ሐሙስ ነሐሴ 21 ቀን 1962 ዓ.ም የታተመው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ከሆድ ቁርጠት ህመም አድናለሁ በሚል የ 20 ዓመት ወጣትን በጥይት ስለገደለ ሰው ተከታዩን ዘገባ አስነብቦ ነበር።
የሆድ ቁርጠት አድናለሁ ብሎ በጥይት ገደላት
የሆድ ቁርጠት ትታመም የነበረችውን አንዲት ወጣት በጠመንጃ አስፈራርቶ ለማዳን የተደረገው ሙከራ የወጣቷን ህይወት ቀጠፈ። በዚህ ያላዋቂነትና ቸልተኝነት በተፈጸመ ሙከራ ከሆዷ ላይ በጥይት ተመትታ የሞተችው ወይዘሮ ተዋበች ማሞ የተባለች የ 20 ዓመት ወጣት ናት።
ይኸው ድርጊት የተፈጸመው በይፋትና ጥሙጋ አውራጃ ግዛት በካራ ቆሬ ከተማ ነሐሴ አምስት ቀን 1962 ዓ.ም ሲሆን ወጣቷ በዚህ ጠንቅ ህይወቷ ያለፈው በማግስቱ መሆኑ ታውቋል። ይኸው አደጋ ሊደርስ የቻለው እመት ማሚቴ የተባሉት የሟቿ ወላጅ እናት የሆድ ቁርጠት ያደረባትን ወጣቷን ልጃቸውን ለማዳን አቶ ወርቁ ወልደየስ የተባለውን የጎረቤት ሰው ጠሩት። ከዚያም አቶ ወርቁ የባለቤትየውን ፍሎበር ጠመንጃ ከራስጌ አስወርዶ ቃታውን በመክፈትና በመግጠም “ውጋት እኔ ቀደምኩህ” እያለ ከታመመችው ወጣት ሆድ ላይ አፈ ሙዙን አዙሮ ምላጩን በመሳብ የገደላት መሆኑ ታውቋል። የአካባቢው ህዝብ የዚህ ዓይነቱን የበሽታ መከላከያ ዘዴ “ጉስሞት” ብለው እንደሚጠሩት ለማወቅ ተችሏል።
ሐሙስ ሐምሌ 23 ቀን 1962 ዓ.ም የታተመው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ያለሰፈርህ መጥተህ ለምን ጠጅ ጠጣህ ብለው የደበደቡት ሰው ሕይወቱ በማለፉ ክስ ተመስርቶባቸው ፍርድ ስላገኙ ጥፋተኞች ተከታዩን ዘገባ አስነብቦ ነበር።
ከሰፈራችን ጠጅ ለምን ጠጣህ ብለው ገደሉት
ሰፈርህ ካልሆነው ቀበሌ መጥተህ ጠጅ በመጠጣትህ ጥፋተኛ ነህ ብለው ኢሌጎ አኮና የተባለውን ሰው በጩቤ ወግተው በጠርሙስና በዱላ ደብድበው የገደሉት ሰዎች በተከሰሱበት ወንጀል ተመስክሮባቸው ለእያንዳንዳቸው የአምስት ዓመት ጽኑ እስራት ተፈረደባቸው።
ሰንቆ ሶሪ እና ዲታ ካራ የተባሉት የ 33 እና የ20 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ሥራቸው ሸማኔ የሆነው ተከሳሾች ሟቹን የገደሉት አዲስ አበባ ኮልፌ ከተባለው ቀበሌ ከአንድ ጠጅ ቤት ውስጥ መሆኑን የአቃቤ ህጉ ማስረጃ ያረጋግጣል። ተከሳሾቹ ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ተኩል በሚሆንብት ወቅት ከጠጅ ቤቱ እንደተቀመጡ ሟቹም ተቀምጦ ሲጠጣ በምን ምክንያት ያለሰፈሩ መጥቶ እነሱ ሰፈር እንደሚጠጣ ይጠይቁታል። ሟችም በገንዘቤ ለምጠጣው የትም ልጠጣ እችላለሁ ቢላቸው በዚሁ መነሾ አባሪ ተነባባሪ ሆነው መደብደባቸው ተመስክሯል።
ሁለቱ ተከሳሾች በፈጸሙት ወንጀል አዲስ አበባ ከፍተኛው ፍርድ ቤት አንደኛ ወንጀል ችሎት ቀርበው ወንጀሉን የፈጸሙት በመጠጥ ኃይል ተሸንፈው መሆኑን በመግለጽ ስላመኑ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን መርምሮ የተከሳሾቹን ሁኔታ በመገመት በአምስት ዓመት እስራት እንዲቀጡ ወሰነ።
ተከሳሾቹ የወንጀሉን ተግባር ሊፈጽሙ የቻሉት በመጠጥ ኃይል ተገፋፍተው ለመሆኑ ሁለቱም ሰዎች ከሟቹ ከኢሌጎ ከጠቡ ዕለት በፊት ምንም ዓይነት የቆየ ቂም በቀል የሌላቸውና ከዚያም አስቀድሞ የማይተዋወቁ መሆናቸውን ፍርድ ቤቱ ገምቶ ፍርዱን አሻሽሎ ወስኗል ሲል በፍርዱ ሐተታ ተመዝግቧል። ሟቹ በሁለቱ ሰዎች እንደተደበደበ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ምንም ቃል ሳይናገር ዳግማዊ ምንሊክ ሆስፒታል እንደተወሰደ በድብደባው ምክንያት ማረፉን ዓቃቤ ህጉ በክሳቸው ማመልከቻ ዘርዝረዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 14/2012
የትናየት ፈሩ