. ለ74ሺ ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ
ደብረ ብርሃን፡- በደብረብርሃን ከተማ ከ60 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 369 ባለሃብቶች ወደ ሥራ መግባታቸውን የሰሜን ሸዋ ዞን ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ አስታወቀ፡፡
የዞኑ የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሽመልስ ጥበቡ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ባለፉት ስድስት ወራት በአምራች ኢንዱስትሪና በአገልግሎት ዘርፍ የተሰማሩ 369 ባለሃብቶች የኢንቨስ ትመንት ፈቃድ አግኝተው ወደ ሥራ መግባት የጀመሩ ሲሆን በሙሉ አቅማቸው ወደ ሥራ ሲገቡም ከ74ሺ በላይ ለሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ፡፡
የደብረብርሃን የኢንቨስትመንት ስበት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን አቶ ሽመልስ አስታውቀው፤ በ2011 በጀት ዓመት በከተማዋ መዋዕለ ንዋያቸውን አፍስሰው የነበሩ የባለሃብቶች ቁጥር 301 እንደነበርና በ2012 ግማሽ ዓመት ደግሞ የኢንቨስተሮቹ ቁጥር ወደ 369 ማደጉን ኃላፊው ገልጸዋል፡፡
በቀጣይ ወደሥራ ከሚገቡት 369 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ውስጥም 269 የሚደርሱት በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚሰማሩ በመሆናቸውም የውጭ ምንዛሬ ከማስገኘታቸውም በተጨማሪ በከተማዋ እና አካባቢው ለሚገኙ ወጣቶች ሰፊ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥሩም አስገንዝበዋል፡፡
በከተማዋ ያለውን የኢንቨስትመንት አዋጭነት በመረዳትም የደቡብ ኮርያ ባለሃብቶች በራሳቸው ሃብት በከተማዋ የኢንዱስትሪ ፓርክ ለማቋቋም ጥያቄ ማቅረባቸውን አቶ ሽመልስ አመልክተዋል፡፡ ይህም መንግሥት ለኢንዱስትሪ ፓርኮችን ለመገንባትና ለመደጎም የሚያወጣውን በሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር ወጪ እንደሚያስቀር ጠቁመዋል፡፡
የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተፈራ ወንድምአገኝ በበኩላቸው፤ ደብረብርሃን ከተማ ሙሉ በሙሉ ሰላም የሰፈነባት ፤ለአዲስ አበባ ቅርብና በልዩ ልዩ ማዕድናትና የተፈጥሮ ሃብቶች የታደለች መሆኗን አስታውሰዋል፡፡ እንዲሁም በቂ የመሬት አቅርቦት ያላት፤ የተሻለ የኤሌክትሪክ አቅርቦት የሚገኝባት፤ የተቀላጠፈ አገልግሎት እና ብድር አቅርቦት የሚሰጥባት ከተማ መሆኗ ከተማዋን ለኢንቨስትመንት እንድትመረጥ ያደረጋት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ከተማዋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሳየች ያለችውን የኢንቨስትመንት እድገት ከግምት ውስጥ በማስገባትም ምርቶችን በፍጥነት ወደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ለማድረስ የሚያስችል ከተማዋን ከአዲስ አበባ ጋር የሚያስተሳስር ፈጣን መንገድ ለመገንባት እቅድ መያዙን አቶ ተፈራ ገልጸዋል፡፡
የፈጣን መንገድ ግንባታውም ከደብረብርሃን በተጨማሪ በሌሎችም የሰሜን ሸዋ አካባቢዎች ተጨማሪ ኢንቨስትመንቶችን ለማስፋፋት እንደሚ ያግዝም ጠቁመዋል፡፡ እንደ አቶ ተፈራ ገለፃ፤ ደብረብርሃን ከተማ ከሌሎች አካባቢዎች በተለየ ኢንዱስትሪ ልማት ከጊዜ ወደ ጊዜ ማደግ የቻለው በዋናነት የሚከናወኑት ኢንቨስትመንቶች የአካባቢውን ማህበረሰብ በተጨ ባጭ ተጠቃሚ ማድረግ በመቻላቸው ነው፡፡
በተለይም አርሶአደሩ የሚያመርተውን ምርት ለኢንዱስትሪዎቹ በማቅረብ ልጆቹም የሥራ እድል ተጠቃሚ መሆናቸው ለዘርፉ ማበብ ጉልህ አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡ በተጨማሪም በአካባቢው የኢንቨስትመንት ፖሊስ በሚል ህዝቡ ተደራጅቶ በዘርፉ መሪ ተዋናይ ሆኖ እንዲንቀሳቀስ አድርጎታል፡፡
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 14/2012
እስማኤል አረቦ