የአልጀዚራዋ የላቲን አሜሪካና የካሪቢያን ቀጣና ዘጋቢ ሻርሎት ሚሸል በጎርጎሮሳውያኑ 2019 በመካከለኛውና በላቲን አሜሪካ አገራት እንዲሁም በሜክሲኮ የሚጠበቁ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎችን እንዲህ ቃኝታቸዋለች፡፡
‹‹የብራዚሉ ትራምፕ›› ቦልሶናሮ
ከ10 ቀናት በፊት የትልቋ የላቲን አሜሪካ አገር የፕሬዚዳንትነት በዓለ ሲመታቸውን ያከበሩትና ‹‹የብራዚሉ ትራምፕ›› በመባል የሚጠሩት አወዛጋቢው ጄይር ቦልሶናሮ፣ ገና በመጀመሪያው የሥልጣን ቀናቸው ያደረጉት ንግግር ሴቶችን፣ የተመሳሳይ ፆታ ጋብቻ ደጋፊዎችንና ጥቁር ብራዚላውያንን አስደንግጧል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ከበዓለ ሲመታቸው በኋላ የእነዚህን ኅብረተሰብ ክፍሎች መብቶች ይጥሳሉ የተባሉ አንዳንድ መመሪያዎችን ማውጣቸው የነዚህን ወገኖች ስጋት ተገቢ ያደርገዋል፡፡ በመጀመሪያው ሳምንት የቢሮ ቆይታቸውም የብራዚል አካባቢ ጥበቃ መስሪያ ቤት ዋና ኃላፊ ኃላፊነታቸውን ለቀዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ በእስራኤል የሚገኘውን የብራዚል ኤምባሲ መቀመጫ ከቴል-አቪቭ ወደ እየሩሳሌም እንደሚያዛውሩት ቃል ገብተው ነበር፡፡ ይህም ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ ተቃውሞ እንዲገጥማቸው ምክንያት መሆኑ ይታወሳል፡፡ ደጋፊዎቻቸው ብራዚልን ሰቅዘው ከያዟት የሙስናና የግድያ ወንጀሎች ያወጧታል ብለው ተስፋ ቢያደርጉም ትግሉ ቀላል እንደማይሆን ግልፅ ነው፡፡ ፕሬዚዳንቱ ራሳቸው በምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ ላይ ሳሉ የግድያ ሙከራ ተፈፅሞባቸው እንደነበር አይዘነጋም፡፡
የኢኮኖሚ ሚኒስትር አድርገው የሾሟቸው ግለሰብ በዘርፉ ያላቸው ልምድና ብቃት ኢንቨስተሮች የብራዚል ኢኮኖሚ ለንግድና ኢንቨስትመንት ስራዎች ምቹ እንደሚሆን ተስፋ እንዲሰንቁ አድርጓል፡፡
ግራ ዘመሙ የሜክሲኮ መሪ እና የባለሀብቶች ጭንቀት
ባለፈው ታኅሣሥ ወር የሜክሲኮ ፕሬዚዳንት ሆነው ኃላፊነቱን ከኤነሬኬ ፔንያ ኒቶ የተረከቡት አንድሬስ ማኑኤል ሎፔዝ ኦብራዶር፣ ስልጣን ከመያዛቸው በፊት የተናገሯቸው ንግግሮች ለባለሀብቶች ራስ ምታት ሆነውባቸው ነበር፡፡ በጥቅምት ወር በሜክሲኮ ሲቲ ከተማ አቅራቢያ ይገነባል ተብሎ እቅድ የተያዘለት ግዙፍ የብዙ ቢሊዮን ዶላሮች የአውሮፕላን ጣቢያ የግንባታው እጣ ፋንታ በሕዝበ ውሳኔ እንደሚለይለት ይፋ ሲያደርጉ አስተዳደራቸው ከባለሀብቶች ጋር ሆድና ጀርባ ይሆናል ተብሎ ነበር፡፡
ከእርሳቸው በፊት የነበሩት የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ኤነሬኬ ፔንያ ኒቶ ሲታሙበት የነበረው በሜክሲኮ ስር ሰዶ የሚገኘውን የወንጀለኛ ቡድኖች እንቅስቃሴ የፕሬዚዳንት ኦብራዶር ዋነኛ ትኩረት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ‹‹ፎሬይን ብሪፍ (Foreign Brief)›› በተባለ የጂኦ-ፖለቲካዊ ጉዳዮች ድረ-ገፅ ላይ ተንታኝ የሆኑት ማክስ ክላቨር ከወንጀለኛ ቡድኖች ጋር የሚደረገው ትግል ለፕሬዚዳንቱ ቀላል እንደማይሆንላቸው ይገልፃሉ፡፡
ኦብራዶር በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት በርካታ የስራ እድሎች እንዲፈጠሩ በማድረግ ስደት አማራጭ እንጂ አስገዳጅ እንዳይሆን ለማድረግ እንደሚጥሩ ገልፀው ነበር፡፡ የአስተዳደራቸው ጥንካሬ ከሚለካባቸው መመዘኛዎች መካከል አንዱ ይኸው የስደት ጉዳይ ይሆናል፡፡ በስልጣናቸው የመጀመሪያ ቀናትም ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ የታገዱ ስደተኞችን ለመርዳት የሚውል ፈንድ ለማቋቋም ከሆንዱራስ፣ ጓቴማላ እና ኤል ሳልቫዶር መሪዎች ጋር ስምምነት ፈፅመዋል፡፡
እየተባባሰ የመጣው የቬነዙዌላ ቀውስ
በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ቬነዙዌላውያን እ.አ.አ ከ2015 ዓመት ጀምሮ በአገሪቱ እየተባባሰ የመጣውን ምጣኔ ሀብታዊ ቀውስ በመሸሽ እየተሰደዱ ይገኛሉ፡፡ የምግብና የመድሃኒት እጥረት የከፋባት ቬነዙዌላ፣ ሕዝቦቿ የዕለት ጉርሳቸውን ማሟላት ካቃታቸው ሰንብተዋል፡፡ የዓለም የገንዘብ ድርጅት (International Monetary Fund – IMF) በ2019 የቬነዙዌላ የዋጋ ግሽበት 10 ሚሊዮን ፐርሰንት ይደርሳል ብሎ ትንበያውን አስቀምጧል፡፡
የኒኮላስ ማዱሮ መንግሥት ግን አሁንም የአገራቸውን ቀውስ ‹‹የኢምፔሪያሊስቶች ሴራ ነው›› በማለት ቀውሱን በምዕራባውያን ላይ እያሳበቡ ነው፡፡ የአካባቢው አገራትም ተቃውሟቸውን እየገለፁ ይገኛሉ፡፡ ባለፈው መስከረም ወር ሰባት አገራት ፕሬዚዳንት ኒኮላስ ማዱሮ በሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲጠየቁ ለዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት (International Criminal Court_- ICC) አቤቱታ አቅርበዋል፡፡
ምንም እንኳን በርካታ የላቲን አሜሪካ አገራትና ካናዳ እውቅና እንደማይሰጡ ቀድመው ቢገልጹም፣ ፕሬዚዳንት ኒኮላስ ማዱሮ ተጨማሪ ስድስት ዓመታትን በስልጣን ላይ የሚቆዩበትን የሥልጣን ጊዜያቸውን ትናንት ጀምረዋል፡፡ የአገሪቱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፕሬዚዳንት ማዱሮ ተጨማሪ ስድስት ዓመታትን በስልጣን ላይ እንዲቆይ ያስችለኛል ካሉትና አሸንፌያለሁ ብለው ሁለተኛ ዙር የሥልጣን ጊዜያቸውን ሕጋዊ ሽፋን ከሰጡበት ምርጫ ራሱን እንዳገለለ ይታወሳል፡፡ ያም አለ ይህ ቀውሱ በ2019 ተባብሶ እንደሚቀጥል ይጠበቃል፡፡
የቀጣናው ስጋት የሆነው ስደት
የስደተኞች ጉዳይ ከደቡብና መካከለኛው አሜሪካ አልፎ የልዕለ ኃያላኗ አሜሪካ ፖለቲካ ማጠንጠኛ ሆኗል፡፡ ከደቡብና መካከለኛው አሜሪካ የሚነሱ ስደተኞች ወደ አሜሪካ መግባትን አልመው አሜሪካ ድንበር ላይ ሲደርሱ የሚገጥማቸው ፈተና የስደተኞቹን ጉዳይ ውስብስብ እያደረገው ነው፡፡ አሜሪካ ከሜክሲኮ ጋር በምትዋሰንበት ድንበር ግዙፍ ግንብ እገነባለሁ እያሉ ከአገራቸው ፖለቲከኞች ጋር ከባድ ውዝግብ ውስጥ ያሉት ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በተለይ ከሜክሲኮ ጋር ትልቅ ፍጥጫ ውስጥ ከቷቸዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከደቡብና መካከለኛው አሜሪካ የሚነሱ ስደተኞች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ መረር ያለ አቋም ቢይዙም የስደተኞቹ መነሻ በሆኑት አገራት የተፈጠሩት ፖለቲካዊና ምጣኔ ሀብታዊ ቀውሶች በ2019 የስደተኞች ቁጥር እየጨመረ እንዲሄድ ማድረጉ አይቀርም፡፡
የፖለቲካ ተንታኙ ማክስ ክላቨር እንደሚሉት፣ የደቡብና መካከለኛው አሜሪካ አገራት ፖለቲካዊና ምጣኔ ሀብታዊ ቀውሶች መባባስና አሜሪካ በነዚህ አገራት ላይ የምትከተላቸው ፖሊሲዎች መራራና ችግሮቹን የሚያባብሱ መሆናቸው የስደተኞቹ ቁጥር አሁን ካለው የበለጠ እንዲጨምር ያደርጉታል፡፡
ይህ የስደተኞች ቀውስ በቀጣናው አገራት መካል ያለውን ግንኙነትም የበለጠ ይጎዳዋል፡፡ በተለይ ደግሞ በቬነዙዌላ እና በኒካራጓ ያሉትን ፖለቲካዊና ምጣኔ ሀብታዊ ቀውሶች ሸሽተው ወደጎረቤት አገራት የሚሰደዱ የአገራቱ ዜጎች ስደተኞቹን እየተቀበሉ ባሉት አገራት ዜጎች ዘንድ ተቃውሞና ቅሬታ መፍጠሩ አይቀርም፡፡
ከምጣኔ ሀብት ቀውስ ጋር ትግል የገጠመችው አርጀንቲና
በ2018 የአርጀንቲና የመገበያያ ገንዘብ ፔሶ አንድ ሦስተኛ የሚሆነውን ዋጋውን አጥቷል፡፡ ይህም የአገሪቱ ዜጎች የመንግሥትን የገንዘብ ፖሊሲ ተቃውመው አደባባይ እንዲወጡ አድርጓቸዋል፡፡ ይህ ቀውስም በጥቅምት ወር 2019 በሚካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ምንም እንኳ በሙስና ወንጀል ተተርጥረው ምርመራ እየተካሄደባቸው ቢሆንም የቀድሞዋ የአርጀንቲና ፕሬዚዳንት ክርስቲና ፈርናንዴዝ ኪችነር የፕሬዚዳንት ማውሪሲዮ ማክሪ ዋነኛ ተፎካካሪ እንደሚሆኑ ይጠበቃል፡፡
መፍትሄ ያጣው የኒካራጓ ፖለቲካዊ ቀውስ
ባለፈው ሚያዚያ በፕሬዚዳንት ዳንኤል ኦርቴጋ ላይ የተጀመረው ተቃውሞ ደም አፋሳሽ ሆኖ እስካሁን ድረስ ቀጥሏል፡፡ ዓለም አቀፉ የመብት ተሟጋች ቡድን አምነስቲ ኢንተርናሽናል አገሪቱ በቅርብ ጊዜ ታሪኳ አይታው የማታውቀው የሰብዓዊ መብት ቀውስ እንዳጋጠማት ገልፆ ነበር፡፡ ተቃውሞው ከተጀመረ ወዲህ ከ320 በላይ ሰዎች ሲገደሉ፣ ከሁለት ሺ የሚበልጡት ደግሞ ተጎድተዋል፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ የአገሪቱ ዜጎች ደግሞ ወደጎረቤት ኮስታሪካ ተሰደዋል፡፡ ፕሬዚዳንት ኦርቴጋ ግን ‹‹ቀውሱ ‹‹ሌቦች›› እና ‹‹መፈንቅ መንግሥት ናፋቂዎች›› የጠነሰሱት ሴራ ነው›› በማለት ተቃውሞ ያነሱባቸውን አካላት ኮንነዋል፡፡ ጋዜጠኞችና የተቃውሞ ሰልፈኞች በሽብርተኝነት ስም ወደእስር ቤት እየተጋዙ ይገኛል፡፡ በአጠቃላይ ሁኔታው ምንም ዓይነት መሻሻል እንዳላሳየና እንዲያውም እየተባባሰ እንደሚሄድ ይጠበቃል፡፡
የለውጥ ነፋስ እየነፈሰባት ያለችው ኩባ
ባለፈው ሚያዚያ ወር ከ60 ዓመታት በፊት ከተካሄደው የኩባ አብዮት ወዲህ ከካስትሮ ቤተሰብ ውጭ የኩባ መሪ መሆን የቻሉ የመጀመሪያው ሰው የተባሉት ሚጌል ዲያዝ-ካነል ቤርሙዴዝ የኩባ ፕሬዚዳንት ሆነው መሾማቸውን ተከትሎ የኮምኒስቷ ደሴት የለውጥ ነፋስ እየነፈሰባት ነው፡፡ ኩባውያን በቀጣዩ ወር በአዲሱ ሕገ መንግሥታቸው ላይ ሕዝበ ውሳኔ ያካሂዳሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የፕሬዚዳንት ሚጌል ዲያዝ-ካነል ቤርሙዴዝ መንግሥት ሌሎች ማሻሻያዎችን ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ከላይ ከተጠቀሱት ተጠባቂ ክስተቶች በተጨማሪ፣ በፔሩ፣ በአርጀንቲና፣ በብራዚልና በኮሎምቢያ እየተካሄዱ ያሉ ዓለም አቀፍ የሙስና ወንጀሎች ምርመራ፣ ቻይና በላቲን አሜሪካ የሚኖራትን ተፅዕኖ ለማስፋት የምታደርገው እንቅስቃሴ፣ የአማፂ ቡድኖች እንቅስቃሴና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዲሁም የቦሊቪያ፣ የአርጀንቲና፣ የኤል ሳላቫዶርና የኡራጓይ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫዎች በ2109 በላቲን አሜሪካ ከሚጠበቁ ምጣኔ ሀብታዊና ፖለቲካዊ ክስተቶች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 3/2011
አንተነህ ቸሬ