አዲስ አበባ፡- ተቋማዊ በሆነ መልኩ በአማራ ህዝብ ላይ የሚሰነዘሩ የተሳሳቱ ትርክቶች ጠንካራ የሆነ ማዕከላዊ መንግሥት ለመገንባት እንቅፋት መሆኑ ተገለጸ። የአማራ ክልል ህገመንግሥቱን በትክክል ተግባራዊ በማድረግ ሕብረ ብሔርን ያረጋገጠ መሆኑን የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የበይነ መንግሥታት ግንኙነት አስታወቀ።
‹‹የአማራ የአብሮነት እሴቶች ለሕብረ ብሔራዊ አንድነት›› በሚል መሪ ቃል የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች፣ አርቲስቶችና የተለያዩ የታሪክ ምሁራን በተገኙበት የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የበይነ መንግሥታት ግንኙነት የቢሮ ኃላፊ ዶክተር ደስታ ተስፋው እንደገለጹት፤ የአማራ ህዝብ በተሳሳቱ ትርክቶች የተነሳ የሚደርሱበትን በደሎች ተቋቁሞ ለሀገር ሰላም እየሰራ ነው።
በብዝሀነት የሚያምን ህዝብ ነው። በአማራ ህዝብ ላይ የሚሰነዘሩ የውሸት ትርክቶች ጥርጣሬን በመፍጠር ህዝቦች በአንድ ሀገር ውስጥ አንድ ሆነው እንዳይቀጥሉና ማዕከላዊ መንግስት እንዳይጠናከር አሉታዊ ሚናን ተጫውቷል። ይህ የውሸት ትርክት የአማራ ህዝብን እንዲሸማቀቅ ከማድረግም በላይ ሀገር እንደ ሀገር ለመቀጠል ስጋት እንዲጋረጥባት አድርጓል።
ኃላፊው እንደሚሉት፤ እነዚህ በአማራ ህዝብ ላይ የተቃጡ ትርክቶች ካልቆሙ ሀገር አይረጋጋም። በአሁኑ ወቅትም የእርስ በእርስ ግጭቶች እንዲፈጠሩ በማድረግ ኢትዮጵያ እንዳትረጋጋ አድርጓል። የአማራ ህዝብ አብረውት የሚኖሩ የተለያዩ ብሔር ብሔሮችን እውቅና በመስጠት የራሳቸውን ሀይማኖትና ባህልን እንዲያሳድጉ በማድረግ ከፍተኛ እገዛ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።
በታሪክ ትምህርት የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪ የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ አውግቸው ‹‹የአማራ የአብሮነት እሴቶችና ተሞክሮዎች›› በሚል ርእስ ባቀረቡት ጥናታዊ ፁሑፋቸው ላይ እንደገለጹት፤ የአማራን የአብሮነት እሴት ከኢትዮጵያ እሴቶች ለይቶ ማየት አይቻልም።አማራ ሰላም ፈላጊና መንፈሳዊ ህዝብ ነው። የራሱ የሆኑ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ እሴቶች ባለቤት በመሆኑ ሀይማኖትን ከሀይማኖትና ብሔርን ከብሔር አስማምቶ የሚኖር ህዝብ መሆኑን ገልጸዋል።
የአማራ ህዝብ ‹‹ደሃ ተበደለ ፍትሕ ተጓደለ›› ብሎ ለወገኑ ሰልፍ የሚወጣ ነው። ፍትህና ነጻነት የሚፈልግ፣ ዘርና አካባቢን ሳይለይ ጀግኖችን የሚያወድስና የሚያበረታታ፣ አቃፊና እንግዳ ተቀባይ፣ ሀይማኖተኛ፣ የጥበብ ባለቤት፣ ቀደምትና ለሀገሩ ሲል የሚዋደቅ ጀግና ህዝብ መሆኑን በጥናታቸው ጠቅሰው ነገር ግን በውሸት ትርክት እንዲሸማቀቅ በማድረግ ሀገር እንዳይረጋጋና በስነ ልቦና እንዲጎዳ ሆኗል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርና የሕግ ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ማናየ ዘገየ ‹‹የተሳሳቱ ትርክቶች፤ መንስኤዎቻቸው ያስከተሉት ጉዳትና መፍትሔዎቻቸው›› በሚል ርእስ ባቀረቡት ጥናት ላይ እንዳስገነዘቡት፤ አማራ ለኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ አበርክቶዎች አሉት። ነገር ግን ካለፉት ሠላሳ ዓመታት ጀምሮ ተቋማዊ በሆነ መልኩ በማንነቱ ብዙ ፈተናዎችን እያስተናገደ ይገኛል። ይህም የሀገር አንድነትን ፈተና ውስጥ ከቶታል፤ ማዕከላዊ መንግሥት የተረጋጋ እንዳይሆን አድርጎታል።
ፖለቲከኞች ፖለቲካዊ ፍጆታ ለማግኘት ሲባል ስርዓትንና ህዝብን አንድ አድርጎ በማቅረብ የአማራ ህዝብን ጨቋኝ በማስመሰል ለዘመናት አብረውት በኖሩ ህዝቦች በጥርጣሬ እንዲታይ መደረጉን ጠቅሰው በዚህም የተነሳ የቆዩ የአብሮነት እሴቶች ተሸርሽረዋል ብለዋል። ከዛም አልፎ ዜጎች በሀገራቸው በጥርጣሬ እንዲተያዩ ሆኗል። በሀገር ግንባታ ላይ እንቅፋት ፈጥሯል። ለአክራሪ ብሔርተኝነት መነሻ በርን ከፍቷል። መሰረታዊ የቡድንና የግለሰቦች መብቶች ተናግተዋል። የዜጎች የመዘዋወር መብቶች ተደፍረዋል ሲሉ ገልጸዋል።
ዶክተር ማናየ በጥናታቸው ላይ እንደጠቀሱት አሁን እያታዩ ያሉ ግጭቶችን ለማስቆምና ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት ለመፍጠር መንግሥት የውሸት ትርክቶችን በህግ ማስቆም፣ በሀገሪቱ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብን የተላበሰ ማህበረሰብን መገንባት፣ አክራሪ ብሔርተኝነትን ወደ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት መቀየርና በታሪክ ለዘመናት ተጋምዶ የኖረ ማህበረሰብን ለአንድ ሀገር እድገት እንዲቆም ማድረግ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 15/2012
ሞገስ ጸጋዬ