አዲስ አበባ፡- ለሃይማኖትና ለብሔር የተቆረቆሩ በመምሰል ፅንፈኛ ሆነው ተከታይ የማብዛት ተግባር የሚፈፅሙ አካላትን እና ጽንፈኝነትን ህዝቡ ሊቃወም እና ሊከላከል እንደሚገባ ምሁራን ገለፁ።
የሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ መምህር ዶክተር ገብረ ክርስቶስ ኑርዬ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል እንደተናገሩት፤ “የአገሪቱ ትልቅ ፈተና ፅንፈኝነት ነው” ብለዋል። አንዳንዶች ፅንፈኝነትን ገበያ አድርገውታል። ያዋጣኛል ብለው በሚያምኑት መንገድ ራሳቸውን ያሰልፋሉ። ብሔርን ወይም ሃይማኖትን በመውሰድ ፅንፈኛ ሆነው ሊያቀነቅኑ ይችላሉ። ህዝቡ ይቀበለኛል ባሉበት መንገድ በአንዱ ተጠቅመው ሰዎችን ከጎናቸው ለማሰለፍ እንደሚጠቀሙበት ገልጸዋል።
የሃይማኖት ጉዳይ ሰዎችን በቀላሉ ስሜት ውስጥ የሚከት መሆኑን አስበው “ሃይማኖቴ ተጎዳ” በማለት ተከታይ ያፈራሉ። ሌሎች ደግሞ “ብሔሬ ተጠቃ” ብለው በብሔር ተቆርቋሪነት ተከታይ ይሰበስባሉ። ይሄ ያልነበረ አይደለም። ያለ እና ወደ ፊትም ይቆማል ብሎ ለማሰብ የሚያዳግት ነው፤ በማለት የገለፁት ዶክተር ገብረ ክርስቶስ፤ በዚህ መንገድ አልፈው የሚያስቡትን ጥቅም ለማግኘት ጥረት ቢያደርጉም፤ ህዝቡ ፅንፈኝነትን ሊከላከል እንደሚገባ አመልክተዋል።
የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አባተ ጌታሁን በበኩላቸው፤ የፅንፈኝነት ችግሩ ያለው ተምረናል በሚሉ ሰዎች ላይ ነው። ከ83 በመቶ በላይ የኢትዮጵያ ህዝብ አርሶ አደር ነው። ፊደል የቆጠረው 17 በመቶ የሚሆነው ብቻ ነው። ከዚህ ውስጥ በርከት ያለው ደግሞ ፖለቲካ ህይወቱ አይደለም። እናም ጥቂት ፅንፈኞች የሚያደርጉት መሆኑ ታውቆ ወደ መሃል የሚመጣበትን ሁኔታ መፍጠር ይገባል በማለት ተናግረዋል።
“ህዝቡ ከሚገባው በላይ የተዋሃደ የተዛመደ ነው።” የሚሉት ዶክተር አባተ፤ “ዝርዝር ጥናት ባይኖርም በርከት ያለው የኢትዮጵያ ህዝብ ከተለያየ ብሔር የተዛመደ፤ ከአንድ ብሔር፤ ከአንድ ቦታ ብቻ የተቀዳ እንዳልሆነ አመላካች ማሳያዎች መኖራቸውን ጠቁመው፤ ችግሩን ለማቃለል ህዝቡ ራሱ ጽንፈኝነትን መቃወምና መከላከል እንዳለበት ጠቁመዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 15/2012
ምህረት ሞገስ