ለኢትዮጵያውያን ሽምግልና አድባር ነው፤ ከቤተሰብ ጀምሮ በየትኛውም ማኅበረሰብ ውስጥ ግጭት አይጠፋምና ይህን ለማለሳለስ በስምምነት ለመቋጨት ሽምግልና ያስፈልጋል። በኢትዮጵያ ባህል ሽምግልና የሚነሳው ከመንፈሣዊ መሠረት ሲሆን የአምላክ ተግባር ተደርጎ እስከ መወሰድም ይደርሳል።
ሽምግልና ለእርቅ፣ ለፍቅርና ለሠላም የቆመ መንፈሣዊ አድባር ከመሆኑም በላይ ሕንፃ ሳይኖረው ለሽምግልና በበቃው ሰው አዕምሮ፣ ልብና መንፈስ ውስጥ ተቀምጦ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ ቆይቷል።
በኅብረተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ያለው የሽምግልና ስርዓት አለመግባባትንና ግጭትን በመፍታት በኩል ጉልህ ሚና ያለው ስለመሆኑ ጥርጥር የለውም፤ በፍርድ ቤት የተያዙ ጉዳዮች ሳይቀሩ በሽምግልና እንዲያልቁ የሚደረግበት ሁኔታም ይህንኑ ያመለክታል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ሽምግልና ተቀባይነት እያጣ መምጣቱ ይገለጻል፡፡ለዚህ አንዱ ምክንያት ሽማግሌዎች ወደ ፖለቲካው ዘርፍ እየገቡ መሆናቸው ሲሆን፣ ሌላው ወጣቶች ሽማግሌዎችን የመስማት ዝግጁነት እያጡ መምጣቸው መሆኑ ይነገራል፡፡
ይህንን የቆየ ባህልና ወግ እንዲሁም በርካታ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል ሥርዓት ወደ ቦታው ለመመለስ ከዚያም አልፎ በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ላይ እየተከሰቱ ያሉ አለመግባባቶችን በቆየው ወግና ልማድ ለመፍታት በማሰብ የሰላም ሚኒስቴር «የአገር ሽማግሌዎች ለአገር ሰላም» በሚል መሪ ቃል የሰላም ጉባዔ ትናንት አካሂዷል። በጉባዔው ላይ ከሁሉም ክልሎች እንዲሁም ከሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ተገኝተዋል።
ከአፋር ክልል የመጡት የአገር ሽማግሌ አቦ ሀመኒኪ ይባላሉ። አፋር ክልል ከቤተሰብ ጀምሮ እንደ ጉሳና ማህበረሰብ አለፍም ሲል እንደ አገር የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል የቆየ የሽምግልና ባህል ያለው መሆኑን ይናገራሉ።
« ማልቦ» በመባል የሚጠራው የአፋር የሽምግልና ባህል የተበዳይን ብቻ ሳይሆን የበዳይንም ድምጽ በመስማት በችግሩ ላይ ሰፋ ያለ ውይይት በማድረግ መንስኤውን በማጥናትና ከአድሎ ነጻ የሆነ ፍትህን በዳይን በሚቀጣ ተበዳይን ደግሞ በሚክስ እንዲሁም ለቂምና ለበቀል በማያነሳሳ መልኩ መፍትሄ በመስጠትም የተመሰገነ መሆኑን ይገልጻሉ።
እንደ አቶ አቦ ገለጻ የ « ማልቦ» ስርዓት በክልሉ የታወቀና ተቀባይነት ያለው ቢሆንም ከዓመታት በፊት ግን ለሥርዓቱ የሚታዘዝ ጠፍቶ ሰዎች በዚህ መሰሉ ዳኝነት ፍትህን ከማግኘት ይልቅ ወደ ዘመናዊ ፍርድ ቤቶች መሄድን መርጠው ነበር፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ በተለይም ወጣቱን ትውልድ አምቢ ባይና የአባቶቹን ተግሳፅ የማይሰማ አድርጓል።
ሆኖም ሥርዓቱ እንደ ክልል ያለውን ችግር ለመፍታትም ሆነ ከሌሎች ጋር ተደምሮ የአገርን ሰላም በማምጣት በኩል የሚኖረው ፋይዳ ትልቅ በመሆኑና አሁን ያለው የመንግሥት አስተዳደርም ይህንን የቆየ ባህል ስለፈለገው እኛም የአገር ሽማግሌዎች ወጣቶችን በመምከር የሚያነሱትን ጥያቄም ሰላማዊ በሆነ መልኩ እንዲያቀርቡ በማድረግ መንግሥትም የሚቀርቡለትን ጥያቄዎች ቸል ከማለት ተቆጥቦ ፈጣንና ተገቢ የሆነ ምላሽ እንዲሰጥ በማድረግ እኩልና ከአድሎ የጸዳ ፍትህን በመስጠት የአገሪቱን ሰላም እናመጣለን በማለት ተናግረዋል።
ከአማራ ክልል ባህር ዳር ከተማ የመጡት መላከ ሰላም አባ ክንፈ ሚካኤል ጫኔ እንደሚሉት፤ በቀደመው ጊዜ የአገር ሽማግሌዎች ሲናገሩ ይከበሩም ይሰሙም ነበር፤ አባቶች ከተናገሩ ከእነሱ ትእዛዝ ዝንፍ የሚል ወጣትም ሆነ ጎልማሳ አይገኝም፤ አሁን ግን ሽማግሌ የሚባሉት ሰዎች በፍርሃት የተዋጡ በመሆናቸውና ደፍሮ መናገር ባለመቻላቸው ይህ አኩሪ እሴት ተሸርሽሯል።
መላከ ሰላም አባ ሚካኤል ‹‹አሁን በአገሪቱ የሚታየው የሰላም እጦት የተወለደው ምን አገባኝ የሚል የአገር ሽማግሌና የሃይማኖት አባት በመብዛቱ ነው፤ ወጣቶች ወደ አልተገባ መንገድ ሲሄዱ ሄደውም ጥፋት ሲያደርሱ ተው የሚል አባት ያስፈልጋል የማንም ልጅ ቢሆን የሁላችንም በመሆኑ ችግር ሲፈጥር የተገኘን አባታዊ በሆነና ሊያስተምረው በሚችል መልኩ መገሰፁ ተገቢና አስፈላጊ ነው›› ይላሉ።
የራሳቸውን ተሞክሮም ሲያካፍሉ «ከደብረ ማርቆስ ወደ ባህር ዳር ስጓዝ ቲሊሊ በምትባል ከተማ ላይ ወጣቶች መንገድ ዘግተው አስቆሙን ፤ እኔ መስቀሌን ወደፊት ይዤ ከመኪናው ቀድሜ ወረድኩ ፤ወጣቶቹ እኔን በሚያዩበት ወቅት በጣም በመደናገጥ አባ ይቅርታ ፤ ብለው መስቀል ተሳልመው ተበተኑ» በመሆኑም አሁንም ቢሆን ያ የደበዘዘ የሚመስለው የሽምግልና ወጋችን ስላልጠፋ አባቶች ከምንቸገረኝ ወጥተን በኃላፊነት በየቤታችንና አካባቢያችን አልፈንም በሌላ ክልል ሄደን ማስተማር እርቀ ሰላም ማውረድ ማስወረድ ይገባናል›› ሲሉ አስገንዝበዋል።
‹‹ወጥቶ ለመግባት፣ የቀረበን ምግብ ለመብላት ሰላም አስፈላጊ ነው፤ እግዚአብሔርም የሚለው ሰላም ለእናንተ ይሁን ነው፤ በመሆኑም ሰላማችንን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት የምንነሳበት ወቅት አሁን ነው፤ ሽማግሌዎች አንሰማ ይሆን በሚል ይሉኝታ ውስጥ መውደቅ የለብንም›› መላከ ሰላም አባ ሚካኤል፣ ለአገር ለወገን ለእግዚአብሔር ብሎ መስራት እንደሚያስፈልግ ያስገነዝባሉ።
«ኢትዮጵያዊነት ለወንድም መሞት እንጂ ወንድምን አሳዶ መግደል አይደለም» የሚሉት መላከ ሰላም አባ ሚካኤል ፣አባቶቻችንም ወንድሞቻቸውን ገለው ሳይሆን ያሳዩን አፍሪካን አንድ ለማድረግ ሰርተው ነው። ጠባቦችም አይደሉም በመሆኑም «የእሳት ልጅ አመድ » መሆን የለብንም። ሽማግሌዎችን አሁን ለሥራ በቁርጠኝነት የምንነሳበት በመሆኑ መስራት ያስፈልጋል ሲሉ ይገልጻሉ።
እንደ መላከ ሰላም አባ ሚካኤል ገለጻ፤ወጣቶች መዘመናቸው ተገቢና አስፈላጊ ቢሆንም የሚያኮራውን ኢትዮጵያዊ የመከባበርና አብሮ የመኖር ባህል በመተው ግን መሆን የለበትም ፤ ይህ ከሆነ ሰላም ይመለሳል፤ እግዚአብሔር የሚወደውንም ሥራ መስራት ይቻላል፤በዚህም ሀገር ወደፊት ትራመዳለች፡፡
«ልጆች አባቶቻችሁን ምሰሉ፤ አባቶች ደግሞ ያለምንም ፍርሃትና አድሏዊነት በእድር፣ በማህበር፣ በሰንበቴ ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ እንቆጣ እንምከር፣ እንዝክር ለማንም ሳናዳላ እውነቱን እውነት ሀሰቱን ሀሰት የምንል እንሁን» ብለዋል።
ከሰላሌ ኩዩ ወረዳ ገብረጉራች አካባቢ የመጡት አያንቱ ዲሪባ ፈይሳ በበኩላቸው ውሃና ሽማግሌ አንድ ናቸው ይላሉ፤ ‹‹እሳት ተነሳ ቢባል መጀመሪያ ተፈልጎ የሚመጣው ውሃ ነው፤ ችግርም ሲከሰት ነገርን የሚያበርደው ሽማግሌ ነው ፤ በመሆኑም በአገራችን በተለይም በኦሮሚያ አካባቢ እዚህም እዚያም የሚታዩ የሰላም መደፍረሶችን በሽምግልና መፍታታችን ጠቃሚ ነውም ሲሉ ይናገራሉ።
በአገራችን ባህል ሦስት ዓይነት ሽማግሌ አለ የሚሉት አያንቱ ድሪባ፣ እነዚህም የፀጉር ሸበቶ ፣የልብ ሸበቶና የእግር ሸበቶ በማለት ከፋፍለዋቸዋል፤ የፀጉር ሸበቶው የተፈጥሮ ነው፣ የልብ ሸበቶው ደግሞ ከወጣቱም ከወንዱም ከሴቱም ልባቸው ከዕድሜያቸው በላይ የበሰለ ለማንም ሳያዳሉ ፍርድ የሚሰጡ ናቸው፣ የእግር ሸበቶው ደግሞ መንገድ እራቀብኝ መሳፈሪያ ይሰጠኝ ወይም በቅሎ ይቅረብልኝ ሳይልና ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይታከልበት ሽምግልናውን በአግባቡ የሚወጣ ነው ይሉታል። ለአገራችንም የሚያስፈልጓት የልብ ሸበቶና የእግር ሸበቶዎች መሆናቸውንም ይናገራሉ።
የ73 ዓመት ዕድሜ ባለጸጋ መሆናቸውን የሚገልጹት አያንቱ ዲሪባ፣ በእነዚህ ዓመታት ውስጥም ከሦስት ያላነሱ የአገዛዝ ዘመኖችን ማለፋቸውንና ፤ ያለፉት መንግሥታት ሁሉ አመጣጣቸው በአፈሙዝ ድጋፍ መሆኑን ያመለክታሉ፡፡ አሁን ያለንበት ወቅትና እያስተዳደረን ያለው መንግሥት ግን አፈሙዝ ሳይስብ እራሱ « አፉን ሙዝ» (ጣፋጭ) አድርጎ የመጣ ነው። ይህንን ዕድል ደግሞ መጠቀም የሁላችንም ግዴታ ነው ይላሉ።
እንደ አያንቱ ድሪባ ገለጻ፤ ወጣቶች በተለያዩ ምክንያቶች ተስፋ ሊቆርጡ፣ ጥያቄዎችም ሊኖራቸው ይችላል፤ ሆኖም ጥያቄያቸውን ለሌሎች መጠቀሚያ ሳያደርጉት በሰላም መንግሥት በመጣበት የጣፈጠ መንገድ ማቅረብና ለምላሹም ትዕግስትን መግዛት ያስፈልጋል። ወጣትነት ይዞት መታገስ አቅቶት ወደ ችግር የሚገባን አካል ደግሞ የአገር ሽማግሌው ለማንም ወገንተኛ ሳይሆን እየሄዳችሁበት ያለው መንገድ ጥሩ አይደለም አንተም ተው አንቺም ተይ ብሎ መልካሙን መንገድ ማሳያት ያጠፋን መገሰጽና ማስተማር ደግሞ ኃላፊነታችን ሊሆን ይገባል ብለዋል።
«የተማከረና የዘከረ መላ አያጣም» የሚሉት አያንቱ ድሪባ ፣በመሆኑም የአገር ጉዳይ የሁላችንም በመሆኑ የሚሞተው ኢትዮጵያዊ ገዳዩም እንደዛው ስለሆነ በተለይም አባቶች ከምናገባኝ ወይም እኔ ላይ እስካልደረሰ በሚል ችላ ከማለት ይልቅ ለጉዳዩ ተገቢውን ትኩረት በመስጠት አስፈላጊውን ማሻሻያ ማድረጉ ጠቃሚ ስለመሆኑም ያስረዳሉ።
« ባቄላና ጤፍ እኩል አይበስሉም» ኦሮሚያን እያመሰ ያለውን ችግር ማጥራት በመንግሥትም ሆነ በአገር ሽማግሌዎች ዘንድ መጀመር አለበት፤ በዚህም ተሳስተው የገቡትን አስተምሮ በመመለስ ወደውና ፈቅደው የገቡትንና አገርን የሚያምሱትን ደግሞ በህግ የእጃቸውን እንዲያገኙ ለማድረግ እንሰራለን በማለትም ሃሳባቸውን ይሰጣሉ።
ከኢሊባቦር መቱ ከተማ የመጡት አደሲንቄ ጫልቱ በቀለ እንደሚሉት፤ ሽምግልና በአገራችን የተጣላ የሚታረቅበት የበደለ በባህሉና በህጉ መሰረት የሚቀጣበት ተበዳይም የሚካስበት በዚህ መካከል ደግሞ ቂምና ቁርሾ የማያድርበት ትልቅ ባህል ነው።
አሁን በተለይም አገራችን ካለችበት ችግር አንጻር የሚያዋጣን ይህንን አኩሪ ባህላችንን መልሶ እንዲጠናከር በማድረግና ያላወቁን በማሳወቅ የተጣሉን በማስታረቅ እንዲሁም ሰላም ለማንም የማይተካ ሚና እንዳለው ማስገንዘብ እንደሚገባ ይናገራሉ። ይህንንም በተለይ የአገር ሽማግሌዎች ከምን ጊዜውም በላይ በተጠናከረ መልኩ ሊሰሩበት እንደሚገባም ይገልጻሉ።
«ተቻችሎ መኖር የእኛ የኢትዮጵያውያን አኩሪ ባህላችን ነው» የሚሉት አደሲንቄ ጫልቱ በመሆኑም በጥቃቅን ችግሮች ተነስተን ጎሳን ከጎሳ ብሔርን ከብሔር በማጋጨት በአጠቃላይ አገሪቱን ወደ አልተገባ የሰላም እጦት መውሰድ ባህላችን እምነታችንም የሚፈቅደው ሥራ አይደለም ይላሉ፡፡ በመሆኑም በተቻለ መጠን ወጣቱ የአባት እናቶቹን ታሪክ በመከተልና ከእኩይ ተግባር ራሱን ማራቅ እንዳለበት ያስገነዝባሉ፡፡አባቶችና እናቶች ደግሞ እንደ ባህል እንደ ወጉ የተጣላ ሲገኝ አንተም ተው አንተም ተው በማለት የሰላምን አስፈላጊነት በማሳየት ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸውም ያስረዳሉ።
«ሰው ሆኖ የማይጣላ ብረት ሆኖ የማይዝግ» የለም ሆኖም ችግር ሲመጣ ግን አፈታቱ ችግሩን ወይ ያበርደዋል አልያም ያቀጣጥለዋል የሚሉት ደግሞ ከሲዳማ ዞን ከአርቤ ጎና ወረዳ የመጡት አቶ ጥላሁን ሀሮ ናቸው።
እንደ እርሳቸው ገለጻ የሲዳማ ህዝብ ከጥንት ጀምሮ በመካከሉ የሚፈጠሩ ግጭቶችን ለመፍታት ወደ ህግ ከመሄዱ በፊት ሽማግሌዎችን በመሰብሰብ በዳይም ተበዳይም ችግራቸውን አቅርበው ሽማግሌውም ለማንም ሳያዳላ ፍርዱን ሰጥቶ ነው የሚያልፈው። ይህንን ፍትህ አልቀበልም የሚልም አይገኝም ነበር ይላሉ።
በአሁኑ ወቅት ለውጡን ለመቀልበስ አንዳንድ ጥቅማቸው የተነካባቸው ወገኖች በሲዳማና በወላይታ ብሔር መካከል ችግር ፈጥረው እንደነበር የሚያስታውሱት አቶ ጥላሁን ይህንን ችግር ለመፍታትም ከፍተኛ ጥረት መደረጉንና በዚህም የተጣሉት እንዲታረቁ ፣ ሰው የሞተባቸውም በአካባቢው ባህል መሰረት እንዲካሱ በማድረግ ኃላፊነታቸውን መወጣታቸውን ይናገራሉ።
«አጄቶ» ወይም የሲዳማ ወጣቶች እስከ አሁን ያልተመለሰላቸው ጥያቄ ያላቸው ቢሆንም ከአገር ሽማግሌ ቃል ውጪ አይደሉም›› ያሉት አቶ ጥላሁን እኛ በሽምግልና ወጣቱን እያሳመንን ነው ይላሉ፤ መንግሥትም ጥያቄውን መመለስ ቢችል ሰላማችንን ከምን ጊዜውም በላይ ለማረጋገጥ እንችላለን በማለት ይናገራሉ።
አባገዳ ከሊፋ ሻኖ ሰላም ለመማር ፣ማስተማር፣ ወጥቶ ለመግባት፣ ሰርቶ ለማግኘት ፣ቤተሰብ ለመመስረት በአጠቃላይ ለሁሉም ነገር አስፈላጊ መሆኑን ያመለክታሉ።ይህ መሰሉ ሰላም እንዲገኝ ደግሞ በተለይም የአገር ሽማግሌዎች ሚናቸው ላቅ ያለ መሆኑን ጠቅሰው፣ተቀባይነቱም ስላላቸው የቆየ ባህላችንን በማስጠበቅ መስራቱ ወሳኝ ነው ይላሉ።
እንደ አባገዳ ከሊፋ ማብራሪያ፤ከገዳ ሥርዓት ብዙ መማር ይቻላል ፤ በሥርዓቱ ያለግጭት እና ጦርነት የሰው ደም ሳይፈስ አጥነት ሳይሰበር ህይወት ሳያልፍ በአጠቃላይ ሰላማዊ በሆነ አካሄድ የስልጣን ሽግግር ይደረጋል ፤ ይህ ደግሞ ለፖለቲከኛውም ለወጣቱም ትልቅ ትምህርት ይሆናል። ‹‹ዛሬ አገራችንን በእርስ በርስ ጦርነት ካጠፋናት ነገ የት ላይ ሆነን ማንንስ ነው የምናስተዳድረው? መጪውንስ ትውልድ እንዴት ነው ስለ ሰላም ማስተማር የምንችለው ?በማለት ይናገራሉ።
በመሆኑም አባገዳ እስከ ዛሬ ስለ ሰላም ከማስተማር በላይ በተግባርም ሲያሳይ የኖረ በመሆኑ አሁንም ይህንን አጠናክሮ በመቀጠልና ለወጣቱ ብቻ ሳይሆን ለመሪዎቹም ጭምር በማስተማርና በተለይም እንደ ኦሮሚያ ችግሮች ባሉባቸው አካባቢዎች ላይ በከፍተኛ ሁኔታ በመንቀሳቀስ ክልሉን የማረጋጋት ወደ ሰላም መንገዱ የማምጣት ሥራ ለመስራት እየተንቀሳቀሱ ስለመሆኑ አብራርተዋል።
ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ጉባ ወረዳ የመጡት አቶ በሽር በሱቱሪ እንደሚሉትም በአካባቢው ከዚህ ቀደም ጥሩ የመከባበርና የመቻቻል ባህል የነበረ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በግለሰቦች አነሳሽነት የሚፈጠሩ ጥቃቅን ችግሮች እየተስተዋሉ ናቸው።
ይህ ደግሞ የጎሳ ግጭትን እንደሚያስከትል በአይነ ቁራኛ እንዲተያዩ እንደሚያደርግ የሚናገሩት አቶ በሽር ለዚህ ምክንያቱ የበላይነትን ለማሳየት የሚደረግ ፉክክር መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ ይህንን ሁኔታ ባለበት ለማቆምና ፍጥጫውን ለማርገብ የአገር ሽማግሌ በማቋቋምና የሰላም ኮሚቴ በመመስረት ችግሩን የሚያረግብ ውይይት በመደረግ ላይ ስለመሆኑም ያብራራሉ።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ከዚህ በኋላም የሰላም ኮሚቴውና የአገር ሽማግሌው በመቀናጀት እስከ ታችኛው የህብረተሰብ ክፍል ድረስ በመውረድ ለማስተማርና ሰላምን ለማስፈን በቁርጠኝነት ለመስራትም ተነስተዋል።
በመድረኩ ላይ ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡት ፕሮፌሰር እዝቅዬል ጋቢሳ እንዳሉት፤ ሽምግልና ማለት የጥበብ ባለቤት ሆኖ መገኘት ሲሆን መሳሪያዎቹም ሰዋዊ ባህርይና ንጹህ ህሊና ናቸው። የአገር ሽማግሌ ሲባልም የዛሬን ብቻ ሳይሆን መጪው ጊዜም ወለል ብሎ የሚታየው አርቆ አሳቢ ፣ታጋሽ የተለያዩ ሃሳቦችን ለማስተናገድ የሚችል ከፍረጃ የጸዳ በአጠቃላይ ሆደ ሰፊ መሆን ያለበት ሲሆን ያለ አድሎ ለሀቅና ለፍትህ የቆመ፣ ለባለስልጣን የማያጎበድድ ቃሉ ንግግሩ እንዲሁም ተግባሩ የተዋሀዱለት ነው፡፡እርሱ አገርን መቀየር የሚችል በመሆኑ የአገር ሽማግሌ ይባላል፡፡
እንደ አገርም ይህ ዓይነቱ ሽማግሌ በጣም እንደሚያስፈልገን ገልጸው ፣ይህ መሆን ሳይችል ህዝብ ደም ከተቃባ መመለሻው ከባድ እንደውም የልጅ ልጆቻችን ሳይቀር ከፍለው የማይጨርሱት እዳም እንደሚሆን ነው የተናገሩት። በመሆኑም በአንድ አካባቢ የተከሰተን ግጭት ወይም አለመግባባት በቦታው ላይ እንዲቆም ማድረግና በዳይንም ተበዳይንም በእኩል ዓይን አይቶ ንጹህ ፍርድን መስጠት በጣም አስፈላጊ ስለመሆኑም ፕሮፌሰሩ ባቀረቡት የጥናት ጽሁፍ ላይ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ታሪክ እርስ በርስ ተጋብቶ ያልተዋለደ፣ ለዘመናት በመቻቻልና በፍቅር አብሮ ያልኖረ ብሔር ቢፈለግ አይገኝም፤ ያሉት ፕሮፌሰር እዝቅዬል ታዲያ ማነው ማንን የሚጠላ ፤ማንስ ነው ከኖረበት ቀዬ ውጣ ተብሎ የሚወጣ ?ሲሉ ይጠይቃሉ፤ በመሆኑም ይህንን የጥላቻ መርዝ በእንጭጩ መቅጨት ፤የችግሩን ስርወ መሰረት መለየት ለነገዬ የሚባል ሥራ ባለመሆኑ የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ከምን ጊዜውም በላይ ተቀባይነታቸውንና ተሰሚነታቸውን በመጠቀም ሰላምን የሚያስጠብቅ የማያዳግም ሥራ መስራት እንዳለባቸው አብራርተዋል።
የሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል በበኩላቸው የሀገር ሽማግሌዎቹን ‹‹ጥላቻ በፍቅር እንዲሸነፍ ቂም በቀል በይቅርታ እንዲታለፍ ሌት ተቀን ስትሰሩ ስትመክሩ ሰትዘክሩ ከትውልድ ወደ ትውልድ ማህበራዊ እሴቶችን ስታሸጋግሩና በሂደትም ሰላም ስትገነቡ እዚህ አድርሳችሁናል፤ አሁንም የእናንተ ሚና እጅግ አስፈላጊያችን ነውም ብለዋል።
በማህበረሰብ ደረጃ ጊዜያዊ የሰላም መደፍረስን ለመግታትም ሆነ ዘለቄታዊ ሰላምን ለማምጣት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ሚናችሁ ተኪ የለሽ ነው ያሉት ሚኒስትሯ፤ ሰላምን በመንከባከብና በማሳደግ ረገድ ማህበረሰባዊ መሰረት የመገንባት ዕድልና ችሎታ በእናንተ እጅ ነው ሲሉ የአገር ሽማግሌዎቹን ገልጸዋቸዋል፡፡
እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ፤ትውልዱ ማንነቱንና ስብዕናውን የሚፈታተኑትን ተጽዕኖዎች ገጥመውታል ፤እነዚህምን መቋቋም እንዲችልም ጠቃሚ እሴቶችን በማውረስ ዘመናዊነትን በጥበብና በብልሀት እንዲያስተናግድና እንዲሻገር አገርንም እንዲያሻግር ማድረግ የሀገር ሽማግሌዎቹ የነገ ታሪክ እና የዛሬ ኃላፊነት ነው።
በትውልዶች መካከል ያለው ግንኙነት እንዳይበጠስ አገናኝ ድልድዩም እንዳይሰበር የማድረግ ኃላፊነትም የእናንተው ነው ያሉት ወይዘሮ ሙፈሪያት የአገር ግንባታ በትውልድ ቅብብሎሽ የሚካሄድ ሂደት እንደመሆኑ ትውልድ በመጣና በሄደ ጊዜ እንደየትውልዱ ፍላጎትና አገራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሁኔታ አዳዲስ መንገዶችን መቀየስ እንደተጠበቀ ሆኖ መሰረታዊ ማህበራዊ እሴቶችን ማሻገር ግን የማንም ኃላፊነት ሳይሆን የእናንተ ብቻ ነውም ሲሉ አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ በመቻቻልና በመተሳሰብ አብሮ የኖረ ሕዝብ ነው። ያልታደለው እኩልነትን አንግሶ በፍቅር የሚያያይዘውና አንድ የሚያደርገው አስተዳደር እስካሁን አለመገኘቱ ነው። ይህ ሕዝብ በእውነት ላይ የተመሰረተ ጥልም ሆነ ጥላቻ አንዱ በሌላው ላይ የለውም። መሪዎች እንደ ሕዝቡ ቅን ሆነው እኩልነትና ፍቅርን ቢዘሩ የሚታጨደው የፍቅር አዝመራ የማያጠግበው የለም።
አዲስ ዘመን ጥር 7/2011
እፀገነት አክሊሉ