አምቦ፤ አበበች ጎበና የህፃናት ክብካቤ ልማት ማህበር በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ሸዋ ዞን ቶኪ ኩታዬ ወረዳ ኮርኮርሳ ውስጥ ከ30 አመት በፊት ሲጠቀምበት የነበረውን ሁለገብ የልማት ማዕከል ለአምቦ ዩኒቨርስቲ አስረከበ፡፡
የማህበሩ ዳይሬክተር አቶ እሸቱ አረዳ የፌዴራል፣ የክልልና የዞን ከፍተኛ አመራሮችና የአካባቢው ማህበረሰብ በተገኙበት ማህበሩ ላለፉት 30 አመታት ሁለገብ የማህበረሰብ አገልግሎት ይሰጥበት የነበረውንና 40 ሄክታር ላይ ያረፈውን ማዕከል ለአምቦ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚደንት ዶክተር ታደሰ ቀነዓ በይፋ አስረክበዋል፡፡
ከርክክቡ በኃላ አቶ እሸቱ ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት የማህበሩ መስራችና ባለቤት ዶክተር አበበች ከ30 አመት በፊት ማዕከሉን ሲያቋቁሙ በኑሮአቸው ዝቅተኛ የሆኑ የአካባቢውን ማህበረሰብ ለማገዝ ሲሆን፣ በወቅቱም የመስኖ፣ በባዮጋዝ የሚሰራ የመብራት አገልግሎት በመስራት የአካባቢው ማህበረሰብ አትክልትና ፍራፍሬ አልምቶ ኑሮውን እንዲቀይር የማድረግ ተግባር ነበር ያከናወኑት፡፡
በወቅቱም 247 አባወራዎች መስኖ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስችሏል፡፡በተጨማሪም 68 የእርሻ በሬዎችን፣ምርጥ ዘርና የተለያዩ ግብአቶችን ማህበሩ መስጠቱንም አመልክተዋል፡፡
እንደ አቶ እሸቱ ገለጻ፤ ማህበሩ አሁን ባለው አቅም ማዕከሉን ማስተዳደር ባለመቻሉ ለዩኒቨርስቲው አስረክቧል፡፡ ዩኒቨርስቲው የማህበሩ አጋር በመሆኑም በተሻለ ያስተዳድረዋል የሚል እምነት አላቸው፡፡
የአምቦ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚደንት ዶክተር ታደሰ ቀነዓ በበኩላቸው በርካታ ማህበራዊ አግልግሎት ሲሰጥ የነበረውን ማዕከል በማስቀጠል የተሰጠውን አደራ እንደሚወጣ ገልጸዋል፡፡
ለተማሪዎቹና ለአካባቢው አርሶአደሮች ለሰርቶ ማሳያነትም እንደሚያውለው ፕሬዝዳንቱ አመልክተዋል፡፡እንዲሁም ዩኒቨርስቲው ላቀደው የልዕቀት ማዕከል ሥራ በማዋል ለዘርፈብዙ አገልግሎቶች እንደሚገለገልበት ተናግረዋል፡፡
የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ታደሰ በበኩላቸው፤ በርካታ ማህበራዊ አገልግሎት ሲሰጥ የነበረውን ማህበር እንደሚያጠናክር እና የተሰጠውንም አደራ እንደሚተገብር ገልፀዋል።
ለተማሪዎች እና ለአካባቢው ነዋሪዎች ለሰርቶ ማሳያነት እንደሚገለገልበት ተናግረዋል። እንዲሁም ዩኒቨርሲቲው ላቀደው የልህቀት ማዕከልነት በማዋል ዘርፈ ብዙ አገልግሎት እንዲሰጥ የሚደረግ መሆኑን ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 16/2012
ለምለም መንግስቱ