– 1615 የግል ትምህርት ቤቶች ለመኖሪያ ቤት ታስበው የተሰሩ ናቸው
አዲስ አበባ፡-በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የግል ትምህርት ቤቶች በተማሪ ብዛት 52 በመቶ ድርሻ ቢኖራቸውም አብዛኞቹ የትምህርት ሚኒስቴርን መስፈርት እንደማያሟሉ ተገለጸ።አንድ ሺህ 615 የግል ትምህርት ቤቶች ለመኖሪያ ቤት ታስበው በተሰሩ ቤቶች ተማሪዎችን በተጨናነቀ ሁኔታ እያስተማሩ እንደሚገኙ መሆኑን ታውቋል።
የትምህርት ስልጠና ጥራት ሙያ ብቃት ማረጋገጫ ባለሥልጣን ምክትል ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ፍቅርተ አበራ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፣ የግል የትምርት ተቋማት በከተማይቱ 47.2 በመቶ የሚሆነው የተማሪ ቁጥር የሚስተናገድባቸው ቢሆንም ከፍተኛ የቦታ እጥረት፣በሙያው የተመረቀ አስተማሪ ችግር፣ ስርዓተ ትምህርትን አለመተግበር እና ሌሎች ዘርፈ ብዙ ችግሮች ያሉባቸው በመሆኑ አብዛኛዎቹ መስፈርቱን አያሟሉም።
ባለፉት ተከታታይ ዓመታት በየዓመቱ የቁጥጥር (ኢንስፔክሽን) ሥራ እየተካሄደና ተቋማት የደረጃ ሽግግር እያደረጉ ቢሆንም ከሁለተኛው የዕድገትና የለውጥ ዕቅድ አንጻር በአብዛኛው ደረጃ ሁለት ( ደረጃቸውን ያላሟሉ ከመሆናቸው ባለፈ የእርምጃ አወሳሰድና የተጠያቂነት ስርዓት ባለመኖሩ ለውጡ አበረታች አለመሆኑን ገልፀዋል። ማሳየት አልቻሉም ብለዋል።
በከተማው በመደበኛ መርሐ ግብር ትምህርታቸውን ከሚከታተሉት 868ሺህ838 ተማሪዎች ውስጥ 410ሺ 641(47.2 በመቶ) የግል ትምህርት ቤቶች ድርሻ መሆኑን አውስተው፤ የግሎቹ በተለይ አጸደ ሕጻናት ትምህርት ቤቶች ብዛት ያለውን ቁጥር የሚይዙ ቢሆንም ተማሪዎች በተጨናነቁ ትምህርት ቤቶች ግቢዎች እንደሚማሩ ተናግረዋል።
“ችግሩ በግሉ ዘርፍ ብቻ የሚስተዋል አለመሆኑን የተናገሩት ምክትል ሥራ አስኪያጇ፤ ነባር የመንግሥት ትምህርት ቤቶችም ቀላል የማይባል ጉድለቶች አሉባቸውና አዳዲስ ለሚከፈቱ ትምህርት ቤቶች መስፈርቱን ሳያሟሉ አይከፈቱም” ሲሉ አስረድተዋል።
የአዲስ አበባ የግል ትምህርት ቤት አሰሪዎች ማህበር ፕሬዚዳንትና የማጂክ ካርፔት ትምህርት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አበራ ጣሰው በበኩላቸው፤ ከከተማ ነዋሪ ልጆች ከፍተኛውን ቁጥር ተቀብሎ ትውልድ በመቅረጽ ላይ የሚገኘው የግሉ የትምህርት ተቋማት ቢሆኑም ተቋማቱ 90 በመቶ የግለሰብ ቤት ተከራይተው የሚያስተምሩ መሆኑን ገልጸዋል።
የግል ትምህርት ቤቶች ሕጻናትንም በአጣብቂኝ ውስጥ ተቀብለው እንደሚያስተምሩ የገለጹት አቶ አበራ ከረጅም ዓመታት ጀምሮ ለሚነሱ የመሬት ጥያቄዎች መንግሥት ምላሽ ሊሰጥ አለመቻሉን ተናግረዋል።
ፕሬዚዳንቱ እንዳሉት፣ የተማሪ ቁጥር ግምት ውስጥ ያስገባ ትምህርት ቤቶችን ማዘጋጀት የመንግሥት ግዴታ ነው።ሆኖም መንግሥት ይሄን ማድረግ ባለመቻሉ በከተማዋ የሚገኙ ከአንድ ሺህ 615 በላይ የግል ትምህርት ቤቶች ለመኖሪያ ቤት ታስበው በተሰሩ የግለሰብ ግቢዎች ተከራይተውና ተማሪዎች ተቀብለው በተጨናነቀ ሁኔታ በማስተማር ላይ ይገኛሉ።
መንግሥት ያለ አንዳች ጨረታ ባለኮከብ ሆቴልና በሌሎች ኢንቨስትመንቶች ለሚሰማሩ ባለሀብቶች መሬት በነጻ ከማቅረብ ጀምሮ ቁሳቁስ ያለቀረጥ እስከማስገባት የሚደርሱ ድጋፎች እንደሚደረጉላቸው ያወሱት አቶ አበራ፣ ለአገር መሰረት የሆኑና የሕጻናት ሰብዕና ለሚገነባባቸው ትምህርት ቤቶች ቅድሚያ መስጠት ይኖርበታል፤ ለትምህርት ቤት በሚመጥን ስፋት ያለው መሬት ቀርቦላቸው እንደሌሎች በጨረታ እኩል ተሳትፎ እንዲኖራቸው መደረግ ነበረበት ብለዋል።
በብዙ ችግሮች ተወጥረው ከሚያስተምሩ የግል የትምህርት ተቋማት መስፈርቱን (ስታንዳርዱን) እንዲያሟሉ መጠበቅ ጉንጭ አልፋ መሆኑን ገልጸዋል።
የችግሩ ጦስ ዞሮ ዞሮ ወደ ወላጆች እንደሚሻገር የተናገሩት አቶ አበራ አከራዮቹ ዋጋ ሲጨምሩ የትምህርት ቤት ክፍያ ላይ እየተቆለለ ትልቅ የመልካም አስተዳደር ችግር ሆኖ እንደቀጠለ ተናግረዋል።
ወይዘሮ ፍቅርተ ያለፈውን ዓመት ምዘና መሰረት አድርገው እንደገለጹት፤ በከተማ አስተዳደሩ ስር ከሚገኙ የመንግሥትም ሆነ የግል ትምህርት ተቋማት ትምህርት ሚኒስቴር ያወጣውን መስፈርት (ስታንዳርድ) ያሟሉት 32 በመቶ ብቻ ናቸው።
አዲስ ዘመን የካቲት 13/2012
ሙሐመድ ሁሴን