አዲስ አበባ፡- በተለያዩ ችግሮች ምክንያት መቀዛቀዝ ታይተውበት በነበረው በታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ መንግሥትና የፕሮጀክቱ አማካሪ መሀንዲሶች ምክንያቶቹን በጥናት ለይተው አፋጣኝ መፍትሄ በመስጠታቸው ከነበረበት ችግር እንዲወጣና አዲስ ለውጥ አንዲያመጣ አድርጎታል ሲሉ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ሥራአስኪያጅ ኢንጅነር ክፍሌ ሆሮ ገለጹ።
ኢንጅነር ክፍሌ በተለይም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት “መቀዛቀዙ በፕላንት ኮንትራክተር፤ በኤሌክትሮ መካኒካልና የብረታብረት የሥራ ተቋራጮች አቅም ማነስ ላይ በስፋት የታየ ነበር፤ እነዚህም ችግሮቹም የፕሮጀክቱን አፈጻጸም ደካማ እንዲሆን አድርገውት ነበር።
ሆኖም በመንግሥት ውሳኔ መሰረት አዳዲስ የሥራ ተቋራጮች ገብተው ሥራዎችን እንዲያከናውኑ በመደረጉ ፕሮጀክቱ እንዲድን እድል ሰጥቷል። “ብለዋል ሥራ ተቋራጮቹ ባላቸው ልምድና ሙያ ፕሮጀክቱን ከጠዋት አስከ ማታ በሦስት ፈረቃ መስራት በመቻላቸው ፕሮጀክቱን እንዲድን አድርጎታል።
አሁንም ቢሆን የተፈለገው ግብ ላይ ለመድረስ ከፍ ተኛ ርብርብ እያደረጉ ነው። ይህ ደግሞ በየጊዜው ውጤት እያስመዘገበ እንዲመጣ አድርጓልና ግባችንን ያሳካዋል ብለዋል።
‹‹ፕሮጀክቱ በታሰበበት ጊዜ አለማለቁ ከፍተኛ ወጪ ያስወጣል። ይህ ደግሞ ህዝብን ተስፋ ያስቆርጣል›› የሚሉት ሥራአስኪያጁ፤ አሁን ባለው ሁኔታ መንግሥት ትክክለኛ ልምድ ያላቸውና በዓለምአቀፍ ደረጃ የታወቁ ሥራ ተቋራጮችን በማስገባቱ አመርቂ ለውጥ እየመጣ መሆኑን ገልጸዋል። በ2013ዓ.ም የመጀመሪያ የኃይል ማመንጨት ሥራ ይጀመራል የተባለውም ከዚህ የሥራ ፍጥነት ጋር በተያያዘ መሆኑን ተናግረዋል።
‹‹አሁን የተሰራው ሥራ ወደዚያ እንደሚያደርሰን እርግጠኛ ነን›› የሚሉት ኢንጅነሩ፤ በግድቡ ግንባታ ለዩኒት 9 እና 10 የውሃ ማስተላለፊያ አሸንዳዎች ተተክለው ሥራ ተቋራጩ ኮንክሪት እየሞላባቸው ይገኛል፤ ለተርባይነርና ጄኔሬተር ሀይል ማመንጫ ጣቢያ ‹‹ ስፓይራል ኬቭ.›› የሚባለው የተርባይን ውሃን አቅጣጫ የሚወስደው ተበይዶ፣ ተስተካክሎ፣ ተተክሎና ሙከራ ተደርጎበት ለሲቪል ሥራ ተቋራጩ ኮንክሪት እንዲሞላ መሰጠቱን ገልጸዋል።
‹‹የግድቡን ሁኔታ አዲስ ለውጥ እያመጣ ነው›› የሚሉት ሥራአስኪያጁ፤ የፕሮጀክት ሥራው ከፍተኛ ማነቆ የነበሩት የብረታብረት ሥራዎች በፍጥነት እየተሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል። ከዩኒት 9እና 10 በተጨማሪ የ11ዱ ጀነሬተሮች ተርባይኖች የብረታብረት ተከላ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም ቀደም ሲል ተገዝተው የመጡት እቃዎች ፍተሻ እየተደረገባቸው መሆኑን አስረድተዋል። ከውሃ መልቀቅ ጋር ተያይዞ ደግሞ የቦተም አውትሌት የብረታብረት ሥራዎች ተጠናቀው ለሥራ ተቋራጩ ኮንክሪት እንዲሞላ መሰጠቱን ጠቁመዋል።
ኢንጅነር ክፍሌ፤ የሚታይና የሚጨበጥ ትክክለኛ መረጃ መስጠት ከተቻለ ህዝቡ ግድቡን ማስቀጠሉን አይተወውም። የአገራችን መመኪያና ምልክት የሆነውን ፕሮጀክት የመጠበቁና የማስቀጠሉ ሁኔታ የራሱ የህዝቡ በመሆኑ ብዙ አገራት ላይ ፕሮጀክቶች እንደሚዘገዩ አምኖ መስራት አለበት።
ከፍተኛ መዘግየት ታይቶባቸው ለአገራቸው መመኪያ የሆኑ ፕሮጀክቶች አሉ ህዳሴ ግድቡም ይህንኑ ስለሚደግመው ተስፋ ይኑረን ብለዋል። የግድቡ ግንባታ አሁን ላይ 71 በመቶ ደርሷል።
አዲስ ዘመን የካቲት 15/2012
ጽጌረዳ ጫንያለው