በፈረሰኞች፣ በሞተረኞች እና ከህፃን እስከ ሽማግሌ እግረኞች የአምቦ ከተማ ተጥለቅልቃለች። ህዝቡ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድን፤ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳን እና የመከላከያ ሚኒስትሩን አቶ ለማ መገርሳን ምስል የታተመባቸው የተለያዩ ባነሮችን በመያዝ ከንጋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ ዶክተር ዓብይን የሚያወድሱ ንግግሮችን በህብረት በማሰማት ወደ ስታዲየም ተሟል። መልዕክቱ ዶክተር ዓብይን እንደሚደግፉ እና ለውጡ እንዲቀጥል እንደሚሹ የሚያመላክት ነበር።
ከድጋፍ ሰልፈኞቹ መካከል ‹‹ፈርዶ ዳማ›› የተባለ ፈረሳቸው ላይ ተቀምጠው በባህል ልብስ ደምቀው ያሸበረቁት አቶ ወርቅነህ ሙሴ አንዱ ናቸው። እንዲህ ደምቀው የተሳተፉት ከዶክተር ዓብይ ጎን መሆናቸውን ለማሳየት መሆኑን ያመለክታሉ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ መምራት ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ እየሄዱበት ያለው የሰላም እና የልማት ተግባር እንደሚደግፉ እና እንዲቀጥል የሚሹ መሆኑንም ይናገራሉ።
የአገሪቱ ሰላም ለማረጋገጥ ከመንግሥት ጎን በመሆን የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንደሚወጡ ፤በሰልፉ ላይ በፈረስ ሳይቀር የታደሙት ሰላም ፈላጊ በመሆናቸው፤ የድጋፋቸውን ግዝፈት ለማሳየት መሆኑን ይገልፃሉ።
‹‹ ባለፉት ጊዜያት ወጣቱን ማዕከል አድርገው በመንቀሳቀስ በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች ችግር እንዲፈጠር ሲያደርጉ የነበሩ አካላት የራሳቸው ጥቅም ለማስጠበቅ ነው።›› ያሉት አቶ ወርቅነህ፤ እነዚህን ሃይሎች ለመከላከል ደግሞ ከመንግሥት ጥረት በተጨማሪ የህዝብ ድጋፍ ሊታከልበት እንደሚገባ ያመለክታሉ።
ዶክተር ዓብይ አንድን ብሔር ብቻ ለይተው ሳይሆን ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ የቆሙ በመሆናቸው በድጋፍ ሰልፉ ላይ የተሳተፈ መሆኑን የሚናገረው ወጣት ሌሊሳ ጋዲሳ፤ በተለይ ለዓመታት ተለያይተው የቆዩት በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ለተፈጠረው ሰላም የዶክተር ዓብይ ድርሻ ከፍተኛ እንደነበር ያስታውሳል። በመካከለኛው ምስራቅ የነበሩ ስደተኛ ኢትዮጵያውያንን ማምጣታቸው እና እስረኞችን ማስፈታታቸውም ለመደገፍ ምክንያት የሆኑት ጉዳዮች መሆናቸውንም ይናገራል።
ወጣት ሌሊሳ እንደሚገልፀው፤ ለብዙ ወጣቶች /ቀሬዎችና ቄሮዎች/ የሥራ ዕድል ለመፍጠር የሚያደርጉት ጥረት የሚደገፍ ቢሆንም፤ አሁንም ብዙ ሥራ አጦች በመኖራቸው ትኩረት መሰጠት አለበት ይላል።ቀደም ሲል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተናገሩት መሰረት እርሱን ጨምሮ ጓደኞቹ ዓለም ዓቀፍ መንጃ ፈቃድ አውጥተው በውጭ አገር የሥራ ዕድል ለማግኘት ጥረት ቢያደርጉም እንዳልተሳካላቸው ተናግሮ፤ የተገባው ቃል እንዲጠበቅ ጠይቋል።
ኦሎንኮሚ ከሚባል አካባቢ በመምጣት በድጋፍ ሰልፉ ላይ የተገኙት ወይዘሮ መብራቴ ሙላቱ ደግሞ፤ ዶክተር ዓብይ ስለሰላም እና ስለፍቅር ከመናገር ውጪ መጥፎ ቃል ከአፋቸው ሲወጣ እንደማያስታውሱ ጠቅሰው፤ ህዝቡ በተለይም ወጣቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ደግፎ ለሰላም ዘብ እንዲቆም ያሳስባሉ።
የምዕራብ ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ድሪርሳ ዋቁማ በሰልፉ ላይ ባደረጉት ንግግር የዞኑ ህዝብ ለአንድነት እና ለዕኩልነት ሲታገል እንደቆየ እና ለለውጡም ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከቱን አስታውሰው፤ ህዝቡ የጀመረውን ሰላምና ልማት አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
በተመሳሳይ ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እና ከባቱ ከተማ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ የአዳማ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች እንዲሁም የባቱ ከተማ ነዋሪዎች በሀገሪቱ እየተካሄደ ያለውን የለውጥ ሥራ እና በዶክተር አብይ አህመድ የሚመራውን የለውጥ አመራር በመደገፍ ሰልፍ አካሂደዋል።
የአዳማ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች ሰልፈኞቹ ‹‹በትግላችን ያመጣነውን ለውጥ እንጠብቃለን እንንከባከባለን ! ለለውጡ ውጤታማነት የድርሻችንን እንወጣለን !›› የሚል መፈክር አንግበው እንደነበረም ነው የተገለፀው።
በባቱ ከድጋፍ ሰልፍ በተጨማሪ ሰልፈኞቹ ለብልፅግና ፓርቲ ስጦታ ማበርከታቸውንም የከተማው የኮሙኒኬሽን ቢሮ ጠቁሟል።
አዲስ ዘመን የካቲት 16/2012
ለምለም መንግስቱ