ዓለም ከሰው ወደ ሰው ተላልፎ የሞት መቅሰፍት የሚያመጣ በሽታ ገጥሟታል። ስልጣኔ፣ የጦር መሳሪያ ብዛትና የገንዘብ አቅም ሊገድበው አልቻለም። አሁን ሁሉም በአንድነት ስለ አንድ ጉዳይ ብቻ የሚያስቡበት ወቅት ላይ ደርሰናል። ተመራማሪውም ሆነ ተራው ዜጋ እኩል ወደሚያምነው አምላክ አንጋጦ ምህረት የሚለምንበት ወቅት ላይ አንገኛለን። ጊዜው እጅግ ከባድ ነው።
ሌላው ዋነኛ አማራጭ ደግሞ የህክምና ባለሙያዎች የሚሰጡትን ምክር መቀበል ነው። ከዚህ ውስጥ አንዱ በተቻለ መጠን በቤት ውስጥ መቆየት ነው። ነገር ግን በብዛት የምንመለከተው ከዚህ በተቃራኒ ነው። ዜጎች ወደ ሞት እግራቸውን ሲሰዱ። የተከለከልነው ሁሉ የሚጠቅም ይመስል ወደ ውጪ ለመውጣት ጉጉታችን ይበልጥ ጨምሯል። ነገሩ ግን በተቃራኒው ነው። አእምሯችን እደጅ ያለው ንፁህ አየር፣ ነፃነትና ደስታ እንዳለ ቢነግረንም ቅሉ እውነታው ግን ወደ ሞት የሚወስድ ሰፊ መንገድ ብቻ ነው ያለው። እስቲ ይሄን ጉዳይ በሚገባ የሚያስረዳን ታሪክ እንመልከት። ከሁሉ በፊት ግን ለራሳችን እንዲህ እንበለው ‹‹የሚያንፀባርቅ ሁሉ ወርቅ አይደለም፤ የተከለከልነው በምክንያት ነው፡፡››
ሃና በሰፊ ደን እና በተለያየ እፅዋቶች በተከበበ መንደር ውስጥ ከቤተሰቦቿ ጋር ትኖራለች። የአምስት ዓመቷ ህጻን ለአባት እና እናቷ ብቸኛ ልጅ ነች። ቤተሰቦቿ ብዙ ገንዘብ ያላቸው ባለፀጎች ባይሆኑም በደስታ አንድ ላይ ይኖራሉ። እነ ሃና የሚኖሩበት መንደር በጣም ደስ የሚል ነው። በትላልቅ እና ውብ በሆኑ ደኖች ከመከበቡ በተጨማሪ አካባቢውን አልፎ የሚሄድ ንፁህ የወንዝ ውሃ አለ። ከቤታቸው ፊት ለፊትም አንድ ትልቅ ተራራ ይገኛል። አካባቢው በተፈጥሮ ውብ መሆኑን ለቤተሰቡ አኗኗር ምቹ ነው።
የቤተሰቡ መኖሪያ ቤት በእንጨት የተሰራ ሲሆን ባለ አንድ መኝታ ቤት ነው። ሃና ቤቷን አትወደውም። ምክንያቱም በጣም ትንሽ እና ንፁህ ያልሆነ ይመስላታል። ከፊት ለፊታቸው ባለው ተራራ ላይ አንድ ትልቅ እና የካስትል ቅርፅ ያለው ቤት አለ። መስኮቱም የወርቅ ቀለም ያለው እና አንፀባራቂ ነው። ከርቀት ስታየው ቤቱ በጣም ደስ ይላታል። በዚህ የተነሳ የሯሷን ቤት ጠልታ በተራራው ላይ የሚገኘውን ቤት በጣም ወደደችው። ዳገታማ ስፍራ ላይ የተሰራውን ቤት ግን ሃና ሄዳ እንድታየው አይፈቅዱላትም። ምክንያቱም በጣም ትንሽ ልጅ በመሆኗ ወደዛ ስፍራ ብቻዋን መሄድ ስለማትችል ነው። ከምንም ነገር በላይ ደግሞ ከቤቱ የወደደችው የወርቅ ቀለም ያለውን መስኮት ነው። ከተራራው ጫፍ ላይ የሚያንፀባርቀው መስኮት ቤቱ የራሴ ቢሆን የሚል ምኞት አሳድሮባታል።
በተደጋጋሚ ጊዜ በቤታቸው ጊቢ ውስጥ ስትቀመጥ ተራራው ላይ ያለውን ቤት ትመለከታለች። በዚህ የተነሳም የቤተሰቦቿን ቤት ይበልጥ እየጠላችው መጣች። ምንም እንኳን እያደር የጥላቻ ስሜቷ እየጨመረ ቢመጣም ቤተሰቦቿ በምን አይነት ሁኔታ ውስጥ እንዳሉ ብሎም ፍላጎቷን ማሟላት እንደማይችሉ ስለምታውቅ ሁሉንም ነገር ተቀብላ ዝምታን መረጠች።
ጊዜው በፍጥነት ይጓዛል። ሃናም በቶሎ አደገች። እድሜዋም 12 ዓመት ደረሰ። ልክ እንደ ንግስት በጣም የምታምር ልጅ ሆነች። አስተሳሰቧም እየተቀየረ መጣ። «አሁን እኔ አድጌያለሁ። ቆንጆ ልጅም ሆኛለሁ። በዚህ አሮጌ ቤት ውስጥ መኖር የለብኝም። እኔ መኖር ያለብኝ የሚያንፀባርቅ እና የወርቅ መስኮት ያለው ቤት ውስጥ ነው» ስትል ለራሷ ማሰብ ጀመረች።
የሃና እናት ልጇ እያደገች በመምጣቷ በአካባቢዋ ዞር ዞር እያለች እንደትጫወት እየፈቀደችላት መጣች። ከእለታት በአንዱ የእረፍት ቀን ሀና በመንደሯ ውስጥ ተዟዙራ መጫወት ፈለገች። እናቷንም አስፈቀደቻት። እንደሁል ጊዜው ሩቅ ቦታ እንዳትሄድ እና እራሷን ለጉዳት እንዳታጋልጥ አስጠንቅቃት እንድትጫወት ፈቀደችላት።
በቤቷ አቅራቢያ ጥቂት ስትጫወት ቆየች። ያለችበት ቦታ ብዙም አላስደስት አላት። ቀና ስትል ተራራው ላይ ያለውን እና የሁል ጊዜ ፍላጎቷ የሆነውን «የካስትል» ቤት ተመለከተች። ወደዚያ ስፍራ ለመሄድ ፈለገች። ነገር ግን እናቷ ርቀሽ እንዳትሄጂ የሚል ማስጠንቀቂያ ሰጥታታለች። ትንሽ ጊዜ በሃሳቧ «ልሂድ ወይስ አልሂድ» የሚለውን ስታውጠነጥን ቆይታ ፈራ ተባ እያለች ወደ ስፍራው ለመሄድ ወሰነች። በግቢ እና በቅርብ አካባቢ ላይ በምትጠቀምበት ብስክሌት ወደ ተራራው ቀረበች። ተራራው ላይ እንደደረሰችም ወደ ከፍታው የሚያስወጣ አንድ ጠባብ መንገድ አገኘች። በመንገዱ ዳር ዳርም ትላልቅ ዛፎች አሉ። ብስክሌቷን በእጇ እየገፋች ወደ ተራራው ጫፍ መውጣቷን ቀጠለች። በብዙ ትግል እና ጥረት ከተራራው ጫፍ ላይ ደረሰች። ከላይ ያለው የተራራው ክፍል ሜዳማ ነው። ከፊት ለፊቷ ከዚህ ቀደም ከርቀት ትመለከተው የነበረው ቤት አለ።
በመጨረሻ ቤቱን ማየት ብትችልም ያልጠበቀችው እና በጣም የሚያስደነግጥ ነገር ነበር የገጠማት። በቦታው ስትደርስ ቤቱ ፍፁም ከዚህ ቀደም ከርቀት ስትመለከተው የነበረ አይደለም። በጣም የሚያስጠላ እና በቆሻሻ የተሞላ ነበር። መስኮቱም ቢሆን ከርቀት እንደምታየው ወርቃማ አልነበረም። ጭራሽ ለማየት ብዙም የሚማርክ አልነበረም። ጥቁር መስኮት ነበር። በተመለከተችው ነገር ተገረመች። ከዚህ ቀደም ታስበው በነበረው ነገር አፈረች። መስኮቱ ወርቃማ መስሎ ይታያት የነበረው ከተራራው ስር ያለው ወንዝ ላይ የሚያርፈው ፀሀይ ነፀብራቅ ነበር። ሁኔታው ከዚህ ቀደም የማታውቀው አይነት ስሜት ፈጠረባት።
በዝምታ ከቤቱ ፊት ለፊት ባለው ሜዳ ላይ ተቀመጠች። ጉጉቷ እና በዚህ ቤት ውስጥ የመኖር ፍላጎቷ ብን ብሎ ጠፋ። ከተራራው ላይ ሆና ወደ ቤቷ ተመለከተች። መስኮቱ ልክ እንደ ወርቅ ያንፀባርቃል። ፈገግ ብላ በአካባቢያቸው ያለው ወንዝ ላይ የወጣው ፀሀይ መስኮቱ እንደወርቅ እንዲያንፀባርቅ እንዳደረገው አሰበች። ያ ማለት ሃና እስካሁን መኖር የምትፈልግበት አይነት ቤት እየኖረች መሆኑ ገባት። ከዚህም ሌላ ትጠላው የነበረው ቤቷ ምን ያክል ውብ እንደሆነ ተገነዘበች። እስካሁን ድረስም የተሳሳተችው ተራራ ላይ ያለውን ቤት ከርቀት ብቻ አይታ እንደሚያምር በማሰቧ ነበር። በመገረም ስሜትም ብስክሌቷን ካስቀመጠችበት ቦታ አንስታ ወደ ቤቷ ሄደች። ለራሷ እንዲህ ስትል ተናገረች «የሚያንፀባርቅ ነገር ሁላ ወርቅ አይደለም፤ የተከለከልኩትም በምክነያት ነው›› ስትል። አሁንም ርቀታችሁን ጠብቁ፣ ሰዎች በሚበዙበት ቦታ አትገኙ ፣ አትጨባበጡ፣… የተባለው በምክንያት ነው። ባህሉ፣ ልማዱ፣ ማህበራዊ ግንኙነቱ ሁሉ ዛሬ እንደ ወርቁ አብርቶ ብናየው የሚጠቅመን ወርቅ አይደለምና እናቆየው። የምንጠላውን አካላዊ መራራቅ ወደን ወገን ዘመዶቻችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ። መቀራረቡ ለከርሞ ይቆየን።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 18/2012
በጋዜጣው ሪፖርተር