የአማራና የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድሮች ከትናንት በስቲያ በምስለ መስኮት ብቅ ብለው በሁለቱ ክልሎች መካከል ያሉት ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ እንደሚፈቱ ቃል ገብተዋል፡፡ ለሰላሙ ሲደክሙ የነበሩ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም ጉዳዩ በዋናነት ይመለከታቸዋል ተብለው የተጋበዙት አቶ ገዱ አንዳርጋቸውና ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ላይ የሰላም ተስፋ ያጫረው ፈገግታ ተንጸባርቋል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብም በተፈጠረው የሰላም ተስፋ የደስታው ተካፋይ እንደሚሆን እሙን ነው፡፡
‹‹በአማራና በትግራይ ክልሎች መካከል ያሉ የተለያዩ ጥያቄዎች ጥይት ሳይተኮስ በጠረጴዛ ዙሪያ በውይይት እንፈታዋለን፡፡ ይህንንም ለማድረግ በፈጣሪና በምንመራው ህዝብ ፊት ቃል እንገባለን›› በማለት ለሰላም ያላቸውን ቁርጠኝነት በወቅቱ መግለጻቸውን የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ምክትል ሰብሳቢ ፓስተር ዳንኤል ገብረስላሴ ይናገራሉ፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ 97 በመቶው አማኝ መሆኑን ያነሱት ፓስተር ዳንኤል የሁለቱ ክልሎች መሪዎች 97 በመቶ ውክልና ባለው የሃይማኖት አባቶች ፊት ቀርበው ህዝባችንን በሰላም ነው የምንመራው፤ ወደ ጦርነት መክተት አንፈልግም ማለታቸውን በመግለጽ ህዝቡም መሪዎቹን ማድመጥ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ የፖለቲካ መፍትሄ የሚፈልጉ ጉዳዮች በፖለቲካ፤ በሀገር ሽማግሌ የሚፈታው በሀገር ሽማግሌ፤ በምሁራን የሚፈቱ ችግሮች በምሁራን እንዲፈቱ ከስምምነት ተደርሷል፤ ይህም ትልቅ ስኬት ነው ብለዋል ፓስተር ዳንኤል፡፡
እንደ ፓስተር ዳንኤል ማብራሪያ አሁን ሀገሪቱን በልማትና በዴሞክራሲ ማሳደግ እንጂ እንደገና ወደኋላ በመመለስ ወደ ውጊያ እንድትገባ ማድረግ አይገባም፡፡ ችግሮችን በመቋቋም የተጀመረው ልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ መሬት እንዲረግጥ ሰላሟ የተጠበቀና ዴሞክራሲ ያበበባት፤ ከሌሎች ካደጉ ሀገራት ጋር ተወዳዳሪ የሆነች ራሷን የቻለች ሀገር ለማድረግ ሰላም አስፈላጊ ነው፡፡በመሆኑም ህዝቡ የመሪዎቹን ጥሪ መቀበል ችግሮች የሚፈቱት በጦርነት፣ በመወቃቀስ አለመሆኑን በማወቅ ለሰላም መረባረብ አለበት፡፡
‹‹የሰላም ባለቤት ህዝቡ ነው፡፡ ለባለቤት ይህን አድርግ አይባልም፡፡ ባለቤቱ ለሌላው ነው ማስተማር ያለበት›› ያሉት ፓስተር ዳንኤል፤ ልጆቹ ተምረውለት ለፍሬ የሚበቁት፤ አግብተው መውለድ የሚችሉት እንዲሁም የወለዱትን መዳር የሚችሉት ሀገር ሲኖር ነው፡፡ ስለዚህ ህዝቡ ለቀዬው ሰላም አምባሳደር ነኝ ብሎ ራሱን ለሰላም ማስገዛት አለበት ብለዋል፡፡
ወደ ሀገሪቱ የተጋዘው የጦር መሳሪያ በምንም አይነት ተዓምር ወንድም ወንድሙን ለማጥፋት ሊጠቀምበት እንደማይገባ የተናገሩት ፓስተር ዳንኤል፤ በሁለቱም ወገኖች መካከል ፀብ እንዲጫር በማድረግ ሆድ እያስባሱ ወደ ጦርነት ለመክተት የሚፈልጉ ህዝቦችን ጦርነት ውስጥ ከተው ጥቅም ለማግኘት የሚፈልጉ እኩይ አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች መኖራቸውን አንስተዋል፡፡ እነዚህ ቅስቀሳዎች በፍጹም ለኢትዮጵያ የማያስፈልጉ፣ የማይጠቅሙና ኋላ ቀር ናቸው፡፡ ይህን የሚፈጽሙ አካላት ከድርጊታቸው ተቆጥበው የሰላም መንገድ እንዲያዩ ፈጣሪ እንዲረዳቸው ጸሎት መደረጉንም ተናግረዋል፡፡
እንደ ፓስተር ዳንኤል ማብራሪያ፤ በሁለቱ ክልሎች መካከል እየተነሱ ያሉት የፖለቲካ፣ የህግ የበላይነት፣ የአስተዳደር ወሰን ጉዳዮች ናቸው፡፡ እነዚህ ችግሮች ዓመታት ያስቆጠሩ ናቸው፡፡ በአንድ ማግስት አይፈቱም፡፡ ችግሮቹ በምን መልኩ መፈታት አለባቸው የሚለውን ቁጭ ብሎ መነጋገርን ይጠይቃል፡፡ ተረጋግቶ መስራት የሚፈልግ በመሆኑ ሁለቱ ክልሎች ተቀራርበው ቀን ከሌሊት መስራት አለባቸው፡፡
ከሀገር ሽማግሌዎች መካከል አንዱ የሆነው አትሌት ሸለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ በበኩሉ አለመግባባቶች በሰላማዊ መንገድ ብቻ መፈታት እንዳለባቸው ሁለቱ ርዕሳነ መስተዳድሮች መግለጻቸውን በማስታወስ የሁለቱ ክልሎች ወንድማማች ህዝብ የመሪዎቹን ሀሳብ ተቀብሎ ሊተገብር ይገባል፡፡ የሁለቱ ክልሎች መሪዎች ባሳዩት አቅጣጫ መሰረት ህዝቡ ለሰላሙ መረባረብ መጀመር አለበት፡፡ ከዚህ በኋላ ለሁለቱ ክልሎች፤ ብሎም ለሀገር ሰላም ተግዳሮት የሆኑ እንቅፋቶችን በጋራ እያስወገዱ መሄድ ያስፈልጋል፡፡ ጥላቻን ማስወገድና የጦርነት ቅስቀሳዎች ማስወገድ የህዝቡ ፋንታ ነው ብሏል፡፡
እንደ ሻለቃ ኃይሌ ማብራሪያ ሁለቱን መሪዎች በአንድ ላይ እንዲወያዩ ለመጥራት ሲታሰብ ፍራቻ ነበር፡፡ በማህበራዊ ሚዲያዎች ሲለቀቁ የነበሩ አሉታዊ መረጃዎች የስጋቱ ምክንያት ሲሆን፤ ሁለቱ መሪዎች ሲገናኙ የታየው ነገር ግን ሲወራ ከነበረው የተገላቢጦሽ ነው፡፡ ሁለቱ መካከል የነበረው መከባበር እጅግ የሚያስደስት ነበር፡፡ አንዱ ሌላውን በትህትና ሲያስቀድም ታይቷል፡፡ ይህ መከባበር በመገናኛ ብዙሃን ፊት ሲቀርቡ ያሳዩት ብቻ ሳይሆን ሚዲያው በሌለበትም ተንጸባርቋል፡፡ ይህም አሸማጋዮችንም ሆነ መላውን ህዝብ የሚያስደስት ነው፡፡
‹‹ህዝብን ከህዝብ ጋር ለማጋጨትና ሀገርን ለመበጥበጥ ጥቂት ግለሰቦች በቂ ናቸው ያለው›› ሻለቃ ኃይሌ፤ እነዚህን ጥቂቶች ህዝቡ በንቃት እየተከላከለ በማጋለጥና ለህግ እንዲቀርቡ በማድረግ የሰላም ትሩፋቶች ተጠቃሚ ለመሆን መስራት አለበት፡፡ ህዝቦቹ ለሺህ ዓመታት የዘለቀ የታሪክ፣ የባህልና የሃይማኖት ትስስር ያላቸው ናቸው፡፡ በመሆኑም ፖለቲከኞቹ የሚፈጥሩትን አሉታዊ ሃሳቦች መወሰድ ትተው የጋራ እሴታቸውን ሊያስቡ ይገባል፡፡
የሁለቱ ክልሎች አዝማሚያ በጥሩ አቅጣጫ ላይ አለመሆኑ እየታየ በመምጣቱና የሁለቱ ክልሎች መሪዎች ለውይይት ፈቃደኛ በመሆናቸው ሽምግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች የሁለቱን ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮችን ማወያየቱን የተናገረው አትሌት ሻለቃ ኃይሌ፤ ችግሮች ግን በመላው ኢትዮጵያ ውስጥ መኖራቸውን አንስቷል፡፡ የተላለፈው መልዕክት በሁሉም ክልሎች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሊተገብሩት የሚገባ ነው፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ለሰላም ዘብ ሊቆሙ ይገባል፡፡
‹‹የፖለቲካውን መጠላለፍ በመተው ኢኮኖሚውን ተረባርቦ ማሳደግ ያስፈልጋል፡፡ የፖለቲካውን ጉዳይ ጋብ በማድረግ ሁሉም ኢኮኖሚው ላይ ሊያተኩር ይገባል፡፡ ኢኮኖሚው ላይ ትኩረት ካልተደረገ ማንም ሊፈታው የማይችል ችግር ሊፈጠር ይችላል›› ያለው ሻለቃ ኃይሌ፤ ይህ የመኖርና የመሞት ጉዳይ መሆኑን አሳስቧል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 9/2011
በመላኩ ኤሮሴ