አዲስ አበባ፡- አዲስ የተሻሻለው የኢንቨስትመንት ህግ ተጨማሪ የኢንቨስትመንት ዘርፎችን የሚፈቅድ በመሆኑ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ዘርፉን ይበልጥ ተወዳዳሪ ያደርገዋል ተባለ።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ መኮንን ኃይሉ በተለይም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፁት፤ በሃገሪቱ እየተካሄደ ባለው የኢኮኖሚ ሪፎርም የሃገር ውስጥ እና የውጭ ባለሃብቶች በአዳዲስ ተጨማሪ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ማለትም በቴሌኮም፣ በኃይል አቅርቦት፣ በሎጀስቲክስ፣ በስኳር ኢንዱስትሪና በሌሎች መሰል ዘርፎች በስፋት እንዲሳተፉ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።
ይህ አዲስ የተሻሻለው የኢንቨስትመንት ህግ ለሀገሪቱ ኢንቨስትመንት የጎላ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ከዚህ በፊት ለግሉ ባለሃብት የማይፈቀዱ ዘርፎችን ክፍት ማድረግ የቻለ በመሆኑ የግሉን ዘርፍ ሚና ይበልጥ የሚያጎለብት ከመሆኑም በላይ ኢንቨስትመንቱ ለዜጎች ሰፊ የስራ ዕድል ይፈጥራል። ይህም በአገሪቷ የሚታየውን የስራ አጥነት ቁጥር በመቀነስ የጎላ አስተዋፅኦ ማበርከት እንደሚችል ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት ስትጠቀምበት የነበረው የኢንቨስትመንት ህግ ከሰባት ዓመት በላይ የቆየ በመሆኑና ይህ የተሻሻለው ህግ ደግሞ በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ ያለውን ተጨባጭና ወቅታዊ የኢኮኖሚ ሁኔታ ያገናዘበ መሆኑን የገለፁት አቶ መኮንን፤ አገሪቷ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ከመሳብ አንጻር ይበልጥ ተወዳዳሪ እንደሚያደርጋት እና የኢንቨስትመንት ፍሰቱንም በከፍተኛ መጠን መጨመር እንደሚያስችላት ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በአገልግሎት ዘርፍ፤ በተለይም በቴሌኮም አገልግሎት ዘርፍ የውጭ ባለሀብት መሳተፍ እንዲችል ክፍት ማድረጓን ተከትሎ፤ በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ በርካታ የውጭ ካምፓኒዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት እያሳዩ ይገኛሉ።
በዚህም መንግስት ሁለት አዳዲስ የውጭ ካምፓኒዎችን በቴሌኮም ዘርፍ መወዳደር እንዲችሉ ፈቅዷል። በማለት በቀጣይ ስድስት ወራት ውድድሩን የሚያሸንፉ ሁለት ካምፓኒዎች ወደ ስራ እንደሚገቡ የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፤ ኢትዮጵያ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ከምስራቅ አፍሪካ ግንባር ቀደም መሆኗን አስታውሰዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 16/2012
ፍሬህይወት አወቀ