የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የህክምና ቡድን በተያዘለት መርሀ ግብር መሰረት በሚገባ ተዘጋጅቶ ምርመራውን ለማድረግ ባለፈው ሐሙስ ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ደርሷል፡፡ ሆስፒታሉ ከጥር 1 እስከ 30 የሚከበረውን የጤና እናትነት ወርን አስመልክቶ በአራት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች በመገኘት በሴት ሠራተኞች ላይ የጡት እና የማህጸን በር ካንሰር ምርመራ ለማድረግ ነው በስፍራው የተገኘው፡፡
የህክምና ቡድኑ ከመሥሪያ ቤቶቹ አንዱ በሆነው የገንዘብ ሚኒስቴር ግቢ በመገኘት የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ሥራዎች ሳይስተጓጎሉ ሠራተኞች ተከፋፍለው በካንሰር ላይ ግንዛቤ እንዲጨብጡ ተደርጓል፡፡ ከዚያም ወደ ተዘጋጀላቸው የምርመራ ክፍል እየገቡ ተመርምረዋል።
የህክምና ባለሙያዎቹ ለሠራተኞች በሰጡት ማብራሪያ ቅድመ ምርመራ ማድረጉ በወቅቱ ራስን በማወቅ መፍትሔ ለማምጣትና በሽታውን ለመከላከል እንደሚረዳ ጠቁመዋል፡፡
በተፈጠረው መልካም አጋጣሚ ለመጠቀም የተገኙት የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ባለሙያዎች ወይዘሮ ሒሩት ኪዳኔ እና ራሔል ጠና ካልታመሙ በስተቀር ሀኪም ቤት እንደማይሄዱ ይገልጻሉ፡፡ ቅድመ ምርመራ የማድረግ ልምዱም ባህሉም እንደሌላቸውም ይናገራሉ።
ሴቶች ከሥራ መልስ የቤት ሥራ እንደሚጠብቃቸው የሚናገሩት ሠራተኞቹ፣ ምርመራውን ጨርሶ እንደማያስቡት ያብራራሉ፡፡ ለምርመራ የሚያስፈልገው ወጪም ብዙ ነው ብለው እንደሚገምቱም ይጠቁማሉ፡፡ የገንዘብ አቅም ያላቸውም ቢሆኑ መዝናናትን ያስባሉ እንጂ በህክምና ተቋም የካንሰር ቅድመ ምርመራ ለማድረግ ወኔው የላቸውም ይላሉ። ‹‹ካንሰር ሲባል የሚገድል አድርገን ስለምናስብ ይድናል ብለን አንገምትም›› ብለዋል።
የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሀኪሞች የካንሰር ቅድመ ምርመራ ለማድረግ ገንዘብ ሚኒስቴር ድረስ መጥተው ጥሩ ግንዛቤ እንዳስጨበጧቸው የሚናገሩት ሠራተኞቹ፣ በተደረገላቸው ምርመራም መደሰታቸውን ይገልጻሉ። ካንሰርን አስመልክቶ በሁሉም የህክምና ተቋማት ግንዛቤ የሚሰጥበት መንገድ እንዲመቻችም ጠይቀው፣ የሆስፒታሉ ሀኪሞች መሥሪያ ቤታቸው ድረስ መጥተው ላደረጉላቸው የካንሰር ቅድመ ምርመራም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የካንሰር ቅድመ ምርመራ በሚያደርጉበት ወቅት ያገኘናቸውና ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ሌላዋ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ባለሙያ ካንሰር ሲባል የፍራቻ ስሜት ያድርባቸዋል፡፡ ቤተሰቦቻቸውን በጡት ካንሰርና በጭንቅላት ካንሰር ማጣታቸውን በመጥቀስም እሳቸው በግላቸው የጡት ካንሰር ለመመርመር ፈልገው መቸገራቸውን ይጠቁማሉ፡፡ ወደ ቤተሰብ መምሪያ ሄደው ቢጠይቁም የፈለጉት እንዳልሆነ ተናግረው፣ የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሀኪሞቹን ልኮ ቅድመ ምርመራ እንደሚ ያደርግ ሲሰሙ በእጅጉ መደሰታቸውን ያብራራሉ።
ዶክተር ሙሉጌታ ካሳሁን በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የካንሰር ቀዶ ሀኪም በተለይ ለዝግጅት ክፍ ላችን እንደገለፁት፤ የቅድመ ምርመራው ከጥር አንድ ቀን ጀምሮ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ለአንድ ወር የሚካሄዱ እናቶችን ከሞት የማዳን ዘመቻ ሥራዎች አካል ነው።
ዶክተር ሙሉጌታ አገልግሎቱ ለሰዎች ግንዛቤ ለማስጨበጥና በጡት እና በማህጸን በር ጫፍ ካንሰር ዙሪያ ግንዛቤ ለመስጠት እንዴትስ መከላከል ይቻላል የሚለውን እንዲያውቁና እንዲጠነቀቁ ለማድረግ የሚጠቅም መሆኑን ይገልጻሉ።
የህመሞቹ ስሜቶች ሳይከሰቱ ቶሎ መመርመር ካንሰርን በእንጭጩ ሳይሰራጭ ለመከላከል እና ለመዳን እንደሚቻል የሚናገሩት ዶክተር ሙሉጌታ፣ የማህጸን በር ጫፍ ካንሰር እና የጡት ካንሰር ቅድመ ምርመራ በዘመቻ እንደሚካሄድ ይጠቁማሉ፡፡ የህክምና ቡድኑ 13 የሚሆኑ ባለሙያዎች እንዳሉት ጠቅሰው፣ በቅድመ ምርመራው ጥርጣሬዎች ካሉን ናሙና ወስደን ወደ ሆስፒታል እንልካለን ይላሉ።
እንደ ዶክተር ሙሉጌታ ማብራሪያ፤ ካንሰር መዳን የሚችል በሽታ እንደሆነ ኅብረተሰቡ መገንዘብ አለበት፤ መዳን የሚችለው ገና እንደጀመረ ወይም ምልክቱ ሳይኖር ህክምና ማድረግ ሲቻል ነው። በሽታው ከፍተኛ ደረጃ ላይ ከደረሰ ግን ህክምናው ለአደጉ ሀገሮችም ያስቸግራል።
የካንሰር ምርመራ ያደረጉት ሴት ሠራተኞች በየወሩ እንዴት መታየት እንዳለባቸው ግንዛቤ እንዲጨብጡ መደረጉን የሚናገሩት ዶክተር ሙሉጌታ፣ ካንሰር ይኖርባቸዋል ብለን የጠረጠርናቸውንም ለሌላ ተጨማሪ ምርመራ ወደ ሆስፒታል እንጠራቸዋለን ይላሉ፡፡ እነዚህ ሴቶች የጡት ራጅ፣ ፓቶሎጂካል ምርመራ እንደሚደረግላቸው ይጠቁማሉ።
ምርመራው ለእናቶችና ለሴቶች የታቀደ መሆኑን በመጥቀስም፣ የጤናማ እናትነት ወርን ታሳቢ በማድረግ በጋራ በየመሥሪያ ቤቱ በመሄድ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ እንደሚሰራም ይጠቁማሉ።
ዶክተር ሙሉጌታ ሴቶች ፍራቻን ወይም የለብኝም ማለትን፣ መደበቅን እና የመሳሰሉትን አመለካከቶች በመተው የትኛውም ሆስፒታል እና ጤና ጣቢያ ሄዶ በመመርመር ሀኪም ማማከር እንዳለባቸው ይጠቁማሉ።
ዶክተር ቤተልሄም ብርሃኑ የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ጠቅላላ ሀኪም እንደገለፁት፤ ምርመራው ለእናቶች /ለሴቶች/ ታቅዶ በያዝነው ጥር ወር የሚከበ ረውን ዘመቻ ታሳቢ በማድረግ እየተከናወነ ይገኛል፡፡ ቅድመ ምርመራው በሽታው ከመስፋፋቱና ሰዎች ምልክት አሳይተው ሆስፒታል ከመም ጣታቸው በፊት ለመከላከል ይጠቅማል።
የህክምና ቡድኑ አስተባባሪ ዶክተር ምትኩ ጌጡ በሀገር አቀፍ ደረጃ በከተሞች ከሚገኙ የካንሰር ህሙ ማን የጡት ካንሰር ተጠቂ ዎች 33 በመቶ መሆናቸውን ጥናቶችን ዋቢ በማድረግ ይናገራሉ፡፡ የማህጸን በር ጫፍ ካንሰር በከተሞች 35 በመቶ ይደርሳል ተብሎ እንደሚገመት ይጠቁማሉ፡፡
በኢትዮጵያ ምርመራው በተለያዩ መንገዶች እየተካሄደ መሆኑን ዶክተር ምትኩ ጠቅሰው፣ ከሁለት ወር በፊት በመድኃኒዓለም መሰናዶ ትምህርት ቤት 796 ሴቶች ተመርምረው፣ 116ቱ ተጨማሪ ምርመራ እንደሚያስፈልጋቸው ታምኖ ወደ ሆስፒታል መላካቸውን ይገልጻሉ፡፡
ባለፈው ወር ከተሽከርካሪ ነጻ በሚል በተካሄደ የእግር ጉዞ መርሀ ግብር ላይም እንዲሁ በአራዳ ጊዮርጊስ አካባቢ ለ180 ሰዎች ተመሳሳይ ምርመራ መደረጉን ጠቅሰው፣ ከመካከላቸውም 15ቱ በሽታው እንደተገኘባቸው ጠቁመዋል፡፡
እንደ ዶክተር ምትኩ ገለጻ፤ አሁን በየመሥሪያ ቤቱ ማካሄድ በተጀመረው ምርመራ በአንድ መሥሪያ ቤት በሁለት ቀናት ብቻ 100 ሴት ሰራተኞችን መመርመር ተችሏል፡፡
የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንዋይ ፀጋዬ እንደሚሉት፤ ምርመራው “በደም መፍሰስ ምክንያት የሚከሰተውን የእናቶች ሞት በጋራ እንከላከል” በሚል መሪ ቃል በያዝነው ጥር ወር የሚከበረውን ዘመቻ ታሳቢ ያደረገ ነው።
የካንሰር ቅድመ ምርመራው በአራት የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሚካሄድ ሲሆን፣ መሥሪያ ቤቶቹ የተመረጡት በርካታ ሴት ሠራተኞች የሚገኙባቸው በመሆኑ ነው፡፡ የመንግሥት ሠራተኞች በተለይ ሴቶች በቤትም ሆነ በሥራ ቦታ ጫና ይበዛባቸዋል፡፡ በትርፍ ጊዜያቸው የሚማሩም አሉ፡፡ ሌሎች የማህበራዊ ህይወት ጉዳዮችም ይኖርባቸዋል፡፡ በዚህም ሳቢያ ወደ ህክምና ቦታ ሄደው ለመመርመር ጊዜ አይበቃቸውም።
ከሁለት ወር በፊት ለመድኃኒዓለም ትምህርት ቤት ሠራተኞች ተመሳሳይ ምርመራ አድርገን ነበር የሚሉት አቶ ነዋይ፣ በምርመራውም በሽታው የተገኘባቸው በሆስፒታሉ ህክምና እንዲታከሙ መደረጉን ተናግረዋል፡፡ በቀጣይም ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ምክር እንደተሰጣቸውም ጠቁመዋል፡፡ በቀጣይም ወደ ሦስት ፋብሪካዎች ሄደን ቅድመ ምርመራ ለማድረግ ዝግጅቱን አጠናቀናል ሲሉ አቶ ንዋይ ፀጋዬ አስታውቀዋል።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ ካንሰር በዓለም ላይ ካሉ ገዳይ በሽታዎች አንዱ ነው። በአውሮፓውያን አቆጣጠር የ2016 ብቻ በዓለም አቀፍ ደረጃ 17 ነጥብ 2 ሚሊዮን የካንሰር በሽተኞች እንደነበሩ እና ከነዚህ ውስጥ 8ነጥብ 9 ሚሊዮኑ ለሞት ተዳርገዋል።
በኢትዮጵያም ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ከፍተኛ የጤና ጉዳት እያደረሱ ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከልም ካንሰር የኢትዮጵያን ወጣቶች በመግደል ሁለተኛ ደረጃ ላይ መቀመጡን የአሜሪካ የህክምና ምርመራ ማህበር ድረ ገፅ መረጃ ይጠቁማል። በእዚህ በሽታ በተለይ ሴቶች በከፍተኛ ደረጃ እየተጠቁ ይገኛሉ፡፡
ከሰባት ዓመት በፊት በአዲስ አበባ ነዋሪዎች ላይ በተካሄደ ምርመራ 8ሺ539፣ በስድስት የሀገሪቱ ክልሎች በተካሄደ ምርመራ ደግሞ 1ሺ648 የካንሰር ህሙማን ተገኝተዋል። ከሦስት ዓመት በፊት በተደረገ ጥናትም 21ሺ 563 ወንዶችና 42ሺ 563 የካንሰር ተጠቂዎች ይኖራሉ ተብሎ እንደሚገመት መረጃው ይጠቁማል።
በኢትዮጵያ በተያዘው ጥር ወር በሚከበረው የጤናማ እናትነት ወር ከጥር 2 እስከ 24 ቀን 2011 ዓ.ም በሚደረገው የማህጸን ጫፍና የጡት ካንሰር ቅድመ ምርመራ የገንዘብ፣ የባህልና ቱሪዝም፣ የሲቪል ሰርቪስ እና የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ሴት ሠራተኞች እንደሚመረመሩ ታውቋል ።
አዲስ ዘመን ጥር 7/2011
ኃይለማርያም ወንድሙ