ትምህርት እና እውቀት የማይነጣጠሉ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው። ለዚህ ደግሞ ትምህርት ቤቶች የእውቀትና ትምህርት የጋራ ማቅረቢያ አውድና ማዕድ ሆነው ይገለጻሉ። ሆኖም እንዲህ እንደ አሁኑ አገርን ሳይሆን ዓለምን ያስጨነቀ፤ ከትምህርት ቤት ቀለም የተገኘ እውቀት የታገዘው ምርምር ብሎም የኢኮኖሚ አቅም ያልበገረው አስጨናቂ ሁነት ሲከሰት ከትምህርቱ ይልቅ ለጤና ቅድሚያ ሊሰጥ ግድ ይላል።
የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ ደግሞ በባህሪው አካላዊ መራራቅን የሚሻ ከመሆኑ አንጻር እውቀትና ትምህርት በትምህርት ቤት ሳይሆን በቤት ውስጥ ሊሆን የግድ ብሏል። እኛም በዛሬው እትማችን የተማሪዎችን ከቤት መዋል ተከትሎ ምን እየተሰራ ነው ስንል የኦሮሚያ ክልል ተሞክሮን ይዘን የቀረብን ሲሆን፤ መረጃውን ያደረሱንን የክልሉን ትምህርት ቢሮ ምክትል የቢሮ ኃላፊ አቶ ግርማ ባይሳ ሀሳብን በሚከተለው መልኩ ይዘን ቀርበናል።
በኦሮሚያ 10 ነጥብ 6 ሚሊዬን ተማሪዎች አሉ። የኮሮና መከሰትን ተከትሎ ደግሞ የእነዚህን ተማሪዎች ህይወት ለመታደግ ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል። በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ ውስጥ ምን መፍትሄ ሊገኝ ይችላል?፤ ምንስ መደረግ አለበት?፣ ተማሪዎች በቤታቸው በሚቆዩበት ጊዜ ከትምህርት እንዳይርቁ ምን መሰራት አለበት? በሚሉ ጉዳዮች ዙሪያ እንደ ኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ማኔጅመንት ውይይት በማድረግ የመፍትሄ ሀሳቦች ቀርበው አማራጮችም እንዲተገበሩ ተደርጓል።
ከእነዚህ መካከል የመጀመሪያው፣ አንድ ተማሪ ወደ ቤቱ ሲመለስ መደበኛ ትምህርት ተቋርጦ በመሆኑ በዚህ ሰዓት ያለው ቤተሰቡጋ እንደመሆኑ የትምህርት ማስታወሻ፣ መጽሃፍትና ሌሎችም አጋዥ የትምህርት ቁሳቁሶች በእጁ ላይ አሉ። ስለዚህ የመጀመሪያው ነገር ተማሪዎች እነዚህን መጽሃፍትና ማስታወሻ ደብተሮች ደጋግመው እንዲያነቡና እንዲገነዘቧቸው በወላጆቻቸው እንዲደገፉና እንዲያበረታቱ ማድረግ ነው። ሁለተኛው የመፍትሄ አቅጣጫ ደግሞ በክልሉ ባሉ ስድስት የትምህርት በሬዲዮ ማሰራጫ ጣቢያዎች ተጠቅሞ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ማድረግ ሲሆን፤ አሁን ላይ በግንባታ ላይ ካለ አንድ (የለገዳዲው) የማሰራጫ ጣቢያ በስተቀር አምስቱ ይሄንኑ በማድረግ ላይ ናቸው።
በዚህ ሂደትም ልክ በትምህርት ቤት እንዳሉ ሁሉ ትምህርት በሬዲዮ ሲሰጥ የወላጆች ልጆቹ ትምህርቱን እንዲከታተሉና ማስታወሻም እንዲይዙ ማገዝና መደገፍ ይጠበቅባቸዋል። የሬዲዮ ትምህርት ስርጭቱ መላውን ኦሮሚያ ያዳርሳል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፤ ከዚህ በተጓዳኝ ግን በከተማ አካባቢ ያሉ ተማሪዎች ትምህርት በሬዲዮ እንዲያገኙ በሶስተኛ አማራጭነት በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ተግባራዊ እንዲሆን ተደርጓል። ከዚህ በተጨማሪም ከዚህ በፊት ያልተሄደባቸው ነገር ግን አሁን ወደተግባር የተገባባቸው የሰባተኛ እና የስምንተኛ ክፍል ተማሪዎችን በኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትዎርክ(ኦ.ቢ.ኤን) ቀን ቀን ከሁለት እስከ አራት ሰዓት ባለው ጊዜ እንዲሰራጭ ፕሮዳክሽኑ ተሰርቶ ወደማስተማር ተገብቷል። ከዚህ በተጓዳኝም ከአምስተኛ እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል ላሉ ተማሪዎች የሚውል አጠር ያለ ነገር ግን የተለያዩ መልመጃዎችን የያዘ ሀንዳውት ለየግል እንዲያገለግል በሚያመች መልኩ ተዘጋጅቶ ተሰራጭቷል።
እነዚህ ሀንዳውቶችም በቢሮው ዌብ ሳይት እና የቴሌግራም አካውንት ላይ ተጭነው ለተማሪዎች ተደራሽ እንዲሆኑ ሆኗል። በየትምህርት ቤቶችም ተልከው መምህራን ወስደው እንዲዘጋጁበት እየተደረገ ይገኛል።
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ቀደም ሲል በምዕራብ ኦሮሚያ አይነት ስፍራዎች በነበረው የሰላም መደፍረስ ምክንያት በቁጥር የበዛ ባይሆንም መስተጓጎሎች በነበሩባቸው አከባቢዎችም ተመሳሳይ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆናቸው ታውቋል። ሆኖም ዋናው ጉዳይ የተማሪዎችን ጤና መታደግና ዜጎችን በህይወት ማቆየት እንደመሆኑ በተቀመጡ አቅጣጫዎች መሰረት መሄድ ከተቻለና ችግሩን መሻገር ሲቻል የማካካሻ ስራዎች የሚከናወኑበት ሂደት ታስቧል።
በመሆኑም ይህ አገራዊ ብቻ ሳይሆን ዓለምአቀፍ ችግር ሆኖ ያለውን ወረርሺኝ በዚህ መልኩ ተጋግዞና አማራጮችን ይዞ ማለፍ ከተቻለና በአጭር ጊዜ ተሻግሮ ወደ ትምህርት ገበታ መመለስ ከተቻለ፤ በዛን ወቅት ተማሪዎች፣ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም ቢሮው ከወላጆች ጋር በመሆን ተማሪዎች መጨበጥ ያለባቸው አንኳር ነጥብ ምንድን ነው በሚለው ነገር ላይ መስራት በሚቻልበት እድል ላይ እንደአቅጣጫ የተቀመጡ ጉዳዮች አሉ። ይህ ደግሞ አንድ ነገር ላይ ብቻ ትኩረት ተሰጥቶ የሚከናወን ነጠላ ተግባር ሳይሆን፤ በመምህራን ልማትና በአመራር ላይ መስራትን፤ ተማሪዎችን ነገ አድጋለሁ፤ እለወጣለሁ ብለው የሚያስቡበትን አቅም እንዲገነባ ማስቻልን፤ የወላጅ ተማሪ እንዲሁም የወላጅ ትምህርት ቤቶች ቁርኝትን ማጎልበት ጭምር የሚመለከት ነው።
ከግል ትምህርት ቤቶች ጋር በተያያዘም ከዚህ በፊት በተለይም ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ከቢሮው ጋር እየተሰራበት ያለ የጋራ አሰራር አለ። ምክንያቱም በእነዚህ ትምህርት ያሉት ተማሪዎችም የህብረተሰቡ ልጆች የሆኑ ታዳጊዎችና የነገ አገር ተስፋዎች ናቸው። እንደ ኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮም እነዚህን የግል ትምህርት ቤቶች እንደ ቢዝነስ ተቋም ሳይሆን ሰፊ ህዝብ ይዘው ስላሉም ጭምር እንደ አጋርና አጋዥ ነው አብሮ እየሰራ ያለው። ለዚህም ነው የግል ትምህርት መስኩ በምን ማዕቀፍ ሊመራ በምን ድጋፍስ ሊሰራ ይገባል በሚለው ላይ የጋራ ሰነድ ተዘጋጅቶ ወደስራ እንዲገባ እና በዛው መሰረት እንዲተገበር እየሆነ ያለው። ለዚህ ደግሞ የግል ትምህርት ቤቶችንና ወላጅ ማህበራትን በማቋቋም እየተሰራ ነው።
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ አሁን ላይ እንደ አገር ባለው ችግር ምክንያትም ከግል ትምህርት ቤቶች ጋር ሊኖር የሚችለውን ክፍተት ለማገዝ እየተሰራ ሲሆን፤ በአንድ በኩል ወላጆች ከፍለው የሚያስተምሩ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ትምህርት ቤቶች በወረርሽኙ ምክንያት ተዘግተው የሚገኙ ከመሆናቸው አኳያ ሂደቱ ላይ ጫና ፈጥሮ ነበር። ምክንያቱም ትምህርት ከሌለና ወላጅ ካልከፈለ ትምህርት ቤቶች ለቤት ኪራይም ሆነ ለመምህራንና ስታፍ ሰራተኞድ ደመወዝ መክፈል አይችሉም፤ ወላጅ ደግሞ ልጁ በቤት እያለ ለምን እከፍላለው ይላል። በመሆኑም አሁን ያለውን ፈታኝ ጊዜና ሁኔታ ከግምት በማስገባት እና በአገር አቀፍ ደረጃ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመወያየት በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ስምምነት የተቀመጠውን አቅጣጫ ማዕከል በማድረግ ችግሩን ለማቃለል እየተሰራ ይገኛል።
አንደኛው፣ የግል ትምህርት ቤቶች ኖት/ማስታወሻዎችን በማዘጋጀት፣ ሌሎች የኤሌክትሮኒክስ አማራጮችን በመጠቀም በማህበራዊ ሚዲያዎች ጭምር በሶፍት ኮፒ ታግዞ ለተማሪዎች የሚያደርስበትን መንገድ እንዲከተሉ፤ ተማሪዎችም ይሄንን ወስደው የሚጠቀሙበት ሁኔታ እንዲመቻች ተደርጓል። ትምህርት ቤቶችም ካለው አገራዊ ችግር አኳያ መምህራንንም ሆነ ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞችን እንዳይቀንሱ እንደ አቅጣጫ በማስቀመጥ፤ ስራቸውን በኪራይ ቤት ለሚያከናውኑ ትምህርት ቤቶችም ከአከራዮቻቸው ጋር በመነጋገር እንዲቀንሱላቸው ወይም እንዲተውላቸው በማድረግ፤ ወላጆችም እንደ ትምህርት ቤቶቹ ሁኔታና አቅም ከ50 እስከ 75 በመቶ ክፍያ ከወላጅ ኮሚቴ ጋር በመነጋገር እንዲከፍሉ በማድረግ ወላጅ የድርሻውን እንዲወጣ የማስቻል እርምጃዎች እየተወሰዱ ይገኛል።
እንደ አጠቃላይ ሲታይ እንደ ክልልም ሆነ አገር ባለው ሂደት ሙሉ በሙሉ ከዚህ ችግር እንወጣለን የሚል እምነት ተይዞ እየተሰራ እንደመሆኑ፤ ፈጣሪ ፈቅዶ እነዚህ ተማሪዎች በአጭር ጊዜ ወደ ትምህርት ቤት የሚመለሱ ከሆነ በየትምህርት ቤቱ የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህርና ምክትር ርዕሰ መምህር ትምህርት ቤቱ ውስጥ ቆይተው ዝግጅት እንዲያደርጉ እና ሌሎች የሚያስፈልጉ ስራዎችን እንዲያከናውኑ እየተደረገ ይገኛል። በየደረጃው ባሉ ትምህርት ጽህፈት ቤቶችም የተወሰኑ ሰዎች ቀርተው ሂደቶችን እንዲያመቻቹና እንዲያሳልጡ እየተሰራ ነው።
አዲስ ዘመን ግንቦት 7/2012
ወንድወሰን ሽመልስ