውን ሽፋን የያዘውም(ከ6ሺ በላይ አባላት ያሉት ነው) የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አለ፡፡ እነዚህ በጋራ የሚሠሩበት አግባብም ተፈጥሮ ነው የተጀመረው፡፡ እነዚህ አካላትም ግንዛቤ እንዲጨብጡና ወርደውም ለህብረተሰቡ ግንዛቤ እንዲያስጨብጡ በመደረጉም በየደረጃው ተመሳሳይ አረዳድ ተይዞ ነው ወደሥራ የተገባው፡፡
በዚህ መልኩ ወደሥራ ሲገባም በእርግጥም የአዳማ ከተማ ህዝብ ሰላም ወዳድ፣ ለሥራ ተነሳሽነት ያለውና ሠርቶ መብላት የሚፈልግ እንጂ፤ ለመበጥበጥ ፍላጎት የሌለው መሆኑን በሚገባ ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ ምክንያቱም በአንዳንድ አካባቢዎች የተከሰቱ ችግሮች፤ አዳማ ላይ አልተከሰቱም፡፡ እስካሁን በሰላም መቆየታችንም የህዝቡን ሰላም ወዳድነትና ሠርቶ የመብላት ፍላጎት የሚያረጋግጥ ነው፡፡ በዚህም ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ክልሉና የክልሉ ፕሬዚዳንት አዳማ የሰላም ከተማ መሆኗን፤ ሰላም ወዳድ ህዝብ እንዳላትና የጸጥታ መዋቅሩም ከህዝብ ጋር ተቀናጅቶ እየሠራ በመሆኑ ምስጋናና ዕውቅና ሰጥተዋታል፡፡ ከዚህ አንጻር በዓመቱ እስካሁን ባለው ሂደት ውጤታማ ሥራ አከናውነናል ማለት ይቻላል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በበጀት ዓመቱ ወደሥራ ስትገቡ እንደ ከተማ አስተዳደር ነባራዊ ሁኔታዎችን ከማገናዘብ፣ የጸጥታ ሥጋቶችን ከመለየትና የመፍትሄ አቅጣጫን ከማስቀመጥ አንጻር በምን መልኩ ጀመራችሁ?
አቶ ለማ፡- እቅዶችን ስናቅድ እንደ ስጋት የለየናቸው ጉዳዮች ነበሩ፡፡ ከእነዚህ መካከል አንዱ በሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢ ተከስቶ በነበረው ግጭት ምክንያት ተፈናቅለው ወደከተማዋ የገቡ ከ2ሺ ያላነሱ ሰዎች ጉዳይ ሲሆን፤ እነርሱን መልሶ የማቋቋም ሥራ በሚሠራበት ሰዓት ከብሶትም አንጻር ወደማይሆን አቅጣጫ ሊሄዱ ይችላሉ፤ ሥነምግባር የጎደላቸው አካላትም ይሄን አጋጣሚ ተጠቅመው በዛ ውስጥ ተሳታፊ ይሆናሉ የሚል ነበር፡፡ በዚህም እነርሱንም ሆነ ህብረተሰቡን በማወያየት መቻቻል እንዲኖርና ችግር ካለም በውይይት መፍታት እንዲቻል አድርገን ነው ችግሮችን እየቀረፍን የቆየነው፡፡
ሌላኛው ስጋታችን ሕገ ወጥ ግንባታ ነበረ፡፡ በሕገ ወጥ ግንባታ ዙሪያም በማይሆን መልኩ ከተለያየ ቦታ እየተጠራሩና በትንሽ ገንዘብ የጸጥታ መዋቅርም ሆነ የአመራር አካሉን በማታለል፤ ከደላላ ጋር ተመሳጥረው በሕገ ወጥ መንገድ መሬት የሚይዙና ሕገ ወጥ ግንባታ የሚያከናውኑ አሉ፡፡ ይህ ትልቅ ችግር ስለነበር በተቻለ መጠን መዋቅሮቻችን ከዛ ውስጥ በማውጣት፤ የገቡበትንም ይዘን ለህግ በማቅረብና ሰው ከእነርሱ እንዲማር በማድረግ በአሁን ሰዓት ሕገወጥ ግንባታው እየተመናመነ የመጣበት፤ በተቻለ መጠንም ፕላኗን የጠበቀችና ጽዱ የሆነች ከተማ እንዲኖረን ለማድረግ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች አሉ፡፡
ከዚህ ውጪም አልፎ አልፎ የንጥቂያና የሌብነት ወንጀሎች ነበሩ፡፡ እነዚህንም በተለያዩ ሰዓቶች ድንገተኛ ፍተሻ በማድረግ መቆጣጠር ችለናል፡፡ ከዚህ ባለፈ አዳማ ውስጥ አልፎ አልፎ ሞባይልና ቦርሳ የመንጠቅ፣ ሌብነትና በስለት አደጋ የማድረስ ሁኔታዎች ነበሩ፡፡ ያንንም አሁን መዋቅሮቻችንን ካጠናከርንና ህብረተሰቡን ካሳተፍን በኋላ እጅ ከፍንጅ እንዲያዙና የወሰዱትም እንዳያመልጡ ተደርጎ ለሕግ እያቀረብን ስለሆነ ከዚህ አንጻርም የተሻለ ሥራ ሠርተናል፡፡
እንደ አጠቃላይ ግን መጀመሪያም እቅዳችንን ስናቅድ ስጋቶች ናቸው የምንላቸውን ነገሮች ከለየን በኋላ ማንን ብናሳትፍ፣ ከማን ጋርስ ብንሆን ነው ችግሮችን ልንቀርፍ የምንችለው የሚለውን አቅደን ነው የገባነው፡፡ በዚህ መልኩ ከህዝብ፣ ከጸጥታ መዋቅሩና ከሌሎች ባለድርሻዎች ጋር ውይይት ተደርጎ እንዲሁም ቼክ ሊስት በመሥራትና ወደታች አውርደን ግብረ መልስ እየሰጠንና ችግር ያለበትን አካልም እየለየን የባሰ ችግር ውስጥ የገባውን ደግሞ እርምጃ እየወሰድን ስንሄድ ቆይተን ነው ሰላሙን ያሰፈንነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- እንደ አገር በተለይም እንደ ክልል ያለውን የጸጥታ ችግር ተከትሎ በአዳማ ያጋጠሙ ችግሮች ነበሩ? እንዴትስ ተፈቱ?
አቶ ለማ፡- በክልሉም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች የሚስተዋለውን ችግር ተከትሎ አንድ ወቅት ላይ ገበያ የማቆም እቅድ ተይዞ ነበር፡፡ በተለይ በተለያዩ ተቃዋሚ አካላት ሲነዛና ሲለፈፍ የነበረው ሁኔታ አዳማ ላይ ለምን አልተከሰተም ተብሎ በዘመቻ መልክ ወጥተው ነበረ፡፡ ሆኖም የጸጥታ መዋቅሩም፣ በፓትሮልም፣ በቋሚ ጥበቃም በተለያየ ቦታ ክትትል ስናደርግ ስለነበር አንድ ሁለት ቀን ገበያውን ለማስቆምና ለማዘጋት እየዞሩ «አትዘጉም ወይ» የሚሉ ሰዎችን በቁጥጥር ስር አውለናል፡፡ በዚህ እርምጃም በአንድ ቀን 32 ሰው፤ በሁለተኛው ዙር ደግሞ ወደ 35 ሰው መያዝ ተችሏል፡፡ ሆኖም በዚህ ተግባር ተሰማርተው ከያዝናቸው ሰዎች ውስጥ የግል መረጃቸውንና አድርሻቸውን ስናጣራ አንድም ሰው የአዳማ ነዋሪ የለበትም፡፡ ከሌላ ቦታ ተልዕኮ ወስደው የመጡ ሰዎች ናቸው፡፡ እነዚህንም ቢሆን ግማሹን በምክር፤ ተጨባጭ መረጃ የተገኘባቸውን ደግሞ ለህግ አቅርበን የተዳኙበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡
ከዚህ ባለፈ ግን እንደ አገርም ሆነ ክልል የተፈጠረውን የሰላም መደፍረስ ጋር ተያይዞ በአዳማ ችግር ተፈጥሮ የተፈናቀለ አንድም ሰው የለም፡፡ አዳማ የተለያዩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች እንዲሁም እምነቶች መኖሪያ ብትሆንም ህዝቡ (በብሔሩም ሆነ በእምነቱ ችግር ሳይፈጥር) ተቻችሎ አብሮ እንዲኖር ለማድረግ በየቦታው የምናደርገው ውይይት የተሻለ መንገድ ሊከፍትልን ችሏል፡፡ የሃይማኖት ተቋማት አሉ፤ የሃይማኖት ፎረምም አለን፤ ሁሉንም ሃይማኖቶች የሚመሩ የአመራር አካላት አሉ፡፡ እነርሱም ጭምር በየእምነት ተቋሙ እንዲያስተምሩ በማድረግ ወንጀል ከመፈጸሙ በፊት ወንጀልን ለመከላከል እንድንችል የጋራ አቋም ይዘን፤ አገራዊ እይታ ኖሮን፤ ወንድማማችነታችን እንደተጠበቀ ተቻችለን መኖር የምንችልበትን ሁኔታ መፍጠር አለብን ከሚል አንጻር ተግባብተን ነው የገባንበት፡፡
እናም በሃይማኖት ወይም በጎሳ ምክንያት የተጋጨ አንድም ሰው የለም፡፡ በሰላምም ተቻችሎ እየኖረ ያለ ህዝብ ነው፡፡ በመሆኑም አስቀድመን የሠራነው የግንዛቤ ማስጨበጡ ሥራ ውጤታማ አድርጎናል፡፡ ለምሳሌ፣ በየቀኑ ወደእዚህ ከተማ እየገባ የሚወጣው ህዝብ ከአርባ እስከ ሃምሳ ሺህ ይደርሳል፡፡ ይሄን ሁሉ ችለን ነው፤ ይሄ ሁሉ ገብቶ የሚወጣው ደግሞ ሰላም ስላለ ነው፡፡ ሰላሙን ለማስጠበቅ የጸጥታ መዋቅሩ ለደቂቃም እረፍት የለውም፡፡ ደከመኝ የማይል መዋቅር ነው ያለው፡፡ ሌሎች አካባቢዎች ጋር እየተከሰቱ ያሉ ችግሮችን እንደ ምሳሌ እየወሰድን ማስተማሪያ አድርገን፤ በሌሎች አገሮችም ሲከሰት የነበረው ኢትዮጵያ ውስጥ ወይም ደግሞ በክልል ውስጥ የሚከሰተው ወደእኛ ክልል ወይም ወደእኛ ዞን ወይም ከተማ መምጣት የለበትም፤ ለራሳችን ዘብ መቆም አለብን በሚል ነው በጋራ ስንሠራ የነበረው፡፡
አዲስ ዘመን፡- አዳማ የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦች መኖሪያ ናት፤ የስብሰባ ማዕከልም እየሆነች ናት፤ ዩኒቨርሲቲም በውስጧ ይዛለች፤ በቅርቡም የኢንዱስትሪ ፓርክ ባለቤት እንደመሆኗ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶችን ተሳትፎ ትፈልጋለች፡፡ እነዚህ ሁሉ የከተማዋን ሰላምና ጸጥታ እንደመፈለጋቸው ይሄን የሚመጥን ሥራ እየሠራን ነው ብላችሁ ታምናላችሁ?
አቶ ለማ፡- እንደተባለው ከተማችን የብሔር ብሔረሰቦች መኖሪያ ናት፡፡ እንደ አገርም የስብሰባ ማዕከል ናት ማለት ይቻላል፡፡ የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክም እንደ አገር ትልቁ የኢንዱስትሪ ፓርክ እንደመሆኑ፤ በዚህ ላይ ትልቅ ራዕይ ነው ያለን፡፡ ከዚህ አንጻር ደህንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን ካሉን የጥበቃ ኃይሎች አካፍለን በእዛ ውስጥ አስገብተን ማንም ሰው ያለስጋት ወጥቶ መግባት እንዲችል ተደርጎ ነው እየተሠራ ያለው፡፡ በዚህ ረገድ እስከዛሬ ችግር ተፈጥሮ አያውቅም፤ በቀጣይም እንዳይፈጠር ትኩረታችን እዛ ላይ ነው ብለን አመራር የሚሰጡ መኮንኖች ሳይቀር እዛ ውስጥ ተመድበው እንዲሠሩና እንዲቆጣጠሩ በማድረግ የከተማው አንድ አካል ተደርጎ እየተሠራ ነው፡፡
ዩኒቨርሲቲን በተመለከተም ዩኒቨርሲቲው ብቻውን አይደለም የጸጥታ ሥራውን የሚሠራው፡፡ አንድ ወጥ የሆነ የጋራ ኮሚቴ አለ፡፡ የጋራ ኮሚቴው ቦርድ የሚመራው በከተማዋ ከንቲባ ነው፡፡ ከእነርሱ ጋርም የማይቆራረጥ የጋራ መድረክ አለን፡፡ ምክንያቱም የዩኒቨርሲቲው ችግር የከተማው፤ የከተማውም ችግር የዩኒቨርሲቲው ነው፡፡ በሌሎች አካባቢዎችና ዩኒቨርሲቲዎች ችግሮች ሲከሰቱ እዚህም ችግር ለመፍጠር የቤት ሥራ ወስደው ለማወክ የሚንቀሳቀሱ አካላት ነበሩ፡፡ በተለያዩ ሁኔታዎች ለማወያየት እንዲቻቻሉ ለማድረግ ተሞክሯል፡፡ ውጪ ወጥተው እንኳን ችግር እንፈጥራለን ሲሉ «አይሆንም» ብለን ከፊታቸው ቆመን አሳምነን የመመለስ ሥራ ተሠርቷል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ግን ተልዕኮ ወስደው ፍላጎታቸውን ከግብ ለማድረስ የሚጥሩ አካላት እንዳሉ የለየንበት ሁኔታ አለ፡፡ በአሁን ሰዓትም የመማር ማስተማሩን ሂደት ለማስተጓጎል ውስጥ ለውስጥ እየሠሩ ያሉ አካላት አሉ፡፡
ትምህርት ሲጀምሩ መማር የማትፈልጉ ከሆነ የሚወሰደው ሕጋዊ እርምጃ ሊጎዳችሁ ስለሚችል ትምህርታችሁን ተማሩ የሚል ምክርም ሰጥተናል፡፡ ሆኖም በወቅቱ ዜጎች በየቦታው እየሞቱና እየተፈናቀሉ መማር የለብንም ድምጻችንን ለሚዲያ እናሰማለን በሚል ወደውጭ ለመውጣት ሲሞክሩም ሚዲያ ባሉበት እንዲሄድላቸው በማድረግ የፈለጉትን እንዲናገሩ እስከማድረግም ተሄዷል፡፡
በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ ግን በቅርቡ ሦስት ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ጊቢ ውስጥ ባለ የውሃ ጉድጓድ ውስጥ ሞተው በመገኘታቸው ሌላ አጀንዳ ለማንሳት ሙከራ ተደርጎ ነበር፡፡ ሆኖም ጉዳዩን የሚያጣራ ቡድን ተዋቅሮ በተደረገው ማጣራት ተማሪዎቹ ውጪ ሲጠጡ ቆይተው ሰዓት እላፊ በአጥር ዘልለው ወደጊቢው ለመግባት ሲሞክሩ ነው ውሃ ውስጥ ገብተው የሞቱት፡፡ የሀኪም ማስረጃ እንዳረጋገጠውም ለሞታቸው ሌላ ምንም ንክኪ ምክንያት አለመኖሩን ነው፡፡ እነዚህ ተማሪዎች ቀደም ሲልም ደጋግመው ሌሊት ይገቡ እንደነበርም መረጃ ተገኝቷል፡፡ በሞቱት በሦስቱም ተማሪዎች ኪሶች ውስጥም ትንባሆ፣ የሃሺሽና ሌሎች ቅጠሎች ተገኝተዋል፡፡ ይህ የሚያመለክተው ደግሞ ተማሪዎቹ በመጠጥና በሃሽሽ ሱስ ራሳቸውን አደንዝዘው እዚህ ውስጥ መግባታቸውን ነው፡፡ ይሄንንም በግልጽ በመለጠፍ ተማሪዎች እንዲያውቁት ተደርጓል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ግን ከምንምና ከመቼውም በላይ ያዘነበት ጊዜ ቢኖር ይሄው አጋጣሚ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በአዳማ ከንብረት ስርቆት ባለፈ በቅርቡ ህጻናት እየተሰረቁ ኩላሊትና መሰል አካላቸው እየተወሰደ ስለመሆኑ በማህበራዊ ሚዲያዎች ሳይቀር በሰፊው ይነገራል፡፡ ይሄ ምን ያክል እውነት ነው? ይሄንንና ሌሎች ሕገ ወጥ ተግባራትን ከመከላከል አኳያስ በምን መልኩ እየተሠራ ነው?
አቶ ለማ፡- ከህጻናት ስርቆት ጋር ተያይዞ የሚነዛው አሉባልታ ሆን ተብሎ ህዝቡ በሰላም ወጥቶ እንዳይገባ፤ ልጆቹን ወደትምህርት ቤት እንዳይልክ ዓላማ ይዞ የሚሠራ አካል እንዳለ ነው የተረዳነው፡፡ ይሄንንም ለህዝብ አስገንዝበን አሁን የተረጋጋ ሁኔታ ነው ያለው፡፡ አንድ ሰው እሱም በመጠጥ ኃይል መንፈሱ የተናወጠ አንድ ህጻን እናትና አባቱ ቤት በሌሉበት ይዞ እጅ ከፍንጅ በመያዙ ወዲያው ለሕግ ቀርቧል፡፡ ከዚህ ውጪ ሌላ የልጅ ስርቆት አልተካሄደም፡፡ አጀንዳ ፈጥረው ልጅ ተሰርቋል፤ ኩላሊት ወጥቷል፤ ሌላም ነገር ሆኗል ብለው የሚያስወሩ አሉ፡፡ ነገር ግን ውሸት ነው፡፡
በእነዚህ ሰዎች አጀንዳ ምክንያት ግን አንድ አባት ልጁን ይዞ ከትምህርት ቤት ወደ ቤት እየሄደ እያለ «ልጅቷ አንተን አትመስልም ጠረጠርንህ» ብለው የተደበደበበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር፡፡ የጸጥታው መዋቅር ደርሶም ነው ሰውዬውን ያስጣለው፡፡ ከዚህ አንጻር ህዝቡ ጉዳዩን በአንክሮ ሲከታተለው ነው የቆየው፡፡ ይህ ደግሞ ውሸት እንደሆነ በአደባባይ ለሁሉም አካላት በየእምነት ተቋሙም፤ በየትምህርት ቤቱም፤ በየመድረኩም፣ ተነግሮ አሁን ህዝቡ ተረጋግቶ በሰላም ወጥቶ እየገባ ነው ያለው፡፡ በመሆኑም ኩላሊት የወጣበትም ሰው የለም፤ ተሰርቀው ሌላ ቦታ የተወሰዱ ሕጻናትም የሉም፡፡
ሕገ ወጥ ተግባርን በተመለከተም፤ ሕገ ወጥ ተግባር በብዙ መልኩ የሚገለጽ እንደመሆኑ ቀደም ብዬ የጠቃቀስኳቸው ስርቆት፣ ሕገ ወጥ ንግድ፣ ህገ ወጥ የመሬት ወረራና ግንባታ ጨምሮ በርካታ የሚነሱ ጉዳዮች አሉ፡፡ እናም እነዚህን መስመር ለማስያዝ ከሌሎች ዘርፎች ጋር በመሆን በተቀናጀ መልኩ በሕጋዊ ሂደቶች እየተሠራ ነው፡፡ ለምሳሌ፣ ሕገ ወጥ ንግድን ወደ ሕጋዊ መስመር ለማምጣት እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች አሉ፡፡ ወደ ሕጋዊነት አልመጣም ያለውንም ወደመስመር የማምጣት ሥራዎች ቀጣይነት ኖሯቸው ይከናወናሉ፡፡ በሌላ መልኩ በሕገ ወጥ መልኩ መኪና መንገድ ላይ አቁመው ለጸጥታ ችግር እንዲሆን የሚያደርጉ አካላትን የማስነሳትና ሁለት ቦታዎች ላይ ሰፋፊ ፓርኮች በማዘጋጀት እዛ እንዲገቡ ተደርጓል፡፡
ሌላው ችግር ከባጃጆችና ሞተሮች ጋር የሚያያዝ ሲሆን፤ ሆን ተብሎ ለስርቆት የተዘጋጁ ባጃጆች አሉ፡፡ እነዚህ ደግሞ ከከተማው ብቻ ሳይሆኑ ከአጎራባች ወረዳዎችም የሚመጡ በመሆናቸው ተለይተው አይታወቁም፤ አንዳንዴም ታርጋቸው እንዳይነበብ ለማድረግ ታርጋቸውን ቀልብሰው ወይም አውልቀው በአሳቻ ሰዓት ገብተው አንድ ነገር አድርገው ለመውጣት የሚንቀሳቀሱ አሉ፡፡ በዚህ ረገድ ታርጋ ነቅለው የሚንቀሳቀሱ በተጨባጭ ለወንጀል ራሳቸውን ያዘጋጁ ወደ ዘጠኝ የሚሆኑ ባጃጆች እና ከአስር በላይ ሞተሮች ተይዘዋል፡፡ ሕገ ወጥ የመሳሪያና የገንዘብ ዝውውርን በተመለከተም ድንገተኛ ፍተሻ በምናደርግበት ጊዜ በስፋት እናገኛለን፡፡ እንደ አጠቃላይ በእነዚህና ሌሎችም በከተማዋ የሚስተዋሉ ሕገ ወጥ ድርጊቶችን ለመከላከል የሚያስችሉ ቅንጅታዊ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ህዝቡን የለውጡ አጋዥ በማድረግ የከተማዋን ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ ቀጣይ ሥራችሁን በምን መልኩ ለማስኬድ አስባችኋል? ከህዝቡና ከባለድርሻዎችስ ምን ይጠበቃል?
አቶ ለማ፡- በከተማዋ ያለው ሰላም ቀጣይነት እንዲኖረውና ህዝቡም አገራዊ ዕይታ እንዲኖረው፤ ተቻችሎ መኖር እንዲቻል ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ለዚህም ቢችል ከራሱ ብሔርና ሃይማኖት ውጪ ያለውን አቅፎ እንዲይዝና የሚያስፈልገውን ጉድለት የማሟላት ሥራ ቅድሚያ ተሰጥቶት መሠራት እንዳለበት ህዝቡ እንዲገነዘብ በመደረጉም ነው የህዝቡ የሰላምና የሥራ እሴት ተደምሮበት ሰላሙ ተጠብቆ የቆየው እናም ይሄው ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡
ከዚህ ባለፈ እንደ አገር አሁን ያለን ራዕይና እየተሠራ ያለው ሥራ፣ እየመጣ ያለው ለውጥም የሁሉም እንደሆነ አምኖ ድጋፍ ማድረግና አብሮም መቆም እንዳለበት ህዝቡን ስላስገነዘብን፤ ሕዝቡም የእኔ ነው ከሚል አንጻር ሥራውን እየሠራ ነው፡፡ የእስካሁኑ ውጤት የመጣበት አንዱ ምክንያትም የወደፊት እድገቱን ለማየት የሚጓጓ አዕምሮ እንዲፈጠር በመደረጉ ስለሆነ ይሄም በትኩረት ይሠራበታል፡፡
ከአጎራባች ወረዳዎች ጋር በቀጥታ የምንገናኝ ባይሆንም ከዞኑ ጋር ባለን የጋራ መድረክ እንወያያለን፤ መረጃ እየተለዋወጥንም በየመዋቅራችን እንሠራለን፤ ግብረ መልስም እንሰጣለን፡፡ ይሄው ተግባርም ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ ምክንያቱም ዙሪያው ሰላም ካልሆነ አዳማ ሰላም የላትም፡፡ አዳማም ሰላም ከሌላት አጎራባቹም ሰላም አይኖረውም፡፡
ለህዝባችንም መልዕክት አዲስ ባይሆንም፣ በማንኛውም ስፍራ ይሁን በማንኛውም ሁኔታ ሰላም ከሌለ ምንም እንደሌለ አምኖ ለሰላም ዘብ መቆም እንዳለበት፤ ከአቅሙ በላይ በሆነበትም ጥቆማ መስጠት እንዳለበት፤ ይሄንንም በሚያደርግበት ሰዓት ተጠቃሚው ራሱ ብቻ እንዳልሆነና ከእርሱ ጋር ሌላውም እንደሚጠቀም፤ እንደ አገርም ተጠቃሚ እንደምንሆንና ለሌላውም አስተማሪ መሆን እንደምንችል ሊረዳ እንደሚገባው ነው፡፡ እንደ እስካሁኑም ከጸጥታ ኃይሉ ጎን ሆኑ የሰላም ባለቤትነቱን ማረጋገጥ፤ ወንድማማችነቱን፣ መዋደዱ፣ መፋቀሩና መተሳሰቡም አብሮት መዝለቅ አለበት፡፡ አዳማ ለመኖሪያነት የሚመኟት እንጂ የሚጠሏት ከተማ መሆን ስለሌለባት ሁሉም ህዝብ ለእድገትና ሰላሟ በትጋት አለበት፡፡ በዚህ መልኩ ከቀጠልን የሚቀናባት ከተማ እንጂ የምትጠላ ከተማ አትሆንም፤ የሚል እምነት ነው ያለኝ፡፡
እኛም እንደ ጸጥታ መዋቅር ከወቅቱ ሁኔታዎች ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ነገሮች በመለየትና በምን ዙሪያ ትኩረት ሰጥተን መሥራት እንዳለብን አስቀድመን ለህዝቡ የማስጨበጥ ግዴታ አለብን፡፡ ባስጨበጥነው ነገር ላይም ህብረተሰቡን አሳትፈን እኛ ከፊት ሆነን ህዝቡን ከኋላችን አድርገን ተረባርበን ችግሮችን መግታትና ማስወገድ መቻል አለብን፡፡ ህዝቡም ከእኛ የሚፈልገውን ነገር እንዲነግረን፤ እኛም ከህዝቡ የምንፈልገውን ነገር ነግረን ተቻችሎ አብሮ መቀጠል የሚቻልበት ሁኔታ እንዲፈጠር ማድረግ አለብን የሚል አቋም ነው ያለን፡፡ ባለድርሻዎችም ይሄንኑ ተገንዝበው ኃላፊነታቸውን መወጣትና የድርሻቸውን ማበርከት ይኖርባቸዋል፡፡
በዚህ መልኩ ለመሥራትም እቅድ ያወጣን ሲሆን፤ በዘመቻ መልኩ ለአንድ ወር የአዳማ ከተማን ሰላም ሊነኩ የሚችሉ ነገሮችን እንዴት ማስወገድ አለብን በሚለው ዙሪያም ውይይት ተደርጓል፡፡ በዚሁ አግባብ በየደረጃው ለመሥራትም መግባባት ላይ በመደረሱ ሥራው የሚቀጥል እንጂ የሚቆም አይሆንም፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለቃለ ምልልስ ስለተባበሩኝ አመሰግናለሁ፡፡
አቶ ለማ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 13/2011
ወንድወሰን ሽመልስ