የጤፍ እርሻ መሬታቸውን ለልማት ሲጠየቁ ቅሬታ ቢኖራቸውም በአሁኑ ወቅት አገልግሎት ጊዜያቸው ያለፈባቸው መድኃኒቶች ማስወገጃ ተገንብቶ መመልከታቸው ግን ደስታን እንደፈጠረላቸው በአዳማ ከተማ ልዩ ስሙ መልካ አዳማ ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡ ተቋሙ የበርካቶችን ሕይወት የሚያተርፍ እንደሆነም ሲመለከቱም ደስታቸው መጨመሩን ነዋሪዎቹ ይናገራሉ፡፡
በወቅቱ በልማት ምክንያት መሬታቸው ከተወሰደባቸው ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ እመቤት ኮርሜ አንዷ ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት ከዚህ ቀደም በአንድ በኩል በመድኃኒት ዕጥረት በሌላ በኩል ደግሞ ያለውም ውስን ሀብት ጊዜው አልፎበት እናቶችና ሕፃናት ለህልፈተ ሕይወት ይዳረጉ ነበር፡፡ ይህ ፋብሪካ መገንባቱ ግን ችግሩን ይቀርፈዋል፡፡ ያም ሆኖ ግን በቤት ውስጥ ያሉ ሥራ ፈላጊዎች በተቋሙ የሥራ ዕድል እንደሚፈጠርላቸው የተገባላቸው ቃል እንዲከበር ጠይቃለች፡፡
ለበርካታ ሥራ ፈላጊዎች የሥራ ዕድል ከመፍጠሩ ባሻገር ተቋሙ ለአገሪቱ የሚያበረክተው አስተዋፅዖም ከፍተኛ እንደሆነ የተናግረው ደግሞ ወጣት ጋዲሳ ኃይሉ ነው፡፡ ጊዜ አለፈባቸው የሚባሉ መድኃኒቶች ለህሙማን ይሰጣል ሲባል መስማቱን የሚናገረው ወጣት ሐይሉ ይህም ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ ሕይወት ስጋት ላይ ይጥል እንደነበር ይናገራል፡፡ ተቋሙ አለመኖሩ በማን አለብኝነት አገልግሎት ጊዜያቸው ያለፈ መድኃኒቶች የሚያሰራጩ እንዲኖሩ ዕድል የሚከፍት በመሆኑ ፋይዳው የጎላ ነውም ይላል፡፡
በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የአዳማ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ መስፍን አሰፋ፤ ከዚህ ቀደም በአገር ደረጃ መድኃኒቶችን በስርዓት አለመጠቀም ትልቅ ችግር እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ መድኃኒቶች እየተፈለጉ ጊዜ እንዲያልፍባቸው ማድረግ፣ ሁኔታዎችን አጥንቶ የትኛው መድኃኒት በየትኛው ስፍራ ያስፈልጋል? የሚለውን ለይቶ ማሰራጨት እንዲሁም ጊዜ ማለፉ ብቻም ሳይሆን በስርዓት የማስወገዱ ሂደት ላይ የሚታዩ ክፍተቶች ነበሩ፡፡
በዚህም እጅግ መርዛማ የጤና ጠንቅ ሊሆኑ የሚችሉ የተበላሹ መድኃኒቶችን በየቦታው በተለይም በጤና ተቋማት ውስጥ ይስተዋላሉ፡፡ በየጤና ተቋማቱ በጭስ የሚወጣው ኬሚካልም አካባቢን ይበክል ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ዘመናዊ በሆነ ሁኔታ በከተማዋ ጊዜያቸው ያለፈባቸው መድሐኒቶችን ማስወገጃ መቋቋሙ የነበረውን ችግር በማቃለል ረገድ የሚኖረው ድርሻ የትየለሌ ነው፡፡ እንደ ከንቲባው ገለጻ፤ መድኃኒትን በማባከን እንዲወገድ ማድረግ ሳይሆን ለተጠቃሚው በአግባቡ ማድረስ ላይ በትኩረት ሊሠራ ይገባል፡ ፡
መድኃኒቶች መንግሥታዊ በሆኑ ጤና ተቋማት በብዛት አለመገኘት በውጭ ደግሞ በጣም ውድ በሆነ ዋጋ መገኘት ህብረተሰቡ መድኃኒቱን የሚገዛበት አቅም አጥቶ መዳን እየቻለ የማይድንባቸው ሁኔታዎች ሲፈጠሩ ይታያል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ መድኃኒቶቹ ጥቅም ላይ ሳይውሉ በየቦታው ይበላሻሉ፡፡ በመሆኑም በዋናነት መድኃኒቶች ሳይበላሹ ለተጠቃሚ እንዲደርስ ማስቻል ትኩረት ተደርጎ ሊሠራበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ማስወገጃው 59 ሚሊየን ብር የፈጀ ሲሆን፤ በአንድ ሰዓት ውስጥ አንድ ሺህ ኪሎ ግራም የማቃጠል አቅም እንዳለው የዩኖፕስ ፕሮጀክት ማኔጀር አቶ ባሳዝነው ተረፈ ተናግረዋል፡፡
ከመድኃኒትና ህክምና መገልገያ ዕቃዎች ውጪ ሌሎች ከኢንዱስትሪ የሚወጡ መወገድ የሚገባቸው ግብዓቶችንም የሚያስወግድ በመሆኑ በቅርቡ ሥራ ለጀመረው የአዳማ ኢንደስትሪያል ፓርክና ሌሎች ተቋማት ዕረፍት ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ኤጀንሲው የአገሪቱን የጤና ተቋማት የጤና ግብዓት ፍላጎት ለማሟላትና የህብረተሰቡን መሠረታዊ የመድኃኒት አቅርቦት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ መሆኑን የፌዴራል መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ አዳማ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ንጉሴ ገልጸዋል፡፡ የመድኃኒትና የሕክምና መገልገያዎች አቅርቦት ትስስር ስርዓት ማዘመኛ አጠቃላይ ማሻሻያ የለውጥ መስመር ጠቋሚ ፓኬጅ ዋነኛ ትኩረቱ አድርጎ ሲሠራም ቆይቷል፡፡
ተቋሙን በአመራርና በባለሙያ የማደራጀት፣ የአገሪቱን ዋና ዋና የጤና ችግሮች በዓይነትና በሚያደርሱት ተፅዕኖ መለየት፣ ዘመናዊ የክምችት አውታሮችን ማጠናከርና የአስተዳደር ስርዓቱን ስር ነቀል በሆነ መልኩ መቀየር፣ የመረጃ ትስስር ስርዓትን ማዘመን፣ ዘመናዊ የስርጭትና የትራንስፖርት አቅምን ማጎልበት እንዲሁም ከተገልጋይ ባለድርሻ አካላት ጋር የተጠናከረ ግንኙነት ማድረግ ኤጀንሲው በልዩ ትኩረት የሚያከናውናቸው ተግባራት ናቸው፡፡ ያዘገመውን ጊዜ በፈጣን ሩጫ ለመካስ እንቅስቃሴ መጀመሩንም አቶ ሰለሞን ተናግረዋል፡፡ የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማን እንደሚሉት፤ በአገርአቀፍ ደረጃ የመድኃኒት አቅርቦት ኤጀንሲን ለማዘመን አራት ትልልቅ ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ ይገኛል፡፡
ሥራዎቹ አጠቃላይ 26 ሚሊየን ዶላር ወጪ ተደርጎ የሚሠሩ ሲሆን፤ 16 ሚሊየን ዶላር ወጪ የተደረገበት የ17 ማከማቻ መጋዘኖች ወለል ማዘመን አንዱ ነው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አምስቱ የተጠናቀቁ ሲሆን፤ ሌሎቹም በቀሪ ወራት ይጠናቀቃሉ፡ ፡ ሥራውን ለማዘመን ከሚከናወኑ ፕሮጀክቶች መካከል 189 ተሽከርካሪዎችን በጂፒኤስ አዘምኖ ወደ ሥራ ማስገባት እንዲሁም በአገሪቱ አራቱም አቅጣጫ በአዳማና ሰባት ቦታዎች ላይ የሚሠሩት ማስወገጃዎች ዋነኞቹ ናቸው፡፡
የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ መድኃኒት አቅርቦት ኤጀንሲና የልማት አጋር ድርጅቶች ጊዜ ያለፈባቸው መድኃኒቶችን ማቃጠያና ማስወገጃ ሲተከል መድኃኒቶች ጊዜ እንዲያልፍባቸው እየተፈቀደ አለመሆኑን ተገንዝበው መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡ ፡ በአገሪቱ በአሁኑ ወቅት ጊዜ የሚያልፍባቸው መድኃኒቶች ብዛት በየጤና ተቋማቱ ያሉትን ሳያካትት ዜሮ ነጥብ ዘጠኝ በመቶ መሆኑን ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 6/2011
በፍዮሪ ተወልደ