ጽሑፌን የምጀምረው ፤ ድሮ በማውቃት ሐገር በቀል ቀልድ መሰል ወግ ነው። መቼም የቆሎ ተማሪ በድሮ ጊዜ ስልቻውን ይዞ ከቤት ቤት እየዞረ ከለመነ በኋላ አኩፋዳውን (ስልቻውን) ባገኛት እህልም ጥሬም ሞልቶ ነው ወደ መማሪያ ደብሩ የሚመለሰው።
እና አንደኛው ቆሎ ተማሪ ከአንዱ በር ወደ አንዱ ጎጆ እያማተረ ስለማርያም ስለቤዛይተ ኩሉ እያለ ይለምናል። ሴትየዋ ደጅ ላይ የሰፌድ ስፌት እየሰፉ አልመለሱለትም፤ ወይም አልፈለጉም። እናቴ ስለማርያም ብሎ ድምጹን ከፍ አድርጎ ደጋግሞ ሲለምን ቀና አሉና ልጄ፣ እግዜሃር ይስጥልኝ ይሉታል። እናቴ በአዛኝቱ ስልዎት አንድ ዋንጫ ጠላ ባገኝ እንኳ በቂ ነበር፤ እናቴ ድካሙ በዚያ ላይ አዝሎኛል፤ ይላል። ምን ነካው ልጁ ማርያም ትስጥልኝ አልኩህ እኮ ሲሉት። ጥሬ እንኳን የለም ? ሲላቸው ቢኖር ምንተዳዬ፣ ወዲህ ጥድቅ ወዲያም ደስታ ነበር፤ ይሉታል። እና የሚላስ የሚቀመስም የለ፤ ነው ያሉኝ እናቴ? አዎ አልኩህ አድርቅ ነገር ነህ ፤ ይላሉ። ታዲያ ምን ሊይዙበት ነው ፤ ስፌት የሚሰፉት ይልቅ እርሱን ስፌት ይተውቱና አብረን እየዞርን እንለምን እንጂ፤ አላቸው ይባላል።
እዚህ ላይ ትንሽ ድፍረት፤ ትንሽ ግፊት፣ የታየበት ቢመስለንም እንኳን የተማሪው ለምኖ መማር ኑሮ ( እነርሱ ቀፈፋ ይሉታል) እርሱ በትምህርቱ እንዲቀጥል የአባና እማ ወራዎቹም ሆነ፣ የማህበረሰቡ ጠቅላላ ድጋፍ ፣ የተለመደና የተጠበቀ መሆኑን እንድታጤኑልኝ እፈልጋለሁ። ለምነው ይማሩ እንጂ፣ በኋላ መልሶ ማህበረሰብን የሚያስተምሩ፣ የመጻህፍት ተርጓሚዎች፣ የእምነት ሊቃውንት የሚፈጠሩትና ጸሐፍት የሚወጡት፤ ከእነዚህ የዛሬ የቆሎ ተማሪዎች እንደሆነ ማህበረሰቡ ስለሚያውቅ እርዳታውን አጓድሎባቸው አያውቅም ፤ ተሜም ኑና አብረን እንለምን ሲል ግድየልዎትም ካለው የሚያካፍልና የእጁን የሚሰጥ በሌላ ስፍራ አለና እንሂድ ማለቱ ነው።
በጎ አድራጊው የኢትዮጵያ ህብረተሰብ በሁለት ምክንያት ለጋስነቱ የተረጋገጠ ነው፤ አንደኛ ከተቀባይነት ይልቅ ሰጪነት እንደሚያስከብር ስለሚያውቅ ሲሆን ሁለተኛ በመስጠቱ ሰማያዊ ባህሪን እንደተካፈለ ስለሚያምን ነው። የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ፤ የመሰጠት አገልግሎት ነው። በበጎፈቃድ አገልግሎት ደካማ ይረዳል፤ ጭጋግ ይገለጣል፤ የዕውቀት ብርሐን ይበራል።
ወጣቶቻችን በእንደዚህ ዓይነት የአገልግሎት ምዕራፋት ላይ እንዲካፈሉ ለማለማመድ በፈቃዳቸው የሚሄዱባቸው ስፍራዎች ትልቅ ሚና አላቸው። ለአብነት ያህል፤ ትምህርት ቤቶች ፣ አብያተ ክርስቲያናት፣ መስጊዶች፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ፣ የኪነጥበብ መለማመጃ ቦታዎች ሁሉ ይህንን ለማድረግ ይችላሉ። ዝርዝር ጉዳዮቹን ለየራሳቸው መተው እመርጥ ነበረ፤ አንድ ዓብይ ነገር ግን ልበል፤ በሁሉም መስክ ለማገልገል በሚሄዱባቸው ስፍራዎች የሚያገኙት የሰዎችን ልጆች ነውና፤ በሚሰማሩበት መስክ የሚያገለግሉት ሰውን መሆኑን ይረዳሉ፤ ሰውን ከማወቅና ከመርዳት በላይም ምንም በጎነት በዚህ ምድር ላይ ፣ የለም ።
በሚሄዱባቸው ዓምባዎች እነርሱ በሰፈራቸው በቀላሉ የሚያገኙዋቸው ነገሮች ሁሉ ሩቅ እና አዳጋች የሆነባቸውን ወገኖቻቸውን ሲያዩ የኑሮን ውጣ ውረድ ይገነዘባሉ፤ ዓለም ማለት ፣ ቤተሰባቸውና ሰፈራቸው ብቻ እንዳልሆነም ይታዘባሉ። ውሃ ብርቁ የሆኑ ወገኖቻቸው ከአዲስ አበባ በ150 ኪሎ ሜትር ወይም 55ና 60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ማግኘት ተነጥለን መቆማችንን ያስታውሳልና በጎነቱ ለመፍትሔና ህብረት አገለገለ ማለት ነው። ማንም መጥቶ ይህንን በጎ ሥራ ሊያሳንስና በባዶ እጁና አፉ ጥሩውን ውሃ ሊያደፈርስ አይችልምና ውሃ እናጠጣቸው፤ ውሃ እንደ ድሮው ብርቄ ሬዲዮ ብርቅ በሆነባቸው ስፍራዎች በጥቂቱ እናፍስስላቸው።
ይህም ብቻ አይደለም፤ አንዲት መረጃ ልስጣችሁ፤ በገጠሩ አካባቢ ሰው ሲበላ እንጂ ከበላ በኋላ ለምን እንደማይታጠብ ታውቃላችሁ? አንድም ውሃ ላለማባከን ፣ ሁለትም እህል እንጂ ነውር አልነካሁበትም ከሚል ልማድ የተነሳ ነው። ግን ከሁሉም ቀዳሚው ምክንያት ነው ፤ እውነቱ !!
አርሶ እያበላን፣ ማኛ ከሰርገኛ ቀላቅሎ እያመረተና እያጠገበን በደረቅ ሌሊት ሚስትና ልጆቹን ውሃ ፍለጋ የሚልክ አባወራ እንዳሸን የሞላበት ሐገር ናት፤ ያለችን። እናም ይህንን የአፍሪካ የውሃ ማማ አስብሎ ውሃ ብርቁ የሆነበትን አርሶ አደር እንድረስለት። ህክምናውም ሌላ የበጎ ፈቃድ ሥራ ያስፈልገዋል፤ የአካባቢ ንጽህናውም እንዲሁ እርዳታችንን ይፈልጋል ፤ ትምህርቱ እጃችሁ ከምን ይለናል፤ ስለዚህ በበጎ ፈቃደኛነት አብረን እንቁምና ልብ ለልብ እንተሳሰር!!
ወጣቱን ህብረተሰብ በበጎ ፈቃድ ማሳተፍ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች አሉት። በቅድሚያ የበጎ ፍቃድ በማከናወኑ የሚያገኘው ሥነ-ልቡናዊ ደስታ ነው። አስፈልጋለሁ፤ ለካ ማለቱ አንዱ ነገር ነው፤ ሌላው ከተቀባይነት ወደ ሰጭነት ተሸጋግሪያለሁ፤ ብሎ ያስባል። ደስም ይሰኝበታል፤ በዚህም ህይወቱ ልዩ ትርጉም ያለው እንደሆነ ይሰማዋል።
ወጣቶች፣ በበጎ ፈቃደኛነት አገልጋይ መሆን ሲጀምሩ ለግላቸው ልዩ የህይወት ልምድን ይቀዳጃሉ። አዳዲስ አካባቢዎችንና መስኮችን ማየት ይሆንላቸዋል። እንዲህም ይሰራል እንዴ፣ ብለው የሚያስቡበት አጋጣሚ ይፈጠራል።
ከዚህ በተጨማሪም በሚሄዱበት ሥፍራ የህይወት ዘመን ጓደኞችን ያፈሩበታል፤ ይህ ብቻ አይደለም የሌላውን ህዝብ አኗኗር ስለሚረዱና ባህላቸውንም ስለሚያውቁ የዚያ ህዝብ አካል እንደሆኑ ይሰማቸዋል፤ ልባዊነትን ያዳብራሉ። ለምሳሌ ያህል “ጣናን ከእንቦጭ እናድን ዓይነቱ ፕሮጀክት”፤ “የረር ጋራን ደን እናልብስ” ፤ ወይም “አላማጣን በጋራ እናድን” በሚል ፕሮጀክቶች ፤ የአንዱን አካባቢ ወጣት ወደሌላው በመውሰድ ሐገራዊ ስሜትን ማሳበብ ይቻላል።
እስራኤሎች የኔጌቭን በረሃማ መሬት ያለሙትና ለኤክስፖርት የበቁ ብርቱካኖች ሎሚዎችና ወይኖች እያመረቱ ለመላክ የበቁት በወጣቶቻቸው የበጎ ፈቃድ ህብረት አማካይነት ነው።
በቅድሚያ ሀገር ማለት ሰው ነው፤ ብዬ በጽኑ አምናለሁ፤ ነገር ግን ወጣቱ አንድ ህዝብ እንደ ህዝብ ተቆጥሮ የሚሰፍርበት አንድ ከባቢ እንዳለው ብቀበልም ከዚህ በላይ ግን ምድር ሁሉ እኖርባት ዘንድ፤ አፈራባት ዘንድ፣ አበቅልባት ዘንድ እሞላት ዘንድ በእጅጉ ተሰጥታኛለች ብሎ የሚያምንና ራሱን ለሌላው ወገኑ በሚችለው መስክ ያለስስት ለመስጠት የተዘጋጀ መሆን እንዳለበትም አስባለሁ። ይህን አስተሳሰብ በወጣቱ ላይ በሚገባ ካሰረጽን የማንወጣው ጋራ፣ የማንሻገረው ወንዝ፣ የማናቋርጠው ሜዳና የማናለመልመው በረሐና ሰብዓዊ በረሐ የለም፤ አይኖርምም። ዋናው ነገር የወጣቱን ልብ ማግኘት ነው። ለማግኘት ራሱን ሆኖ መገኘትና ዝንባሌውን መረዳት ይገባል፤ ብዬ አምናለሁ።
አህያ ሲጭኑት የሚጫነው ስለለመደ ነው፤ የሰውን ልጅ ግን የምንጭነው ሲፈቅድ ነው፤ ፈቃዱንም የምናገኘው በመንገር ነው። የተነገረውን የሰማ ወጣት ሰምቶ ብቻ የሚያቆም እንዳይመስላችሁ፤ ሰምቶ ያሰማል፤ ተጋርቶ ያጋራል። ለድካሙ እውቅና ከሰጠነው፣ ለበጎ ፈቃዱ ተገቢውን ፍቅር ከመለስንለት ሌሎችን በዚሁ መንገድ ለማስጓዝ እንደ አገልጋዩ ወጣት የተመቸ እንደሌለ ያለፉት አራት ዓመታት ተሞክሮዬ አሳይቶኛል።
በሌላ በኩል ወጣቶችን በበጎ ፈቃደኛነት የማካፈሉ ጥቅም የምንፈልገውን መሪ ሐሳብ ወደ ህብረተሰቡ ለማስረጽ ብርቱ መሳሪያዎች ስለሆኑ ነው። የሰሙትን ባልተቆጠበ ጉልበት ፍጥነትና ጥረት ወደሚፈለገው አካል ማድረስ ይችሉበታል። በዚህም ከፍተኛ የሆነ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ለላካቸው ተቋም ፣ ለመንግስትም ሆነ ለማህበረሰብ ያስገኛሉ። ከአላስፈላጊ ወጪም ያድናሉ።
እኔ ግን ከእኔ ጋር የሚሰሩትን ወጣቶች ሳይ ፊታቸው ላይ የማየው ለማገልገል የጋለ ጸዳል፤ ቅልጥፍናና ለፈጻሚነት ያላቸው ትጋት ሁሉ ልቤን በኩራት ከፍ ያደርገዋል።
በጎ ፈቃደኛነት ለሰብዕና ንቃት ትልቅ ድርሻ አለው፤ ከተጠቃሚነት ይልቅ ጠቃሚነትን ያሳድጋል፤ ጭንቀትን ያስወግዳል፤ ወጣቶች ከሚሰሩበት ስፍራ አዳዲስ ክህሎትን ያገኛሉ። ህብረትን ፈጥረው ህብረቱን እንደ ብረት ያጠነክሩታል፤ ደግሜ እለዋለሁ በሄዱበት ስፍራ የሚያገኙት መስተጋብር እና ጎሽታ ደግሞ ራሳቸውን ከምንም ነገር በላይ ልበ-ሙሉ እንዲሆኑ ይረዳቸዋል።
እንድናገርም ሆነ እንድጽፍና ቃል እንድዘራበት፣ ዕድሉን ባገኘሁባቸው አጋጣሚዎች ሁሉ ፤ ራሴን የማይበትን መነጽር ተገቢነትን እየተቀበልኩ የላቀ እድል ሁሉ እየፈጠረልኝ የመጣው በውስጤ ከቀድሞ ጊዜ ጀምሮ ያለውን የበጎ ፈቃድ ልብ የምገልጽበትና የምተገብርበት መድረክ በማግኘቴ ነው። ስለዚህም ነው፤ ለወጣቶቻችን እንደየዝንባሌያቸው በተጠና መልክ ራሳቸውን የሚገልጹበት፣ መድረክ አቅማቸውን የሚያሳዩበት መስክ ካመቻቸንላቸው ውጤታማ እንሆናለን ብዬ የማምነው።
የሐገሬ ህዝብ ከቶውንም ካለው ላይ ለመስጠት ታክቶ አያውቅም ። ሰጥቶ ቤት በደቦ ይገነባል፤ ለግሶ በወንፈል ይድራል ፤ ለግሶ ተረባርቦ ያጭዳል ፤ ለግሶ ፤ ከብቱን እንኳን ለአሂዶና ኋላም እህል ለማበራየት፤ ይዋዋሳል። ለመጫኛም አህያውን ይቀባበላል። ( መጋቢ ሐዲስ እሸቱ ያሉትን የህዳር አህያ አያድርገኝና ማለቴ ነው። ) ቸርነት የሐገሬ ሰው ባህላዊና ትውፊታዊ ህግ ነው፤ ሳይጻፍ የጸደቀ፤ ሳይዋዋል የረቀቀ የልብ ላይ ማህተም ነው። ይህንን ነው፤ በተደራጀ መልክ ፣ ወደ ወረቀት አውርደንና አሳድገን መልክና ደርዝ፤ አገባብና አወጣጥ ሰጥተነው ማሳደግ ያለብን ። በዚህ ስንት እንዳተረፍንና እንዳኖርን አናውቅም፤ ግን ቢለካ ትርፉ ዕልፍ አዕላፍ ነው።
በኢኮኖሚያቸው የዳበሩት የሰሜን አውሮፓውያኑ ስካንዴኒቪያኖች ሀገራቸውን ያሳደጉት በዚህ ባህል ነው። ካመረቱት አዝመራ በነጻ ሁሉ ለማህበረሰብ አገልግሎት የሚሰጡት አላቸው። በመስጠታቸው ግን አልደኸዩም። የመስጠት ህግ መቀበልን በውስጡ የያዘ መሆኑን ህይወት አስተምራቸዋለች፤ እኔም በእውኑ ተምሪያለሁ። በተገቢው ስፍራ ጉልበቴን እውቀቴንና ገንዘቤን ሁሉ ለሚገባቸው ሰጥቻለሁ፤ እንኳንስ ለሚገባቸው የማይገባቸው ወስደው ላስቀሩብኝ ንብረት ከእኩሌታው እጥፍ በላይ በሌላ በኩል ተመልሶልኛል። ይኸው ህይወቴ ምስክር ነው።
እናም ደግነትን ከሌሎች አንማርም፤ ሳይተርፈው ለመጣው ደራሽ እንግዳ ራቱን አብልቶ እርሱ ውሃውን በደረቅ ቂጣ አጣጥሞ የሚያድር የዋህ ህዝብ ነው ያለን። ከዚህ ህዝብ ተወልጄ ያለኝን አለመስጠት ፤ ልምድ አለመጋራት ፣ እውቀቴን አለማካፈልና መካፈል አይቻለኝም ።
ቀደም ሲል ፣ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የመሰጠት አገልግሎት ነው፤ ብያችኋለሁ። በመሰጠት የተሻለ ቀን በሀገራችን ላይ ለማምጣት ሁላችንም በአርዓያነት እንቁም፤ በጎ-ፈቃድን ለአገልግሎት በመስጠት የከሰረም የተጎዳም ማንም የለም፤ ለዚህ መልካም አገልግሎት አብረን እንቁም፤ እናንተም መልካም ፈቃዳችሁ ሆኖ እኔም በጎ ፈቃዴ ሆኖ እዚህ የበጎ ፈቃድ ለህብረት አስፈላጊነት መድረክ ላይ ስለተገናኘን የተሰማኝን ልባዊ ደስታ የምገልፀው ከፍ ካለ የኃላፊነት ስሜት ጋር ነው።
መልካምነት የክፉ ቀን ስንቅ ነው፤ ይላሉ አበው። ስንቅም ባይሆን እንኳን ለበጎነት ጠንቅ ባለመሆን እያንዳንዳችን በግል ሁላችንም በጋራ እንትጋ!! (በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ የካቲት 15/2012 የቀረበው ንግግር ለዚህ ዓምድ ተመቻችቶ የተጻፈ ነው። )
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 21/2012
ከአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ