አዲስ አበባ፡- በዘንድሮው ዓመት በበርካታ ዩኒቨርሲቲዎች ተቀስቅሶ የነበረውን ረብሻ ተከትሎ በዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች ላይ የተለያዩ ዛቻና ማስፈራሪያዎች እየደረሰ መሆኑ ተጠቆመ።
በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ደቻሳ ጉርሙ፤ በተለይም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ በአሁኑ ወቅት የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ሆኖ መስራት ፈታኝ እየሆነ የመጣና በተለይም የፀጥታ ስጋት ባለባቸው አካባቢዎች ፕሬዚዳንቶቹ የተለያዩ ማስፈራሪያዎችና ዛቻ ስለሚደርስባቸው በስጋት ውስጥ ሆነው እየሰሩ ነው።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተማሪዎችን በሐይማኖትና በብሔር በማጋጨት የዩኒቨርሲቲ አስተዳደሮችን ለማጥቃት የሚደረግ ሙከራ መኖሩን የገለፁት ዳይሬክተሩ፤ በዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች ላይም በየጊዜው ዛቻና ማስፈራሪያዎች ይደርሳል ብለዋል።
በዓመቱ መጀመሪያ አካባቢ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በተፈጠረው ግጭት በተማሪዎች ላይ ርምጃ ሲወሰድ፤ “የእገሌ ብሔር ስለሆነ ነው እርምጃ የተወሰደበት” በማለት የብሔሩ አክቲቪስትና እምባ ጠባቂ ነን ባዮች ይዝታሉ ያስፈራራሉ። ይህም ፕሬዚዳንቶቹ በነፃነት ስራቸውን እንዳይሰሩ ከማድረጉም በላይ ተማሪዎች ከትምህርታቸው ውጭ በሆነ አጀንዳ እንዲዋጡ አድርጓል ሲሉም ገልጸዋል።
እነዚህ ዛቻና ማስፈራሪያ የሚደርስባቸው የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች የህግ ከለላ ያላቸው መሆኑን የሚገልፁት ዳይሬክተሩ፤ ከህግ ከለላውና ጥበቃው በላይ መምህር እንደመሆናቸው በነፃነት መንቀሳቀስና መስራት እንዳለባቸው አስታውሰዋል። ይሁን እንጂ፤ ፕሬዚዳንቶቹ ጥበቃ የሚደረግላቸው ቢሆንም እንደ ፖለቲካ ሹመኛ እንዲሁም እንደ ሌሎች የአስተዳደር ሰራተኞች መታየት የሌለባቸው መሆኑን አስረድተዋል።
“መምህር አያዳላም” ያሉት አቶ ደቻሳ፤ ከየትኛውም ጫፍ የሚመጡ ተማሪዎች ተማሪ መሆናቸውን ብቻ በማመን ያለአድልኦ ማስተማር ይኖርበታል። ተማሪዎችም ኦሮሞ ነኝ፤ አማራ ነኝ፤ ትግሬ ነኝ ወዘተ… ሳይሉ ተማሪ መሆናቸውን ብቻ አስበው መማር አለባቸው እንጂ ከዓላማቸው ውጭ በሆኑ አጀንዳዎች መረበሽና ወደ ጥፋት ጎዳና መጓዝ የለባቸውም ብለዋል።
በዘንድሮ ዓመት በዩኒቨርሲቲዎች ለተቀሰቀሰው ረብሻ መንስኤ ናቸው የተባሉ 170 ተማሪዎች ሙሉ በሙሉ ከትምህርት ሲወገዱ 654 ተማሪዎች ተመክረው በማስጠንቀቂያ የታለፉ ሲሆን፤ ሁለት መምህራን ከስራ ተባረዋል። ከ40 በላይ የሚሆኑ መምህራን ደግሞ ከቀላል እስከ ከባድ የስነምግባር ቅጣት ሲቀጡ፤ 256 የአስተዳደር ሰራተኞችም ከስራ የተባረሩ፣ ከደረጃ ዝቅ ያሉ እና በደመወዝ የተቀጡ መኖራቸውን ዳይሬክተሩ አስታውሰዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 16/2012
ፍሬህይወት አወቀ