ባለፈው ሳምንት በተጠናቀቀው እአአ 2018 የዓለምን ከራሞት ለማየት ሙከራ አድርገን ነበር፡፡ በተደረገው ዳሰሳም ዓበይት ሁነቶችን በተለይም በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና ማህበራዊ ዘርፎች የተከናወኑ ተግባራትን ለማየት ሞከረናል።
በተደረገው በዚያ ምጥን ምልከታ፣ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን እንደዓለም አካልነቷ አፍሪካንም ገረፍ አድርገን አልፈናል። በዚህ ጽሑፍ ደግሞ እራሷን አስችለን እናያለን።
በአፍሪካ በተጠናቀቀው ዓመት /2018/ ቀደም ሲል የዓለምን ሁኔታ በዳሰስንባቸው ዘርፎች ምን ምን ሁነቶች ተከናወኑ? ምን ምን ጥፋት፣ ልማቶችስ ተስተዋሉ ምንስ ታቅዶ ምን ተሠራ፣ ምንስ ቀረ 2018 ለ2019 ምን አስተላለፈ? 2019ስ ከ2018 ምን ተረከበ? የሚሉትን አለፍ አለፍ እያልን እንመለከታለን። ከዛ በፊት ግን አፍሪካ ማን ናት? የሚለውን ነካ አድርገን እንለፍ።
አፍሪካ ማን ናት?
አፍሪካ በቆዳና በሕዝብ ብዛቷ ከዓለም በሁለተኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ ከሰባቱ አህጉራት አንዷ የሆነች ከሌሎች አህጉራት በተሻለ ተመራጭ የአየር ንብረት ባለቤት፣ ብዝሀነትን የታደለች ከ1 ሺህ 500 በላይ ቋንቋዎች የሚነገሩባት፤ በተፈጥሮ ሀብት እጅግ የበለፀገች 54 አገራትን በቤተሰብነት የያዘች አህጉር ነች። ይህ ብቻ አይደለም፤ ሌሎች ሊጠቀሱ የሚገባቸው በርካታ ፀጋዎችና ከቀረው ዓለም የሚለዩዋት ታሪክና ቅርሶች ያሏት አህጉርም ናት አፍሪካ፤ ጉዳያችን ይህ ስላልሆነ ለጊዜው እንለፈው።
አፍሪካ በዓለም መገናኛ ብዙሃን
የአሜሪካው ሲኤንኤን የቴሌቪዥን ጣቢያ የ2018ን መጠናቀቅና የ2019ን መግባት አስመልከቶ አንድ ፕሮግራም ሠርቶ ነበር። ጣቢያው አበይት ያላቸውን አሥር ጉዳዮች ወሰዶ በመረጃ በማስደገፍ ለተመልካቾቹ ያቀረበ ሲሆን፤ የግምገማ ዕይታው ካነጣጠረባቸው መካከል መሠረተ ልማት ናይጄሪያን፣ ኢትዮጵያን፣ ግብፅን፣ ቱኒዚያንና ዩጋንዳን በማስቀደም ምርጫ ግብፅ፣ ዚምባብዌ፣ ሴራሊዮን፣ ማሊን ቢዝነስ በግብፅ ካይሮ በ20 ሚሊዮን ዶላር መዋዕለ ንዋይ ሊገነባ የታሰበውና ውዝግብ ያስነሳው የታክሲ አገልግሎት፤ የአፍሪካ ህብረትን ይሁንታ አግኝቶ ተግባራዊ ለመሆን የተቃረበው ነፃ የንግድ ቀጣና የአህጉር አቀፍ (CFTA) ስምምነት ረቂቅ፤ ጦርነትና የእርስበርስ ግጭቶች ደቡብ ሱዳን ሶማሊያ እና ሌሎች ሁነቶች ይገኙበታል።
ዘገባው ከላይ የጠቀስናቸውን ሁነቶች በመልካም ክንውንነታቸው በማሳያነት ያንሳ እንጂ አብዛኛው ትርክቱ ወቀሳ አዘል ነው። ወቀሳውንም ከእርስበርስ ግጭት፣ መልካም አስተዳደር እጦት፣ የከፍተኛ አመራሮች ፀረ-ሕገመንግሥት ተግባራት ሙስና አምባገነንነት … ጋር በማያያዝ የተነተነ ሲሆን፤ እነዚህ ሁሉ ሊወገዱና የሕዝቦች ኑሮ ሊሻሻል እንደሚገባ ይመክራል።
የምድርን ገፅታ (Surface area) ስድስት በመቶ፤ የመሬትን (Land area) 20 በመቶ፤ የዓለምን ሕዝብ 15 በመቶ የያዘችው አፍሪካ ከጥንካሬዋ በናረ በድክመቷ ስትጠቀስ መስማት እንግዳ አይደለም። በተለይ በድህነት፣ በረሀብና በዲሞክራሲ እጦት።
« አፈር ይዞ ውስጡ አረንጓዴ፣
ለምን ይሆን የራበው ሆዴ»
የሚለውን የከያኒ ግጥም እዚህ መተንተኑ ብዙም አይጠቅምምና የድህነትና የረሀቡን ጉዳይ በዚሁ እንለፈው።
አፍሪካና እድገት
የዓለም ባንክና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እንደሚገልፁት፤ አፍሪካ በተለይ ከ2000 ወዲህ ከ1970 እና 80ዎቹ በተሻለ ደረጃ እያደገችና ኢኮኖሚያዊ እየተነቃቃ ይገኛል፡፡ የቱርክ መንግሥት የቻይና ኩባንያዎችን ከመገዳደር አንፃር ከአፍሪካ ብቸኛና ቀዳሚ መሆኑ፤ ካሜሩንና ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የመሳሰሉ አገራት የኢንተርኔት አገልግሎት በመዝጋት ዜጎችን መረጃ እንዳያገኙ ማድረጋቸውና አፍሪካ ከ2015 ጀምሮ የኢንተርኔት አገልግሎት በመዝጋቷ ምክንያት 237 ሚሊዮን ብር እያጣች መሆኗ፤ ሊያባራ ያልቻለው የማሊ ጀሃድስቶች ጦርነት፤ የደቡብ ሱዳንንና የሶማሊያዊንን ግጭት … ሁሉ አፍሪካን በተመለከተ ከፍተኛ የሚዲያ ሽፋን የተሰጣቸው ርዕሰ ጉዳዮች ሆነው አልፈዋል፡፡
ቀደም ሲል የጠቀስነው የሲኤንኤ ፕሮግራም ትኩረት ሰጥቶ የዘገበው ቢኖር፤ በአፍሪካ ፈጣን እድገት እያስመዘገቡ ያሉ አገራትን በደረጃ (TOP TEN) ማስቀመጥ ሲሆን፤ ጋና በ8.3 በመቶ፣ ኢትዮጵያ በ8.2 በመቶ አማካይ እድገት በማስመዝገባቸው 1ኛ እና 2ኛ ሲያስቀምጥ ፤ ደቡብ አፍሪካ ፣ ናይጀሪያ፣ አንጎላ በዓመቱ ኢኮኖሚያቸው ከቀደመው ዓመት ጋራ ሲወዳደር እየቀዘቀዘ መምጣቱንም አብራርቷል፡፡
የቴሌቪዥን ጣቢያው ኢትዮጵያን አስመልክቶ ያስመዘገበችው እድገት በአማካይ 8.2 መሆኑን ይግለጽ እንጂ፤ የዓለም ባንክና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት በአማካይ በየዓመቱ 10 በመቶ እያደገ መሆኑን መጥቀሳቸውን እዚህ ጋ ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡ ከወቀሳው ጎን ለጎን አፍሪካ በተለያዩ ሚዲያዎች ስትወደስባቸው የቆየችው ቀደም ሲል እንደጠቀስነው የኢኮኖሚ መነቃቃት እያሳየች መሆኗ ነው፡፡ የዓለም ባንክ እንዳስታወቀው እና የተለያዩ ሚዲያዎች በስፋት እንዳስደመጡት በ2018 የአፍሪካ ኢኮኖሚ 3.2 በመቶ እድገት ያሳየ ሲሆን፤ ይህም በ2019 ወደ 3.5 በመቶ ከፍ በማለት እድገቱ እንደሚቀጥል ተንብየዋል፡፡
ድህነት ቅነሳ
የአፍሪካ ኢኮኖሚም በመነቃቃት ላይ ይሁን እንጂ አህጉሪቷ ከነበሩባት ችግሮች ተላቅቃ ማየት አልተቻለም። በአፍሪካ ድህነት ሲቀንስ ማየት አልተቻለም፡፡ የምግብ አቅርቦት የበለጠ እየጠፋና ልመናው እየናረ ነው። የሥራ አጡ ቁጥር ሰማይ ደርሷል። የሥራ ዕድል ጉዳይ የህልም እንጀራ የሆነባት አፍሪካ ለወጣቶቿ የዘረጋችላቸው እጅ የላትም፡፡ እያንዳንዱ አፍሪካዊ ከአጠቃላይ አህጉራዊ የነፍስ ወከፍ ገቢው ከ900 ዶላር በላይ በሙስናና ለሙሰኞች ይተገብራል። የዓለምን 20 በመቶ ወጣት የያዘችው አፍሪካ፤ ዓለምን ሊምግብ የሚችል የተፈጥሮ ሀብት ያላት ለምለሚቱ አፍሪካ በመረዳትና በመበደር ተወ ዳዳሪ ልታገኝ አልቻለ ችም።
ስለዚህ በ”Economic performacne and outlook 2018″ ላይ በዝርዝርና በግልፅ እንደተቀ መጠው አፍሪካ መዋቅራዊ ሽግግር እና የፖሊሲ አቅጣጫ ለውጥ የግድና በአስቸኳይ ያስፈል ጋታል። ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልን ማስፈን፤ ሰብአዊ መብትን ማክበር፤ ከርስ በርስ ግጭትና ትርጉም የሌለው ጦርነት በአስቸኳይ መወ ጣት፤… ከአፍሪካ ይጠበቃል፡፡
አፍሪካዊ ወንድማማችነት
አፍሪካ በ2019 የድንበር ውዝግቦች፤ የይገባኛል/ አይገባህም ንትርኮች፤ የሥል ጣን ልቀቅ/አልለቅም ጭቅ ጭቆች … እንዲቆሙ የእው ነተኛ አፍሪካ ወዳጆችም ሆኑ ሌሎች ወገኖች ጥልቅ ምኞች ነው። በቅኝ ግዛት ዘመን ባረጁና ባፈጁ ሕጐች የተተበተበውን የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም ህግ በጣጥሳ የምትወጣበትና የራሷን ሀብት ሙሉ ለሙሉ የምትጠቅምበት ዘመን እንዲሆነ የሚመኙ አፍቃሬ አፍሪካ ወገኖች ቀላል አይደሉም። ይህ እንደሚሳካም የብዙዎች እምነት ነው፡፡ በ2019 “Scrabbling of Africa” ን ሊቀራመቷት ያስቡ የነበሩ ወገኖችን አስተሳሰብ ነቅላ ጥላ በአፍሪካዊ ወንድማማችነት ላይ የተመሠረተ አንድነትን የምታስተናግድ አፍሪካን ማየት የበርካቶች ፍላጐት ነው፡፡ በ2019 ከአፍሪካ ህብረትም ሆነ መሰል ተቋማት የሚመጡ ውሳኔዎችና ደንቦች የሁልጊዜ መልዕክትም ይኼውና ይኼው ነው።
አዲስ ዘመን ጥር 8/2011
ግርማ መንግሥቴ